ኬሪያ ጀማል ትባላለች:: የ18 ዓመት ወጣት ነች:: በድሬዳዋ ከተማ በየማርያም ትምህርት ቤት የ11ኛ ክፍል ተማሪ ስትሆን ወደዚህች ምድር ስትመጣ ጀምሮ ነው ሁለት እጆቿን ያጣችው:: ቢሆንም ግን ለእሷ እግሮቿ በተፈጥሮ የተሰጧት ገጸበረከት ሆነውላታል:: እግሮቿን ልክ እንደእጆቿ መልካም ዕድል አድርጋ ትጠቀምባቸዋለች:: በእግሮቿ ትጽፋለች፣ ትመገባለች፣ ፊቷን ትታጠባለች ልብሷን ማጠቢያም አድርጋቸዋለች::
አካል ጉዳተኛ መሆኗ መጀመሪያ አካባቢ በተለይም ወደትምህርት ቤት ስትሄድ በብዙ መንገድ ፈትኗታል:: ነፃነት የማይሰጣት በርካታ ችግርም ገጥሟታል:: አንዱ በተማሪዎች ዝቅ ተደርጋ መታየቷ ነው:: ይሁንና መብለጧን በተግባሯ ስታሳያቸው ነገሮች ሁሉ ተቀይረዋል:: በዚያ ላይ በትምህርትቤት ያለው የመማር ማስተማር ሥራ ለእርሷ አግዟታልና ዛሬ የደረሰችበትን የክፍል ደረጃ ደርሳለች:: በእርግጥ አካል ጉዳቷ ታይቶ ወደ ከተማ ባትመጣ ኖሮ ነገሮች የተገላቢጦሽ ይሆንባት ነበር:: ከመገለል ባሻገር የትምህርትቤት ቁሳቁስ አቅርቦቱ እጅግ ይፈትናት ነበር:: ሆኖም እናቷና እህቷ ከዚህ የመከራ ሕይወት አላቀዋታል:: ችግሮችን እንድትጋፈጥ አድርገዋታል::
ሌላኛዋ ተማሪና አካል ጉዳተኛ ሀጃኢባ ያሲን ሽኩር ስትሆን፤ እርሷም እንደ ኬሪያ እጇን በተፈጥሮ አጥታ እግሯን የምትጠቀም ናት:: በዘንድሮው የፈተና ጊዜ በአዲስ አበባ ሳይንስናቴክኖሎጂ ዩኒቨርሲቲ የ12ኛ ክፍል ብሔራዊ ፈተናን በእግሯ እየሠራች ብዙዎችን አስደምማለች:: ለዚህ ደግሞ መሠረቱ ብርቱና ምቹ የትምህርት አካባቢ እንዲሁም ጠንካራ የቤተሰብ እገዛ ስላገኘች ነው::
አካል ጉዳተኝነት ትምህርትን ጨምሮ ከማንኛውም ማህበራዊ መስተጋብር እንደማያግድ ታምናለች:: ነገር ግን ብዙ ፈተናዎች እንዳሉበት ታውቃለች:: ቢሆንም ግን እነርሱን የሚያግዝ የመማር ማስተማር ሥርዓት ከተዘረጋለትና ለተግባራዊነቱ ሁሉም ከተጋ የአካል ጉዳተኝነት ችግሮች መፍትሄ እንጂ መከራ አይሆኑም ባይ ናት:: ከእነዚህ ባለታሪኮቻችን የምንረዳው ነገር አካል ጉዳተኞች በትምህርት ዘርፉ በሚገባ ከታገዙ የአሰቡበት ላይ መድረስ እንደሚችሉ ነው:: የተሰጣቸውን ዕድሎች እንደሚጠቀሙም በሚገባ መገንዘብ እንችላለን:: ታዲያ እንደ አገር ምን ምቹ ሁኔታ ተፈጠረላቸው ስንል ሁለት መሠረታዊ ነገሮችን እንድናነሳ እንገደዳለን:: የመጀመሪያው የትምህርት ዘርፉ በአካል ጉዳተኞች ዙሪያ እስከዛሬ ምን ሠራ የሚለው ሲሆን፤ ሁለተኛው የሚሻሻሉት የትምህርት ሥርዓቶች ምን አዲስ ነገር አላቸው የሚለው ነው::
