የኢትዮጵያ ውሃ ቴክኖሎጂ ኢንስቲትዩት በውሃ ዘርፍ በአገሪቱ ፈጣን ልማት ለማምጣት በዘርፉ ጥናትና ምርምሮችን በማካሄድ የቴክኖሎጂ ሽግግር ለማምጣትና በሰባት ክልሎች የሚገኙ ዘጠኝ የፖሊ ቴክኒክ ኮሌጆች ብቃት ያላቸውን ባለሙያዎች በማፍራት ሂደት የሚጠበቅባቸውን ሚና እንዲወጡ የቴክኒካል ድጋፍና ብቃት ምዘና አገልግሎት ይሰጣል፡፡ ኢንስቲትዩቱ ወደ ሥራ ከገባ 2008 ዓ.ም ጀምሮ በ15 የስልጠና ዘርፎች ከተለያዩ ክልሎችና የከተማ አስተዳደሮች ለተውጣጡ ሁለት ሺ 700 በላይ ለሆኑ የዘርፉ ባለሙያዎችና አሰልጣኞች አጫጭር ተግባር ተኮር ስልጠናዎች ሰጥቷል፡፡ የሰልጣኞችን ቁጥር ወደሦስት ሺ ለማድረስ እየሰራ ይገኛል፡፡
በኢንስቲትዩቱ ውስጥ የሚገኙ አሰልጣኞች በቴክኒክና ሙያ የትምህርትና ስልጠና ስርዓት ከማስገባት አንፃር የአሰልጣኝነት ስነ ዘዴ እና የምዘና ስነ ዘዴ ስልጠናዎችን እንዲወስዱ የተደረገ ሲሆን፣ «ለማብቃት መብቃት» በሚል የኢንስቲትዩቱ መርህ መሰረት አሰልጣኞች በምዘና ስርዓት ውስጥ እንዲያልፉ ተደርጓል፡፡ በዚህ መሰረት 26 አሰልጣኞች ተመዝነዋል፡፡ ምዘናው የመጠጥ ውሃና ሳኒቴሽን እንዲሁም የመስኖ ልማት ላይ ያሉትን ችግሮች ሊፈቱ የሚችሉ ቴክኖሎጂ አጠቃቀሞች ላይ ያተኮረ ነው፡፡
ከውሃ ብክለትና ጥራት ጋር ተያይዞ ለሚነሱ ችግሮች ኢንስቲትዩቱ የፍተሻ ቤተ ሙከራ በማቋቋም የችግሩን ደረጃ ለይቶ የመፍትሄ እርምጃ ለመውሰድ እየተንቀሳቀሰ ይገኛል፡፡ ለዚህ የሚረዳ እና በአገሪቱ የማይሰጡ ውሃና ተያያዥ አካላት ፍተሻ አገልግሎት የሚሰጥ የቤተሙከራ ግንባታ በማስገንባት ላይ ነው፡፡ የቤተ ሙከራው ግንባታ ሲጠናቀቅ በአገር አቀፍ ደረጃ ያለውን ክፍተት ከመሙላት ባለፈ ለፍተሻ አገልግሎት እየወጣ ያለውን የውጭ ምንዛሪ ማዳን ያስችላል፡፡ በተጨማሪም ለጎረቤትና ለሌሎች አገራት የፍተሻ አገልግሎት በመስጠት አገሪቱ ተጨማሪ ገቢ እንድታገኝ ያደርጋል፡፡
የኢትዮጵያ ውሃ ቴክኖሎጂ ኢንስቲትዩት ዋና ዳይሬክተር አቶ ታመነ ሀይሉ እንደሚናገሩት፤ በኢንስቲትዩቱ የተለያዩ ሥራዎች የሚከናወኑ ሲሆን፣ ከዚህ ውስጥ ትምህርትና ስልጠና በመስጠት በውሃው ዘርፍ ባለሙያዎችን ማፍራት አንዱ ነው፡፡ ሌላው ደግሞ የምርምርና የቴክኖሎጂ ሽግግር ማድረግ ነው፡፡ በኢንስቲትዩቱ የተሰሩ የውሃ ማውጫ ቴክኖሎጂዎች ለህብረተሰቡ እንዲጠቅሙ በአነስተኛ ዋጋም ይተላለፋሉ:: የውሃ መፈተሻ ቤተሙከራም ያለ ሲሆን ቤተሙከራው ከአገር ውጭ ሲደረጉ የነበሩ የውሃ ማጣራት ሥራውን እዚሁ ለማከናወን የሚያስችሉ ናቸው፡፡ በክልል ከሚገኙ የቴክኒክና ሙያ ተቋማት ጋር በትብብር እየተሰራ ይገኛል፡፡
