ተማሪ ዳዊት ፍጹም የዳግማዊ ምኒልክ ትምህርት ቤት የሰባተኛ ክፍል ተማሪ ነው:: ተማሪ ዳዊት ከድሃ ቤተሰብ የተገኘ በመሆኑ በርካታ ችግሮችን አሳልፏል:: እናቱን ላለማስቸገር ምሳ ሳይቋጠርለት ወደ ትምህርት ቤት የሚሄድባቸው ጊዜያት በርካታ ናቸው። እናቱም ቢሆኑ በሰው ቤት ልብስ አጥበውና ለውዝ ሸጠው ስለሚያስተዳድሩት ሁልጊዜ ሞልቶላቸው ምሳውን ላይቋጥሩለት ይችላሉ። ምግብ ሲኖር ጎርሶ ሲያጣም ረሀቡን ችሎ እንዲማር ተገዷል። ክፍል ውስጥ ቢገባም ትምህርቱን ለመከታተል ግን ይቸገር ነበር። ስለዚህ አብዛኛውን ጊዜ የትምህርቱን ሰዓት በእንቅልፍ እንደሚያሳልፍ ያስታውሳል። ይሄ ውጤቱ ዝቅ እንዲል አድርጎታል።
‹‹እስከ ስድስተኛ ክፍል ግንፍሌ የመጀመሪያ ደረጃ ትምህርት ቤት ነው የተማርኩት። በደረጃ ከ20 በላይ እንጂ ከዚያ በታች ወጥቼ አላውቅም›› የሚለው ተማሪ ዳዊት፤ በእናቱ ብርታትና ከእርሱ የባሱ ሰዎችን ሲያይ እንደሚጽናና ይናገራል። ምክንያቱም በረሃብ ምክንያት ራሳቸውን ስተው የሚወድቁ፣ የተማሪዎችን ፊት ላለማየት ከክፍል የሚቀሩ ጥቂቶች እንዳልነበሩ ያስታውሳል።
‹‹የድሃ ልጅ መሆን በትምህርት ቤት ውስጥ በብዙ መልኩ ያሸማቅቃል። ይዞ ከሚመጣው ምግብና መጠን አንጻርም ብዙ ፈተና ነው።›› ያለን ተማሪ ዳዊት፤ አንድ ቀን የገጠመውንና ዘላለም የማይረሳውን ነገር ያነሳል። ጊዜው እናቱ ምሳ ያልቋጠሩለት ነበር። ነገር ግን አብሮ መብላት የተለመደ ስለነበር ጉጉት አድሮበታል። ስለዚህም ከእነርሱ ጋር እመገባለሁ ብሎ አስቦ ትምህርቱን በአግባቡ ተከታትሎ ወጣ። ሆኖም ያሰበው አልሆነም። ጓደኞቼ ችግሬን ይሸከሙልኛል የሚላቸው ተማሪዎች ምሳ ስላልያዝክ አብረኸን መብላት አትችልም አሉት። በዚህም እጅግ አዘነ።
ከእረፍት በኋላ የሆነውን እያሰበ የባሰ ረሃቡ ጠናበት። በዚህም እንቅልፍ ብቻ ሳይሆን እንባም ተናነቀው። ከዚያን ጊዜ ጀምሮ ከጓደኞቹ ጋር መብላቱን አቋረጠ። ከተቋጠረለት ይበላል ካልተቋጠረ ደግሞ ጦሙን ውሎ ወደቤቱ ይመለሳል። ያን ጊዜ የሆነውን መቼም ማሰብ እንደማይፈልግ አጫውቶናል።
አሁን ነገሮች በመቀየራቸው ደስተኛ ብቻ ሳይሆን በውጤትም የተሻለና የደረጃ ተማሪ እንደሆነ የሚናገረው ዳዊት፤ ይህንን ሥር የሰደደ ችግር በመጠኑም ቢሆን እንደሚቀርፍ ተስፋ የተጣለበት የትምህርት ቤት ምገባ ፕሮግራም እነርሱን ብቻ ሳይሆን ቤተሰቦቻቸውንና መምህራንን እፎይ እንዳስባላቸው ያምናል። በተለይም መንግሥት ወጥ በሆነ መንገድ መተግበሩ ዝቅ ያለ ስሜት ሳይሰማቸው ከእኩዮቻቸው እኩል እንዲማሩና ውጤታማ እንዲሆኑ እንዳስቻላቸውም ያነሳል።
