
አዲስ አበባ፡- አፍሪካ በተባበሩት መንግሥታት ድርጅት የጸጥታው ምክር ቤት ቋሚ ወንበር እንዲኖራት በሚል ኢትዮጵያ የምታሰማውን ድምጽ ማስተጋባቷን ትቀጥላለች ሲሉ በውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር የዓለም አቀፍ ድርጅት ጉዳዮች ዳይሬክቶሬት ጄኔራል አምባሳደር አየለ ሊሬ ተናገሩ።
የተባበሩት መንግሥታት ቻርተር ሥራ ላይ የዋለበትን ዓመታዊ “የተመድ ቀን” ክብረ በዓል ትናንትና በአፍሪካ ኢኮኖሚክ ኮሚሽን ግቢ ተከናውኗል።
በወቅቱ በውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር የዓለም አቀፍ ድርጅት ጉዳዮች ዳይሬክቶሬት ጄነራል አምባሳደር አየለ ሊሬ ለኢትዮጵያ ፕሬስ ድርጅት እንደገለጹት፤ የተመድ ጸጥታው ምክር ቤት የአፍሪካን ድምጽ እንዲያከብር የሚደረገው ጥረት ይቀጥላል።
እንደ አምባሳደር አየለ ሊሬ ገለጻ፤ ከአንድ ነጥብ አራት ቢሊዮን በላይ ሕዝብ የያዘችው አፍሪካ እስካሁን ድረስ በጸጥታው ምክር ቤት በቋሚነት ድምጽ የምታሰማበት ዕድል አለመፈጠሩ ስህተት ነው።
አፍሪካ በተመድ የጸጥታው ምክር ቤት ቋሚ ጽምጽ ማግኘት አለባት የሚለውን ሃሳብ ኢትዮጵያ ቀጣይነት ባለው መልኩ ታቀርባለች ሲሉ ተናግረዋል።
አፍሪካም ድምጿን በቋሚነት የምታቀርብበት ዕድል እንዲፈጠር ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር ዐቢይ አሕመድና የተለያዩ ከፍተኛ የኢትዮጵያ ባለስልጣናት በዓለም አቀፍ መድረክ ድምጻቸውን አሰምተዋል፤ ኢትዮጵያም ይህንን አቋም በቀጣይ ጊዜያትም ማንጸባረቋን ትቀጥላለች ብለዋል።
በተመድ የጸጥታው ምክር ቤት አሁን ያሉት አምስት ቋሚ አባል አገራት ናቸው፤ ሌሎች 10 አገራት ደግሞ በጊዜያዊነት የሚያገለግሉ ተለዋጭ አባላት ናቸው። አፍሪካ ድምጽን በድምጽ የመሻር መብት ያላቸው ቋሚ አባላት ውስጥ ድምጽ የላትም። ይህ ደግሞ የቢሊዮኖችን ሃሳብ ቦታ ያልሰጠ ነው ሲሉ ገልጸዋል።
አምባሳደር አየለ እንደገለጹት፤ ከተመድ አባል ሀገራት ውስጥ ከአንድ አራተኛው በላይ አባላት የአፍሪካ ሀገራት ናቸው። በመሆኑም የአፍሪካውያን ድምጽ በአግባቡ ሊደመጥ የሚችልበትን መንገድ የማመቻቸት ኃላፊነት የሁሉም አካላት ነው።
ኢትዮጵያም በየመድረኮቹ ይህን ሃሳብ የምታንጸባርቀው የአህጉሪቷ ሕዝብ በተመድ ተገቢውን ውክልና እንዲያገኝና ውሳኔዎቹም በተገቢው መንገድ እንዲተላለፉለት ነው ብለዋል።
አምባሳደር አየለ እንዳስታወቁት፤ ኢትዮጵያም ከሌሎች የአፍሪካ ሀገራት ጋር በመሆን አህጉራችን በተመድ የጸጥታው ምክር ቤት ቋም ወንበር እንዲኖራት በመሥራት ላይ ትገኛለች፤ ይህን ጥረቷንም አጠናክራ ትቀጥላለች።
ኢትዮጵያ ለተመድ መመሥረት ምክንያት የሆነው የሊግ ኦፍ ኔሽን ሲቋቋም ኢትዮጵያ ከአፍሪካ ብቸኛዋ ሀገር ሆኖ አባል ነበረች።
ከሊግ ኦፍ ኔሽን መፍረስ በኋላ ተመድ ሲመሠረት ኢትዮጵያ ነፃ ከነበሩ ጥቂት የአፍሪካ ሀገራት ውስጥ አንዷ ሆና ለአፍሪካውያን መብት ስትሟገት መቆየቷ የሚታወስ ነው።
ሁለተኛው የዓለም ጦርነት ማብቃቱን ተከትሎ መሰል ጦርነቶችን ለመከላከል የተመሠረተው የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት 77ኛ ዓመቱን በማክበር ላይ ነው።
ጌትነት ተስፋማርያም
አዲስ ዘመን ጥቅምት 15 ቀን 2015 ዓም