
- 18 ሚሊዮን ወጣቶች ተሳትፈዋል
አዲስ አበባ፡- የኢትዮጵያ ወጣቶች ፌዴሬሽን በ2014 ዓ.ም የክረምት በጎ ፈቃድ አገልግሎት 14 ቢሊዮን ብር የሚያወጣ የበጎ ፈቃድ አገልግሎት መስጠቱን አስታወቀ። በበጎ ፈቃድ አገልግሎቱ 18 ሚሊዮን ወጣቶች መሳተፋቸውም ተገልጿል።
የኢትዮጵያ ወጣቶች ፌዴሬሽን ቢሮ ኃላፊ አቶ ሙሕዲን ናስር ለኢትዮጵያ ፕሬስ ድርጅት እንደገለጹት፤ በኢትዮጵያ የበጎ ፈቃድ አገልግሎት ከጊዜ ወደ ጊዜ እየተጠናከረ መጥቷል። በ2014 ዓ.ም በተከናወነው የክረምት በጎ ፈቃድ አገልግሎትም መንግሥትና ሕዝብ ሊያወጡ ይችሉት የነበረን 14 ቢሊዮን ብር ማዳን መቻሉን ጠቁመዋል።
ፌዴሬሽኑ ከሴቶችና ማኅበራዊ ጉዳይ ሚኒስቴር ጋር በትብብር መሥራት መቻሉ ከፍተኛ ውጤት አስገኝቷል ያሉት ቢሮ ኃላፊው፤ በተለይም የወሰን ተሻጋሪ ወጣቶች የበጎ ፈቃድ አገልግሎት በዚህ ዓመት ከተከናወኑ ተግባራት ትልቅ ውጤት የተገኘበት ነው ብለዋል።
የወሰን ተሻጋሪ ወጣቶች የበጎ ፈቃድ አገልግሎት ወጣቶች የሌሎች አካባቢዎችን ባህልና ወግ እንዲረዱ በማድረግ ሕዝብ ለሕዝብ ግንኙነት መጠናከር ትልቅ ሚና ያለው በመሆኑ በቀጣነትም በተጠናከረ መልኩ እንደሚሠራበት አስገንዝበዋል።
እንደ አገር የገጠመንን ችግር ለመወጣት የወጣቶች ሚና የማይተካ ነው ያሉት ቢሮ ኃላፊው፤ ለመከላከያ ሠራዊትና ለሌሎችም ሰብዓዊ እርዳታ ለሚያስፈልጋቸው ወገኖች የእርዳታ ማሰባሰብ ሥራ ሲሠራ ቆይቷል። በቀጣይነትም ወጣቶችን በማስተባበር የሚደረገው እገዛ ተጠናክሮ ይቀጥላል ብለዋል።
በ2014 ዓ.ም በጎ ፈቃድ አገልግሎት 18 ሚሊዮን የሚጠጉ ወጣቶች መሳተፋቸውን አስታውሰው፣ አረንጓዴ አሻራ፣ የክረምት ማጠናከሪያ ትምህርት፣ ደም ልገሳና ሰብዓዊ ድጋፎች፣ የአቅመ ደካሞችን በሥራ ማገዝና ቤት መጠገን፣ የጤና መከላከል፣ የአካባቢ ጥበቃና የአካባቢን ሰላም ማስጠበቅ ፌዴሬሽኑ በክረምት በጎ ፈቃድ ካከናወናቸው የበጎ ፈቃድ አገልግሎቶች መካከል የሚጠቀሱ መሆናቸውን ጠቁመዋል።
የበጎ ፈቃድ አገልግሎቱ በተመረጡ ዘርፎች በበጋም እንደሚቀጥል ያመለከቱት አቶ ሙሕዲን፤ የትራፊክ አገልግሎት፣ የአካባቢን ሰላምን ማስጠበቅ፣ ደም ልገሣና ሌሎችም ሰብዓዊ ሥራዎችና የተተከሉ ዛፎችን መንከባከብ በበጋ ወቅት ከሚሠሩ ሥራዎች ውስጥ መሆናቸውን ተናግረዋል።
የበጎ ፈቃድ አገልግሎት እንደ አገር ያሉብንን ክፍተቶች ለመሙላት ጉልህ ሚና እንዳለው የጠቀሱት አቶ ሙሕዲን፤ በጎ ፈቃድ አገልግሎት ወቅት ጠብቆ የሚሰጥ ሳይሆን ባህል ሆኖ ሁሌም መቀጠል ያለበት ነው። በመሆኑም የአገር ተረካቢ የሆኑ ወጣቶች በየአካባቢያቸው ያሉ ክፍተቶችን በመለየት በበጎ ፈቃድ እንዲሳተፉና ለሁለንተናዊ አገራዊ ለውጥ የበኩላቸውን አስተዋጽኦ እንዲያበረክቱ ጥሪ አቅርበዋል።
ፋንታነሽ ክንዴ
አዲስ ዘመን ጥቅምት 15 ቀን 2015 ዓም