ለአካል ጉዳተኞች የሚሰጥ ትምህርት ትናንት
የአካል ጉዳተኞች ትምህርት እስከ 20ኛው መቶ ክፍለ-ዘመን መጀመሪያ ድረስ በልግስና፣ በዕምነት ተቋማት እና ድጋፍ እየተደረገላቸው የቀለም ትምህርትና የክሂሎት ስልጠና ሲሰጣቸው እንደነበር በታሪክ ተመዝግቦ ይገኛል። በ20ኛው መቶ ክፍለ ዘመን መጀመሪያ ልዩ ትምህርት እንደ አንድ የእውቀት ዘርፍ ተቋቁሟል። በዚህም ጊዜ የተከናወነው መዋቅር በመፍጠር ሥራውን በቅንጅት መምራት ሲሆን፣ ይህም አካል ጉዳተኛ ሕፃናትን እንደአካል ጉዳታቸው ዓይነት ለማስተማር ይቻል ዘንድ ልዩ ትምህርት ቤቶችን ማቋቋም፣ መምህራንን በማሰልጠንና ለትምህርት ሥራው አስፈላጊ የሆኑ መሣሪያዎችን ማሟላት ተጀመረ:: ሆኖም የተደራሽነቱ ጉዳይ አዝጋሚ ነበር። ከዚህ አንጻርም 2012 ዓ.ም የመደበኛው ትምህርት ተሳትፎ 104 ነጥብ 9 በመቶ ሲሆን፣ የልዩ ፍላጎት ትምህርት ተሳትፎው 11 ነጥብ 1 ብቻ እንደነበር መረጃዎች ያሳያሉ::
የልዩ ፍላጎት ትምህርት ነባራዊ ሁኔታ ትንተና ይህንን የትምህርት አገልግሎት በተቀናጀና ሥርዓት ባለው መልክ ለማቅረብ፣ ልዩ ፍላጎት ትምህርትን ለተጠቃሚዎች ተደራሽ በማድረግና የትምህርቱን ጥራት ለማስጠበቅ እንዲቻል በሦስተኛው የትምህርት ዘርፍ ልማት መርሃግብር ውስጥ ተካቶ መተግበሩን ቀጠለ:: ይህንንም እውን ለማድረግ በ1998 ዓ.ም የመጀመሪያው የልዩ ፍላጎት ትምህርት ፕሮግራም ሰትራቴጂ ተዘጋጀና ወደ ሥራው ተገባ:: ዓመታት እየተጠበቁም ችግሮች እየታዩ መሻሻሎች ይደረጉበት ጀመር::
አንዱ የ2004 ዓ.ም ስትራቴጂ ሲሆን፤ ይህንን በተመለከተ የትምህርት ሚኒስቴር ጥናት አካሂዷል:: እናም ጥናቱ እንደሚያሳየው የ2004 ዓ.ም ስትራቴጂ የአካል ጉዳተኛ ዜጎች መብትን መሠረት ያደረገ ትምህርት ሊሰጣቸው ይገባል የሚለውን የአካቶ ትምህርትን መሠረታዊ ፍልስፍናን የያዘ ነው:: በዚህም አካል ጉዳተኞችን ጉዳት ከሌለባቸው ጋር በጋራ እንዲማሩ የሚደረግበትን የማስተማር ዘዴ ፈጥሯል። በተጨማሪም ከቀለም ትምህርቱ ባሻገር ከማኅበረሰቡ ጋር የሚኖሩበትን ሁኔታ የሚያለማምዳቸውን ዕድል ሰጥቷል:: የልዩ ፍላጎት ተማሪዎች በተለያዩ ተጽዕኖዎች የተነሳ ከሌሎች አቻዎቻቸው ጋር በእኩል ደረጃ ተሳትፎ እንዳያደርጉ ሊገድቡ የሚችሉ አካላዊ፣ ኢኮኖሚያዊ፣ ሥነአዕምሯዊ ወይም የስሜት ህዋሳት እክሎች ይገጥማቸዋል። በመሆኑም በትምህርት አሰጣጡ ውስጥም እኩል አካልጉዳተኝነታቸውን ያገናዘበ የትምህርት አሰጣጥ መተግበር ያስፈልጋልና ይህ እንዲሆንም መስመሩን የከፈተ ነበር።
