ምስክር ጌታነው ሚዲያና ፕሮሞሽን መጋቢት 9 ቀን 2011 ዓ.ም በብሔራዊ ቴአትር ‹‹ኢትዮጵያ ዛሬ እና ነገ›› በሚል ርዕስ ባዘጋጀው የዲስኩር፣ የወግ፣ የግጥም እና የሙዚቃ መርሃ ግብር ላይ ዲያቆን ዳንኤል ክብረት ካቀረቡት ዲስኩር ክፍል ሁለት እንደሚከተለው አቅር በነዋል፡፡
ይቺን አገር ማዳን፤ ከፖለቲካ ፓርቲዎች፣ ከሀሳብ መሪዎች፣ በየዘውጋቸው ከቆሙ ፖለቲከኞች የምንጠብቅ ከሆነ ተከትለን መጥፋት ነው፡፡ እኛ ራሳችን ዜጎች ነን ተነስተን ማዳን ያለብን፤ እኔ ኢትዮጵያዊ አርበኝነት የምለው እሱን ነው፡፡ የኢትዮጵያ አርበኞች ምንድነው ያደረጉት?
አገራቸው ተወረረች፤ በወቅቱ ንጉሡ አልቻሉም፡፡ የአገር ርዕስ ተደርገው የሚታዩት ንጉሡ ሄዱ፡፡ ሲሄዱ ኃያላን ኃያላን የሆኑ የተወሰኑ ሰዎችን ይዘው ሄደዋል፡፡ የተረፉትን ደግሞ ጣሊያን ያዘ፡፡ ቀሪዎቹም ወደ ሱዳን ገቡ፡ ፡
አርበኞቹ መሪ አልነበራቸውም፤ የታወቀው መሪ በእኛ አገር ንጉሡ ነው፡፡ በቃ እንግዲህ ንጉሡ ከሄዱ፤ ባላባቶችም ከሄዱ፤ እነ እገሌም ከሌሉ ‹‹እንተዋት ኢትዮጵያን›› አላሉም፡፡ የዜግነት ግዴታ ውስጥ ነው የገቡት፤ ቃል ኪዳን ነው የመሰረቱት፡፡ ይቺን አገር አንተዋትም፤ መሪ ከሌለ መሪ እንፈጥራለን! ለጊዜው ምድራዊትን አገር ቢወስዱብን እንኳን ሀሳባዊትን አገር ይዘን እንቀጥላለን፡፡ አርበኞች ጭንቅላት ውስጥ ያለችው ኢትዮጵያ ያልተገዛች ኢትዮጵያ ነች፡፡ እነርሱ ጣሊያንን እንደ ወራሪ እንጂ እንደ መሪ አላዩትም፡፡
እስኪ አስቡት! ታጥቆ የመጣ፣ ቤተ መንግሥቱን የተቆጣጠረ፣ ሥልጣን ያለው ኃይል ይዞት፤ እልም ያለ በረሃ ውስጥ ኢትዮጵያን ነፃ አውጣለሁ ብሎ የገባ አርበኛ ‹‹ምን ይሆን ፍልስፍናው?›› ብላችሁ አስቡት! እንዴትስ ተሳካላቸው? እኩል የሚመስሉ ሰዎች ከመካከላቸው የጎበዝ አለቃ መርጠው፣ በእሱ ታዝዘው አምስት ዓመት ተዋግተው አሸንፈው ኢትዮጵያ ውስጥ ለመግባት የቻሉበት የዜጋ አርበኝነት ነው፡፡ እያንዳንዱ ነው ግዴታውን የተወጣው፡፡ ጣሊያን ውስጥ የነበሩ ሰዎች ማንም ሳይከፍላቸው ነው መረጃ በመስጠት የተባበሩት፡፡
አብርሃም ደቦጭ እና ሞገስ አስገዶም በግራዚያኒ ላይ ቦምብ ለመወርወር ሲሄዱ የታክሲ ሾፌር ነው በነፃ የወሰዳቸው፡፡ ይሄ የታክሲ ሾፌር ማን ከፈለው? እንዲያውም እንድታወቁ ለእንዲህ ዓይነት አርበኞች ነበር ሐውልት የሚያስፈልገው፡ ፡
