ሁሉም ቋንቋዎች ከአገሪቱ የኢኮኖሚ ዕድገት ጋር በተጣጣመ መልኩ በጥንቃቄ ተጠንተው ወደ ትምህርት አገልግሎት ከተቀየሩ የቋንቋ ተናጋሪዎች የተሻለ መደበኛ ትምህርት ማግኘት እንደሚችሉ ማንም የሚያምነው ጉዳይ ነው፡፡ ይህ ከተደረገ ጥናቶች እንደሚሉት ማህበረሰቡ ባህሉን፣ ታሪኩን እና ቅርሶቹን በቀላሉ ማስተዋወቅ እንዲችል እድል ይፈጥራል፡፡ ለሌሎች ማንነቱን ማስተማሪያ ዘዴውም ይሆንለታል፡፡ አስተማሪን ከተማሪዎች ጋር ለማገናኘትም ቀላል መንገድ ይፈጥራል፡፡ እናም እንደ አገር በአዲሱ የትምህርት ስርዓት የተመረጡ የአፍ መፍቻ ቋንቋዎች በትምህር አገልግሎቱ ውስጥ እንዲገቡ መደረጉ ይህንን ታሳቢ በማድረግ ነው፡፡
እስከዛሬ እንደ አገር ለትምህርት አገልግሎት የሚውሉ የተመረጡ የአፍ መፍቻ ቋንቋዎች ጥቂት ቢሆኑም አሁን ግን ሰፍተዋል፡፡ በትምህርት ሚኒስቴር የተጠናው ጥናት እንዳመላከተው፤ ከ53 በላይ የሚሆኑት ቋንቋዎች አገልግሎቱን ይሰጣሉ፡፡ ይህ መሆኑ ደግሞ የጥራትን ጉዳይ መፍትሄ ለማበጀት እጅግ ይጠቅማል የሚል እሳቤም አለ፡፡
ትምህርት ሚኒስቴር ሥርዓተ ትምህርቱን ጨምሮ በተለያዩ የትምህርት ሥርዓት ጉዳዮች ላይ ብዙ ጥናቶችን አካሂዷል፡፡ በፖለቲካ አስተዳደር እና ፖሊሲዎች ላይ የተደረጉ የጥናት ምክሮች እና ለውጦች ላይ በመመርኮዝም ብዙ ለውጦች የሚመጡበትን ሥርዓት ፈጥሯል፡፡ አንዱ ከላይ እንዳልነው ሁሉም ቋንቋዎች ከአገሪቱ የኢኮኖሚ ዕድገት ጋር በተጣጣመ መልኩ በጥንቃቄ ተጠንተው ወደ ትምህርት አገልግሎት እንዲቀየሩ ማስቻል ነው፡፡ በአዲሱ ስርኣተ ትምህርትም ይህ ተካቶ በአፍ መፍቻ ቋንቋ ተናጋሪዎች የተሻለ መደበኛ ትምህርት እንዲሰጥ እየተደረገ ነው፡፡
የአዲሱ ስርዓተ ትምህርት በአፍ መፍቻ ቋንቋ መሰጠቱ ለምን አስፈለገ፤ እንዴት ይሰጣል፤ ከንባብ ጋር በማዋሃድ እንዴት ተማሪዎች ጋር መድረስ አለበትና መሰል ነገሮችን በማካተት ሚኒስቴሩ የተለያዩ ጥናቶችን በማድረግ የወሩ ማብቂያ በንባብ ላይ ሰፊ ሥራ ሲሰራ ከነበረው ኢትዮ ኪድስ ጋር በመተባበር በአዘጋጀው ፕሮግላም ላይ አቅርቦ ነበር፡፡ እኛም ይህንን መነሻ በማድረግ በአዲሱ ትምህርት ስርዓት ቋንቋና ንባብ እንዴት ተግባራዊ እንደሚሆኑ ለማሳየት ወደድን፡፡
