በኢትዮጵያ የሚገኘውን የአይኮግ ኩባንያ ፕሮጀክት ሥራ አስኪያጅ ስትሆን፤ ብዙዎች ኢትዮጵያዊት ‹‹ቴክ ንግስት›› እያሉ ይጠሯታል። አንዳንዶች ደግሞ ወጣቷ የቴክኖሎጂ ፈር ቀዳጅ የሚል ስያሜን ሰጥተዋታል። በዚህም እ.ኤ.አ በ2019 አይነ ግቡ አፍሪካዊ ሥራ ፈጣሪ ተብላ ተካታለች ቤተልሄም ደሴ። ይህ ሁሉ ውጤት ግን ሁሉ ነገር አልጋ በአልጋ ሆኖ የመጣላት አልነበረም። ብዙ ለፍታና ግራ ነው ለዚህ የበቃችው። በተለይም በገጠሪቷ ኢትዮጵያ ማለትም ሐረር ውስጥ ተወልዳ ማደጓ ተማሪዎች ቴክኖሎጂውን ለማወቅ ያላቸው የሳሳ እድል እንድትመለከተው አድርጓታል።
ዛሬ የገጠሩ ተማሪ ከሁሉም በላይ በቂ እውቀት የሚያስጨብጥ ነገር ያስፈልገዋል እንድትል ያስቻላትም ትናንት ያየችው ነገር ነው። ትናንት ልክ እንደከተማው ልጅ ቴክኖሎጂውን በሚፈለገው ደረጃ አውቃ አልተጓዘችም። እንደውም የአባቷ የኮምፒውተር መሸጪያ ሱቅ ባይኖር ኖሮ የዛሬዋን ቤተልሄም ላታገኛት ትችል ነበር። ስለዚህም ትግሏ ሁልጊዜ የማህበረሰብ ችግር የሚፈታ ቴክኖሎጂ መፍጠርን ያለመ ነው።
የራስ ጥረት ካልታከለበት በስተቀርም ምቹ ነገሮችም ቢኖሩ ከውጤት ላይ መድረስ እንደማይችል በሚገባም አይታበታለች። እንደሚታወቀው ገጠር ላይ መማር በተለይም ከቴክኖሎጂ እውቀት ጋር በተያያዘ ብዙ ፈተናዎች አሉት። አንዱ የኮምፒውተር እውቀት ጉዳይ ሲሆን፤ ትምህርቱ እንኳን የሚሰጠው በንድፈ ሃሳብ ነው። ስለዚህም ኮምፒውተር ለመንካት ቀርቶ ለማየትም አዳጋች ነው። እናም ማውዝ ምንድነው፣ ኪቦርድስ፣ ሮቦት ምንድነው ወዘተ ቢባል በንድፈሃሳቡ የተማሩትን እንጂ መልኩንና እንዴት እንደሚሰራበት ማብራራት አይቻላቸውም። ቤተልሄም ግን የአባቷ የኮምፒውተር መሸጫ ሱቅ ይህንን ነገር ሁሉ ፈቶላታል።
ልምምዷ የጀመረው አባቷ ሱቅ ለሽያጭ የመጣውን ኮምፒውተር በመክፈት፣ በመዝጋትና በመነካካት ነው። ይህም ዘጠኝ ዓመቷ ላይ የሆነ ነው። እስከ 10 ዓመቷ ድረስም ዘልቃበታለች።
በ10 ዓመቷ ኮድ ማድረግ የጀመረችው ቤተልሄም፤ የብዙዎችን ቀልብ ሳበች። መምህሮቿም ሆኑ የአካባቢው ሰዎች ይህቺ ልጅ ከፍ ያለና በደንብ እውቀቷን ልታዳብር የምትችልበት ቦታ መሄድ አለባት አሉዋት። ቤተሰብም ቢሆን በዚህ ይስማማልና አዲስ አበባ ሄዳ እንድትማር አመቻቹላት። ይህ ደግሞ በ12 ዓመቷ “ኢንሳ”ን እንድትቀላቀል አደረጋት። ቦታው ምን ያህል ብቁ እንደሚያደርግ መናገር ለቀባሪው አረዱት ነውና ቤተልሄምም ጥሩ ልምድን ቀሰመችበት።
