አቶ ኢብራሂም አሊ ሁሴን ይባላሉ። ነዋሪነታቸው ሱማሌ ክልል ሲሆን፤ አራት የመጀመሪያ ደረጃ ተማሪ ልጆች አሏቸው በወረዳቸው የወላጆች ተማሪ መምህራን ጥምረት (ወተመህ) ተጠሪ ናቸው። ልጆቻቸውን በተጀመረው የተማሪዎች ምገባ ተጠቃሚ ያደረጉት አቶ ኢብራሂም ምገባውን በተመለከተ ይህንን ይላሉ። “ምገባው የአምላክ በረከት ነው። ምክንያቱም ብዙ ነገራቸውን አቅሎልናል። ልጆቻችን በትምህርት ቤት መመገባቸው ምግብ ፍለጋ የሚደረገውን ጉዞ ቀንሷል። በወጪ ላይም በእጅጉ ለውጥ አምጥቷል”ይላሉ።
ክልሉ ብዙ አርብቶ አደር ማህበረሰብ ያለበት እንደመሆኑ ብዙ ጊዜ ልጆቸን ይዞ ለራስም ለከብቶችም ምገብና ውሃ ፍለጋ ከቦታ ቦታ መንቀሳቀስ የተለመደ ነው በዚህም ምክንያት ልጆችን ወደ ትምህርት ቤት ለመላክ ያስቸግራል። አሁን ግን ለልጆች ተብሎ የሚታሰበው የምግብ ፍላጎት በመንግስትና በረጂ ተቋማት አማካኝነት ስለተቃለለ እፎይታን አግኝተዋል። ይህ እድል በሁለት ነገር እንዳተረፋቸውም አቶ ኢብራሂም ያምናሉም። የመጀመሪያው ለልጆቻቸው ምግብ ሰጥቶ ትምህርታቸው ላይ ትኩረት እንዲያደርጉ ማስቻሉ ሲሆን፤ ሁለተኛው ለልጆች ምግብ ብለው የሚያስቡት ወጪን ሸፍኖላቸዋል።
የአቶ ኢብራሂም ልጆች ምገባው ከመጀመሩ በፊት ቁርስ ሳይበሉ ወደ ትምህርት ቤት ስለሚሄዱ ትምህርታቸውን በአግባቡ አይከታተሉም ነበር። አንዳንድ ጊዜም መቅረት ይፈልጋሉ። ይህንን ያወቁት አባትም ነገሮችን ለማስተካከል ቢጥሩም ምንም አይሞላላቸውም። አሁን ችግራቸው የተፈታው ምገባው ከተጀመረ በኋላ ነው።
እርሳቸው እንደሚሉት፤ አሁን የወላጆች እፎይታ በብዙ ነገር እየታየ ነው። ልጆቻቸውን ማስተማር ብቻ ሳይሆን መመገብ የማይችሉ ጭምር ነገሮች ተስተካክሎላቸዋል። ተማሪዎችም ቢሆኑ ከዚህ ቀደም ሥራ ሰርተው ወላጆቻቸውንና ራሳቸውን ማገዝ እንጂ መማርን አያስቡም ነበር። ተረዳድተው የበረሃውን ችግር መመከት ካልቻሉ ነገሮች ቀላል ስለማይሆኑ። እናም እነርሱም ሆኑ ቤተሰቦቻቸው በርሃብ እንዳያልቁ መማርና ማስተማርን ትተው ነገሩን ሆድን መሙላት ላይ አድርገው ቆይተዋል። አሁን ግን ነገሮች ሁሉ ተለውጠው ተማሪዎች የምንመገበው አይሉም፤ ቤተሰብም ካላገዝከኝ ብሎ አይጠይቅም። ሁለቱም በአንድ ሀሳብ ተስማምተው ኑሮም ቀለል ብሎላቸው ልጆቻቸው ዋና ትኩረታቸውን ትምህርታቸው ላይ ብቻ አድርገዋል ይህ ደግሞ የተማሪዎችን የትምህርት ተሳትፎ በእጅጉ ጨምሯል።
