ከሁለት ሳምንታት በፊት በማኅበራዊ ገጾች አንድ አስገራሚ መረጃ ሲዘዋወር ነበር። ከሆነ ሆስፒታል አስከሬን ሲወጣ ጫኝና አውራጆች እኛ ነን የምንጭነው ብለው ግርግር ተፈጥሮ ነበር የሚል። ከዚያ በፊት ደግሞ አውቶብስ ተራ የሆነች እናት ልጇን ከጀርባዋ ላይ ካላወረድንልሽ አሉ ተብሎ በቀልድም በቁም ነገርም ሲወራ ነበር።
እነዚህ አጋጣሚዎች በአጋጣሚ የተከሰቱ ናቸው ወይም የችግሩን አሳሳቢነት ለመግለጽ የተጋነኑ ናቸው እንበል፤ ግን በገሃዱ በራሳችን ዓይን ያየናቸው ክስተቶች ራሱ ከዚህ ብዙም የተለዩ አይደሉም።
2011 ዓ.ም ሰኔ ወር አካባቢ ነው። አንድ ጓደኛዬ ኮዬ ፈጬ ቤት ተከራይቶ ዕቃ ጭነን ሄድን። ዕቃው ከእኛ የሚያልፍ አይደለም። ልክ ገና መኪናው ሲደርስ ከአካባቢው ነዋሪ በላይ የሚሆኑ ጫኝና አውራጆች ከየሥርቻው ተንጋግተው መጡ።
ማንንም ሳያናግሩ እየዘለሉ መኪናው ላይ መውጣትና መፍታት ጀመሩ። ጓደኛዬ በከፊል ነገሩን ያውቅ ስለነበር ማባበልና መለማመጥ ጀመረ፤ እኔ ስለማላውቅ፣ ሲጀመር እኛ አውርዱልን ሳንል ለምን መፍታት ጀመሩ ብየ ስገረምና ስቆጣ እኔን እያስረዱ አረጋጉኝ።
ልጆቹ ዕቃውን አውርደው የትኛው ቤት እንደሆነ ብቻ አሳዩን ነው ያሉት። ያለማንም ፈቃድ ራሳቸው አወረዱት፤ አስገቡት።
አናዳጁ ነገር ይህ አይደለም፤ ዋጋ የጠየቁት ዕቃውን ካወረዱ በኋላ መሆኑ ነው። የጠየቁት ገንዘብ ዕቃው ራሱ ቢሸጥ አያወጣውም። በቀልድም በቁም ነገርም በቁጣም ብንነግራቸው አልሰሙም፤ እንዲያውም ነገሩ ወደሌላ (የብሔር መልክ ያለው) ነገር እንደሚሄድ አስፈራሩን። የዚህን ጊዜ ታግሶ የቆየው ጓደኛዬም ያመጣችሁትን አምጡ አልከፍልም ብሎ ተቆጣ። የአካባቢው ሰውና ዕቃውን ያደረሱልን ሾፌር (ሽማግሌ ናቸው) በብዙ ማግባባት አግባቡንና ጣጣው አለቀ።
በኋላ የአካባቢው ሰዎች ሲነግሩን በዚህ ምክንያት ብዙ አይነት ጥፋቶች ደርሰው እንደነበር ገጠመኞችን ነገሩን። መገናኛ ከቤልቪው ሆቴል ከፍ ብሎ ባሉ መንደሮች ውስጥ አንድ ግለሰብ አልከፍልም ብሎ የደረሰበትን ጉዳት በዚያው ሰሞን ሰማሁ።