በ21 ዓመቷ የአርቴፊሻል ኢንተለጀንስ ቴክኖሎጂን ከአይኮግ የሮቦት ቤተሙከራ ጋር በመሆን ‹‹ሶፊያ›› የተሰኘችውን ሮቦት ግንባታን ጨምሮ በርካታ ሥራዎች ላይ እንድትሳተፍም አገዛት። በዚህም በግሏ አራት የሶፍትዌር መተግበሪያዎችን ሰርታ የባለቤትነት ማረጋገጫ እንድታገኝ ረዳት። ከሰራቻቸው መተግበሪያዎች ውስጥ መንግሥት የሚጠቀምበት የመስኖ አገልግሎት የሚሰጡ ወንዞችን በካርታ ላይ ለማመላከት የሚያስችለው መተግበሪያ አንዱ ነው።
ቤተልሄም ኢትዮጵያዊት ዌብ ዲዛይነር እና ሞባይል ቴክኖሎጂ ዴቨሎፐር ስትሆን ፣ በፕሮጀክቶቿ ከ20ሺህ በላይ ሕፃናትን ኮድ ማድረግን በማስተማር የኢትዮጵያን ቴክኖሎጂ ወደፊት እንዲጓዝ አስችላለች። ይህንን በማድረጓም በርከት ያሉ የማህበረሰብ ችግሮች እንዲፈቱ ሆነዋል። በተለይም የገጠሩ አካባቢ የቤቴልሄም ዕውቀት ተጠቃሚ መሆን ጀምሯል።
በመማር ማስተማሩ ሥራም ቢሆን የላቁ ተግባራትን በመከወን ጠንካራ ትውልድ እንዲፈጠር ሰርታለች። ለዚህም አብነት የምናደርገው ‹‹ዲጅ ትራክ ኢትዮጵያ›› የተሰኘው ፕሮጀክት ነው። በፀሐይ ሃይል የሚሰራ ተንቀሳቃሽ የኮዲንግ እና ሮቦቲክ ቤተ- ሙከራ ሲሆን፤ የሮቦቲክ ሳይንስ ማሰልጠኛ ማዕከልን የያዘ ነው። ተማሪዎች በቴክኖሎጂ የዳበሩ እንዲሆኑ ያስችላል። በተለይም በገጠሪቱ ኢትዮጵያ የሚኖሩት። ምክንያቱም ቤተ ሙከራው መብራት አንጡ አይልም፤ ክፍል ፈልጉልኝም አይባልበትም። ተማሪዎች በውስጡ ገብተው በቴክኖሎጂ እንዲጠቀሙ የሚያደርግ ብቻ ነው። ይህ ደግሞ ቴክኖሎጂውን በሚገባ የሚረዳ ትውልድ ለማፍራት ሰፊ ዕድል ይሰጣል።
‹‹አሁን ያለው ትውልድ በትምህርቱ ዘርፍ ብዙ ነገሮች የተመቻቹለት ነው። በዚህም ጠንካራ ብቻ ከሆነ ነገሮችን በቀላሉ ማድረግ ይችላል። ራሱን ለመቻል የመፍትሄ አፈልቂ ለመሆንም ያቀርበዋል። የበለጠ አማራጭ እያገኘ የበለጠ እድልን መስጠት የሚችልበት ላይም ነው። ምክንያቱም ቴክኖሎጂውን ተጠቅሞ የማይሰራው ነገር የለም። እናም እንደ ሀገር ኃላፊነት ያለበት እንደሆነ አምኖ በቻለው ሁሉ ማህበረሰቡን ማገልገል ይኖርበታል። ለዚህ ደግሞ ጠንካራ ተማሪና ቴክኖሎጂውን ለራሱ በሚመጥን መንገድ የሚጠቀም መሆን አለበት።›› ትላለች የቴክኖሎጂ ንግስቷ።
ቤተልሄም ሌሎችን መርዳት የሚቻለው ራስን በትምህርት አብቅቶ መውጣት ሲቻል ብቻ ነው የሚል አቋም ያላት ሲሆን፤ የሚፈልጉት ነገር ላይ ብዙ ርቀት ሄዶ መማር ከተቻለ ለራስ ብቻ ሳይሆን ለሌሎችም መፍትሄ መሆን ይቻላል ባይ ነች። ምክንያቱም እርሷ ሌሎችን ማስተማር የቻለችው ያስተማራት ማህበረሰብ ስላለ ነው። እርሷ ከብዙዎች ጋር አብራ ማደግ የቻለችው ጥረቷ ከቀረበላት ትምህርት ጋር ተዳምሮ ነው። ስለዚህም ተማሪዎች በተማሩት ልክ መስራትና የመፍትሄ አካል መሆን እንደሚገባቸው ትመክራለች።