ጥናቱ እንደሚለው፤ የአፍ መፍቻ ቋንቋ ሲኖር ሰዎች ባህላቸውን፣ ታሪካቸውን እና ቅርሶቻቸውን በቀላሉ ለማስተዋወቅና ለማወቅ እድል ይፈጥርላቸዋል፡፡ ተቀራርበው እንዲሰሩም ያደርጋቸዋል፡፡ ልዩነት ውበት መሆኑን እንዲረዱ ከማድረግ አንጻርም የማይተካ ሚና አለው፡፡ ስለሆነም እንደ አገር ለተግባራዊነቱ በርካታ ሥራዎች ተከናውነዋል፡፡ እንደ ኢትዮጵያ ባሉ አገራት ይህ ነገር ተግባራዊ መሆኑ ደግሞ አገርን ለመገንባት ሁነኛ መፍትሄ ነው፡፡
የትምህርት ጥራት ጉዳይ እንደ አገር ችግር እየሆነ ከመጣ ሰነባብቷል የሚለው መረጃው፤ በቀላሉ ውሉን የሚያገኝበት መንገድ በአፍ መፍቻ ቋንቋ ማስተማር ሲቻል ነው፡፡ በትምህርት አቅርቦትና ተደራሽነት ዙሪያ የተፋጠነ ሥራ በመሰራቱ መሻሻሎች መጥተዋል፡፡ በቋንቋ ላይም ይህንን ያህል ጠንክሮ ከተሰራ ለውጡን በአጭር ጊዜ ማየት እንደሚቻልም ጥናቱ ያመላክታል፡፡ በተለይም የ21ኛው ክፍለ ዘመን ብቃቶችን ለማዳበርና ህብረተሰቡን ወደፊት እንዲያራመድ ለማስቻል ቋንቋ ሁነኛ መድሀኒት እንደሆነ ያብራራል፡፡
በትምህርት ሥርዓት ውስጥ ቋንቋን መማር እንዴት?
ቅድመ-መደበኛ ደረጃ፡- በዚህ የክፍል ደረጃ ውስጥ ያሉ ሕጻናት አምስት ዓመትን የያዙ በመሆናቸው በአፍ መፍቻ ቋንቋቸው የቃል እና የማንበብ ክህሎቶችን እንዲያዳብሩ ተደርገው ይማራሉ፡፡ ሁለት ዓመት ብቻ የሚቆዩበትም ይሆናል፡፡
አንደኛ ደረጃ፡- በዚህ የክፍል ደረጃ ደግሞ ከቃል እና ከማንበብ አልፈው የመፃፍ ክህሎትን በተመጣጠነ መልኩ ማዳበር እንዲችሉ በአፍ መፍቻ ቋንቋቸው እንዲማሩ ይደረጋል፡፡ ይህ መሆኑ ደግሞ ከማንበብ ተሻግረው መጻፍን እንዲለማመዱ እድል ይሰጣቸዋል፡፡
መካከለኛ ደረጃ፡- በእዚህ የክፍል ደረጃ ውስጥ የቋንቋ ክህሎትን ወደ ሕይወት መመሪያቸው መለወጥ የሚለማመዱበት ጊዜ ነው፡፡ በተጨማሪም የሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ዘርፎችን ለመቀጠል በሚያስችላቸው ሁኔታ ያሳድጉበታል፡፡ ለዚህ ደግሞ ኢትዮጵያ ከ80 በላይ ቋንቋዎች የሚነገሩባት የብዙ ቋንቋ ተናጋሪ ሀገር መሆኗ እጅጉን ይጠቅማቸዋል። በቅድመ ክፍል እና በአንደኛ ደረጃ እንደ ማስተማሪያ ሚዲያ የተጠቀሙበትን ለፈጠራ ጭምር የሚጠቀሙበት ያደርጋቸዋል፡፡ ስለሆነም በዚህ ክፍል ደረጃ ላይ የአፍ መፍቻ ቋንቋን መጠቀማቸው በየጊዜው ከፍ የሚሉበትን እድል ይሰጣቸዋል፡፡
