የካቲት 1967 ጥቂት የትግራይ ተወላጆች የነበረውን ስርዓት በመቃወም ነፍጥ አንግበው ደደቢት በርሃ ከተቱ:: የትግራይ ነጻ አውጪ ግንባር /አሸባሪው ትህነግ/ መመስረቱም ተበሰረ:: ከአንድ አመት በኋላም በ1968 የመጀመሪያውን ማኒፌስቶ (ድርጅቱ የሚመራበት ሰነድ) በሚስጢር ተሰራጨ:: የነበረውን ስርዓት ለመቃወምና በኢትዮጵያ ዴሞክራሲያዊ ስርዓት ለማንበር በርሃ ገብተናል ያሉት ግለሰቦች በወራት ውስጥ ሃሳባቸውን ለውጠው ትግራይን ከእናት ሃገሯ የመገንጠል አላማ እንዳላቸው አስታወቁ:: አማራም ዋነኛ ጠላታቸው እንደሆነ አወጁ::
በድንገት የተቀየረውና ትግራይን ከእናት ሀገሯ ኢትዮጵያ ለመገንጠል የተሸረበውን ሴራ የሚቃወሙ ንጹሃን የትግራይ ልጆች በድብቁ ማኒፌስቶ አልተስማሙም:: በአገኙት አጋጣሚ ወደ በርሃ የገቡበት አላማ ትግራይ መገንጠል እንዳልሆነና ከሌላው ኢትዮጵያዊ ጋር ያለውን ኋላቀር ስርዓት በጋራ ማስወገድ ዋነኛ የትግል ስልት መሆን እንደሚገባው በየአገኙት አጋጣሚ ተሟገቱ::
ሆኖም እነዚህ አገር ወዳድ ኢትዮጵያውያን በሴራ በየአሉበት መታረድ ጀመሩ:: ኢትዮጵያዊነትን ስለመረጡ በያሉበት ተረሸኑ፤ እድለኛ የሆኑትም ባዶ ስድስት የሚባል ከምድር በታች እስር ቤት ለአመታት ታሰሩ:: ተንገላቱ:: ግማሾቹም እራሳቸውን በተገኘው አጋጣሚ ሁሉ አጠፉ:: በአጠቃላይ በ17 አመታቱ ጦርነት ውስጥ ኢትዮጵያንና ኢትዮጵያዊነትን ያሉ ከ20 ሺ በላይ ንጹሃን የትግራይ ልጆች በአሸባሪው ትህነግ አመራሮች የጭካኔ በትር መገደላቸውን በትግሉ ወቅት የነበሩ ነባር የቡድኑ አመራሮች ይናገራሉ::
እስከ 1977 ዓ.ም ድረስ ትህነግ በሚያራምደው ጸረ-ኢትዮጵያዊ አካሄድ በርካታ ተቃውሞዎች ሲገጥሙት ቆይቷል:: ንጹህ ኢትዮጵያዊ የሆነው የትግራይ ህዝብም ትግራይን ከኢትዮጵያ የመገንጠል አስተሳሰብን ስለማይቀበለው በትህነግ የተረቀቀው ማኒፌስቶ ለህዝቡ ይፋ ሳይሆን ቆይቷል:: አልፎ አልፎ ሾልከው የሚወጡ ወሬዎችም የትግራይን ህዝብ ተቃውሞ እንዳይቀሰቅሱ በማለት በፍጥነት የማዳፈን ስራዎች ሲሰሩ ቆይተዋል:: የህዝብ ተቀባይነት ያላቸውን እንደ ሙሴና አግአዚ የመሳሰሉ ጠንካራና ንጹሃን ኢትዮጵያዊ የትግራይ ልጆችን ከጀርባቸው በመተኮስ እንዲገደሉ ተደርጓል::