ቤተልሔም ቴክኖሎጂን እንዳለ መቀበል ያስፈልጋል በሚለው ሃሳብ አትስማማበትም። ምክንያቷ ደግሞ ሁለት ነገር ነው። የመጀመሪያው ተማሪ የሚማርበትና የሚመራመርበት አይሆንም የሚለው ሲሆን፤ ሁለተኛው የማህበረሰቡን ችግር አይፈታም የሚለው ነው። አገር በቀል መፍትሄዎች ካልታከሉበት የሰው ማንነትን ያሲዛል እንጂ የራስን ሥራ አያሰራምም ባይ ነች። ቴክኖሎጂዎች ሲሰሩ እንደአገሪቱ ነባራዊ ሁኔታ ተቃኝተው መሆን አለባቸው። ስለሆነም ለእኛ የሚያስፈልገን እኛን የሚመስል ቴክኖሎጂ ነው ትላለች።
የተማረውን በተግባር ለመተርጎም ፈቃደኛ የሆነ ተማሪ ካለ አገራችን ብዙ ነገሯ የተመቸ ነው። ማለትም የተፈጥሮ ሁኔታዋ፣ የአስተሳሰብ ባለጠጋነቷ፣ የሰው ሳይሆን የራስን አጥብቃ መውደዷ ብዙ የመፍትሄ አካል ለመሆን የሚያስችለን ነው። ምክንያቱም እነዚህ ባህሪያት ለምንሰራው ሥራ ተጽዕኖ ፈጣሪ ናቸው። ከዚያም ቴክኖሎጂውን በትምህርት እንዲታገዝ እናደርገውና ሁሉም እንደፍላጎቱ እንዲጠቀም ማስቻል ላይ እናደርሰዋለን። ይህ ደግሞ በነጻነት የምንለምዳቸውና በአዲስ መልክ የምንሰራቸው ብዙ የፈጠራ ውጤቶች እንዲኖረን ያደርገናል። አንድ ተማሪ ተማረ የሚባለውም በዚህ ደረጃ ሲጓዝ ብቻ እንደሆነ ታስረዳለች።
ቤተልሔም ቴክኖሎጂ እንደ ነዋሪው ባህሪ፣ ወግና ልምድ የተወሰነ ነው። ኢትዮጵያን ደግሞ አይደለም እንደአገር እንደ ሰፈርም ቢታዩ የብዙ ባህል ባለቤቶች ናቸው። እንደ ባህሪያቸው የሚሄድ ቴክኖሎጂ ያስፈልጋቸዋል። የአካባቢው ነዋሪ ቴክኖሎጂውን ቢፈጥረው የበለጠ የማህበረሰብ ተጠቃሚነት ይኖራል። ለዚህም ነው ቴክኖሎጂ ሰፈር ድረስ ወርዶ መሰራት አለበት የሚባለው።
‹‹እኛ አሁን የሚያስፈልገን ራሳችንን እያሰለጠንንና ራሳችን እየተማማርን ያለብንን ጎዶሎ መድፈን ነው። ከሌሎች በምናገኘው እውቀት እኛነታችንን የሚመጥንና ችግሮቻችንን የሚፈታ ሥራ መስራት ይገባናል። ስለሆነም በገጠሪቱ ኢትዮጵያ የሚኖሩ ተማሪዎች አማራጮችን እያዩ ቴክኖሎጂውን ለመልመድ ጥረት ማድረግ አለባቸው። በተለይ ደግሞ የሚማሩትን በተግባር ለመተርጎም መሞከር የበለጠ አዋጭነት አለው›› የምትለው ‹‹አይኮግ ኤኒዋን ካን ኮድ›› የተሰኘው አገር በቀል ድርጅት መስራችና ዋና ሥራ አስፈጻሚ ቤተልሄም፤ ‹‹ዲጅ ትራክ ኢትዮጵያ››ን ከሕዋዌ ኢትዮጵያ ጋር በመሆን የሰራችውና ወደተግባር እንዲገባ ይፋ ያደረገችው የእርሷ ፈተና የሌሎች ልጆችም እንዳይሆን ነው።