በአዲሱ የአጠቃላይ ትምህርት ሥርዓተ ትምህርት ጋር በተጣጣመ መልኩ የተዘጋጀው አዲሱ የእንግሊዝኛ ቋንቋ ሥርዓተ ትምህርትም በዚህ ደረጃ የሚሰጥ በመሆኑ ብዙ ነገሮችን በውጤታማነት ለመምራት ያስችላቸዋል፡፡ በተለይም አለማቀፋዊነትን ከማወቅ አንጻር የማይተካ ሚና ይኖረዋል፡፡ ምክንያቱም ትምህርቱ ሲሰጥ የመማሪያ ውጤቶች፣ የይዘት ፍሰት ቻርት፣ የሚመጥናቸውን የመማር ብቃቶች እና ሥርዓተ ትምህርትን የሚከተል ነው፡፡ በተጨማሪም ከዘጠነኛ እስከ አስራ ሁለተኛ ክፍል ድረስ እንደ ግዴታ እንግሊዝኛ ቋንቋ የማስተማሪያ ዘዴ ይሆናልና ተማሪዎች ዘጠነኛ ክፍል ላይ ሲደርሱ መደናገር እንዳይኖርባቸው ያደርጋቸዋል፡፡
ከቋንቋ ቀጥሎ ጥራቱ ላይ የሚያሳስበው ነገር ተማሪዎች ከንባብ ጋር ያላቸው ቁርኝት ሲሆን፤ በጥናቱ ትኩረት ከሚሹ መሰረታዊ ነገሮች መካከል አንዱ ተደርጎ ታይቷል፡፡ ለአገሪቱ አጠቃላይ የትምህርት ሥርዓት የተዘጋጀው የሥርዓተ ትምህርት ማዕቀፍ ዋና ዓላማም ሆኖ ወደ ትግበራው የተገባበት ሁኔታ አለ፡፡ ይህንን የንባብ ክህሎት ከማሳደግ አኳያ ልዩ ትኩረት ተችሮታል፡፡
‹‹ያለ ንባብ ፈጠራ፣ አምራችነት፣ ራስን መረዳትና ኃላፊነትን መውሰድ ሊመጡ አይችሉም፡፡ ያለንባብ ኃላፊነት የሚሰማቸው ሰውም መሆን አይቻልም፡፡ ያለ ንባብ ስለአገራዊ ልማት ማውራት አይታሰብም›› የሚለው ጥናቱ፤ በንባብ ላይ ንቁ አስተዋጾ ያላቸው ዜጎችን ለማፍራት የንባብ ክህሎትን ማሳደግ ግድ እንደሆነም አስቀምጧል፡፡
እንደ መረጃው ከሆነ፤ ንባብን ከማሳደግ አኳያ ትልቅ ኃላፊነት የተጣለባቸው ተቋማት ትምህርት ሚኒስቴር ፣የመምህራን ትምህርት ኮሌጆች፤ ከቅድመ መደበኛ እስከ ሁለተኛ ደረጃ ጀምሮ ለአጠቃላይ ትምህርት ኃላፊነት የሚወስዱ አካላት ናቸው፡፡ ስለዚህም ትምህርት ሚኒስቴር እነዚህን አካላት በማሳተፍ የ10 ዓመት የትምህርት ፍኖተ ካርታ አዘጋጅቶ ወደ ትግበራው ገብቷል፡፡ በኢትዮጵያ የትምህርት ሥርዓት ውስጥ ዋና ዋና ስትራቴጂካዊ ለውጦች ይሆናሉ ብሎ ካሰባቸው መካከልም አንዱ ንባብ ሆኗል፡፡
ከንባብና ከቋንቋ አንጻር ያለፈው ስርዓተ ትምህርት ምን ጉድለቶች ነበሩበት ?