በ2004 ዓ.ም ስትራቴጂ ድክመቶች
ከትምህርት ሚኒስቴር እስከ ወረዳ ትምህርት ጽሕፈት ቤት ድረስ የአካቶ ትምህርትን ለመምራትና ለመተግበር የሚያስችል ወጥ የሆነ አደረጃጀት የለውም:: የልዩ ፍላጎት ትምህርት መምህራን የደረጃ እድገት መሰላል የሥራ መደባቸውንና ስምሪታቸውን በግልጽ የሚያሳይ የአሠራር ሥርዓት አልተዘረጋበትም:: የተጠያቂነት አሠራር ሥርዓትም የለም:: በተለያዩ የትምህርት እርከኖች ላይ የሚገኙ አስፈጻሚና ፈጻሚዎች የስትራቴጂውን ውጤት አተገባበር ለማሳለጥ የነበራቸው ቁርጠኝነትና ግንዛቤ አናሳነው:: የልዩፍላጎት/አካቶ ትምህርት ጉዳዮችን በዕቅድ፣ በጀት ፣በክትትል፣ በግምገማና በሪፖርት ውስጥ አካቶ አይሠራም::
በሁሉም የትምህርት እርከኖች ከፍተኛ የሆነ የልዩፍላጎት ትምህርትና የድጋፍ ስጪ ባለሙያዎች እጥረት ነበረበት:: በመምህራን ትምህርት ተቋማት በመሰጠት ላይ ያሉት የልዩፍላጎት ትምህርት ኮርሶች ንድፈሃሳብ ላይ ያተኮሩ በመሆናቸው ምሩቃኑ የተግባር ክህሎት ውስንነት ይታይባቸው ነበር:: በአካልጉዳተኝነት ዙሪያ ግንዛቤ ለመፍጠር የተደረገው ጥረት ውስን በመሆኑ በባለድርሻዎችና በአብዛኛው ማህበረሰብ ዘንድ የተዛባ አመለካከት በስፋት ታይቶበታል::
አንዳንዶች ካልሆኑ በቀር ብዙዎቹ ክልሎች ለአካል ጉዳተኞች የሚሆን በጀት አይመድቡም:: ግልፅና አግባብነት ያላቸው የመረጃ መሰብሰቢያ መሣሪያዎችም የሉም:: በመረጃ ሰብሳቢዎች ክህሎት ማነሰና ቸልተኝነት ምክንያት ተዓማኒ መረጃ ማግኘት አለመቻሉ፣ አካል ጉዳተኞች የሚፈልጉትን አገልግሎት አለማግኘታቸው፤ በቴክኒክና ሙያ ትምህርትና ሥልጠናና በከፍተኛ ትምህርት ተቋማት ውስጥ የትምህርትና ሥልጠና አገልግሎት የሚያገኙት አካል ጉዳተኛ ወጣቶች በቁጥር አነስተኛ መሆናቸውም ችግር ነበር:: ዕድሉን አግኝተው በመማር ላይ የሚገኙትም ቢሆኑ ለሚያጋጥማቸው የትምህርት መቅሰም ችግር በቂ ድጋፍ አለማግኘታቸው ድክመት እንደነበር ተነስቷል::
የትምህርት ቤቶች ምድረ ግቢና አገልግሎት አሰጣጥ (መፀዳጃቤት፤ ቤተመጻሕፍት፤ የግቢ ውስጥ አቅጣጫ ጠቋሚ ስሌዳ፤ መዝናኛ ስፍራ፤ የስፖርት ማዘውተሪያና መጫወቻ ቦታዎች፣ተዳፋታዊ መተላለፊያ፤ ውሃ መጠጫ ቦታ፤ ወዘተ) ለአካል ጉዳተኛ ዜጎች ተደራሽ አለመሆናቸው፤ የትምህርት ቤቶች የሕንፃ ግንባታ ዲዛይን አካል ጉዳተኞችን ታሳቢ ያደረገ አለመሆኑም ሌላው ችግር እንደነበር ጥናቱ አስቀምጧል::