ይህንን ተንቀሳቃሽ የኮምፒዩተር ፕሮግራሚንግ እና ሮቦቲክ ሳይንስ ቤተ – ሙከራ መፈጠሯ ደግሞ ቴክኖሎጂውን እያዩና እየነካኩ የሚማሩ ተማሪዎችን ያበራክታል። ፈጣሪ ትውልድንም ለማፍራት ያግዛል። ከሁሉም በላይ ከንድፈ ሃሳብ የወጣ ትምህርት ለመስጠት ያስችላል። ምክንያቱም ገጠሪቱ አካባቢ ላይ ያሉ የሳይንስ ትምህርቶች በቂ የቴክኖሎጂ መማሪያ ቁሳቁስ ስለሌላቸው ትምህርቶች የሚሰጡት በንድፈሃሳብ ብቻ ነው። እናም ይህ ተንቀሳቃሽ ቤተሙከራ ይህንን ችግር ከመፍታት አኳያ የማይተካ ሚና እንዳለው ቴክኖሎጂው ይፋ በተደረገበት ወቅት የትምህርት ሚኒስትሩ ፕሮፌሰር ብርሃኑ ነጋ ሲናገሩ ነበር።
እርሳቸው እንዳሉት፤ ኢትዮጵያ እንደ አውሮፓውያን አቆጣጠር በ2025 የዲጅታል ቴክኖሎጂን ተደራሽ የማድረግ እቅድ ይዛለች። በዚህ ደግሞ ብቁ፣ ተወዳዳሪና ሥራ ፈጣሪ ዜጎችን ታፈራለች። እናም ይህንን ለማሳካት አሁን እየታዩ ያሉ የፈጠራ ሥራዎች የሚበረታቱ ናቸው። ይፋ የተደረገው የቴክኖሎጂ ውጤትም እጅግ ጠቃሚ ነው። በተለይም የተመረቀው ተንቀሳቃሽ የኮምፒዩተር ፕሮግራሚንግ እና ሮቦቲክ ሳይንስ ቴክኖሎጂ በመላ አገሪቱ የሚገኙ ተማሪዎች ከልጅነታቸው ጀምሮ የቴክኖሎጂ ዕውቀትና ክህሎት እንዲጨብጡ ዕድል ይሰጣል። ምክንያቱም ትምህርት ሚኒስቴር ከቻይናው ቴሌኮሙኑኬሽንና የኤሌክትሮኒክስ ዕቃዎች አምራች ሕዋዌን ጨምሮ ከበርካታ በዘርፉ ከተሰማሩ ኩባንያዎች ጋር በቅርበት እየሰራ ነውና በቀላሉ ፍላጎታቸውን ያሟላላቸዋል።
በቴክኖሎጂው የኮዲንግና የሮቦቲክስ ክህሎት ከጊዜ ወደ ጊዜ አስፈላጊ እየሆነ መምጣቱን የሚያነሱት ደግሞ ‹‹በአይኮግ ኤኒዋን ካን ኮድ›› የተሰኘው አገር በቀል ድርጅት ፕሮግራም ፕላነርና ‹‹ዲጅ ትራክ ኢትዮጵያ›› የፕሮጀክት ኃላፊ ጳውሎስ ብርሃኑ ናቸው። እርሳቸው እንደሚሉት፤ ቤተ- ሙከራው ኢትዮጵያ በኮምፒዩተር ፕሮግራሚንግና ሶፍትዌር ዘርፍ ያለባትን የሰው ኃይል ችግሯን ለመቅረፍ ያስችላታል። በተለይም ‹‹ዲጅ ትራክ ኢትዮጵያ›› በዘጠኝ የክልል ከተሞች ላይ ለሰባት ዓመታት ስልጠና የሚሰጥ መሆኑ ብሱ ተስፋ የሚሰጥ ነው። በገጠሪቱ ኢትዮጵያ የሚኖሩ ተማሪዎችን ከማገዝ አኳያም ትልቅ አቅም ይፈጥራል። ምክንያቱም ቤተ ሙከራው በውስጡ ኮምፒውተር፣ ሮቦቶችን፣ ቴሌቪዥንና ማስተማሪያ ሰሌዳን ጭምር የያዘ ነው። በተጨማሪም በርካታ ዲቫይዞች