ጥናቱ ጉድለቶቹን በሦስት ከፍሎ ያሳያል፡፡ የአፍ መፍቻ ቋንቋ፣ የፌደራል ቋንቋዎች እና እንግሊዝኛን በመጥቀስ፡፡ ከዚህ አኳያም የአንደኛ ደረጃ ትምህርት ቤት ሕጻናት ከባድ የቋንቋ ችግር አለባቸው ይላል፡፡ በሁሉም ቋንቋዎች የማንበብ እና የመፃፍ መሰረታዊ ክህሎት እንደሌላቸውም ያብራራል፡፡ በተለይም የሳይንስና ቴክኖሎጂ ቋንቋ ተደርጎ የሚወሰደው እንግሊዘኛ ለብዙ የርዕሰ ጉዳይ አስተማሪዎች እንዲሁም እንግሊዘኛን እንደ አንድ የትምህርት አይነት በሚያስተምሩ መምህራን ላይ ከባድ ፈተና እንደሆነም ተጠቁሟል።
የልጆችን የንባብ ክህሎት አፈጻጸምና የብቃት ደረጃ ጥናቱ እንዳስቀመጠው፤ በአንደኛም ሆነ በመካከለኛው የክፍል ደረጃ ላይ ያሉ ተማሪዎች ብዙ መቶኛ በዜሮ አንባቢዎች ስር ይወድቃሉ፡፡ በተለይም የሕጻናት የማንበብ አዝማሚያ በትርፍ ሰዓት እንደሚቀንስ በደንብ ታይቷል፡፡ ለዚህ ደግሞ ዋና ዋና ምክንያቶች ተደርገው የሚወሰዱት የትምህርት ቤት ርዕሰ መምህራን እና መምህራን ብቃት፣ ሙያዊ እድገት ያለመኖርና በስልጠናዎች አለመዳበር፤ የትምህርት ቁሳቁስ (የመማሪያ መጽሀፍት፣ የአስተማሪ መመሪያ) በበቂ ሁኔታ አለመገኘት ፤ የትምህርት ቤት መገልገያዎች (ተግባራዊ ቤተ-መጻሕፍት፣ የንባብ ማዕዘኖች) ምቹ አለመሆንና ያለመኖር የሚሉት ናቸው፡፡
ለልጆች ንባብ ድጋፍ ( ቤተሰብ፣ ትምህርት ቤቶች) የሚጠበቅባቸውን አለመስራታቸው፤ የማንበብ ክህሎት በመማር ማስተማር እና የምዘና ዘዴዎች አለመካተታቸው ከሚጠቀሱ መሰረታዊ ችግሮች መካከል መሆናቸውን ጥናቱ ያስቀምጣል፡፡ በመሆኑም ንባብን አገራዊ አጀንዳ በማድረግ መላውን ህብረተሰብና ሁሉንም ባለድርሻ አካላት ማሰባሰብ ይኖርበታል በሚል እየተሰራ እንደሚገኝ መረጃው አመላክቷል፡፡ እንደ ትምህርት ሥርዓት ንባብ ከእነአተገባበሩ የገባበት ምክንያትም ይህ እንደሆነ አብራርቷል፡፡
ከመምህራን ጋር ተያይዞ ያሉ ችግሮች
በመምህራን ማሰልጠኛና በዩኒቨርሲቲ ውስጥ የማስተማር ዘዴው እንግሊዝኛ መሆን፤ በመጀመሪያ ደረጃ ተማሪዎችን በአፍ መፍቻ ቋንቋ ለማስተማር ተመራቂዎች የሚመረቁበት የትምህርት አይነት መለያየት፤ ተመራቂዎቹ በእንግሊዝኛ የተማሩትን ወደ አፍ መፍቻ ቋንቋ ቀይሮ ለማቅረብ መቸገራቸው፤ የአተገባበር መመሪያ አለመኖሩ የመሳሰሉት ናቸው፡፡
በትምህርት ልማት ፍኖተ ካርታ (2018 እስከ 2030) ለቋንቋ የታቀዱ ማሻሻያዎች ምን ይመስላሉ?