እኛ ዛሬ የተገኘንበት በአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ስር ያለው የካራ አሎ ቅድመ መደበኛና አንደኛ ደረጃ ትምህርት ቤት ይህንን ከሚያረጋግጡ መካከልም ይጠቀሳል::
የተማሪዎች ፈገግታ ሲበሉና ሳይበሉ እንኳን የሚለይበት ነው:: ተሰልፈው ሲታዩም እውነትም ይህ ምገባ ብዙ ነገሮችን ከቤተሰብ ተጋርቷል እንድንልም እንሆናለን:: ምክንያቱም ዛሬ ባለው ኑሮ ውድነት ስንቶች ልጆቻቸውን በሚገባ መመገብ ይችላሉ ብንል ምንም ሊሆን ይችላል ምላሻችን:: በመንግስት በተቀረጸ መርሃ ግብር ግን ከቅድመ መጀመሪያ እስከ ስምንተኛ ክፍል ባሉ በሁሉም የመንግሥት ትምህርት ቤቶች ይህ ተግባር ይከናወናል:: በዚህ ደግሞ ባለፈው ዓመት በነበረው መረጃ እንደተመላከተው ከ300 ሺህ በላይ ተማሪዎች ተጠቃሚ ሆነዋል::
የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር እንደገለጸው ደግሞ በባለፈው በጀት ዓመት ለትምህርት ምገባ ከ1ነጥብ2 ቢሊዮን ብር በላይ በመመደብ በከተማዋ እና በዙሪያዋ የሚገኙ ከ600 ሺህ በላይ ተማሪዎችን የምገባ መርሃ ግብሩ ውስጥ ተካተው ምግብ አግኝተዋል:: ይህ የሆነው ደግሞ ቀደም ሲል ከነበረው በጀት ዓመት ተጠቃሚዎቹን በእጥፍ በማሳደግ ነው:: በተጨማሪም የከተማ አስተዳደሩ የዜጎችን ፍትሃዊ ተጠቃሚነት ለማረጋገጥ በተለያዩ አምስት ክፍለ ከተሞች በቀን አንድ ጊዜ መመገብ የማይችሉ ዜጎችን በመለየት የምግብ አገልግሎት እንዲያገኙ በአንድ ጊዜ 1000 ዜጎችን ማስተናገድ የሚችሉ የመመገቢያ ማዕከላትን በማቋቋም በሺዎች የሚቆጠሩ የጎዳና ተዳዳሪዎች እና በዝቅተኛ የኑሮ ደረጃ ላይ ያሉ ዜጎችን ተጠቃሚ ማድረግ ችሏል።
የተማሪዎች ምገባ መርሐ ግብርን ጨምሮ የከተማ አስተዳደሩ በምገባ ዘርፍ የጀመራቸው ሥራዎች ለሌሎች አገራት ምርጥ ተሞክሮ ሆኗልም:: በጣሊያን ሮም ከተማ በተባበሩት መንግስታት ድርጅት አዘጋጅነት በተካሄደው የዓለም ስነ ምግብ ኮንፈረንስ ላይ በተሞክሮነት ቀርቧል። ሽልማትም ተሰጥቶታል:: ምክንያቱ ደግሞ ሥራው ተማሪዎች የተመጣጠነ ምግብ እንዲያገኙ ከማድረጉ እና የተማሪዎችን ውጤት በማሳደግ የመድገምና የማቋረጥ ምጣኔን በከፍተኛ ደረጃ መቀነስ ከመቻሉ ባለፈ፣ በምገባ መርሃ ግብሩ ምግብ በማብሰል ሥራ ከ10 ሺህ በላይ ለሚሆኑ እናቶች የሥራ ዕድል በመፍጠር ቋሚ ገቢ እንዲያገኙ ማስቻሉ ነው::
ከተማ አስተዳደሩ በምገባ ሥራው በዓለም አቀፍ ደረጃ ሽልማትን በአገኘበት ወቅት ሽልማቱን የተቀበሉት የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ከንቲባ ወይዘሮ አዳነች አበቤ እንዳሉት፤ ኢትዮጵያ ይህን ሽልማት ያሸነፈች ብቸኛ የአፍሪካ አገር ሆና ነው:: ይህ መሆኑ ደግሞ ሽልማቱ ኢትዮጵያን ብቻ ሳይሆን አፍሪካንም እንዲወክል አድርጎታል:: ከሁሉም በላይ ኢትዮጵያ በብዙ መንገድ ሁልጊዜ ምግብ የምትለምን አገር ተደርጋ የምትታወቅበትን ገፅታ ቀይሮታልና እውቅናው ለአገራችን ታሪካዊ ለውጥ ነው::