‹‹እኔ የተማሪዎች ወደ ትምህርት ቤት የመሄድ አዝማሚያ ጨምሯል የሚለው በምክንያት ነው።›› የሚሉት አቶ ኢብራሂም፤ የልጆቼን የትምህርት ፍላጎት ሳየው እጅጉን ያስደምመኛል። ምክንያቱም ምገባ መኖሩ ልጆቼን ማወዳደር እንድጀምር አድርጎኛል። ውጤታቸውንም ስመለከት የማልጠብቀው ሆኖ አግኝቼዋለሁ። በትምህርት ውጤታቸው ብቻ ሳይሆን በስነምግባርም ተለውጠዋል። እናም ምገባ ጸባይን ጭምር እንደሚያሻሽል ተመልክቻለሁ ባይ ናቸው።
ሌላው ያነሱት ነገር በምገባው ምክንያት በአካባቢው ያሉ ሴት ልጆች የመማር ዕድላቸው መጨመሩን ሲሆን ከዚህ ቀደም በሴት ተማሪዎች ዙሪያ መጠነ ማቋረጥ፣ መድገምና አርፍዶ በትምህርት ገበታ ላይ መገኘት ነበር። አሁን ግን ምገባው በመጀመሩ እነዚህ ችግሮች ቀንሰዋል። ልጆቻቸውን ወደ ትምህርት ቤት የሚልኩ ወላጆችም ተበራክተዋል። ትማርና ራሷን ከችግር ታውጣ የሚለው አስተሳሰብም ሰፍቷል። ስለዚህ የወላጆችም ሆነ የተማሪዎች አስተሳሰብ በምገባው ዙሪያ አንድ መስመር ላይ ተገናኝቷል ይላሉ።
ምግባ ከመጀመሩ በፊትና አሁን ያለውን ሁኔታ ሲያነጻጽሩ ልዩነቱ ሰፊ ነው ከዚህ በፊት ልጆቻችን ቁርስ በልተው ስለማይሄዱ በክፍል ውስጥ የሚሰጠውን ትምህርት በአግባቡ አይከታተሉም ውጤታማም አልነበሩም። አሁን ግን የመራብ እና የመርሳት ስሜት ስለማይታይባቸው ውጤታቸውም ጥሩ ነው ሲሉ ያረጋግጣሉ።
አካባቢው የዝናብ እጥረት ያለበት እንደሆነ የሚያነሱት አቶ ኢብራሂም፤ በውሃ እጥረት ምክንያት የምግባ ፕሮግራም የሚቋረጥበት ወቅት አለ። በመንግስትም ይሁን መንግስታዊ ባልሆኑ ድርጅቶች የውሃ ድጋፍ ፕሮግራም ቢካተት የተሻለ እንደሆነ አስተያየታቸውን ይለግሳሉ። ይህ ካልሆነ ግን ከዚህ ቀደም ምገባ ባልነበረበት ወቅት የሚታዩት በትምህርት ላይ የነቃ ተሳትፎ ያለማድረግ፣ መጠነ ማቋረጥ፣ መጠነ መድገድገና ሌሎች ችግሮች እንዳይከሰቱ ሁሉም ድጋፍ አድርጎ በተሻለ መንገድ ልጆቹን ውጤታማ ማድረግ እንደሚያስፈልግ ያስገነዝባሉ።
“እንደኛ በድርቅና በውሃ እጥረት የሚሰቃዩ አካባቢዎች ላይ ምገባ መጀመሩ ዝናብ ኖረ አልኖረ የሚለውን ስጋት ይቀነሰልናል። የተማሪውም ትኩረት ትምህርት ላይ ብቻ ይሆናል፤ እንደ ወላጅ ብቻ ሳይሆን እንደ አገርም ተጠቃሚነታችን ይሰፋል። ምክንያቱም ምገባው የተማረ ዜጋን ከማፍራት አኳያ የማይተካ ሚና አለው። ከሁሉም በላይ እንደ ክልል የተማሪዎችን የመማር ፍላጎት በመጨመር ውጤታማ እንዲሆኑ በማድረግ በኩል ሚናው ላቅ ያለ ነው። እንደ ወላጅም ቢሆን ነገ የሚጦር የሚቀብር ልጅ ማግኘት ነው። የሚንከባከብና ለአገር ባለውለታ የሚሆን ልጅ ማፍራትም ነው›› የሚሉት ደግሞ የሱማሌ ክልል ዳዎ ዞን ሙባረክ ወረዳ ትምህርት ቢሮ ኃላፊ አቶ ሲራጅ አሊ ናቸው።
