ሀገር መውደድን መግለጫው መንገድ ብዙ ነው። ስለ ሀገር መቆርቆር፤ ስለህዝብ ያገባኛል ማለት ባህል በመጠበቅና በማክበር፣ ስለ ሀገር ህልውና በመቆርቆር፣ ታሪክ አውቆ በማሳወቅና ፋይዳውን በማጉላት ለጥቅም ማዋል፣ ሀገር ያሉዋትን ቅርሶች በመጠበቅና በመንከባከብ ለትውልድ ማስተላለፍ የሀገርን ፍቅር ማመላከቻ መንገድ ነው።
ስለባህሉ የሚቆረቆር ትውልድ ለሀገሩ ከፍ ያለ ፍቅርና ክብር ያለው መሆኑ ማሳያ ነው። እራሱን የሚያከብር፣ ለራሱ ትልቅ ቦታ ያለው ትውልድ ደግሞ ለባህልና ማንነቱ ትልቅ ትኩረት ይሰጣል። የትናንት ባህሉን ጠብቆ በማቆየት መልኳን እየለየ ዛሬን ይሻገርበታል። ባህልና ወጉን ጠብቆ ቅርሱን ተንከባክቦ በማቆየት ትናንትን እያሰበ ነገን ወደፊት ለመራመድ ወደፊትም ለሚገጥመው መሰናክል መሻገሪያ ልምድ ይቀስምበታል።
ቅርስ ታሪክን ማቆያ ባህልን ማንጸባረቂያና ያለፈን ዘመን አሻራ ማሳያ ነው። ባህላዊ ቅርስን ሰብስቦና ተንከባክቦ ማቆየት ሀገራዊ ፋይዳው የጎላ ነውና ሀገራት ለዚሁ አላማ ብቻ የሚሰራ ተቋም በመመስረትና ቅርስ በማሰባሰብ ጥቅም ላይ የማዋል ስራ በመስራት ላይ ይገኛሉ። ይህንን ሃላፊነት ተሰጥቶት ከሚሰራ አካል ወጪ በግለሰብ ደረጃ ቅርስን አሰባስቦ
በመጠበቅ ሀገራዊ ሃላፊነቱን ሲወጣ ሲመለከቱት የግለሰቡ ሀገራዊ ተቆርቋሪነትና ባህል አክባሪነት ትልቅ ማሳያው ይሆናል።
እዚሁ መዲናችን ከሁለት አስርት ዓመታት በላይ በራሳቸው ተነሳሽነት ለትውልድ ታሪክና ባህልን ለማስተዋወቅ ባህላዊ ቅርሶችን አሰባስበው በመጠበቅ ሀገራዊ ሃላፊነታቸውን እየተወጡ ያሉ ታታሪ ኢትዮጵያዊት እናት ማንሳት ወደናል። እኚሁ እናት ወይዘሮ ለምለም አስራት ይባላሉ።
ባህሉን ከሚወድ ቤተሰብ የተገኙት ወይዘሮ ለምለም ከወጣትነት እድሜያቸው ጀምሮ ወደተለያዩ የሀገራችን ክፍሎች በመዘዋወር ኢትዮጵያውያን ሲጠቀሙበት የቆዩትን ቅርሶች በማሰባሰብ እና ቤታቸውን እንደ ሙዚየም በመጠቀም ባህላዊ ቅርሶቹን በማስተዋወቅ ላይ ይገኛሉ። የመኝታ ክፍላቸውን ጨምሮ ባሰባሰቡዋቸው ባህላዊ ቅርሶች በመሙላት የራሳቸውን ምቾት እና ጊዜ ለሀገራዊ ቅርስ ጥበቃና እንክብካቤ የሰጡ ሀገር ወዳድ፤ ሀገራዊ ሃላፊነትን ከሌላው በተለየ እየተወጡ ያሉ ጠንካራ ሴት ናቸው።