ነገ የሚመጡ የታክሲ ሾፌሮች፣ የአውቶቡስ ሾፌሮች፣ የአውሮፕላን ካፒቴኖች ‹‹እኛም አርበኞች ነን!›› ማለት እንዲችሉ የባለታክሲ ሐውልትም ነበር መስራት፡፡ ማንም ያልከፈለው የታክሲ ሾፌር ‹‹አገሬ!›› የሚባል ነገር ውስጥ ስላለበት አገሩን በታክሲው ልክ አይደለም የለካት። ዛሬ ግን አገርን በታክሲ ልክ የሚለኩ ሰዎች አሉ፡፡ እነዚያን ጀግኖች ጭኖ ሲሄድ የነበረው ኢትዮጵያን እያዳነ እንደሆነ ገብቶት ነው የሚችለውን ያደረገው፡፡
ያ የታክሲ ሾፌር መዋጋት አይችልም፣ መተኮስ አይችልም፣ መምራት አይችልም፣ መጻፍ አይችልም፣ ቦምቡን መወርወር አይችልም፤ እነዚያን ጀግኖች ጭኖ መሄድ ግን ይችላል! በሚችለው ችሎታ ኢትዮጵያን ብድግ አድርጎ ለማሻገር እነዚያን ጀግኖች ጭኖ ሄደ፡፡
እንዲህ የሚያስቡ የቢሮ ሠራተኞች፣ ፖሊሶች፣ ወታደሮች፣ ጸሐፊዎች ስናፈራ፤ ምንም ይነሳ፣ ማንም ‹‹እበትናለሁ! አፈርሳለሁ!›› ይበል ‹‹እኛ አንፈርስም!›› ካልን እኮ ማንንም ማፍረስ አይችልም፡፡ እኛን እኮ ነው ‹‹አፈርሳችኋለሁ›› እያለ ያለው፤ ‹‹አንፈርስም›› ካልነው ማንን ያፈርሳል?
ጫፍና ጫፍ ላይ ሆነው የሚጓተቱ ሰዎች እንዳያፈርሷት እናንተ ያዟት፡፡ እኛ እሺ
ካላልን ማነው ከዚያ ውስጥ የሚያወጣት? እኛ እሺ እስካላልን ድረስ እኮ ከፉከራ ያለፈ ነገር ምንም አይመጣም፡፡ ለዚህ ነው ቃል ኪዳን የሚያስፈልገን፡፡ ለዚህ ቃል ኪዳን ደግሞ የግድ የሆነ ማህበር ወይም የሆነ ድርጅት ላያስፈልገን ይችላል፤ በእያንዳንዳችን ውስጥ ነው መሰራት ያለበት፡፡
ብዙ ሰዎች የኢትዮጵያን ታህታይ መዋቅር አያውቁትም፡፡ ከታች ያለው መሠረት ዝም ብሎ የሲሚንቶ ግርፍ አይደለም፡፡ በዘመነ መሳፍንት እኮ ተሞክሮ ነበር፤ በዚያን ጊዜ የሚደርስላቸው አጥተው የተቸገሩ ወገኖች ነበሩ፡፡ ግን እነርሱ ውስጥ በነበረችው ኢትዮጵያ አድነዋታል። የኢትዮጵያ ታህታይ መዋቅር የተሳሰረ ነው።
አጼ ዮሐንስ በጉርዓ ጦርነት በሚዋጉበት ጊዜ አንድ ከጉራጌ አካባቢ የሄዱ ሰውዬ፤ እንዲያውም ቅጽል ስማቸውም አባ ጉራጌ ነበር፤ ከአጼ ዮሐንስ ጋር አብረው ነበሩ፡፡ እንግዲህ አጼ ዮሐንስ ቤተ መንግሥታቸው መቀሌ ነው ያለው፣ ብዙ ውጊያዎችን ያደረጉት ኤርትራ ነው፣ አብረዋቸው ያሉት ሰው ግን ከጉራጌ ነው የመጡት፡፡ የኢትዮጵያ ታህታይ መዋቅር ይሄ ነው፡፡ አጼ ዮሐንስ በውስጣቸው የነበረችው ኢትዮጵያ ነበረች፡፡
በዮዲት ጉዲት ጊዜ የአክሱም ጽዮን ካህናት መጥተው የተረፉት ዝዋይ ነው፡፡ እንደ አሁኑ እንኳን ስልክ የለም፣ ቴሌቪዥን የለም፣ ኢንተርኔት የለም፤ በምን አወቁ ዝዋይ የሚባል መኖሩን? ዛሬ ቢሆን ግን ባለው ፖለቲካ ላይመጡ ይችሉ ነበር፡ ፡