አቶ ሲራጅ እንደሚሉት፤ ክልሉ በጣም በድርቅ የተጎዳ ነው። ህዝቡም ቢሆን አርብቶ አደር በመሆኑ በአንድ ቦታ ተረጋግቶ ልጆቹን ወደ ትምህርት ቤት ለመላክ እጅግ ይቸገራል። በተለይ ለምግብ የሚሆን ነገር መፈለግ የልጆች ሥራ በመሆኑ የመማር ማስተማሩን ሂደት በአግባቡ ለማከናወን አዳጋች አድርጎት ቆይቷል። ምገባው ሲጀመር ግን ነገሮች ሁሉ ተቀይረው 50 በመቶ የሚሆነው ተማሪ ወደ ትምህርት ገበታው የተመለሰበትን እድል ሰጥቷል።
የመድገም ምጣኔ በብዙ መልኩ ቀንሷል። አሁን ላይ እንደወረዳ ብቻ ቢታይ ከምገባ በፊት የተማሪዎች ብዛት 3ሺ 32 ነበር። ምገባው ከተጀመረ በኋላ ቁጥሩ ወደ 5 ሺ 542 ደርሷል። እንደ ትምህርት ቤት ቢወሰድ እንኳን ጭላቆ ትምህርት ቤት ከምገባ በፊት 340 ተማሪ ያስተምር የነበረ ሲሆን ምገባ ከተጀመረ በኋላ ቁጥሩ ወደ 763 አድጓል።
እንደ ዞንም ሁለት ትምህርት ቤቶች በምገባው እየተሳተፉ በመሆኑ፤ ከምገባ በፊት ከዘጠኝ ሺህ የማይበልጥ ተማሪ የነበራቸው አሁን ቁጥሩን ወደ 12ሺ በላይ ተማሪ በትምህርት ገበታቸው ላይ እንዲገኙ አድርጓል። በተጨማሪም ማርፈድ እንዲቀነስ፣ የተማሪ ውጤት በእጅጉ እንዲሻሻል አግዟል። ይህ ደግሞ ምገባው ከሰጠው ገጸ በረከት አንዱ ነው ብሎ መውሰድ ይቻላል ይላሉ።
ምገባው ላይ በጣም የሚያስቸግረው ነገር የውሃ እጥረት መሆኑን ገልጸው ትምህርት ቤቶች ውስጥ ለምግብ መስሪያ፣ ለመታጠቢያ ጭምር ውሃ ይጠፋል። ይህንን እንደ መንግስት መፍትሄ ቢሰጠው መልካም ነው። መንግስታዊ ያልሆኑ ድርጅቶችም ቢሆኑ ምገባው ላይ የሰሩትን ያህል የውሃ አቅርቦቱ ላይም የተቻላቸውን ቢያደርጉ ነገሮች የበለጠ ይቀላሉ። ተማሪዎችን በአግባቡ እንዲማሩ ከማድረግ አኳያም ሚናቸውን ይወጣሉ።
እንደ ወረዳ ባሉት 39 ትምህርት ቤቶች ቢያንስ ሁለት እና ከዚያ በላይ ሰራተኞች ተቀጥረዋው ምገባውን ያከናውናል። በዚህም ከ80 ያላነሱ ወላጆች የስራ እድልን አግኝተዋል። በሌላ ትምህርት ቢሮ በክላስተር ተዋቅሮ ኤሌክትሪክን የሚተካው የማገዶ እንጨት ማህበረሰቡ የሚያቀርብበትን ሁኔታ አመቻችቷል። የውሃ ችግር ሲያጋጥምም እንዲሁ ማህበረሰቡ እንዲያግዝ ይደረጋል።