እንደ ጥናቱ ከሆነ፤ በአንደኛ ደረጃ ትምህርት ስርዓት (ከ 1 እስከ 6ተኛ ክፍል) የልጆችን የመናገር፣ የማንበብ እና የመጻፍ ችሎታዎች ተገቢውን ትኩረት ሊሰጣቸው እና ሊጠናከሩ ይገባል። በዚህ መሠረት ተማሪዎች ከአንደኛ ክፍል ጀምሮ የአፍ መፍቻ ቋንቋን እንደ ማስተማሪያ ዘዴ መጀምር አንዱና መሰረታዊ ነገር ተደርጎ ተወስዷል፡፡
ከ1ኛ ክፍል ጀምሮ እንግሊዘኛን እንደ ትምህርት ጀማሮ ትኩረቱ በቃል/በንግግር/በማዳመጥ ጉዳዮች ላይ መሆን አለበት፡፡ እስከ 3ኛ ክፍል ድረስ የሚዘልቅም ይሆናል፡፡ በዚህ ክፍል ደረጃ ተማሪዎች ከፌዴራል ቋንቋዎች አንዱን ወስደው መማር ይጠበቅባቸዋል። በሚመለከታቸው የክልል ባለስልጣናት ውሳኔ መሰረት የተመረጠው የፌደራል ቋንቋ ከየትኛውም ክፍል ጀምሮ መማር መቀጠል ይገባልም፡፡ ንባብም በዚሁ ልክ የሚተገበር ይሆናል፡፡
ስርዓተ ትምህርቱን የመተግበሪያ ዘዴ
ጥናቱ እንደሚለው፤ የመምህራን ማሰልጠኛ ተቋማት የትምህርት ቋንቋን የሚያሰለጥኑበት ደረጃን ማሻሻል፤ ለወደፊት መምህራን የተለያዩ የኢትዮጵያ ቋንቋዎችን እንዲማሩ እድል መፍጠር፤ የእንግሊዘኛ ቋንቋዎች ሥርዓተ ትምህርት በአዲሱ ሥርዓተ ትምህርት መዋቅር የማዳመጥ፣ የመጻፍ፣ የመናገር እና የማንበብ ችሎታዎችን እንዲያሟሉ ማድረግ ማለትም የማንበብ ክህሎት በቅድመ እና በድህረ ንባብ እንቅስቃሴዎች እንዲሁም ተማሪዎቹ የእንግሊዘኛ ስነ-ድምጾች ከተገቢ ፊደሎች ጋር በማገናኘት እንዲለማመዱ ማድረግ በዋናነት የሚጠቀሱ ናቸው።
የኢትዮጵያ የትምህርትና የሥልጠና ሥርዓት ተግባራዊ ሲደረግ እያንዳንዱ ተማሪ ሊያገኛቸው የሚገቡ ልዩ ሙያዎች፣ ብቃቶችና ባህሪያትን ማዳበር የሚጠበቅበት፣ የተሟላ ብቃት ያለው፣ አምራች፣ በአገር አቀፍና በዓለም አቀፍ ደረጃ ተወዳዳሪ ዜጋ ሆኖ ከለውጡ ኢኮኖሚ፣ ኅብረተሰብና የቴክኖሎጂ ዕድገት ጋር መላመድ የሚችል ዜጋ እንዲሆን በሚያስችል ሁኔታ ነው። .እናም በትግበራ ዘዴው ይህ እንዲታይ ይፈለጋል፡፡
በጥናቱ እንደተጠቆመው፤ በትምህርት ቤቶች ውስጥ ያለው ሥርዓተ ትምህርት እና የመማር ማስተማር ልምምዶች በትግበራው ወቅት ተማሪዎች ሌሎችን እንዲገነዘቡ፣ የጋራ እሴቶችን እንዲያሳድጉ፣ ብዝኃነትን እንዲያዳብሩ፣ የሰብአዊ መብቶች ግንዛቤ እንዲኖራቸው የሚያደርግ መሆን አለበት፡፡ የተሳትፎ ክህሎትን እና ኃላፊነት የተሞላበት ተግባርን እንዲያዳብሩ ማድረግም ይጠበቅበታል።