ጉዳዩ ሀብታም ወይንም ድሃ የመሆን ጉዳይ ሳይሆን፣ የመንግስትን የፖሊሲም፣ የተግባርም ቆራጥነትና ካለችው ውስን ሃብት ለዜጎች ቅድሚያ በመስጠት በተሰራው ስራ የተገኘ ሽልማት ነው:: በቀጣይም ይህ ተግባር ተጠናክሮ የሚቀጥል ይሆናል ብለዋል:: ለመሆኑ እንዴት ቢሰራ ተሸለመ ካልን ከላይ እንዳልነው የካራ አሎ ትምህርት ቤት ምላሹን ይሰጠናል::
የትምህርት ቤቱ ርዕሰ መምህር አቶ አሰፋ መላኩ እንደሚሉት፤ ምገባ የተማሪዎች ብቻ ሳይሆን የወላጆችም ተስፋ ነው:: የመምህራንም እፎይታ መሰረት ነው:: ምክንያቱም መርሃ ግብሩ ከመጀመሩ በፊት መምህራን የተማሪዎቻቸው በልቶ አለመምጣት ስለሚያሳስባቸው ካላቸው ደመወዝ ላይ ቀንሰው ሲመግቡ ነበር:: ያም ሆኖ ብዙዎችን መደገፍ አላስቻላቸውም:: ብዙዎችን ከማቋራጥ ማስቆም አልሆነላቸውም:: ማርፈድና መቅረትንም በምንም ተአምር ሊታገሉት አልቻሉም:: በዚህም ምንም እንኳን የአቅማቸውን ቢያስተምሩም የሚጠብቁትን ውጤት አያገኙም:: አሁን ግን ነገሮች በምገባው ተቀይሮላቸዋል:: ብዙ ነገሮች ቆመዋል በሚባል ደረጃ ላይ ደርሰዋል::
ምገባው ተግባራዊ መሆን ሲጀምር ተማሪዎች በየትምህርት ዘመኑ ወደ ትምህርት ገበታ የሚመጡበትን እድል ሰጥቷል:: በትምህርታቸው ከፍተኛ ውጤት አምጥተው የሚያልፉ ተማሪዎችን ቁጥር ጨምሯል:: በተማሪ ቤተሰብ ውስጥ የሚፈጠረው የኢኮኖሚ ችግር ጭምር ተቃሏል:: ይህ ደግሞ በተማሪው ስነልቦና ላይ በቀጥታም ሆነ በተዘዋዋሪ አወንታዊ ተጽዕኖ አሳድሯል ይላሉ::
የመርሃ ግብሩ ተግባራዊ መሆን ወላጆች በመንግስት ትምህርት ቤቶች ላይ መተማመን እንዲኖራቸው ከማድረጉም ባሻገር መጠነ መቋረጥ እንዲቀንስ እድል ሰጥቷል:: የትምህርት ምገባ መርሃ-ግብሩ የወላጆችን ጫና ከማቃለሉ ባሻገር ተማሪዎች ትምህርታቸውን ተረጋግተው እንዲከታተሉም እንዳደረገ ያነሳሉ::
እየተተገበረ ያለው የተማሪዎች ምገባ መርሐ-ግብር ለተማሪ ወላጆች የሥራ ዕድል በመፍጠር ረገድም የማይተካ ሚና እንዳለው የሚናገሩት ደግሞ የትምህርት ቤቱ የትምህርት መሻሻል ምክትል ርዕሰ መምህርና የምገባ መርሃ ግብሩ አስተባባሪ አቶ አይሸሽም ልየው ናቸው:: እርሳቸው እንደሚሉት፤ በተፈጠረው የሥራ ዕድል ተደራጅተው እንዲሰሩ በማድረግ የተማሪ ወላጆች በኢኮኖሚ አቅማቸው ከፍ ብሏል:: ለአብነትም በትምህርት ቤቱ ከ110 በላይ እናቶች የሥራው ተጠቃሚ ሆነዋል::