የመማሪያ-ማስተማሪያ ቁሳቁሶችና ድጋፍ ሰጪ መሣሪያዎች በበቂ ሁኔታ አለሟላታቸው፤ የኢንፎርሜሽን ኮሙዩኒኬሽን ቴክኖሎጂዎችና አጋዥ የቴክኖሎጂ አቅርቦት አለመሟላት፤ በመደበኛ ትምህርት ቤቶች፤ በቴክኒክና ሙያ ትምህርትና ሥልጠና ተቋማት፤ በምልክት ቋንቋ ተርጓሚዎች እጥረት በመኖሩ መሰማት የተሳናቸው ተማሪዎች የምልክት ቋንቋ የትርጉም አገልግሎት ባግባቡ አለማግኘታቸውም ችግር ናቸው ተብለው ከሚጠቀሱት መካከል ተነስተዋል::
የሥርዓተ-ትምህርቱ ይዘቶች፣ የማስተማሪያ ሥነ- ዘዴዎች፣ የመማሪያ-ማስተማሪያ ቁሳቁሶች እና የምዘና ሥርዓት ልዩ የትምህርት ፍላጎት ላላቸው ዜጎች እንደ ፍላጎታቸውና ችሎታቸው ተስማሚ አድርጎ አለመተግበርና አካልጉዳተኛ ጎልማሶች ለትምህርት አገልግሎት ተደራሽ አለመሆናቸው እንዲሁም አወንታዊ ድጋፍ አሰጣጡ ሁሉንም የአካል ጉዳተኞች አለማካተቱም እንዲሁ ድክመት ተደርጎ የተወሰደ ጉዳይ ነው::
በአንደኛ ደረጃ ትምህርት ቤቶች የታቃፊ የአዕምሮ ውስንነት ላለባቸው ተማሪዎች የሙያ ስልጠና ሥርዓት አለመዘርጋቱ፤ በልዩ ትምህርትቤቶችና ልዩ ክፍሎች የሚያስተምሩ የልዩ ፍላጎት መምህራን ሥራው ከሚጠይቀው ጥረት ውስብስብነትና ክብደት አንጻር የማበረታቻ ጥቅማጥቅም አለመኖሩ፤ የአካል ጉዳተኛ ተማሪዎች የትምህርት ተደራሽነት፣ ተሳትፎና የትምህርት ማጠናቀቅ ለማበረታታት የድጎማ ጥቅማጥቅም አለመኖሩ እንዲሁም ቀጣይነት ያለው ድጋፍና ክትትል በማድረግ ተገቢውን ግብረመልስ መስጠት አለመቻሉም ሌላው ደካማ ጎን እንደነበረ በጥናቱ ተቀምጧል::
አዲሱ የትምህርት ሥርዓት ምን ይዞ መጣ?
አዲሱ የትምህርት ስትራቴጂና ሥርዓት በ2004 ዓ.ም የነበሩ ድክመቶችን በሙሉ ያየና ወደ ትግበራ እንዲገባበት ሥርዓት የዘረጋ ሲሆን፤ በጥናቱ እንደተለየውም የልዩፍላጎት/ አካቶ ትምህርትን የሚመራ ከፌዴራል እስከ ወረዳ ድረስ አደረጃጀት ይቋቋማል:: በየደረጃው ለሚመደቡ ባለሙያዎች የሚያገለግል የሥራ ምዘናና የደረጃ ምደባ አወሳሰን ጥናት ይከናወናል፤ ተግባራዊ ይደረጋል:: በየደረጃው ለተመደቡ የሥራ ክፍሉ አመራሮችና ባለሙያዎች ተከታታይ የሙያ ማሻሻያ የሥራ ላይ ስልጠና ይሰጣልም::
በልዩ ትምህርት ቤቶችና በልዩ ክፍሎች የሚማሩ አካልጉዳተኛ ተማሪዎችን ለሚያስተምሩና ለሚደግፉ መምህራንና ርዕሰ መምህራን ልዩ የማበረታቻ ጥቅማ ጥቅም የሚያገኙበትን ሥርዓት ይዘረጋል:: ከጤና ኤክስቴንሽን ባለሙያዎችና ከመሠረተ ማህበረሰብ ተሃድሶ ሠራተኞች ጋር በመተባበር ልዩ የትምህርት ፍላጎት ያላቸው ዜጎች ወደ ትምህርት ቤት እንዲመጡ የቤትለቤት ምዝገባና የግንዛቤ ማስጨበጫ ሥራዎች ይሠራል::