መሰራት አለባቸው የተባሉ ጥቆማዎች
የትምህርት ቤት አመራሮች፤ የክፍል መምህራንን እንዴት መደገፍ እንዳለባቸው በማሰልጠን ብቃታቸውን ማሳደግ አለባቸው፡፡ ለዚህ ደግሞ የትምህርት ቤት አመራር ጥራትን ማሻሻል ላይ ትኩረት ሰጥቶ መስራት ያስፈልጋል፡፡ ሌላው በጥናቱ የተነሳው ነገር በፍኖተ ካርታው አንዳንድ መምህራን አሁንም ያለ ምንም ስልጠና ንባብ በማስተማር ላይ ያሉ እና አብዛኛዎቹ ሰርተፍኬት የነበራቸው በመሆኑ የመምህራንን እውቀት ማሻሻል ተጠናክሮ መቀጠል ይኖርበታል የሚለው ነው።
መምህራን የተለያዩ የማስተማር እና የምዘና ዘዴዎችን ለምሳሌ፡- ማንበብን እንዴት ማስተማር እንዳለባቸው የተለያዩ ስልጠናዎችን መውሰድ አለባቸው፡፡ የትምህርት ቁሳቁሶች (የመማሪያ መጽሀፍት፣ የመምህራን መመሪያ) እና የትምህርት ቤት ግብዓቶች (ቤተ-መጽሐፍት ወይም የንባብ ማዕዘኖች) ማሟላትም ትኩረት ሊሰጠው ይገባል፡፡ ተግባራዊ የወላጅ-መምህር-ተማሪ-ማህበርን ማጠናከር፤ በትምህርት ቤት እንቅስቃሴዎች ላይ እንዲሳተፉ ማድረግ፤ ተማሪዎች እየተማሩ መሆናቸውን ማረጋገጥ ፤ የትምህርት ሴክተሩን ቁርጠኝነት እና ተጠያቂነት ስርዓት መዘርጋት፤ የትምህርት መሪዎች እንደ ኮቪድ-19 ያሉ ድንገተኛ የትምህርት መቆራረጦችን እንዴት መቋቋም እንደሚችሉ ግንዛቤ መፍጠርና ለችግሩ መፍትሄ ሰጪ የሚሆኑበትን መንገድ ማሳየት፤ በየጊዜው የትምህርትና ጥራቱ ጉዳይ በምን ሁኔታ እየተጓዘ እንዳለ መገምገም እና ግብረመልሶችን መስጠት ዋነኛ ተግባራቱን ከሚያሳልጡ መካከል እንደሆኑ ጥናቱ ያስቀምጣል፡፡
ሌላው በጥናቱ ቢሰራ ተብሎ የተጠቆመው ነገር በመምህራን ትምህርት ኮሌጆች ውስጥ የቋንቋ ትምህርት መምህራንን በትምህርት ቤት ማስተማር የሚለውም ነው፡፡ ይህ ደግሞ አጀንዳ 2063ን ያሳካልም የሚል እምነት ተጥሎበታል፡፡ ምክንያቱም በአጀንዳ 2063 የምንፈልጋትን አፍሪካ በቀጣዮቹ ሃምሳ ዓመታት ውስጥ ይሰጠናልና ነው፡፡ ይህም አፍሪካን ያሳተፈ ዕድገትና ቀጣይነት ያለው ልማት ማረጋገጥ ነው፡፡ ስለሆነም ለዚህ እቅድ መሳካት ሁሉም የበኩሉን ያበርክት በማለት ጽሑፋችንን ቋጨን፡፡
ጽጌረዳ ጫንያለው
አዲስ ዘመን ጥቅምት 21/2015