ይህ ቤት አማኑዔል አካባቢ ወረዳ 3 ቀበሌ 24 የሚገኝ የወይዘሮ ለምለም አስራት የግል ሙዚየም ነው። ያለመታከት ለ22 ዓመታት ባህላዊ ቅርሶች አሰባስበው በእንክብካቤ የያዙበት የግል ባህላዊ ሙዚየም። ከ1989 ዓ.ም ጀምሮ ከሀገራችን ልዩ ልዩ ክፍሎች ያሰባሰቡት ባህላዊ ቅርስ በጠበበ መኖሪያ ቤታቸው ለቅርሶቹ ማቆያና ማሳያ በማድረግ ለባህላቸው ያላቸውን ክብርና ፍቅር ያሳዩበት ነው።
የግል ሙዚየማቸውን “ውብ ኢትዮጵያ” ብለው የሰየሙት እኚህ ድንቅ ኢትዮጵያዊት እናት እስካሁን ድረስ ቁጥራቸው ከ600 በላይ የሚሆኑ ባህላዊ ቅርሶችን ሰብስበዋል። ከመቶ ሃምሳ ዓመታት በላይ የቆዩ ባህላዊ የቤት ውስጥ መገልገያ እቃዎች፣ የጥንት መገበያያ ገንዘቦች፣ ባህላዊ አልባሳት፣ የምግብ ማብሰያና ማቅረቢያዎች ፣ጥንታዊ ማጌጫ እቃዎች ካሰባሰቡዋቸው ታሪካዊ ቁሳቁሶች መካከል ይገኙበታል።
በተለያዩ የሀገራችን ክፍሎች በመዘዋወር እድሜ ጠገብ የሆኑ ባህላዊ ቅርሶችን የመሰብሰብ ልምድ ያላቸው ወይዘሮ ለምለም የወደፊት ህልማቸው እስካሁን ያሰባሰቡትንና ወደፊት የሚያሰባስቡትን ባህላዊ ቅርስ ማሳያ የግል ዘመናዊ ሙዚየም በመስራት ታሪክን ማስተማርና ባህልን ማስተዋወቅ ነው። እጅግ ጠባብ በሆነው መኖሪያቸው ተገኝቶ ያሰባሰቡትን ባህላዊ ቅርስ ለማየትና ለመጎብኘት የመጣን እንግዳ በኢትዮጵያዊ እንግዳ አቀባበል ሥነ ሥርዓት በክብር ወደ ቤታቸው ያስገባሉ። ስለቅርሶቹ ማብራሪያ ይሰጣሉ።
የቤታቸው ሳሎን፣ የመኝታ ክፍላቸው፣ ምግብ ማብሰያ ክፍሎቻቸውን ምርጫ በማጣት በባህላዊ ቅርሶች የሞሉት ወይዘሮ ለምለም አብዛኛውን ሰዓታቸውን የሚያሳልፉት ያሰባሰቡት ቅርስ ለብልሽት እንዳይዳረግ በማጽዳት፣ አቀማመጡን በማስተካከልና ቦታዎችን በማዘጋጀት ነው።
ሰው “ማን ነህ?” ሲባል ማንነቱን ለመንገር ማስረጃ ያስፈልገው ይሆናል፤ ያለፈበትን ለማሳየት “ምኔን ላመላክት?” ብሎ ራሱን ይጠይቅ ይሆናል። ያኔ መልሱ ቀደምቶቹ በታሪክ የቆዩለትን ቅርሶች በመጠቀም በማስረጃ አስደግፎ ማስረዳት ይቀለዋል። ትናንት አባቶቹ ዓለምን ኖረው ያለፉበትን መንገድ የአኗኗር ዘይቤ፣ ባህል እና ስልጣኔ ቅሪቱን መሰረት አድርጎ ይተነትናል።
እኚህ እናት ለባህል ያላቸው ትልቅ ምልከታና በጎ እሳቤ በዛሬው ትውልድ አለመታየቱ ያሳስባቸዋል። በምክንያት ካልሆነ በቀር ታሪኩን ለማወቅ፣ ባህሉን ለመማር የሚጥረው ወጣት ጥቂት መሆኑን ታዝበዋል። ያለ ታሪክ እውቂያ፣ያለ ባህል ስንቅ ሩቅ መጓዝ ጉዞው አመቺ አያደርገውምና ወጣቱ ትውልድ በባህል እውቂያ ላይ ያለውን ለዘብተኛ አቋም ሊያጤነው ይገባል።