በልዩ ትምህርት ቤቶች፣ በልዩ ክፍሎች፣ በመደበኛ ትምህርት ቤቶች እና በከፍተኛ ትምህርት ተቋማት ለሚማሩ አካልጉዳተኛ ተማሪዎች በመማር ማስተማር ሂደቱ የሚያጋጥቸውን እንቅፋቶች ተቋቁመው በትምህርታቸው ውጤታማ እንዲሆኑ የሚያስችል የድጎማና ማበረታቻ ሥርዓት ይዘረጋል:: ተስማሚ የቴክኖሎጂ ውጤቶችን በአገሪቱ ሕግ መሠረት ከቀረጥ ነፃ በሆነ አግባብ ወደ አገር ውስጥ እንዲገቡ ይደረጋል:: ተስማሚ የትምህርት ቁሳቁሶችንና አጋዥ ቴከኖሎጂዎችን በአገር ውስጥ ኢንዱስትሪዎች ለማምረት ከሚመለከታቸው ተቋማት ጋር በትብብር እንዲሠራ ይሆናልም ተብሏል::
ሌላው በአዲሱ የትምህርት ስትራቴጂ ውስጥ የተካተተው ነገር በቅድመ- አንደኛና በአንደኛ ደረጃ ትምህርት ልዩ የትምህርት ፍላጎት ላላቸው ተማሪዎችና መምህራን ቋንቋ፣ በብሬል መጻፍና ማንበብ፣ በዳሰሳ ምልክት ቋንቋ እና በመሳሰሉት ስልጠናዎች መስጠት ነው:: በተጨማሪም በአካታች የመማር-ማስተማር ሂደት ውስጥ መስማት የተሳናቸው ተማሪዎች ተሳትፎን ለማሳደግ የምልክት ቋንቋ ተርጓሚዎችን መመደብ፤ ለዚህም የሥራ ምዘናና ደረጃ ምደባ አወሳሰን ጥናት ይደረጋል:: ትምህርት ቤቶችን ልዩ የትምህርት ፍላጎት ላላቸው ዜጎች የትምህርት ተሳትፎዎቹና አካታች ማድረግ አንዱ በአዲሱ የትምህርት ሥርዓት ይካተታል የተባለ ጉዳይ ነው:: ለአካል ጉዳተኞች ፈታኝ የሆነው የትምህርት ቤት ዲዛይን ደግሞ ከዚህ መካከል የሚጠቀስ ሲሆን፤ ነባር የትምህርት ቤት ሕንፃዎች ሳይቀሩ ሁለንተናዊ ንድፍ መርሆችን ይከተላሉ ተብሏል:: በተጨማሪም በትምህርት ቤቶች ስታንዳርድ መሠረት የትምህርት ቤቶች ምድረ-ግቢና አገልግሎት መስጫዎች ለአካል ጉዳተኛ ተማሪዎች እንቅስቃሴ ምቹ እንዲሆኑ ይደረጋል:: ለአፈጻጸሙም የተደራሽነት ስታንዳርድ መመሪያ ይዘጋጃል::
የአካል ጉዳተኞችን መሠረት ያደረጉ ግቦች፣ ይዘቶች፣ የማስተማሪያ ሥነ-ዘዴዎች፣ የመማሪያ-ማስተማሪያ ቁሳቁሶች እና የምዘና ሥርዓት እንደፍላጎታቸውና ችሎታቸው ተስማሚ ማድረግም አንዱ በአዲሱ ሥርዓት የሚካተት ነው:: ከፍተኛ የአካል ጉዳት ያለባቸው ተማሪዎች ካለባቸው ጉዳት አንጻር በቀለም ትምህርት መዝለቅ ለማይችሉት ደረጃ ትምህርት ቤቶች (የመንግሥትና የግል) የሙያ ስልጠና መርሃ-ግብር ይመቻቻል:: የፈተና እና ምዘና ሥርዓቱ ልዩ የትምህርት ፍላጎት ያላቸው ዜጎች እንደ ጉዳታቸውና የትምህርት ፍላጎታቸው ተግባራዊ ይሆን ዘንድ በጥናት ላይ የተመሠረተ ተስማሚና የተለየ የፈተና እና ምዘና (አዎንታዊ ድጋፍን ጨምሮ ሥርዓት መዘርጋት፤ ለዚህም የአፈፃፀም መመሪያ ተዘጋጅቶ ሥራ ላይ እንደሚውልም ጥናቱ አመላክቷል::