እንደ ክልል አሁን ለምገባ የሚቀርበው ሩዝና ሾርባ ነው። አካባቢው ሞቃታማ በመሆኑ ሾርባው ብዙ መቆየት አይችልም። በዚህም ምክንያት እየተደፋ ብክነት እያጋጠመ፤ ተማሪዎች ጋርም በበቂ ሁኔታ እየደረሰ አይደለም። ስለሆነም ድርጅቶቹ ከዚህ ቀደም ቁርስ ላይ እንቁላልን ይጠቀም የነበረ ቢሆንም እሱን በመተካት በሳምንት አንድ ጊዜ የፍየል ስጋ ጥብስ ይቀርብ ነበር አሁን ይህም በአቅም ማነስ ምክንያት የቀረ በመሆኑ ፕሮግራሙን ወደነበረበት መልሶ ማስቀጠል ቢቻል ስራው ውጤታማ እንደሚሆን ይናገራሉ።
በአንዳንድ አካባቢዎች ተማሪዎች በቂ ምግብ ሳያገኙ ወደ ትምህርት ቤት የሚመጡበት፤ ከትምህርት ቤት የሚቀሩበት፤ ወደ ትምህርት ቤት የመጡትም በሚገባ ትምህርታቸውን የማይከታተሉበት ሁኔታ እንደነበረ ከእነዚህ መካከል ደግሞ አፋር ክልል አንዱ እንደሆነ ያነሱት የዓለም አቀፉ ህፃናት አድን ድርጅት (save the children) ውስጥ በአፋር ክልል የትምህርት ቤት ምገባን የሚመሩት አቶ ጀማል ሰይድ ናቸው።
እርሳቸው እንደሚሉት፤ በክልሉ ምገባው እንዲጀመር የሆነው በሦስት ወረዳ ላይ ሲሆን 18ሺ 762 ተማሪዎችን ያቀፈ ነበር። ሆኖም በሚታዩ ችግሮች ምክንያትና በተደረገ ጥናት 20ሺ 460 ተማሪዎች በምገባው ተጠቃሚ እንዲሆኑ ተደርጓል። በተጨማሪም አፋር ክልል ግጭት የተፈጠረበት አካባቢ በመሆኑ 18ሺ10 ተማሪዎችን ብስኩትና ውሃ በመስጠት ተጠቃሚ የሚሆኑበትን እድል በማመቻቸት 12 ወረዳዎች ላይ መድረስ ተችሏል። በአጠቃላይ እንደ አፋር ክልል በምገባው አገልግሎት ተጠቃሚ የሆኑት ተማሪዎች ከ38 ሺህ በላይ እንዲሆኑ አድርጓል።
ምገባ ምግብ ማቅረብ ብቻ እንዳልሆነ የሚያነሱት ኃላፊው፤ ምገባውን ለማሳለጥ ወሳኝ የሆኑ አገልግሎቶችም ያስፈልጋሉ። ከእነዚህ መካከልም ውሃ በዋናነት የሚጠቀስ ነው። ስለዚህ “የዋሽ “ አገልግሎት የሚጀመርበትን ሁኔታ ተፈጥሯል። የኮንስትራክሽን ስራዎች ማለትም እንደ ማብሰያ ቤት “ኩሽና” ፣ መጸዳጃ ቤቶች መገንባት፤ በክልሉና በትምህርት ሚኒስቴር ፈቃድ መሰረትም የመመገቢያ አዳራሾችን መስራት ተችሏል። በተጨማሪም መምህራን የተሻለ ነገር ሲያገኙ ነውና ተማሪዎችን በአግባቡ የሚያስተምሩት የትምህርት ቤቱ ማህበረሰብ በአጠቃላይ የምገባ አገልግሎቱ ተጠቃሚ የሚሆንበት ስርዓት ተዘርግቶም ሲሰራ እንደቆየ ያስረዳሉ።
የግሎባል ፓርትነርሺፕ ፎር ኤጁኬሽን ተወካይ ዶክተር ሰበረታ ድሃር በአቶ ጀማል ሀሳብ ይስማማሉ። ፕሮጀክቱ ጠቃሚነቱ አጠያያቂ አይደለም ምክንያቱም በአፈጻጸም ደረጃ ተጠቃሚ ካደረጋቸው የትምህርት ቤቶችና የተማሪ ብዛት አንጻር ሲታይ ከእቅድ በላይ ነው። በተለይ በአሁን ወቅት በግጭት ምክንያት ጉዳት በደረሰባቸው አካባቢዎች ውስጥ በሚገኙ ህጻናት ላይ ያተኮረ ሥራ መስራት ግድ በመሆኑ አሁን 209 ሺ700 ተማሪዎችን ተደራሽ የሚያደርግ አዲስ የአንድ ዓመት ፕሮጀክት ወደ ተግባር መግባቱን ያነሳሉ።