በዘርፉ የሚገኙ ባለሙያዎች ብቁ ሆነው ማገልገል እንዲችሉ የጉድጓድ ቁፋሮ ምዘና የመስጠት ሥራም በኢንስቲትዩቱ እየተሰራ እንደሚገኝ ዋና ዳይሬክተሩ ይገልፃሉ፡፡ ከክልል ከመጡ ባለሙያዎች የተሰሩ ቴክኖሎጂዎችም እንዲሸጋገሩ እየተሰራ ሲሆን፣ በአገሪቱ በቂ የሆነ የውሃ ሀብት ቢኖርም በአግባቡ ጥቅም ላይ እየዋለ አለመሆኑን ያመለክታሉ፡፡ ይህን ለማስተካከል ደግሞ ቴክኖሎጂና የተማረ የሰው ኃይል የሚያስፈልግ በመሆኑ ኢንስቲትዩቱ እነዚህ ሁለት ነገሮች ማምጣት ትልቁ ሥራው መሆኑን ያመለክታሉ፡፡ በምርምር የታገዘ ቴክኖሎጂዎችን በማምጣት እና በዘርፉ ብቃት ኖሯቸው አስፈላጊ ግብዓት በመስጠት እንዲሰራ ከተደረገ የተሻለ የውሃ አጠቃቀም እንደሚኖር ይጠቅሳሉ፡፡
እንደ ዋና ዳይሬክተሩ አባባል፤ በኢንስቲትዩቱ በአሁኑ ወቅት በአሥራ አምስት የስልጠና መስኮች ስልጠና እየሰጠ ይገኛል፡፡ በውሃና ፍሳሽ አጠቃቀምና አወጋገድ፣ ጂአይ ኤስ፣ ድሪሊንግና ኤሌክትሮ መካኒክ ተጠቃሽ ናቸው፡፡ እነዚህ ደግሞ በዘርፉ ላይ በቁልፍ ችግርነት የተቀመጡ ናቸው፡፡ ከጉድጓድ የሚወጣውን ውሃ አጣርቶ ለመጠቀም ክልሎች የየራሳቸው ቤተሙከራዎች አሏቸው፡፡ ነገር ግን ከነሱ አቅም በላይ የሆኑ ችግሮች ሲመጡ ወደ ኢንስቲትዩቱ ይመጣል፡፡
በቀጣይ የዘርፉ ችግር ናቸው የሚባሉትን በመለየት ስልጠና ለመስጠት እቅድ እንዳለ የሚናገሩት አቶ ታመነ፤ እነሱን ለመፍታት ሥራዎች እየተከናወኑ ናቸው፡፡ በተለይ የፍሳሽ ችግር በምን አይነት መንገድ መፍታት እንደሚቻል ስልጠና ለመስጠት ታስቧል፡፡ አዲስ የታሰቡት ስልጠናዎች ቀደም ብሎ የተሰራባቸው አይደሉም፡፡ ነገር ግን ስልጠናዎቹ በከፍተኛ ትምህርት ተቋማት የሚሰጡ ቢሆኑም ተማሪዎቹ ብቃት እንዲኖራቸው ለማስቻል ከቴክኖሎጂ ጋር የታገዘ ስልጠና በኢንስቲትዩቱ ለመስጠት ዝግጅት ተደርጓል፡፡ ስልጠናውን ከቴክኒክና ሙያ እንዲሁም ከከፍተኛ ትምህርት ተቋማት ለሚመጡ ተማሪዎችና አስተማሪዎች እንደሚሰጥ ያስረዳሉ ፡፡
የኢንስቲትዩቱ ምክትል ዳይሬክተር አቶ ታምሩ ፈቃዱ በበኩላቸው እንደሚገልጹት፤ የኢትዮጵያ ውሃ ቴክኖሎጂ ኢንስቲትዩት ከተሰጡት ሥራዎች መካከል የመጀመሪያው ስልጠና መስጠት ነው:: የከርሰ ምድር ውሃ ቁፋሮ ጥናት ትምህርት በመስጠት የሚሰራ ብቸኛ ኢንስቲትዩት ነው፡፡ ሌላኛው ኃላፊነት ደግሞ የብቃት ምዘና አገልግሎት መስጠት ነው፡፡ በአሁኑ ወቅት በውሃ ቁፋሮ ሲሰሩ የነበሩ ባለሙያዎች እየተመዘኑ ይገኛሉ፡፡ ቀደም ብሎ ደረጃ አንድና ሁለት ምዘና ወስደዋል፡፡ በቁፋሮና በውሃው ዘርፍ የተመዘኑ ባለሙያዎች ጥቂት ናቸው፡፡ ኢንስቲትዩቱ ከቴክኒክና ሙያ የሚመረቁትንም የምዘና አገልግሎት ይሰጣል:: የውሃ ቁፋሮ ምዘና ከኦሮሚያ የውሃ ቁፋሮ ኢንተርፕራይዝ የመጡ ባለሙያዎች ወስደዋል:: አጠቃላይ 18 ባለሙያዎች የብቃት ማረጋገጫ ፈተና ሲወስዱ ከኢንስቲትዩቱ ሁለት ባለሙያዎች ከኦሮሚያ የውሃ ቁፋሮ ኢንተርፕራይዝ ደግሞ 16 ባለሙያዎች ይገኙበታል፡፡ ከተመዘኑ በኋላ እውቅና ያለው ሰርተፍኬት ይሰጣቸዋል፡፡