በትምህርት ቤቱ ምገባው መጀመሩ ብዙ ለውጦችን እንዳመጣ ምስክርነታቸውን የሚሰጡት ምክትል ርዕሰ መምህሩ፤ የመጀመሪያው ነው የሚሉት በትምህርታቸው የተሻሉ ተማሪዎችን ማፍራት መጀመሩን ነው:: ለዚህ ደግሞ መነሻው መጠነ ማቋረጡ፣ መውደቁን፤ ማርፈዱና ትምህርትን በአግባቡ መከታተል እንዲችሉ ማድረጉ እንደሆነ ያነሳሉ:: ምገባው ከመጀመሩ በፊት በርካታ ተማሪዎች የመማር ማስተማር ስራውን ያስተጓጉሉት እንደነበርም ያስታውሳሉ::
ለአብነት የሚጠቅሱትም በክፍል ውስጥ እንቅልፍ ሲወስዳቸው ማየቱ፤ በርሃብ ምክንያት መውደቃቸውና የጤና እክል እንዲያጋጥማቸው መሆኑን ነው:: መምህሩ እነርሱን በመርዳት የሚያጠፋው ጊዜ እንዲበዛና በአግባቡ ለተማሪዎቹ ትምህርቱን እንዳያቀብል ያደርገዋል:: አሁን ግን ነገሮች ተቀይረዋል:: ተማሪዎች ከራሳቸው አልፈው ቤተሰቦቻቸውን መመገብ ችለዋል:: እንዴት ከተባለ ተማሪዎች በራሳቸው ምሳ እቃ ምግቡ ስለሚሰጣቸው ግማሹን በልተው ለተራቡት ቤተሰባቸው ግማሹን ይወስዳሉ:: ይህ ደግሞ ምገባው ተማሪዎች ቤት ድረስ ሄዶ የስነልቦና ህክምና እንደሚያደርግላቸው ያሳየናል ይላሉ:: ወላጆች ሲቀምሱት አስተያየትን ይቸራሉና ምግቡ ማስተካከያ እንዲደረግለትም ያግዛል:: እናም ምገባው የትየለሌ ጥቅም አለው ባይ ናቸው::
ምገባው ከመማር ማስተማሩ ባሻገር የብዙ ወላጆችን እንባ የጠረገና እፎይታን የሰጠ ነው:: ምን ልቋጥር፣ ከተማሪዎች ያንስብኛል እያሉ እንዳይሳቀቁም አግዟቸዋል:: ውሎ ሲመጣም በቀን አንዴ ብቻ የሚመግቡትን ነገር ነው የሚያዘጋጁት:: ይህ ደግሞ በዛሬ የኑሮ ውድነት ያለውን ሸክም መንግስት ምን ያህሉን እንደሸፈነ መረዳት ይቻላል ይላሉ::
ትምህርት ቤታቸው መንግስት በፈጠረው የምገባ እድል ከ3715 ተማሪዎች ውስጥ ወላጆቻቸው ትምህርት ቤቱን እስኪላመዱ በሚል ምሳ የሚቋጥሩላቸው 60 ተማሪዎችን ቀንሶ ሌሎቹን በምገባው ተጠቃሚ ያደርጋል:: የቅድመ መደበኛ ክፍሎችን ለብቻ በተለየ ሜኑና ክፍልም ይመግባል:: አንደኛ እስከ አራተኛ ያሉትን ከአምስት እስከ ስምንት ካሉት ነጥሎም እንደየባህሪያቸው የሚመገቡበትን ስርዓት ፈጥሯል::
ለቅድመ መደበኛ የተለየ እንክብካቤ የሚደረግበት ምክንያት ሕጻናት የተመጣጠነ ምግብ ማግኘት አለባቸው ስለሚባል ያንን ተግባራዊ ለማድረግ ነው የሚሉት አቶ አይሸሹም፤ ምገባ ተከፋፍለውና በጥራት የሚያቀርቡ 110 እናቶችን በመያዝ የሚሰራ ነው:: ጥራቱ እንዳይጓደልም ቀደም ሲል የቁጥጥር ቡድን ተመድቦ እየቀመሰ መጠኑንና ጥራቱን በማየት ያያል:: አሁን ደግሞ መንግስት ያወረደው አቅጣጫ ስላለ በእርሱ ተግባራዊ እየተደረገ እንደሆነ ያነሳሉ::