ባለፉት ዓመታት በግሎባል ፓርትነርሺፕ ፎር ኤጁኬሽን ድጋፍ ተግባራዊ ሲሆን የነበረው ሁሉን አቀፍ አገር በቀልና አካታች የትምህርት ቤት ምገባ ፕሮጀክት በስኬት መጠናቀቁን በወሩ መጀመሪያ ላይ የተገለጸ ሲሆን፤ በምገባው ከ200ሺ በላይ ተማሪዎች ተደራሽ ተደርገዋል። በመሆኑም ውጤቱ ይበል የሚያሰኝ ሆኖ ተገኝቷልና የዓለም አቀፉ ህፃናት አድን ድርጅት፤ ግሎባል ፓርትነር ሺፕ ፎር ኤጁኬሽን (ጂፒኢ) ከትምህርት ሚኒስቴር እና ክልል አጋር ተቋማት ጋር በመሆን ሲተገብር የቆየው ሁሉን አቀፍ ሀገር በቀልና አካታች የትምህርት ቤት ምገባ መርህ ዳግመኛ በስድስት ክልሎች በተመረጡ 578 አንደኛ ደረጃ ትምህርት ቤቶች የትምህርት ቤት ምገባ አገልግሎት እና ሌሎች ተያያዥ ድጋፎችን ለማስቀጠል የሚያስችል ተጨማሪ የገንዘብ ድጋፍ ጸድቋል።
ድጋፉ በጸደቀበት ወቅት የትምህርት ሚኒስትር ዴኤታ ዶክተር ፋንታ ማንደፍሮ እንደተናገሩት፤ ምገባው ብዙ ነገሮችን እየቀየረ ነው። ትምህርት ሚኒስቴርም ሀገር በቀል የትምህርት ቤት ምገባ ፖሊሲ ማዕቀፍና የመተግበሪያ ስትራቴጂ ቀርጾ እስከ 2030 በሀገር አቀፍ ደረጃ በሁሉም የአንደኛ ደረጃ ትምህርት ቤቶች መርሃ ግብሩን ተግባራዊ ለማድረግ እየሠራ ነው። ይህ ተግባራዊ ሆነ ማለት ደግሞ ወላጆች በመንግስት ትምህርት ቤቶች ላይ መተማመን እንዲኖራቸው ከማድረጉም ባሻገር መጠነ መቋረጥ እንዲቀንስ ያደርጋል፤ ተማሪዎች ትምህርታቸውን ተረጋግተው እንዲከታተሉም ያስችላል።
ስለሆነም የተማሪዎች የምገባ ፕሮግራም አማራጭ ሳይሆን ትውልድን የመቅረጽ ጉዳይ ነውና ሥራው ተጠናክሮ ይቀጥላል። ምክንያቱም ፕሮግራሙ በመማር ማስተማሩ ሂደት ላይ የሚፈጥረው መልካም ተጽእኖ በቀላሉ የሚወሰድ አይደለም። የተማሪዎችን ተሳትፎ ከማሳደግ ባሻገር እንደ ሀገር ውጤታማና ንቁ ዜጎችን ለመፍጠር ያስችለናል። በተለይም በተፈጥሮ እና ሰው ሰራሽ ችግር ምክንያት የተጎዱ አካባቢዎች ላይ የሚኖሩ ተማሪዎችን ከማገዝ አኳያ የማይተካ ሚና ይኖረዋል።
የምገባ መርሃ ግብሩ በአገር በቀልም ሆነ መንግስታዊ ባልሆኑ ድርጅቶች አማካኝነት መሰራቱ ለመማር ማስተማር ሥራው የሚኖረው ፋይዳ በቃላት የሚገለጽ አይደለም። የተጠቀመበት ያውቀዋልና። ስለሆነም ሁሉም ለዚህ ሥራ መሳካት የበኩሉን ያበርክት በማለት ሀሳባችንን ቋጨን። ሰላም!!
ጽጌረዳ ጫንያለው
አዲስ ዘመን ህዳር 12/2015