እንደ አቶ ታምሩ ገለፃ፤ የከርሰ ምድር ቁፋሮ ማለት ከባድና ውስብስብ ነው፡፡ የመቆፈሪያ ማሽኖችን ማንቀሳቀስ፣ የከርሰ ምድር ውሃ መገኛዎችን ማግኘትና ውሃ ያለበትን መሬት ቆፍሮ ለህብረተሰቡ ውሃ እንዲሰጥ የማድረግ የቴክኖሎጂ ብቃትን ይጠይቃል፡፡ ስልጠናው ሲሰጥ ለአጭር ጊዜ ነው፡፡ በቀጣይ በከርሰ ምድር ውሃ ቁፋሮ ኢንጅነሪንግ የረጅም ጊዜ ስልጠና ለመስጠት እቅድ አለ፡፡ የከርሰ ምድር ውሃ ቁፋሮ ትምህርት በቴክኒክና ሙያ ተቋማት ላይ የጀመሩ አሉ፡፡ ነገር ግን ትምህርቱ ቴክኖሎጂ ስለሚጠይቅና ሥራው ውስብስብ ስለሆነ በሁሉም ተቋማት እየተሰጠ አይደለም፡፡ የከርሰ ምድር ውሃ ከተቆፈረ በኋላ ውሃው በቤተ ሙከራ ተፈትሾ ነው አገልግሎት ላይ መዋል ያለበት፡፡ ውሃው ተቆፍሮ ከወጣ በኋላ የግድ መመርመር አለበት፡፡ ውሃው በገጠራማ ቦታዎች ላይ የሚወጣ ከሆነ በውሃ ማከሚያ አክሞ መጠቀም ያስፈልጋል፡፡
አቶ ተክለማርያም ጎቼም በኢንስቲትዩቱ ከፍተኛ የኤሌክትሪክ መሀንዲስ የቴክኖሎጂ ሽግግር ባለሙያ ናቸው፡፡ እንደእሳቸው አባባል ከሆነ ውሃን ከመሬት ውስጥ በማውጣት ህብረተሰቡ እንዲጠቀም ለማድረግ የተለያዩ ቴክኖሎጂዎች ጥቅም ላይ እየዋሉ ይገኛሉ፡፡ ውሃ ከወጣ በኋላ መጣራት አለበት በተለይ በእጅ የሚቆፈሩ ጉድጓዶች ትኩረት ያስፈልጋቸዋል:: በቴክኖሎጂ የተደገፈ ቁፋሮና ውሃ የማውጣት ሲሰራ የውሃ ብክለትን ይቀንሳል፡፡ ለመጠጥ ውሃ ለመጠቀም ግን የውሃ ማጣሪያና ማከሚያ መጠቀም ያስፈልጋል፡፡ በኢንስቲትዩቱ ከተለያዩ ቴክኒክና ሙያ ተቋማት ለመጡ ባለሙያዎች ስልጠና መስጠት ከተጀመረ አንድ ዓመት ሞልቶታል:: በመጀመሪያ ከኔዘርላንድ የመጣ ባለሙያ ስልጠናውን ከሰጠ በኋላ ወደሌሎች ባለሙያዎች ለማሸጋገር ስልጠና ተሰጥቷል፡፡ ለምሳሌ ወደ ዲላ አካባቢ የአሰልጣኞች ስልጠና ተሰጥቷል:: ከዛ ውጤታማ የሆነ የጉድጓድ ውሃ ተቆፍሮ ለአገልግሎት እንዲበቃ ተደርጓል፡፡
ዋናው የሚያስፈልገው ነገር የውሃ ማውጫ ቴክኖሎጂዎችን ለተጠቃሚው ማድረስ ነው የሚሉት አቶ ተክለማርያም፤ በአገሪቱ የውሃ ተደራሽነት ችግር ካለ ለመፍታት በቴክኖሎጂ የታገዘ ሥራ ያስፈልጋል፡፡ ከተለያዩ ክልል የውሃ ቴክኒክና ሙያ ኮሌጆች ላይ የመጡ ባለሙያዎች ስልጠና እየወሰዱ ይገኛሉ፡፡ ስልጠናውን እንዳጠናቀቁ በየአካባቢያቸው ቴክኖሎጂውን ያሸጋግራሉ፡፡ በቀጣይ በመራዊ ከተማ አካባቢ የተግባር ስልጠና ለመስጠት እቅድ ተይዟል:: ቴክኖሎጂዎችን ወደ ኀብረተሰቡ በማድረስ ህብረተሰቡ መቆፈሪያውና የውሃ ማውጫ ማሽኑ እንዲኖረው ማድረግ መቻል እንዳለበት ይናገራሉ::
አዲስ ዘመን መጋቢት 30 /2011
መርድ ክፍሉ