አቶ አይሸሽም የምገባው ጥቅም መተኪያ የሌለው ተግባር እንደሆነ አንስተው፤ በአሰራር ዙሪያ በርካታ ችግሮች እየገጠሟቸው እንደሆነ ይናገራሉ:: የመጀመሪያው ያደረጉትም በተደጋጋሚ ጥያቄ የሚቀርብበት የእናቶች ልፋትና ክፍያቸው ያለመመጣጠን ነው:: ተማሪዎችን ልክ እንደልጆቻቸው አድርገው ለመመገብ ቢጥሩም ክፍያቸው ግን በቀን 20 ብር ነው:: ይህ ደግሞ የዛሬውን ኑሮ ውድነት ለመደጎም ቀርቶ አንድ እቃ ለመግዛት አያስችላቸውም:: እናም መንግስት ምላሹን በአፋጣኝ ቢሰጣቸው መልካም ነው ይላሉ::
በሁለተኛ ደረጃ እንደችግር የሚያነሱት የውሃ ጉዳይ ሲሆን፤ በሳምንት አንድ ቀን ለያውም ለትንሽ ሰዓት መጥቶ የሚጠፋ ነው:: ይህ ሁኔታ ደግሞ ብዙ ሮቶዎች ቢኖራቸውም ጠብታ እንጂ ብዛት ያለው ውሃን አያስገኛቸውም:: ምክንያቱም አካባቢው ላይ ያለው ውሃ ወዲያው ከማጠራቀሚያው ያልቃል:: የዚህን ጊዜ ለምግብ መስሪያ ብቻ ሳይሆን ለመታጠቢያ ጭምር ያጣሉ:: የምግብ ስራው በእናቶች ጉልበት ከቤታቸው በጀሪካን በመጣ ውሃ ቢሰራም እጃቸውን ሳይታጠቡ የሚበሉ ልጆችን አበራክቷል:: ይህ በመሆኑ ደግሞ ተማሪዎች ጤናቸው ላይ ችግር መፍጠሩ አይቀሬ ነው:: እናም መንግስት ሊያያቸው እንደሚገባ አጥብቀው ይናገራሉ::
እንደ አቶ አይሸሹም ገለጻ፤ የውሃ ችግሩን ለመፍታት በራሳቸው በኩል ብዙ ጥረት አድርገው አንድ ግብረሰናይ ድርጅት አግኝተው ነበር:: የከርሰ ምድር ውሃ እንደሚያወጣላቸውና ቦታውን ጭምር አይቶ ሄዶ ነበር:: ሆኖም የተለያዩ ቦታዎች ሄደው ለማስፈቀድና ጉዳዩን ለማስረዳት ቢሞክሩም በመንግስት ቢሮክራሲ የተነሳ ሊሳካላቸው አልቻለም:: ይህ ብቻ ሳይሆን አካባቢው በውሃ ችግር ይታወቃልና የከተማ አስተዳደሩ ከንቲባ ወይዘሮ አዳነች አቤቤ በቅርቡ ምላሽ እንደሚሰጡት ቃል ቢገባም ችግሩ ግን አሁን ድረስ አልተፈታም:: ስለሆነም እንደመንግስት ከሁለት አንዱ መፍትሄ እንዲሆን ቢያግዝ መልካም ነው::
ውሃ እናገኛለን በሚል ተስፋ በግቢው ውስጥ የጀመሯቸው በየመደቡ ተከፍለው መምህራንና ተማሪዎች እንዲሁም መጋቢ እናቶችና የአስተዳደር ሰራተኞች የሚንከባከቧቸው አትክልቶች ነበሩ:: በውሃ እጥረት ምክንያት ግን የተፈለገውን ያህል እያመረቱላቸው እንዳልሆነ የሚገልጹት አስተባባሪው፤ የውሃ ጉዳይ አፋጣኝ ምላሽ የሚፈልግ በመሆኑ ሊታይ እንደሚገባ አበክረው ያስረዳሉ::
በመጨረሻ ፈተና ሆኖብናል ብለው ያነሱት ጉዳይ የኤሌክትሪክ ነገር ሲሆን፤ የምግብ አገልግሎቱን ለማቅረብ ዛሬም እናቶች ልክ እንደገጠሩ በእንጨት እየሰሩ መሆናቸውን ነው:: በኤሌክትሪክ የመስራት እድሉ ቢኖራቸው ሰዓታቸውን ቆጥበው ለሌሎች ሥራዎች የሚነሱበትን እድል ሰጣቸው ነበር:: በተጨማሪም አንድ አይነት ጣዕም ያለው ምግብ መስራት እንዲችሉ ያግዛቸዋል:: የጤና ጉዳያቸውም የተስተካከለ ይሆናል:: ከሁሉም በላይ ለማገዶ የሚወጣው ከፍተኛ ገንዘብ ብዙ ችግሮችን ቀርፎ ለሌላ ማዋል የሚቻልበትን እድል ይፈጥራል:: ስለሆነም ይህም ሊታሰብበት ይገባል ይላሉ::
