ገበያን ፍላጎት ይመራዋል፤ አቅርቦት ደግሞ ፍላጎትን ይከተላል የሚባል የኢኮኖሚ ሰዎች ሀሳብ አለ። በእርግጥ ይህን ለማወቅ የኢኮኖሚስት ባለሙያ ድረስ አያስኬድም። ለማንም ተራ ግለሰብ ሁሉ ግልጽ ነው።
አንድ ነጋዴ ዕቃ የሚያመጣው የሚሸጥለትን ነው። ደንበኞቹ በተደጋጋሚ ‹‹… አለህ?›› የሚሉትን ዕቃ ያመጣል። በተመሳሳይ አቅራቢም እንደዚያው፤ የሚፈልገውን ነገር ነው የሚያቀርብ።
ይህን ነገር ያነሳሁት ስለ ኢኮኖሚ ልተነትን አይደለም። ይልቁንም ከሰሞኑ የታዘብኩትን ከዚህ ጋር ለማመሳሰል ነው።
ነፍሱን ይማረውና ተወዳጁን አርቲስት ታሪኩ ብርሃኑ (ባባ) በዚህ ሳምንት በሞት አጥተናል። ታዲያ ታዋቂ ሰው በሞተ ቁጥር አንድ የሚደጋገም አሰልቺ ነገር ቢኖር የ‹‹ዩትዩቦች›› የማጭበርበሪያ አሉባልታ ነው። ታዋቂ ሰው በሞተ ቁጥር ዋና ጉዳይ የሚሆነው እነርሱ የሚፈጥሩት የሀሰት አጀንዳ ነው።
በሌላ በኩል ደግሞ ለለቅሶ የሚሄደውን ሀዘንተኛ የግል ገመና ሁሉ ሳይቀር ለገበያ ማቅረብ ነው። ማን ሳቀ ማን አለቀሰ የሚል ግምገማ ሁሉ ሳይቀር ይካሄዳል። ይህ ቅጥ ያጣ ሥራቸው በታሪኩ ብርሃኑ የአስከሬን ሽኝት ስነ ሥርዓት ላይ ጭራሹንም እንዳይገቡ አስደረጋቸው።
ዋናው ጥያቄና ትዝብት ግን ይህ ለምን ሆነ? የሚለው ነው!
መግቢያ ላይ እንዳልኩት ነው። ዩትዩበሮችን እንደ ነጋዴ እንያቸው። እኛ ደግሞ ሸማች (ደንበኛ ነን)። እያቀረቡልን ያሉት የምንፈልገውን ነገር ነው። በእርግጥ አንድ ነጋዴ ጥራት የሌለው ዕቃ ወይም ጎጂ የሆነ መርዛማ ነገር ሲሸጥ ይጠየቃል። በዚህ መሰረት አገርና ሕዝብ የሚጎዳ ነገር የሚያቀርቡት የዩትዩብ ሸቃዮች መጠየቅ ነበረባቸው። እስከዚያ ድረስ ግን የእኛን የሸማቾችን ችግር ልብ እንበል!
ከእውነተኛ ነገር ይልቅ ለአሉባልታ አይደለም ወይ ቅድሚያ የምንሰጠው? አንድ የሕክምና ዶክተር ስለአንድ ገዳይ በሽታ የሚያብራራ ቪዲዮ ቢለቀቅ እና ‹‹የታሪኩ ብርሃኑ አሟሟት ምሥጢሮች›› የሚል ቪዲዮ ቢለቀቅ የትኛው ነው ብዙ ተመልካች የሚያገኘው ?
