ከአለም ጤና ድርጅት በቅርቡ የወጡ መረጃዎች እንደሚያሳዩት፤ የኩላሊት ህመም በአለም አቀፍ ደረጃ 850 ሚሊዮን የሚጠጉ ሰዎችን በየአመቱ ያጠቃል፡፡ ከነዚህ ውስጥ ደግሞ 2 ነጥብ 4 ሚሊዮን የሚሆኑት ስር በሰደደ የኩላሊት ህመም እንዲሁም 1 ነጥብ 7 ሚሊዮኖቹ በአጣዳፊ የኩላሊት ህመም ምክንያት ለሞት ይዳረጋሉ፡፡ ይህም የኩላሊት ህመምን በአለም ስድስተኛው የሞት ምክንያት ያደርገዋል፡፡
በኢትዮጵያም ከ5 እስከ 10 በመቶ የሚሆኑት አዋቂዎች በተለያየ ደረጃ የኩላሊት ህመም ተጠቂዎች እንደሆኑ ሲገመት በየአመቱም 7 ሺ ያህሎቹ ስር በሰደደ የኩላሊት ህመም ምክንያት ይሞታሉ:: አብዛኛዎቹም እድሜያቸው ከሃምሳ አምስት በታች እንደሆነ ይገመታል፡፡
የኩላሊት ህመም በከፍተኛ ደረጃ እየተስፋፋ ከመምጣቱ አኳያና የህክምና አገልግሎትም በስፋት አለመኖር ችግሩን የበለጠ አባብሶታል፡፡ ህመሙ ከሰዎች የማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ ሁኔታ ጋር የተያያዘ መሆኑም ጫናውን ከፍ ያደርገዋል፡፡
አቶ ዋለልኝ መኮንን በአዲስ አበባ ከተማ ላፍቶ አካባቢ ነዋሪ እንደሆኑና በንግድ ስራ እንደሚተዳደሩ ይናገራሉ፡፡ከሁለት ወራት በፊት የገጠማቸው ህመም በእጅጉ እንዳስደነገጣቸው ያስታወሳሉ:: በወቅቱ ባደረጉት ምርመራም ሁለቱም ኩላሊታቸው መስራት እንዳቆመ በሃኪሞች እንደተነገራቸውና ከዛ ጊዜ ጀምሮ የኩላሊት እጥብት በግል ሆስፒታሎች ሲያደርጉ እንደቆዩ ያስረዳሉ፡፡ ወደ ውጭ ሀገርም ዘልቀው እንደዚሁ የኩላሊት እጥበት እንዳደረጉም ይገልፃሉ፡፡
ይሁንና የኩላሊት እጥበት በሳምንት ሶስት ጊዜ ለማድረግ ወጪው ከባድ በመሆኑና ከዚህ ይልቅ የኩላሊት ንቅለ ተከላ ማድረግ አዋጭ መሆኑን ይናገራሉ፡፡ ኩላሊት የሚለግሳቸው የቤተሰብ አባል በማግኘታቸው ነው ወደ ቅዱስ ጳውሎስ ሆስፒታል እንደመጡ የሚናገሩት፡፡ ኩላሊት የሚለግሷቸው ታላቅ እህታቸውን ደም አስመርምረው ከእርሳቸው ጋር ተመሳሳይ በመሆኑ በቀጣይ ንቅለ ተከላውን ለማድረግ ቅድመ ሁኔታዎች እያሟሉ እንደሆነም ይገልፃሉ፡፡
የኩላሊት ንቅለ ተከላ ማዕከል መከፈት እርሳቸውን ጨምሮ የኩላሊት ንቅለ ተከላ ማድረግ ለሚፈልጉ ዜጎች መልካም አጋጣሚ እንደሆነም የሚገልፁት አቶ ዋለልኝ፣ በቀጣይም ተመሳሳይ የኩላሊት ንቅለ ተከላ ማዕከላት በሌሎች አካባቢዎች ላይም መስፋፋት እንደሚገባቸው ይጠቁማሉ፡፡
ወጣት ዳዊት ዘመድኩን በአዲስ አበባ ከተማ ሳሪስ አካባቢ እንደሚኖር ይናገራል፡፡ ከአራት አመት በፊት በገጠመው የጤና እክል ምክንያት ምርመራ ለማድረግ ወደ አንድ ክሊኒክ እንዳመራና ሁለቱም ኩላሊቶቹ ስራ እንዳቆሙ እንደተነገረው ያስታውሳል፡፡ በገጠመው የኩላሊት ህመም ምክንያት የአስረኛ ክፍል ትምህርቱን እንዳቋረጠና የኩላሊት እጥበት በቅዱስ ጳውሎስ ሆስፒታል በሳምንት ሶስት ጊዜ እያካሄደ እንደሆነ ያስረዳል፡፡