በ1977 የተከሰተው ድርቅ ግን የትህነግን ታሪክ ቀየረ:: ትግራይን ጨምሮ በሰሜኑ ክፍል የተከሰተው ድርቅ ለትህነግ አመራሮች ሰርግና ምላሽ ሆነ:: በሰዎች ርሃብ እና ዕልቂት የፖለቲካ መሰረቱን አጠነከረ:: በጣዕረ ሞት ውስጥ ካሉና ከሚያቃትቱ ነፍሶች በተነጠቀ የእርዳታ እህል የአሸባሪው ትህነግ ክንድ ፈረጠመ:: ከዓለም አቀፉ ማህበረሰብ ለድርቁ ተጎጂዎች ከተሰበሰበው 100ሚሊዮን ዶላር ውስጥ 95 ሚሊዮን ዶላሩን በመስረቅ እራሱን በመሳሪያ አጠናከረ:: በምትኩ የትግራይ ህዝብ በርሃብ ረገፈ::
በቂ ምግብ ያላገኘው የትግራይ ህዝብ ሕይወቱን ለማትረፍ ወደየትኛውም ቦታ እንዳይንቀሳቀስ ታገተ:: የትግራይ ህዝብ መላወሻ አጥቶ አይኑ እያየ በርሃብ ረገፈ:: ለህዝብ ዕልቂት ምንም አይነት ርህራሄ የማይሰማው የቡድኑ አመራር በሰረቀው ገንዘብ መሳሪያ በገፍ አስገባ:: ቀደም ሲል አንዲት ስንዝር መሬት ተቆጣጥሮ የማያውቀው ትህነግ በየቦታው በለስ ቀናው::
ሰኔ 15 ቀን 1980 ዓ.ም በትግራይ ህዝብ ላይ ሌላ ክህደት ተፈጸመ:: ለደርግ ወታደራዊ ኃይል የተሳሳተ መረጃ በመስጠት ለገበያ የወጣውን የሃውዜንን ህዝብ በማስጨረስ ሌላ ክህደት ፈጸመ:: ጸረ- ኢትዮጵያ አቋም በነበራቸው ሀገራት ድጋፍም ጉዳዩን ዓለም አቀፍ ለማድረግ ተሞከረ:: በሁኔታው ግራ የተጋባው ዓለም አቀፉ ማህበረሰብም በወቅቱ የነበረውን መንግስት አውሬ አድርጎ ሳለው::
በርካታ ወከባ የደረሰበትም የመንግስቱ ኃይለማርያም አመራር በሂደት መፍረስ ጀመረ:: 1983 ዓ.ም የስርዓቱ ማብቂያ ሆነ:: በንጹሃን ደም ላይ እየተረማመደ የመጣው የትህነግ አመራርም በለስ ቀንቶት ታላቋን ኢትዮጵያን የመምራት ዕድል አገኘ::
ሳያስበው ኢትዮጵያ የመምራት ዕድል ያገኘው የትህነግ አመራር በወረደ አስተሳሰቡ ኢትዮጵያን ከታላቅነት ወደ ቁልቁለት ማውረድ ጀመረ:: የ3ሺ አመት ታሪክ ባለቤት የሆነችውን ኢትዮጵያ በአንድ ሽማግሌ ዕድሜ በ100 ዓመት ቀንብቦ አስቀመጣት:: ከኢትዮጵያዊነት ይልቅ ዘርና ጎሳ ገነነ፤ በመላ ሀገሪቱ ብሔርተኝነት ተቀነቀነ:: ኢትዮጵያዊነትም ጭጋግ ለበሰ:: ጸረ ኢትዮጵያዊ የሆኑ አካላትም ጮቤ ረገጡ:: ኢትዮጵያ እና ኢትዮጵያዊነት እንዳበቃላቸው ታመነ::
ሆኖም በጽኑ መሰረት ላይ የቆመው ኢትዮጵያዊነት አቧራ ቢወርሰውም፤ ጉም ቢሸፍነውም፤ አቀበትና ቁልቁለት ቢበዛበትም እንዳደፈጠ አንበሳ ክንዱ ብርቱ ነበር:: በአገዛዝ ዘመኑ ኢትዮጵያንና ኢትዮጵያዊነትን ይጠላ የነበረውን የትህነግ አመራርን ለማሰወገድ ሁሉም የልቡን በልቡ አድርጎ ሲጠብቅ ቆይቷል:: የትህነግ አመራር ውዳቂ እንዳገኘ ጥንብ አንሳ ሙስናና ዘረፋ ላይ ሲርመሰመስ ኢትዮጵያዊነትን የሚያቀነቅኑ አመራሮች ብቅ አሉ::