ስለ ታሪኩ የማይጠይቅ፣ ባህሉንም የማያውቅ ትውልድ ለራሱ የሚሰጠው ግምት አነስተኛ መሆኑ እርግጥ ነው፡ ስለራስ ግምት የማይሰጥ ያለውን በጎ ነገር የማይጠብቅ ደግሞ አድራሻውም፣ መድረሻውንም ለማወቅ ያዳግታል።
ወይዘሮ ለምለም ውብ ኢትዮጵያ ብለው በራሳቸው የሰየሙት የቅርስ ማቆያ ቤታቸው በ2001 ዓ.ም የቅርስ ጥናትና ጥበቃ ባለስልጣን እውቅና እንደተሰጣቸው ቢናገሩም ለቅርሶቹ ማስቀመጫና ማሳያ አመቺ ቦታዎችን ማግኘት ባለመቻላቸው እቃዎቹ ይበላሹ ይሆን የሚል ስጋት ፈጥሮባቸዋል። ቅርስ በሥርዓት ሊያዝ የሚገባውና በአያያዝ ጉድለት የሚበላሽ በባህሪውም ጥንቃቄ የሚፈልግ ሀገራዊ ሀብት ነው። ቅርሶቹን በማሰባሰብና በመጠበቅ ሂደት ከግል ጥረት በቀር እንደ ሀገር ቅርሶችን ሰብስቦ መጠቀም ዋነኛ ተግባሩ ካደረገ የቅርስ ጥበቃ ባለስልጣንም ሆነ ከከተማው አስተዳደር ምንም እገዛን አግኝተው አያውቁም።
ስለ ባህሉ የሚጨነቅ ስለ ማንነቱ ግድ የሌለው ትውልድ እየተፈጠረ ባለበት በዚህ ወቅት ባህል ያለውን ትልቅ ጠቀሜታ ቀድመው በመረዳት ሀገራዊ ተግባርን ግለሰቦች ሲከውኑት ሲታይ የባህል ጠባቂና አስተዋዋቂውን ማክበር እና ተገቢውን ቦታ መስጠት ወሳኙ ጉዳይ ነው።
እጅግ በተጣበበ መልኩ የተቀመጡት ቅርሶች ለብልሽት እንዳይዳረጉ ቁሶቹን ማስቀመጫ አመቺና ከብልሽት በራቀ መልኩ ማቆየት የሚያስችል ስፍራ ሊመቻችላቸው ይገባል። ሀገራዊ ቅርሶቹ ታሪክ ነጋሪ ባህልን አስተዋዋቂ ናቸውና ተጠብቀው ለረጅም ጊዜ አገልግሎት መስጠት እንዲችሉ በግለሰብ ደረጃ ለሚታትሩት እኚህ ሀገር ወዳድ እናት በቂ ድጋፍ ማድረግ ሀገራዊ ሃላፊነት ከመወጣት ባለፈ ለባህል መጠበቅ ትልቅ ሚና መወጣት ነው።
ወይዘሮ ለምለም የመኖሪያቸው ክፍሎች ሁሉ በባህላዊ ቅርስ ሞልተው የእለት ተዕለት ስራቸውን ለመከወንና ማህበራዊ ህይወታቸው ላይ ተፅዕኖ መፍጠሩ አይቀሬ ነው። የራሳቸው ምቾት በመተው በግል ተነሳሽነት ይህንን ሀገራዊ ትልቅ አላማ ይዘው ለሚለፉት እናት ጉዳዩ የሚመለከተው አካል በቂ ድጋፍ ሊያደርግላቸው ይገባል መልዕክታችን ነው።
አዲስ ዘመን ሚያዝያ 6/2011
በተገኝ ብሩ