ኩላሊት ሊለግሱት ፈቃደኛ የሆኑ አክስቱን በማግኘቱ ምርመራ አካሂዶ የኩላሊት ንቅለ ተከላ ለማካሄድ እንደተዘጋጀና ተራው ደርሶት የኩላሊት ንቅለ ተከላውን ካከናወነ በኋላ ወደቀድሞው ጤንነቱ ተመልሶ ያቋረጠውን ትምህርቱን መቀጠል እንደሚፈልግም ወጣት ዳዊት ይገልፃል:: በማዕከሉ የሚሰጠው የኩላሊት እጥበት አገልግሎት መልካም ቢሆንም አሁንም የኩላሊት እጥበት አገልግሎት የሚፈልጉ በርካታ ሰዎች በመኖራቸው አገልግሎቱ በሌሎች ሆስፒታሎችም መስፋፋት እንዳለበትም ይጠቁማል፡፡
በቅዱስ ጳውሎስ ሆስፒታል የብሄራዊ ኩላሊት ንቅለ ተከላ ማዕከል የዲያሊሲስ ክፍል ኬዝ ቲም አስተባባሪ አቶ የሺዋስ ምትኬ እንደሚግልፁት፤ በማዕከሉ የኩላሊት እጥበት አገልግሎት የሚሰጠው የኩላሊት ንቅለ ተከላ ለማድረግ ዝግጁ ለሆኑ ህመምተኞች ነው፡፡ በ14 የኩላሊት ማጠቢያ ማሽኖችም አገልግሎቱ ይሰጣል፡፡ በተመሳሳይም በዋናው ሆስፒታል 18 የኩላሊት እጥበት ማሽኖች አገልግሎት በመስጠት ላይ ይገኛሉ፡፡
ማሽኖቹ በቀን በሁለት ፈረቃ የኩላሊት እጥበት አገልግሎት የሚሰጡ ሲሆን፣ በዋናው ሆስፒታል የሚገኙ ማሽኖች ደግሞ ለሃያ አራት ሰአታት አገልግሎት ይሰጣሉ፡፡ በዚህ ማዕከል ታካሚዎች በሳምንት ሶስት ቀን ለአራት ሰአታት የኩላሊት እጥበት ያደርጋሉ፡፡ ለአንድ እጥብትም 500 ብር ይከፍላሉ፡፡ የኩላሊት ንቅለ ተከላ ማድረግ የሚፈልጉ ደግሞ እጥበቱን እያደረጉ ተመዝግበው ይጠባበቃሉ፡፡ ምርመራውን ሲጨርሱም በወረፋቸው መሰረት ንቅለ ተከላውን ያካሂዳሉ፡፡
እንደ አስተባባሪው ገለፃ፤ በማዕከሉ የሚሰጠው የኩላሊት ንቅለ ተከላና እጥበት ህክምና አገልግሎት በዋጋ ዝቅተኛ ነው፡፡ በዚህም ምክንያት በርካቶች አገልግሎቱን ለማግኘት ወደ ማዕከሉ ይመጣሉ፡፡
የኩላሊት እጥበት አገልግሎት ለማግኘትና ለንቅለ ተከላ ዝግጁ ለመሆን ደግሞ የዲያሊሲስ ማሽኖቹ እስኪለቀቁ ድረስ ወረፋ ለመጠበቅ ይገደዳሉ፡፡ ይህም የአቅርቦትና ፍላጎት ልዩነት መኖሩን የሚያሳይ ነው፡፡ በመሆኑም የዲያሊስስ ማሽኖችን ማሟላት ብቻ ሳይሆን ማዕከሉንም ማስፋትና አገልግሎቱን በሌሎች ሆስፒታሎችም ጭምር ማስጀመር የግድ ይላል፡፡
በቅዱስ ጳውሎስ ሆስፒታል የብሄራዊ ኩላሊት ንቅለ ተከላ ማዕከል የኩላሊት ንቅለ ተከላ ኬዝ ቲም አስተባባሪ አቶ ተስፋዬ ይሁኔ እንደሚናገሩት፤ በማዕከሉ የኩላሊት ንቅለ ተከላና የኩላሊት እጥበት ለሚያካሂዱ የክንድ ደም ስር ማስተካከል ወይም /arteriovenous fistula/ አገልግሎቶች ይሰጣሉ፡፡ የክንድ ደም ስር ማስተካከል እንደአስፈላጊነቱ በሳምንት ሶስትና አራት ጊዜ ሲሰራ የኩላሊት ንቅለ ተከላ ደግሞ በወር አንድ ጊዜ ሁለት የቀዶ ህክምና ክፍሎችን በመጠቀም ይከናወናል፡፡