ያኔ ግን መጡና ወደ 40 ዓመት አካባቢ ኖሩ፡ ፡ እንደ አሁኑ ዘመን ‹‹ውጡ! ምጡ›› የሚላቸው አልነበረም፡፡ ይህን ሲያደርጉም ዝም ብለው አይደለም፤ እነርሱ ህሊና ውስጥ ያለች ኢትዮጵያ ነበረች፡፡ እሷን አሳልፈው አይሰጡማ! እሷን አሳልፈን ከሰጠን ግን ማንም ይጫወትብናል፡፡
በተለያየ ዘመን የተለያየ የፖለቲካ ርዕዮት ዓለም ነበሩ፤ ግን ኖረዋል፡፡ እነሆ ሕያው ምስክር ሆኖ አሁንም ይናገራል፡፡ እጅግ ክፉ በሚባለው ዘመን እንኳን ደግ ዜጎች ነበሩ፡፡
አያድርገውና ዘጠኙም ክልሎች አንድ አንድ አገር ሆኑ እንበል፡፡ መጀመሪያ ምን እንደሚጀመር ታውቃላችሁ? ጦርነት ነው! ምክንያቱም አንድ ላይ ሆነን በወሰን ያልተስማማን ሰዎች ተለያይተን በድንበር የምንስማማ ይመስላችኋል? ከኤርትራ ጋር እኮ አንድ ወሰን ነው ያጣላን፡፡ የጋራ ታሪክ ያለን፣ የጋራ ቋንቋ፣ የጋራ እምነት ያለን እኮ ነን። መረብ ምላሽ እያልን እንጠራው የነበረው አጣልቶን ቁጭ አለ፡፡ ልክ አገር መሆን ሲጀመር ጦርነት ተጀመረ፡፡ ለምን? አንድ ላይ ተሰፍቶ የኖረን ማላቀቅ ከባድ ነዋ! እነዚህ እናደርገዋለን የሚሉ ሰዎችም እኮ እንደማይሆን ያውቁታል፤ ሌላ ማሳበጃ ስላጡ ሰዎችን ለማሳበድ ነው እንጂ!
ሰሜን የነበሩ ሕዝቦች ደቡብ ድረስ ወርደዋል፤ እነ አጼ ገብረመስቀል አርባ ምንጭ ድረስ ወርደዋል፤ ደቡብ የነበሩ ወደ ሰሜን፣ የምዕራቡ ከምሥራቁ ሄደዋል። ይሄንን መለያየት አይቻልም፡ ፡ አገር መመስረት ዝም ብሎ መስመር ማስመር አይደለም፤ የነገውን ነገር ነው ማሰብ የሚጠይቅ፡፡ ለዚህም የዜጋ ቃል ኪዳን ያስፈልገናል፡፡
ልጆቻችንን ጎረቤቶቻችንን ‹‹እሺ እና እምቢ›› ማለት እንዲችሉ ማድረግ አለብን፡፡ ይሄ ከሆነ የማንም የማፍረስ ምኞት አይሳካም። ዝም ብሎ የሚነዳ ሳይሆን ማሰብ የሚችል ትውልድ እንፍጠር!
እኔ ለምሳሌ ሽጉጥ አንስቼ ተኮስኩ፡፡ የሆነ ሰው መታ! እኔ ተኳሹ ለምን እንደምተኩስ፣ ማንን ለመምታት እንደሆነ፣ ሰውየውን ከገደልኩ በኋላ ምን እንደማገኝ አውቀዋለሁ። ጥይቱ ግን ይሄን አያውቅም! ማንን እየመታ እንደሆነ፣ ለምን እንደሚመታ አያውቅም። ምታ ያልኩትን ብቻ ይመታል፡፡ ስለተኳሹ ዓላማ ምንም የሚያውቀው ነገር የለውም፡፡ ጥይት ግዑዝ አካል ነው፤ ማሰብ አይችልም፡፡ እንዴት ሰው ጥይት ይሆናል?
እኛ የነገዋ ኢትዮጵያ እጃችን ላይ ያለች ኩሩ ሕዝቦች እንጂ ጥይት አይደለንም!
አዲስ ዘመን ቅዳሜ ሚያዝያ 5/2011