
አዲስ አበባ፡- አሸባሪው ትሕነግ በስልጣን ዘመኑ ለውጭ ኃይሎች ጥቅም ሲል የሀገሩን ክብር ያዋረደ ቡድን ነው ሲሉ የፖለቲካ ተንታኙ ኤፍሬም ማዴቦ ገለጹ፡፡
የፖለቲካ ተንታኝ ኤፍሬም ማዴቦ ለኢትዮጵያ ፕሬስ ድርጅት እንደገለጹት፤ አሸባሪው የትሕነግ ቡድኑ ለ27 ዓመታት ለውጭ ኃይሎች ጥቅም የሀገሩን ክብር አሳልፎ የሰጠና ያዋረደ ቡድን ነበር፡፡ በኢትዮጵያ ሕዝብ ላይ የፈጸመው በደልም ታሪክ ይቅር የማይለው ነው።
የውጭ ኃይሎች አሸባሪውን ቡድን ስልጣን ካስያዙ በኋላ ከኢትዮጵያ መውሰድ የሚፈልጉትን ሁሉ በመውሰድ በሀገሪቷ ላይ ችግር የሚያመጣ ፖሊሲን እንዲጠቀም ሲያደርጉት ነበር። የለውጡ መንግሥት
ከመጣ በኋላ ግን የውጭ ኃይሎች ጥቅም በመነሳቱ በኢትዮጵያ ማኅበራዊ፣ ኢኮኖሚያዊና ፖለቲካዊ ጉዳይ ላይ ጫና እንዲፈጠር አድርጓል።
በአሸባሪው ትሕነግ ሀገራዊ ክህደት ምክንያት የኢትዮጵያ ሕዝብ በኑሮ ውድነት፣ በብሔር ክፍፍልና መሰል ጉዳዮች ዋጋ እንዲከፍል ሆኗል። ባለፉት አራት ዓመታት ሀገሪቷ በአስቸጋሪና መጥፎ ሁኔታዎች ውስጥ እንድትጓዝም አድርጓታል። ይህም በውጭ ኃይሎች ተጽዕኖና በአሸባሪው ትሕነግ የተፈጠረ በመሆኑ ሊቆም ይገባል ብለዋል።፡
የኢትዮጵያ መንግሥት አሸባሪው የትሕነግ ቡድን ለ27 ዓመታት የሠራውን በደል ረስቶ ለሀገር ሰላም ሲል የሰላም አማራጭን አቅርቧል። ነገር ግን አሸባሪ ቡድኑ በውጭ ኃይሎች እየተመራ የኢትዮጵያን ሕዝብ ተዋግቼ አሸንፋለሁ የሚል እሳቤን አንግቧል። በመሆኑም የሚዋጋለት ዓላማን የማያውቅና የትግራይን ሕዝብ ለውጭ ኃይሎች ጥቅም ሲል ችግር ላይ እንዲወድቅ እያደረገ ያለ አሳፋሪ ቡድን ነው ብለዋል።
አሸባሪ ቡድኑ መንግሥት በተደጋጋሚ የሰጠውን የሰላም እድል አሻፈረኝ ብሏል።
ሁል ጊዜ ከጦርነት ይልቅ ነገሮችን በውይይት መፍታት የተሻለ ነው። አሸባሪው ትሕነግ ግን በውይይት የሚያምን ባለመሆኑ ኢትዮጵያ አሁን እያጋጠማት ላለው ችግር ተጠያቂ መሆኑን ሁሉም ሊገነዘብ ይገባል ብለዋል።
አሸባሪ ቡድኑ የድርድር እምነትና ባህል የሌለው ነው። ቡድኑ ድርድር ውስጥ ለመግባት ከፈለገም ሙሉ ለሙሉ ድርድሩ እሱ በሚፈልገው መንገድ መሆን አለበት። ይህ የሚያሳየው ደግሞ አሸባሪ ቡድኑ ለድርድርም ለጦርነትም የማይመች መሆኑን ነው ሲሉ ገልጸዋል።
በኢትዮጵያ ያለው ችግር በሰላማዊ መንገድ እንዲፈታ ከሆነ ሊታይ በሚችል መልኩ አሸባሪው ትሕነግ ትጥቁን መፍታት አለበት ያሉት የፖለቲካ ተንታኙ አቶ ኤፍሬም ማዴቦ፤ መንግሥት ሆኖ ሲመራ በነበረበት ጊዜና አሸባሪ በሆነበት ጊዜያት በኢትዮጵያ ሕዝብ ላይ በደል የፈጸሙ ሰዎችን በፍቃደኝነት ሕግ ፊት እንዲቀርቡ ማድረግ ይገባልም ብለዋል።
የኢትዮጵያ የፖለቲካ ሁኔታ ከጊዜ ወደ ጊዜ በፍጥነት እየተቀያየረ ነው። በኢትዮጵያ ፖለቲካ ውስጥ የውስጥና የውጪ ኃይሎች የሚፈጥሩት ተጽዕኖ ሀገሪቷ የምትሄድበትን አቅጣጫ በየጊዜው ሲቀያይር ተስተውሏል። አሁን ያለው መንግሥት ግን በዚህ ረገድ የተሻለ እንደሆነም ገልጸዋል።
የኢትዮጵያ መከላከያ ሠራዊት የሀገርን ክብርና ሉዓላዊነት ለማስጠበቅ ባለፉት አራት ዓመታት በተሻለ አቋምና ደረጃ ላይ እንደሚገኝ በሰሜኑ ጦርነት በተደረጉ እንቅስቃሴዎች ማየት ይቻላል ያሉት አቶ ኤፍሬም፤ የሠራዊቱ አቋም ኢትዮጵያ ከገባችበት መከራና ስቃይ ማውጣት እንደሚችል እተማመናለሁም ብለዋል።
ሳሙኤል ወንደሰን
አዲስ ዘመንጥቅምት 15 ቀን 2015 ዓም