በኦሮሚያ፤ በአማራ በአዲስ አበባና በተለያዩ የሀገሪቱ ክፍሎች ጸረ ትህነግ እንቅስቃሴዎች በረከቱ:: በሁኔታው የተደናገረው የትህነግ አመራር የሚይዘው የሚጨብጠው አጣ:: መሳሪያ ቢተኩስም፤ አስቸኳይ ጊዜ አዋጆችን ቢያዥጎደጉድም የኢትዮጵያን ህዝብ ማቆም አልቻለም::
በሁኔታው ተስፋ የቆረጠው ሴረኛው የትህነግ አመራር 27 አመታት በፈላጭ ቆራጭነት ከኖረበት አራት ኪሎ ቤተ መንግስት ፈርጥጦ መቀሌ ገባ:: የኢትዮጵያ ህዝብም በመጠኑ እፎይታ አገኘ:: ሆኖም በሴራ ተወልዶ በሴራ ያደገው የትህነግ አመራር መቀሌ መሽጎ ኢትዮጵያን ማተራመስ ቀጠለ::
ቀድሞ የዘራቸውን መርዞችና የቀበራቸው የጥፋት ፈንጆች አንድ በአንድ ማፈንዳት ጀመረ:: ብሔርን ከብሔር መፋጀት፤ ሃይማኖትን ከሃይማኖት ማናቆር ጀመረ:: በዚህም በበርካታ አካባቢዎች ሞት፤ ስደትና መፈናቀል ነገሰ:: ዩኒቨርስቲዎችም የዕውቀት ማዕከል መሆናቸው ቀርቶ የሞት ማእከላት እንዲሆኑ አበክሮ ሰራ::
አሸባሪው ትህነግ ከሃዲ ቡድን ነው:: ውለታን የማያስታውስ፤ በቀለኛና አረመኔ ነው:: ለዚህ ትልቁ ማሳያ በሰሜን ዕዝ ላይ የወሰደው ትውልድ ይቅር የማይለው አጸያፊ ተግባር ነው:: የሰሜን ዕዝ አባላት ከ20 አመታት በላይ በቀበሮ ጉድጓድ ውስጥ የትግራይ ህዝብን ሲጠብቁ ኖረዋል:: ሆኖም ከሃዲው ትህነግ የሰሜን ዕዝ ወታደሮችን በውድቅት ጨለማ ከጀርባቸው አርዷቸው ተገኝቷል:: ይህም አልበቃ ብሎት በጠራራ ጸሃይ ከበድን ላይ ልብስ ገፎ በጸሃይ አንቃቅቷል:: በተጋደሙ ሬሳዎች ፊት ከበሮ አንስቶ ደልቋል::
ሆኖም ጀግናው የመከላከያ ሰራዊት ይህን አረመኔ ቡድን የገባበት ገብቶ ቀጥቶታል:: የመከላከያ ሰራዊትን ምት መቋቋም ያልቻለው ቆላ ተንቤን ገብቶ ለመሸሸግ ተገዷል:: ሆኖም ለትግራይ ህዝብ በሚል መንግስት ከተቆጣጠረው የትግራይ መሬት መውጣቱን ተከትሎ በውጭ ደጋፊዎቹ አማካኝነት እንደገና ነፍስ ዘርቶ ወደ አማራና አፋር ክልል በመምጣት እንደገና የበቀል እርምጃውን ፈጽሟል:: መነኩሴዎችን ደፍሯል፤ በልጆቿ ፊት እናትን ደፍሯል፤ የሰዎችን ሆድ በሳንጃ ቀዷል፤ ገሏል፤ አፈናቅሏል፤ ቤተ እምነቶችን ደፍሯል::
አሸባሪ ቡድኑ ይህን አስጸያፊ ተግባር እየፈጸመ ደብረሲና ድረስ ቢመጣም የኢትዮጵያ የጸጥታ ኃይሎች አስራ አምስት ቀን ባልሞላ ጊዜ ውስጥ ቀጥቅጥጠው ከአማራና ከአፋር ክልል በማስወጣት አንገቱን ሰብሮ መቀሌ እንዲገባ አድርገውታል:: የተሰበረ አከርካሪውን ለስድስት ወራት ሲጠገን ቆይቶ ነሐሴ 18 ቀን 2014 ለሶስተኛ ጊዜ ትንኮሳ በማድረግ ጦርነት ቀስቅሷል:: እራሱ በጫረውም እሳት የመጨረሻ ግብዓተ መሬቱን ቆፍሯል::