አሉት። ስለዚህም የተማሪዎችን የዲጅታል ክህሎት ያዳብራል። ዲቫይዞቹ ከኮምፒውተር ስልጠና ባሻገር ተማሪዎች በሳይንሱ መስክ የተሻለ ውጤት የሚያመጡበትን ሁኔታ የሚያመቻቹ ናቸው። ምክንያቱም ስልጠናውን ከወሰዱ በኋላ ተማሪዎች ፍላጎታቸውን ለይተው ምርጫቸውን እንዲያስተካክሉ ያግዛቸዋል። የችግር ፈችነት ክህሎታቸውንም ያዳብርላቸዋል።
የመጀመሪያው የሙከራ ተግባር የሚከወነው ለሁለተኛ ደረጃ ተማሪዎች ትምህርቱን በመስጠት ሲሆን፤ መሰረታዊ የቴክኖሎጂ ክህሎቶችን ታሳቢ የሚያደርግ ነው። እንደሚታወቀው አብዛኞቹ ተማሪዎች ዩኒቨርሲቲ ወይም ኮሌጅ ሲገቡ ፈተና የሚሆንባቸው የዲጅታል አጠቃቀም ጉዳይ ነው። እናም ይህንን ለመፍታት ቅድሚያ የሚሰጣቸው በመሆኑ ብዙ ተማሪዎችን ከፈተና ይታደጋቸዋል ይላሉ አቶ ጳውሎስ።
ተንቀሳቃሽ ዲጅታል ቤተ ሙከራው ስልጠናውን የሚሰጠው በአንድ ቦታ ላይ ቢያንስ ሁለት ሳምንት በመቆየት ሲሆን፤ ብዙዎች ጋር እንደሚደርስም ይታመናል። ድርጅቱ የሚሰራቸው ሥራዎች ደግሞ ተመጋጋቢነት ያላቸው ስለሆኑ ተማሪዎችን አሰልጥኖ ብቻ አይቆምም። ሶልቪትና ሰመር ካንፕ የሚባሉ ፕሮጀክቶችም አሉ። በእነዚህም ሥራቸው ውጤት እስኪያገኝ ድረስ ክትትል ይደረግበታል። ኮዲንግ ክለብም ስላለ በቋሚነት ሥራውን እንዲለማመዱት ይሆናልም ብለውናል።
ብዙ ሃሳብ ያላቸው ተማሪዎች በአገሪቱ ሁሉም አካባቢ ላይ አሉ። እድል ግን የላቸውም። እናም በኢንኮዲንግና ሮቦቴክስ ቴክኖሎጂ ሁሉም ጋር በመድረስ የእድላቸው ተጠቃሚ ማድረግ ላይ እንሰራለን ያሉት አቶ ጳውሎስ፤ ለዚህም ‹‹ዲጅ ትራክ ኢትዮጵያ›› ከ75 ሺህ ዶላር በላይ ወጪ ተደርጎበት እንዲሰራበት ሆኗል። ይህ ደግሞ በመጀመሪያው ዙር ብቻ ከ3 ሺህ 500 በላይ ተማሪዎች ተጠቃሚ ይሆኑበታል። ተንቀሳቃሽ ቤተ- ሙከራው በዘጠኝ ክልሎች ተዘዋውሮ ለሚሰጠው ስልጠናም ከሁለት ሚሊዮን ብር በላይ በጀት ተይዞበታል።
ተማሪዎች አሁን ካለው ዘመን እኩል እንዲራመዱና የማህበረሰብ ችግር ፈቺ እንዲሆኑ ከመንግሥት ባሻገር ሌሎች ድርጅቶችም ቢሰሩ መልካም እንደሆነ ያነሳሉም። ትውልድን ማፍራት አገርን መገንባት ነውና ዛሬ ላይ እንዲህ አይነት ሥራዎች ያስፈልጉናል። እናም መንግሥት ይስራው ከሚል አስተሳሰብ ሁሉም ሰው ወጥቶ፤ ተማሪዎችም የሚመጣላቸውን እድል ተጠቅመው ደረጃችንን ከፍ ማድረግ አለብን ሲሉ መልዕክታቸውን ያስተላልፋሉ። እኛም መልዕክቱ ለሁላችንም ይሁን በማለት ሃሳባችንን ቋጨን። ሰላም!!
ጽጌረዳ ጫንያለው
አዲስ ዘመን ህዳር 26/2015