ሌላው በአዲሱ የትምህርት ሥርዓት የተካተተው ነገር የነፍስ-ወከፍ የትምህርትመርሃ-ግብር የሚያስፈልጋቸውን አካል ጉዳተኛ ተማሪዎችን በመለየት የአካቶ ትምህርት የድጋፍ መስጫ ሥርዓትን መዘርጋት ነው:: መንግሥታዊ ካልሆኑ ተቋማት ጋር በመተባበር በትምህርት ሥርዓቱ የተዘጋጁ የተማሪዎች መማሪያ መጻሕፍትን ተደማጭና ለእይታ በሚመች መልክ የሚቀይርና እንደየ ጉዳታቸው ዓይነት የሚያሰራጭ፣ የትምህርት ቁሳቁስ የሚያዘጋጅ አገራዊ ማዕከል ማቋቋምም አንዱ ነው::
ልዩ የትምህርት ፍላጎት ያላቸው ሕፃናት፣ ወጣቶችና ጎልማሶች ከቤተሰብ ወደትምህርትቤት፣ ከክፍል ወደ ክፍል ከአንድ ተቋም ወደ ሌላ ተቋም እንዲሁም ከትምህርትና ስልጠና ሂደት ወደ ሥራ መስክ በሚሸጋገሩበት ወቅት በነበሩበት ቦታ ይደረግላቸው የነበረውን ድጋፍና አጠቃላይ የባህሪ ገጽታ የሚገልጽ ማስረጃ በማዘጋጀት የትስሰር ሥርዓት እንዲሁም የአተገባበር መመሪያ ይዘጋጃል:: በአገር አቀፍ እና በክልል ደረጃ አገልግሎት የሚሰጡ የመለያ፣ የዳሰሳ ማዕከላት እና የሪፈራል ሥርዓት በመዘርጋት አስፈላጊውን ድጋፍ እንዲያገኙ ይደረጋል:: በትግበራ ላይ ያለን የክላስተር ትምህርት ቤቶችን ወደ አካቶ ትምህርት የድጋፍ መስጫ ማዕከልነት የመለወጥ ሂደት በማስፋት በክልል/ከተማ አስተዳደር ት/ቢሮዎች፣ በዞን ትምህርት መምሪያዎች እና በወረዳ ትምህርት ጽሕፈት ቤቶች አማካኝነት ተጠናክሮ ይቀጥላልም የሚለው በአዲሱ የትምህርት ሥርዓት ይተገበራል ከተባለው መካከል ነው::
በመጨረሻ አዲሱ የትምህርት ሥርዓት ለአካል ጉዳተኞች ይዞ የመጣው ነገር የጉድኝት ማዕከላት ትምህርት ቤቶችን በሰለጠነ የሰው ኃይል እና መሠረታዊ የሆኑ ተስማሚ የትምህርት ቁሳቁሶችና ቴክኖሎጂዎች (ብሬይል ወረቀት ስሌትና ስታይለስ፣ ተናጋሪ የሂሳብ ማሽን፣ አባከሰ፣ ብሬልታይፕራይተር፣ ተናጋሪ መጻሕፍት፤ ዲጅታል መቅረፀ-ድምፅ፣ ተናጋሪ ሶፍትዌሮች የተጫኑ ኮምፒዩተሮች፣ የምልክት ቋንቋ መጻሕፍት፣ የብሬይል መጻሕፍት፣ የጎላ ጽሑፍ፣ የጽሑፍ ማጉያ) መሣሪያዎች፣ አማራጭና አጋዥ የተግባቦት ዘዴዎች ሌሎችን በማሟላት በማዕከላቱ እና በሳተላይት ትምህርት ቤቶች ልዩ የትምህርት ፍላጎት ያላቸው ዜጎች ድጋፍ እንዲያገኙ ማድረግ የሚለውነው:: ይህ ሲሆን ግን አተገባበሩ ላይ ከሁሉም አካላት ልዩ ትኩረትን እንደሚሻ በጥናቱ ገልጸዋል:: ስለዚህም ለተግባራዊነቱ ሁሉም ይትጋ በማለት ጽሑፋችንን ቋጨን:: ሰላም!!
ጽጌረዳ ጫንያለው
አዲስ ዘመን ሰኞ ኀዳር 5 ቀን 2015 ዓ.ም