
- የሳይንስ ሙዚየሙ የነፃ ጉብኝት ጊዜ ለአንድ ወር ተራዝሟል
አዲስ አበባ፡- በቴሌ ብር አገልግሎት ከ101 ነጥብ አንድ ቢሊዮን ብር በላይ ግብይት ማስተናገድ መቻሉን ኢትዮ ቴሌኮም አስታወቀ። በኢትዮ ቴሌኮም እና በንግድ እና ቀጠናዊ ትስስር ሚኒስቴር መካከል የአገልግሎት ክፍያዎችን በቴሌብር ለመፈጸም የሚያስችል ስምምነት በትላንትናው ዕለት ተደርጓል። የሳይንስ ሙዚየም ነጻ የጉብኝት ጊዜ ለአንድ ወር መራዘሙም ተጠቁሟል።
ኢትዮ ቴሌኮም ትላንት ስምምነቱን ሲፈርም የድርጅቱ ዋና ሥራ አስፈፃሚ ፍሬሕይወት ታምሩ በሰጡት ጋዜጣዊ መግለጫ እንዳስታወቁት፤ ኩባንያው በቴሌ ብር አገልግሎቱ ከ101 ነጥብ አንድ ቢሊዮን ብር በላይ ግብይት (Transaction Value) ማስተናገድ ችሏል።
ኩባንያው በቴሌብር አገልግሎት እስከ አሁን ድረስ 24 ነጥብ ዘጠኝ ሚሊዮን ደንበኞችን፣ 101 ዋና ወኪሎችን (Master Agents) ፣ 87 ሺህ ወኪሎች 23 ሺህ ነጋዴዎች /Merchants/ ማፍራት የቻለ ሲሆን፣ ከ101 ነጥብ 1 ቢሊዮን ብር በላይ ግብይት ማስተናገድ (Transaction Value) ችሏል ብለዋል።
በተጨማሪም ከ16 ባንኮች ጋር ትስስር (Integration) በማድረግ ከባንክ ወደ ቴሌብር ገንዘብ ማስተላለፍ የተቻለ ሲሆን፣ ከ13 ባንኮች ጋር ደግሞ ከቴሌብር ወደ ባንክ የገንዘብ ዝውውር እየተደረገ ይገኛል ሲሉም ጠቅሰዋል።
ኢትዮ ቴሌኮም የዲጂታል ኢትዮጵያን ራዕይ እውን የማድረጉን ጉዞ መጠነ-ሰፊ ሥራዎችን በቁርጠኝነት በማከናወን እየገፋበት የሚገኝ እንደሆነ ያመለከቱት ዋና ሥራ አስፈፃሚዋ፤ ከንግድ እና ቀጠናዊ ትስስር ሚኒስቴር ጋር የመግባቢያ ስምምነት በመፈራረም የመሥሪያ ቤቱ ባለጉዳዮች ከንግድ ምዝገባ፣ ከንግድ ፈቃድ እና ከንግድ ስያሜ ጋር ተያያዥነት ላላቸው የአገልግሎት ክፍያዎች ያለምንም ውጣ ውረድ በኦንላይን አገልግሎት እንዲያገኙ እንደሚያስችል ገልጸዋል።
ስምምነቱ ቀላል፣ ፈጣን፣ ምቹና አስተማማኝ የሆነውን የዘመኑን የዲጂታል ክፍያ ሥርዓት ቴሌብርን ተጠቅመው የአገልግሎት ክፍያቸውን እንዲፈጽሙ ያስችላቸዋልም ነው ያሉት።
በተለይም የንግድ እና ቀጠናዊ ትስስር ሚኒስቴር ባለጉዳዮች ለአዲስ ንግድ ምዝገባ፣ ማሻሻያ፣ ምትክ እና የውል ማቋረጥ አገልግሎት ክፍያዎችን እንዲሁም አዲስ የንግድ ፈቃድ ለማውጣት፣ ለማሳደስ፣ ምትክ ለመውሰድ፣ ውል ለማቋረጥ/ለመሰረዝ፣ ለአዲስ የንግድ ስም፣ የንግድ ስም ለማሻሻል፣ ለመቀየር እና ለመሰረዝ የአገልግሎት ክፍያዎችን በቀላሉ በቴሌብር የክፍያ አማራጭ እንዲያከናውኑ ያስችላቸዋል።
ዋና ሥራ አስፈጻሚዋ፤ ባለጉዳዮች አገልግሎቱን ለማግኘት ወደ www.etrade.gov.et በመግባት እና የሚፈልጉትን የአገልግሎት አይነት በመምረጥ እንዲሁም የአገልግሎት ቅጹን በቀጥታ (online) በመሙላት ለአገልግሎቱ ክፍያ ለመፈጸም የሚሰጣቸውን የመክፈያ ቁጥር በመጠቀም በቴሌብር መተግበሪያ ወይም በቴሌብር አጭር ቁጥር (*127#) የአገልግሎት ክፍያቸውን በቀላሉ መፈጸም ይችላሉ ብለዋል።
በሌላ በኩልም ከበርካታ አገልግሎት ሰጪ ተቋማት እና ድርጅቶች ጋር ስምምነት በማድረግ የአገልግሎት አሰጣጥ እና የክፍያ ሥርዓታቸውን በማቀላጠፍ ለተቋማቱም ሆነ ደንበኞቻቸው እፎይታን አጎናጽፏልም ብለዋል።
በቀጣይ ጊዜያትም ኩባንያችን ከሌሎች መሰል ተቋማት ጋር በመተባበር የክፍያ ሥርዓታቸውን በቴሌብር የሚተገብሩበትን አሠራር በማመቻቸት ደንበኞቻቸው የዲጂታል ክፍያ ሥርዓት ተጠቃሚ እንዲሆኑ ለማድረግ እና የቴሌብር ደንበኞች በአንድ ሥርዓት ሁሉንም ክፍያ ባሉበት ሆነው እንዲፈጽሙ ለማድረግ እና የዲጂታል ኢትዮጵያን ራዕይ ዕውን የማድረጉ ተግባር ተጠናክሮ እንደሚቀጥል እናረጋግጣለን ብለዋል።
በተያያዘ ዜናም የሳይንስ ሙዚየም የነፃ ጉብኝት ጊዜ ለአንድ ወር መራዘሙንም ዋና ሥራ አስፈጻሚዋ ገልጸዋል።
እንደ ወይዘሪት ፍሬሕይወት ገለፃ፤ የሳይንስ ሙዚየሙን ለመጎብኘት ባለው ሰፊ ፍላጎት ምክንያት የመጎብኛ ጊዜውን መጨመር አስፈልጓል። የሳይንስ ሙዚየሙ በ19 ቀናት ውስጥ 357 ሺህ በላይ ሰዎች የጎበኙት ሲሆን ባሳለፍነው ቅዳሜና እሁድ ብቻ ከ109 ሺህ በላይ ሰዎች እንደጎበኙት ተናግረዋል።
መዚየሙን ከአዲስ አበባ ውጪ ያሉ ሰዎች እንዲጎበኙት ለማድረግ የሚያስችል ሥራ እየተከናወነ መሆኑንም አስረድተዋል።
ዳግማዊ ግርማ
አዲስ ዘመን ጥቅምት 15 ቀን 2015 ዓም