በአጠቃላይ በጫኝና አውራጆች ምክንያት የተፈጠሩ ጥፋቶች ይቆጠሩ ቢባል ሰልፍ ራሱ የሚያስወጡ ናቸው። ከላይ የገለጽኳቸው ገጠመኞች በጣም ቀላል የሚባሉት ናቸው። ለሕክምና ወይም በስደት የመጡ መንገደኞች መናኸሪያ ዙሪያ ሲያለቅሱ ማየት የየዕለት ክስተት ሆኗል። ለፌስታል ቁጥራት እና ለትንንሽ ቦርሳዎች ሳይቀር ኩንታል ጤፍ የሚገዛ ዋጋ ይጠይቋቸዋል። ‹‹ይህ እኮ እኔ ራሴ መያዝ የምችለው ነው›› ሲሉ ከእጃቸው ላይ ቀምተው ይይዙታል። ምክንያታቸው ደግሞ ተደራጅተን የምንሠራ ስለሆነ ማንም ሰው የትኛውንም ዕቃ በእኛ በኩል ነው መጫንና መውረድ የሚችል ብለው ነው የሚያምኑት።
በዚሁ በጫኝና አውራጅ ምክንያት የሰው ሕይወት ሁሉ አልፏል። እጅግ አሳሳቢ ከመሆኑ የተነሳ በዚሁ በጫኝና አውራጅ ጉዳይ ላይ በሚያዚያ ወር መጨረሻ አካባቢ የአዲስ አበባ ፖሊስ ኮሚሽን የውይይት መድረክ አዘጋጅቶ ነበር። በውይይቱ ላይም በጫኝና አውራጆች የደረሱ ጥፋቶችን የሚያሳይ ጽሑፍ ቀርቦ ነበር።
የአዲስ አበባ ፖሊስ ኮሚሽን የማኅበረሰብ አቀፍ ፖሊስ ዳይሬክተር ኮማንደር ሰለሞን ፋንታሁን ራሳቸው ‹‹ባለንብረቶች እቃው ከተገዛበት በላይ የተጋነነ ዋጋ እየተጠየቁ ነው›› ብለው ነበር። ፖሊስ ጠንካራ እርምጃ እንደሚወስድም አሳስበው እንደነበር አስታውሳለሁ።
እንግዲህ ችግሩ እዚህ ድረስ አሳሳቢ ሆኗል ማለት ነው። ምናልባትም ሌሎች ወቅታዊ ሀገራዊ ውጥረቶች ስለነበሩ የመገናኛ ብዙኃኑም ያን ያህል ትኩረት አልሰጡትም እንጂ የጫኝና አውራጆች ነገር በጠራራ ፀሐይ ዝርፊያ እየሆነ ነው። የተፈጠረው ችግር አጀንዳ የሚሆነውም ችግሩ የደረሰበት ሰው የተማረ ወይም ታዋቂነት ያለው ሲሆን ነው። ያጋጠመውን ነገር ወደ አደባባይ ማውጣት የሚችል ሲሆን ነው።
ነገሩን ወደ አደባባይ ማውጣት የማይችሉና ከሀገር ቤት የሚመጡ ብዙ ወገኖች ብዙ አይነት ስቃይ ደርሶባቸዋል። እነዚህ ሰዎች ወደ አዲስ አበባ የሚመጡት ለመዝናናት አይደለም፤ በሆነ አስቸኳይ ምክንያት ነው። በእንዲህ አይነት ምክንያት የሚመጡ ደግሞ ትርፍ ገንዘብ አይዙም። ምናልባትም ለትራንስፖርት እና ለመጡበት ጉዳይ የተቆጠረ ገንዘብ ብቻ ሊይዙ ይችላሉ። እነዚህን ሰዎች ነው ትንንሽ ከረጢት ሁሉ ሳይቀር ለአገር አቋራጭ ጉዞው ከከፈሉት በላይ የሚጠይቋቸው።