የክንድ ደም ስር ማስተካከል አገልግሎት ከተጀመረ ወዲህ 639 የኩላሊት እጥበት የሚያካሂዱ ታካሚዎች አገልግሎቱን አግኝተዋል:: ማዕከሉ ከተመሰረተ ጊዜ ጀምሮ የኩላሊት ንቅለ ተከላ ህክምና አገልግሎት ያገኙ ታካሚዎች ደግሞ 102 ደርሰዋል፡፡ የኩላሊት ንቅለ ተከላ ለማካሄድ ሂደቱ ረጅምና እስከ ስድስት ወር ድረስ የሚፈጅ በመሆኑ ከዚህ ቁጥር በላይ መስራት አልተቻለም::
የኩላሊት ንቅለ ተከላ ለማካሄድ ወረፋ የሚጠባበቁ ታማሚዎች እንዳሉ የሚገልፁት አስተባባሪው፤ኩላሊት የሚሰጠው በቤተሰብ ከመሆኑ አኳያ አልፎ አልፎ ኩላሊታቸው ከቤተሰቦቻቸው ጋር ላይመሳሰል ይችላል፡፡ በዚህ ሂደት በቶሎ ኩላሊት ስለማያገኙ ንቅለ ተከላውን በፍጥነት ማድረግ አይችሉም፡፡ የባለሙያዎች እጥረትና የግብአት ችግሮችም ታማሚዎች በቶሎ ህክምናውን እንዳያገኙ አንዱ ምክንያት በመሆኑ በቀጣይም እነዚህን በማስተካከል አገልግሎቱን በተሻለ ሁኔታ መስጠት ያስፈልጋል፡፡
በጤና ሚኒስቴር ተላላፊ ያልሆኑ በሽታዎች ቡድን መሪ ዶክተር ሶስና ኃይለማርያም እንደሚሉት፤ የኩላሊት ጤና ዋነኛ የትኩረት አቅጣጫዎች ህብረተሰቡ፣ የጤና ባለሙያዎችና ፖሊሲ አውጪዎች ግንዛቤ እንዲኖራቸው ማድረግ፣ የኩላሊት ህክምና አገልግሎትን ማስፋት፣ ህብረተሰቡ ጤናማ የአኗኗር ዘይቤ እንዲከተልና መንግስትም አዋጭ የፖሊሲ
ስትራቴጂዎችንና አቅጣጫዎችን በመንደፍ የመከላከል ስራዎችን ማጠናከር ነው፡ ፡ ይሁንና የኩላሊት እጥበትና ንቅለ ተከላ ህክምና አገልግሎት ፍትሃዊነትና ተደራሽነት አሁንም አጠያያቂ በመሆኑ ይህን አገልግሎት ተደራሽነቱንና ፍትሃዊነቱን ለማረጋገጥ በቅንጅት መስራት ያስፈልጋል፡፡
እንደ ቡድን መሪዋ ገለፃ፤ የኩላሊት ህክምና ውድና የቤተሰብ አቅምን የሚፈትን በመሆኑ የተለያዩ የጤና መድህን አማራጮችን በጥልቀት ማጥናትና መተግበርን ይጠይቃል:: የጤና ሚኒስቴርም የኩላሊት እጥበት ህክምናን በሁሉም ክልሎች በሚገኙ ዋና ዋና ሆስፒታሎች ተዳራሽ እንዲሆን በመስራት ላይ ይገኛል፡፡ የኩላሊት ንቅለ ተከላ ህክምናም በአዲስ አበባ በቅዱስ ጳውሎስ ሆስፒታል ሚሊኒየም ህክምና ኮሌጅ የተጀመረ ሲሆን፣ እስካሁንም ከመቶ በላይ ታካሚዎች አገልግሎቱን አግኝተዋል፡፡
በቀጣይም የኩላሊት ንቅለ ተከላ ህክምና አገልግሎት ፍኖተ ካርታ ተዘጋጅቶለትና የህግ ማዕቀፍ ኖሮት አገልግሎቱ እንዲስፋፋ እየተሰራ ነው፡፡ ሁሉንም ባለድርሻ አካላትን በማስተባበርና ህብረተሰቡን በማሳተፍ የኩላሊት ህመሞች የሚያመጡትን የጤና፣ የማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ ጫና ለመቅረፍም ርብርብ ማድረግ ይገባል፡፡ የጤና ሚኒስቴርም የሚጠበቅበትን ስራዎች ሁሉ አጠናክሮ የሚሰራ ይሆናል፡፡
አዲስ ዘመን ሚያዝያ 1/2011
በአስናቀ ፀጋዬ