አሸባሪው ሕወሓት ሶስተኛውን ጦርነት የጀመረው የውጭ ደጋፊዎቹን በመተማመን ነው:: የውጭ ኃይላት የሽብር ቡድኑ እስትንፋስ እንዳትቆረጥ የሳተላይት እና የመሳሪያ ድጋፍ፤ የሚዲያና የኮሙኒኬሽን እገዛ፤ ዲፕሎማሲያዊ ጫናና የኢኮኖሚ ዕቀባ ቢያደርጉም አሸባሪ ቡድኑን ሊያድኑት አልቻሉም:: አሁን የትግራይ ህዝብም የትህነግን ሴራና የማደናገሪያ ስልት የተረዳ ይመስላል:: ለዘመናት በዚህ ቡድን አደንቋሪ እና አደንዛዥ ፕሮፓጋንዳ ልጆቹን ከመገበር ባለፈ ያገኘው አንዳች ጠቀሜታ እንደሌለ ከተጨባጭ የህይወት ተሞክሮው ለመረዳት እድል አግኝቷል ።በተለይም ቡድኑ በህዝባዊ እንቢተኝነት ከስልጣን ተወግዶ ትግራይ በመመሸግ የሄደበት የጥፋትና የእብሪት/የእብደት / መንገድ ለትግራይ ህዝብ የቱን ያህል ደንታ ቢስ እንደሆነ ከመቼውም ጊዜ በላይ እንዲያገናዝብ እድል ሰጥቶታል።
ለትግራይ ህዝብ ቅርብ በነበረው ፤ በቀበሮ ጉድጓድ ሆኖ ለአመታት ሲጠብቀው የነበረውን የመከላከያ ሰራዊት ከኋላው ከመውጋት ጀምሮ ለሰላም የተዘረጉ እጆችን በመርገጥ ለስልጣን ጥማቱ ሲል ተጨማሪ ሁለት ጦርነቶችን በሀገር ላይ በማወጅ የትግራይ ወጣቶችን ለእልቂት ዳርጓል ።ሕዝቡን ከፍ ወዳለ ማህበራዊ ምስቅልቅል ውስጥ ከቶ ፤ በዚህም በአለም አቀፍ ደረጃ ለመቆመር ረጅም ርቀት ተጉዟል ።
ከሁሉም በላይ መቼም ቢሆን ሊለያቸው ከማይችላቸው የአማራና የአፋር ወንድም ህዝቦች ጋር ደም በማቃባት የህዝቦቹ ቀጣይ ግንኙነት ችግር ውስጥ እንዲወድቅ ስራዬ ብሎ በተጠናና ጭካን በተሞላበት መንገድ ተጉዟል ።ይህ ሁሉ የቡድኑ ጥፋት የትግራይ ህዝብ የቡድኑን የጥፋት መንገዱ አይኑን ከፍቶ ማየት እንዲችል ረድቶታል። ለዚህም ነው ነጻ በወጡ የትግራይ መሬቶች ህዝቡ ለሰራዊቱ የእንኳን ደህና መጣችሁ መልካም ምኞቱን እየገለጸ ያለው ። ለዚህ ነው እዚህ እዚያም የቡድኑን አገዛዝ የሚቃወሙ ድምጾች በትግራይ ምድር መሰማት የጀመሩት።
በአሁኑ ወቅት አሸባሪ ቡድኑን ለማዳን የሚችል ምንም አይነት ምድራዊ ኃይል የለም:: ስለሆነም አሁን የቀረው አሸባሪው ትህነግ በ1967 ተወልዶ በ2015 ከዚህ ዓለም በሞት ተለየ የሚል የሙት መታሰቢያ ሃውልት ማቆም ብቻ ነው::
እስማኤል አረቦ
አዲስ ዘመን ጥቅምት 14/2015