ይህን የአደባባይ ውንብድና ሁላችንም ልንታገለው ይገባል፤ በእኔ ካልደረሰ… በሚል ማለፍ የለብንም። ለዚህ ሥራ ደግሞ ፖሊስ ተባባሪ መሆን አለበት። ልክ ባለፈው ሳምንት ጽሑፋችን ፖሊስ ለሚሠራቸው አኩሪ ሥራዎች እንዳመሰገነው ሁሉ ቅሬታዎች ሲኖሩም እንወቅሳለን። ብዙ ጊዜ የሚነሳው ቅሬታ ለፖሊሶች ስንነግራቸው ‹‹ሥራቸው ነው›› እያሉ ችላ ይሏቸዋል የሚል ነው። አንዲትን ከገጠር የመጣች ምስኪን ለፌስታል ዕቃ ብዙ ብር ሲጠይቁ ፖሊስ ዝም ሊል አይገባም፤ ምክንያቱም ይህ ከዝርፊያ አይተናነስም።
የተጋነነ ዋጋ መጠየቃቸው ብቻ አይደለም ችግሩ። በሚፈጠረው ግርግር በዕቃ ላይ ጉዳት እየደረሰ ነው። በተለይም ተሰባሪ ዕቃዎች በመጓተት ጉዳት ይደርስባቸዋል። መንገደኛው ‹‹ራሴው መያዝ የምችለው ነው››ሲል ጫኝና አውራጆቹ በኃይል ለመንጠቅ ይሞክራሉ፤ ይህኔ ዕቃው ይጎዳል፤ ባለንብረቶቹ አቅመ ደካማ ከሆኑ ደግሞ አካላዊ ጉዳትም ይደርሳል ማለት ነው።
ከዓመታት በፊት እንደማውቀው አንድ ሰው ዕቃ የሚያስጭነውና የሚያስወርደው በራሱ ፈቃድ ነበር። እንደ ሻንጣ እና የፌስታል ዕቃዎች ደግሞ ማሸከም ከፈለገ ተሸካሚ ራሱ ባለንብረቱ ጠርቶ ነው። ወይም ተሸካሚዎች ጠጋ ብለው በትህትና እና በልመና አይነት ‹‹ጋሼ ልሸከመው?›› ብለው ነው። ይህኔ ሰውየው በሰብዓዊነት (ለተሸካሚ ልጆች ሲል) ወይም መያዝ ስላልተመቸው ያስይዛቸዋል። ብር የሚሰጣቸው እንኳን ባለንብረቱ የፈቀደውን ነበር። ‹‹ስንት ነው?›› ሲላቸው በትህትና ‹‹አንተ የፈቀድከውን›› ይላሉ። የሰጣቸው ትንሽ ሆኖ ቅር ቢላቸው እንኳን ‹‹ኧረ ጋሼ ሩቅ እኮ ነው›› ይላሉ፤ ወይም በቂ ነው ካሉ በትህትና አመስግነው ይሄዳሉ።
ከቅርብ ጊዜያት ወዲህ ግን ውንብድና ሆነ! ይሄ ደግሞ እልህ ያጋባል። ባለብንረቱም ‹‹እንዲያውም ራሴ ነኝ የምሸከመው!›› በማለት ወደ እልህ ውስጥ ይገባል። በመተሳሰብ መሆን የነበረበት ነገር ወደ መጨቃጨቅ ሲሄድ ግርግሩ ለአካባቢው ሁሉ ይተርፋል ማለት ነው።
አሁን ተስፋችን ያለው ፖሊስ ላይ ነው። ፖሊስ ለተወሰነ ጊዜ ከልቡ ቢሠራ የሚቸገረው ለትንሽ ጊዜ ነው፤ ከዚያ በኋላ ስለሚፈሩ ልክ ይገባሉ። ሙሉ ሥራቸውን ላለማጣት ሲሉ ሥርዓታቸውን ይዘው ይሠራሉ። ስለዚህ ይህ ችግር መስመር እስከሚይዝ ፖሊስና ሕዝቡ ተባብሮ ሊሠራ ይገባል።
ዋለልኝ አየለ
አዲስ ዘመን ጥቅምት 30/ 2015 ዓ.ም