ሕይወታችንን የሚያድን ሙያዊ ማብራሪያ ከሚሰጠው ሐኪም ይልቅ የሌላ ሟች የአሟሟት ሁኔታ ምን ይሆን የሚለው ያሳስበናል። ይሄ መጥፎ ልማዳችን ነው።
ግዴለም! ምሥጢራዊ ነገሮችን ለማወቅ መጓጓት የሰው ልጅ ባህሪ ነው እንበል! ቢያንስ ግን የዩትዩብ ተደጋጋሚ ውሸት ግልጽ ማጭበርበሪያ መሆኑ እየታወቀ እንዴት ሰው ደጋግሞ ይሸወዳል? እንደዚያ የሚያደርጉት እኮ ውሸት መሆኑን እያወቅንም ቢሆን ስለምናይላቸው ነው።
ኢትዮጵያ ቴሌቪዥን ወይም ፋና ወይም ዋልታ ወይም ሌላ ‹‹ሜይንስትሪም›› ሚዲያ እንደዚያ አይነት ርዕስ ቢሰጥ ምናልባት የምርመራ ዘገባ ሰርተው ነው በሚል ያጓጓል፤ ሀሰት ቢሆን እንኳን ግልጽ የሆነ ተጠያቂነት ያለባቸው እና ለመውቀስም ባለቤት ያላቸው ስለሆኑ አያደርጉትም ብለን እናምናለን። በአጠቃላይ መረጃውን ለማየት እንገደዳለን።
ሰው እንዴት በአንድ ግለሰብ የሚመራ፣ የኤዲቶሪያል ሕግ የሌለው፣ ለአገር ግንባታ ሳይሆን ለግለሰብ ሳንቲም መልቀሚያ ተብሎ የተከፈተ የማህበራዊ ሚዲያ ገጽ ይሸውደዋል ? የዚያ ገጽ (ቻናል) ባለቤት እኮ ግለሰብ ነው። በአንድ ግለሰብ ስሜት ብቻ የሚመራ ነው። ስለዚህ ብዙ ተመልካች ያስገኝልኛል ያለውን ነገር ሁሉ ያደርጋል።
እዚህ ላይ ግን በኃላፊነት የሚሰሩ የሉም ማለቴ አይደለም። ፈቃድ አውጥተው፣ ብቁ ባለሙያዎችን ቀጥረው፣ በትልልቅ መገናኛ ብዙኃን የብዙ ዓመት ልምድ ያላቸው ጋዜጠኞች የሚሰሩባቸው የዩትዩብ ቻናሎች መኖራቸውን አምናለሁ። እነርሱ እንዲህ አይነት የበሬ ወለደ ዜና አይሰሩም፤ እያወራሁ ያለሁት ተመልካች ለማግኘት ብቻ ብለው ስለሚያጭበረብሩት ነው።
ሲጀመር በተገቢው የጋዜጠኝነት ሙያ የሚሰራ ዜና የሚጮህ ርዕስ የለውም። አንድ የዜና ርዕስ ጯሂ ከሆነ የውሸት ወይም የተጋነነ የመሆኑ ምልክት ነው። አርዕስተ ዜና ይዘቱን ጠቅልሎ የሚነግር ጥቅል ርዕስ ነው። በዜናው ውስጥ የማይገኝን ነገር መግለጽ የለበትም። በዩትዩብ ውስጥ ግን እንዲህ አይነት የነጭ ውሸት ርዕሶች የተለመዱ ሆነው ሳለ በተደጋጋሚ የሚሸወዱ ሰዎች ናቸው የሚያሳዝኑት።
በበኩሌ በዩትዩብ ርዕስ ተሸውጄ አላውቅም። ገና ርዕሱን አይቼ ነው የሚገባኝ። ‹‹አዳምና ሔዋን ከገነት ሲባረሩ ለማየት ሊንኩን ይጫኑ›› አይነት የማይመስሉ ነገሮችን ለማየት ደቂቃ አላባክንም። ምክንያቱም ቀደም ሲል እንዳልኩት እውነተኛ ነገር ጯሂ ርዕስ አይጠቀምም።