ለምገባ ተብሎ የሚመደበው ገንዘብ አይደለም እነዚህን ጥቂት ችግሮች ብዙ ነገር የሚፈታ እንደሆነ የሚጠቅሱት አቶ አይሸሽም፤ ባለፈው ዓመት ብቻ ቢታይ ለእነርሱ ትምህርት ቤት ወደ 25 ሚሊዬን ብር ተመድቧል:: ይሁንና ጥቅም ላይ የዋሉት በዛ ከተባለ 12 ሚሊዬን ብር ነው:: ቀሪው ተመልሷል:: ስለዚህም፣ ተመላሽ ከማድረግ ይልቅ መንግስት አሰራሩን ቃኝቶ ችግሮችን መፍቻ ቢያደርጋቸው ብዙ የተሻለ እድሎችን ለተማሪዎች ብቻ ሳይሆን ለማህበረሰቡ ማቅረብ ይችል እንደነበር ያነሳሉ:: አሁንም እንዳረፈደ በመጥቀስ ለተግባራዊነቱ ቅን የሆኑ ልቦች ይምጡ ይላሉ::
ትምህርት ቤታቸው በምገባው ዙሪያ የቀጣይ እቅዶችን ጭምር ይዞ እንደሚንቀሳቀስ የሚናገሩት አቶ አይሸሽም፤ አንደኛው ምገባውን ለመደጎም የሚያስችሉ ሥራዎችን እየከወኑ መሆኑን ያነሳሉ:: ይህም የጓሮ አትክልቶችን በትምህርት ቤቱ ቅጥር ግቢ ውስጥ በመስራት ነው:: ነገር ግን የውሃ ጉዳይ መፍትሄ ካላገኘ የሚቻል እንዳልሆነ ይናገራሉ::
ሌላው ያነሱት ነገር ለምገባው መሻሻል ከአንዳንድ ተቋማት ጋር ማስተሳሰርና በዝቅተኛ ዋጋ ግብዓቶች እንዲቀርቡ ማድረግ ነው:: ይሁንና መንግስት ቢታከልበት የበለጠ እንደሚሆን ያምናሉ:: ምክንያቱም የግብርና ምርቶች አቅርቦትን በብዛት ማሳካት የሚቻለው በእርሱ በኩል ሲመጣ ነው:: እንደ ሸገር አይነቶችም የዳቦ አቅርቦቱን የተሳለጠ የሚያደርጉት መንግስት ጣልቃ ሲገባ ነው:: ስለሆነም ይህ ቢታይና ምገባ ማዕከላቱ ቢደገፉ ባይ ናቸው::
በመደጋገፍ ውስጥ ብዙ ለውጥ አምጪ ሥራዎችን እናያለን:: ለዚህም በአብነት የምናነሳው በቅርቡ የተደረገው አለማቀፋዊ ሽልማቱ ነው:: ምገባው የተማሪዎችን ብቻ ሳይሆን የሁሉንም ማህበረሰብ ችግር የሚፈታ መሆኑን በቅርብ እያየነው ነውና ይገባናልም ሳልል አላልፍም:: ከዚያ ባሻገርም እንደሚያስኬደን አምናለሁ የሚሉት አቶ አይሸሽም፤ በምገባው ብዙዎች እስትንፋሳቸው ተመልሷል፤ ተስፋ አግኝተዋል፤ ጠንካራ ተማሪዎች ተፈጥረዋል፤ ህልመኛና የሚደርሱበትን የሚያውቁ ተማሪዎችን መምህራን እንዲያዩ ሆነዋል:: ቤተሰብም ተስፋው እየለመለመለት ነው:: ምክንያቱም በምገባው እፎይታን አግኝቷል፤ ኑሮ ውድነቱን መቋቋም ችሏል:: ስለዚህ ምገባው ፖለቲካ ሳይሆን ለውጥ ነውና ሽልማቱ የውጤቱ ነው:: ወደፊትም አጠናክረን እንድንሰራ የሚያበረታን ነው:: እናም ሁላችንም ስኬቱን እያየን በምንችለው መልኩ እንደግፈው ሲሉ መልዕክታቸውን ያስተላልፋሉ:: እኛም ምክራቸውን እንቀበለውና እንተግብረው በማለት ጽሑፋችንን ቋጨን:: ሰላም!!
ጽጌረዳ ጫንያለው
አዲስ ዘመን ጥቅምት 14/2015