ሚዲያን የመከታተልና የማወቅ ልማዳችን ለማጭበርበር ምቹ ነው። የውሸት ርዕስ የሚጠቀሙ ሰዎች ሌላ የተለየ ዓላማ ኖሯቸው ሳይሆን ሳንቲም ለማግኘት ነው። የፖለቲካ ዓላማ ያላቸው በሚፈጠረው ውዥንብር የሚጠቀሙት ነገር ስላለ ነው። እነዚህኞቹ ግን በተመልካች ብዛት ክፍያ እንደሚገኝ ስለሚያውቁ ለክፍያው ነው። ለፖለቲካ አጭበርባሪዎችም ሆነ ለሳንቲም አጭበርባሪዎች ምቹ ሁኔታ የፈጠረላቸው ግን ተመልካቹና ተከታዩ ነው።
መነሻዬ የአርቲስት ታሪኩ ብርሃኑ (ባባ) ሕልፈት ነውና በዚሁ እግረ መንገድ ሌላም ትዝብት ላንሳ። ብዙዎች ‹‹በሕይወት እያለ ነበር ማገዝ የነበረባችሁ›› እያሉ ሀዘናቸውን የሚገልጹ ሰዎችን ይወቅሳሉ። ለሞት የተዳረገው እነዚህ ሀዘናቸውን የሚገልጹ ሰዎች ባለመርዳታቸው ነው እያሉ ይወቅሳሉ።
አዎ! ሰውን ማገዝ ያለብን በሕይወት እያለ ነበር፤ ዳሩ ግን አንዳንድ ጊዜ ደግሞ በአጋዥ ብዛት የማይተርፍ ሕይወትም አለ። በአጋዥ እጦትም ሆነ ከአቅም በላይ በሆነ ችግር ሰው ከሞተ ያላገዘ ሰው ሀዘኑን አይግለጽ አይባልም። በዚያ ላይ በአንድ ታዋቂ ሰው ሞት ጥልቅ ሀዘን የተሰማው ሁሉ ሰውየውን የማገዝ ዕድል አለው ማለት አይቻልም። ማገዝ ማለት የግድ በገንዘብ ብቻ እንዳልሆነ ግልጽ ነው፤ ሰው በቻለው ሁሉ ያግዛል። ዳሩ ግን የሰውየው ሕይወት ለብዙዎች ግልጽ ላይሆን ይችላል። ሰውየው የሞተው መታከሚያ አጥቶ ነው? ከጎኑ የሚሆን ሰው አጥቶ ነው? የሚለውን የሚያውቀው በጣም ቅርብ የሆነ ሰው ብቻ ነው። አንድ የማደንቀው አርቲስት በድንገት መሞቱን ስሰማ ልደነግጥና ሀዘኔን ልገልጽ እችላለሁ፤ ቀደም ብየ ማገዝ ነበረብኝ ለማለት ግን ምን ሁኔታ ላይ እንዳለ የማውቅ ከሆነ ብቻ ነው።
ይሄ ሁሉ ወቃሽ ይህን ያህል ከተቆጨ አሁንም አጋዥ አጥተው የሞት አፋፍ ላይ ያሉ አሉና እነርሱን በማገዝ አዲስ ልማድ መፍጠር ይቻላል። እርግጥ ነው በዚህ በኩል እንኳን አንታማም፤ ኢትዮጵያውያን መረዳዳት የምርም ባህላችን ነው። ይሄ ሁሉ እርዳታ ፈላጊ እያለ እንኳን ሰጪ አለ። ዳሩ ግን ‹‹በሽታውን ያልተናገረ መድሃኒቱ አይገኝለትም›› እንደሚባለው ችግሩ ሳይታወቅ ሕይወቱ ያለፈ ሰው ግን አድናቂዎቹ ምንም ማድረግ አይችሉም።
መነሻዬ በሀሰት ዜና ብዙ ተመልካች የሚያገኙ ናቸውና መደምደሚያየም እሱ ነው። ከቁም ነገር እና በመረጃ ከተደገፉ ፕሮግራሞች በላይ አሉባልታና ውሸት የምንወድ ከሆነ የምንፈልገውን ነው የሚያቀርቡልን፤ አሉባልታ ደግሞ የመውጣትና መውረድ ልፋት አይጠይቅም፤ ስለዚህ እንዲህ አይነት ደላላዎችን መቅጣት የሚቻለው ባለመከታተል ነውና እኛው ልክ እናስገባቸው!
ዋለልኝ አየለ
አዲስ ዘመን ታኅሣሥ 5 /2015