በዚህ ጋዜጣ የጥቅምት 5 ቀን 2015 ዓ.ም እትም “የኢትዮጵያን ስም የተሸከሙ የሙያ ማኅበራት” በሚል ርዕስ በተግባራቸው ግዝፈት ሳይሆን በስማቸው ብቻ “የኢትዮጵያ…” የሚል ቅጽል እያከሉ ያለ ፍሬ ኮስምነው የሚገኙ በርካታ “ብሔራዊ ማኅበራት” ከሚያንጎላጅጁበት እንቅልፍ እንዲባንኑ መቀስቀሳችን ይታወሳል። ለምን ከገባንበት ጥልቅ ድባቴ “አወካችሁን” እንደማይሉ ተስፋ በማድረግ ጭምር።
ሃሳባችንን ዘለግ በማድረግም አላግባብ የተሸከሙትን ግዙፍ የኢትዮጵን ስም አንድም በአግባቡ ተጠቅመውበት ለሀገር የሚበጅ ፍሬ እንዲያፈሩ፤ አለበለዚያም አላቅማቸው “እንኮኮ” ብለው ፊጥ ካሉበት “የኢትዮጵያ ስም” ጫንቃ ላይ እንዲወርዱ ጠንከር ያለ የወዳጅነት ሃሳብ ለመሰንዘርም ተዳፍረናል።
ለማዋዣነት እንዲረዳም የፈረንሳዩ ገናና መሪ ናፖሊዮን ቦናፓርቴ በጦር ሜዳ ዐውደ ውጊያ ላይ በነበረበት አንድ ወቅት ፈሪ ወታደሩ ሲሸሽ አስተውሎት ካስጠራው በኋላ፤ “ስምህ ማነው?” ብሎ እንደጠየቀው፤ ወታደሩም “ናፖሊዮን” እባላለሁ ብሎ ሲመልስለት “ወይ እንደ እኔ እንደ ናፖሊዮን ጀግና ሁን፤ አለበለዚያ ስሜን መልስልኝ” አለ መባሉን ጭምር ጠቅሰናል።
ናፖሊዮንን በምሳሌነት የጠቀስነው ኢትዮጵያም ጨከን ብላ ስሟን አላገባብ የተሸክሙትን የሙያ ማኅበራት “ወይ ስሜን መልሱ፤ አለበለዚያም የስሜን ክብር ያህል አገልግሉኝ!” ብላ “በብሔራዊ ማኅበርነት” መንበሩን የያዙትን ቡድኖች እንድትገስጻቸው ጭምር ምክር ሃሳብ አቅርበንላታል። የዛሬው ርዕሰ ጉዳያችን ከላይኛው የመንደርደሪያ ሃሳብ ጋር ተቀራራቢ ቢመስልም በይዘቱ ጠነን እና ጠጠር የሚል የመሟገቻ ፍሬ ነገሮች የተንዠረገጉበት መሆኑን አስረግጠን ማስታወስ እንደወዳለን።
ዝክረ አትላስ፤
ከሀገራችን ተጠቃሽ ገጣሚያን መካከል አንዱ የሆነው ብዕረኛ የቀመራቸውን ጥቂት ስንኞች በመዋስና በግጥሙ ውስጥ ስለተጠቀሰው አንድ “ገጸ ባሕርይ” ጥቂት መዘከሪያ ሃሳብ ፈነጣጥቀን ወደ ሞጋቹ ርዕሰ ጉዳያችን እናቀናለን።
”አትላስ የግሪኩ፣ አትላስ ‘የተረቱ› ምድርን ስላዘለ፣
ሲዘከር ጉብዝናው፣ ሲወደስ መጠሪያው ጽኑ እየተባለ።
”የእኔ ስስ ትከሻ ምን ተብሎ ይጠራ፣
ተሸክሞ የሚኖር ምድርን ከአትላስ ጋራ።‘
በእነዚህ ስንኞች ውስጥ የተጠቀሰው “አትላስ” ጥንታዊ ግሪኮች የፈጠሩት የአፈ ታሪክ ውላጅ ነው። ከአማልክቱ መካከል አንዱ እንደነበርና በሰራው ስህተት ምክንያት ከፍ ባሉት አለቆቹ አማልክት ውሳኔ ፍጻሜ በሌለው ዘለዓለም፤ ዓለምን ከነግሳንግሷ ተሸክሞ እንዲኖር ፍርድ እንደተላለፈበት አሳዛኙ ተረክ ዝርዝሩን ይነግረናል።
ዛሬም ድረስ “አትላስ” በፍርደኛነቱ እንደቀጠለና “ዓለም” በጫንቃው ላይ ተቀምጣ እንደምትንፈላስ የሚያሳዩ በርካታ ሐውልቶች በአቴንስ አደባባዮችና በበርካታ ሀገራት ተገሽረው ማስተዋል እንግዳ አይደለም። በጂኦግራፊ ትምህርት ደጋግመን ስሙን የምንጠራው የዓለም ካርታ “አትላስ” ተብሎ የተሰየመውም የዚህ ምስኪን ተሸናፊ የግሪክ “አምላክ” ፍርደኛ ታሪክ መነሻ ሆኖ መሆኑን ልብ ይሏል። ለማንኛውም ወደ ዋናው ርእሰ ጉዳያችን እንዝለቅ።
ባለወርቃማ ትከሻዎች፤
ኢትዮጵያ በሉዓላዊ ክብሯ፣ በሞገስና በነፃነቷ “እመቤት ሆይ!” እየተባለች ተከብራና ተወዳ እንድትኖር ምክንያት የሆኑት ያለፉትና ዛሬም በሕይወት ያሉት ብሩካን ልጆቿ ናቸው። “ልጆቿ” ስንል ሁሉንም ማለታችን አይደለም። አንዳንዶች ልጅ ሳይሆኑ ግብርም ስምም የሌላቸው “የእንግዴ ልጅ” የሚባሉ ዓይነቶች ናቸው።
የእናት ሆድ ዝንጉርጉር እንዲሉ ከዜጎች መካከል አንዳንዶች ለመጻፍ (ለታሪክ ክብር የበቁ ማለት ነው)፣ አንዳንዶችም ለወናፍ (ለአልባሌ) ተግባር የተፈጠሩ መሆናቸውን ልብ ይሏል። ይህንን አገላለጽ የተዋስነው፡- “‹የዋህ በግ› ሁለት ወልዳ አንዱን ለመጻፍ አንዱን ለወናፍ” የሚለው ሀገራዊ ብሂል ትዝ ቢለን ነው።
ኢትዮጵያን አስከብረውና እያስከበሩልን ያሉት ተወዳሽ ልጆቿ ዋነኛው መለያቸው ሀገራቸውን በትከሻቸው ላይ ተሸክመው ለመኖር ራሳቸውን ሙሉ ለሙሉ አሳልፍ መስጠታቸው ነው። እንደነዚህ ዓይነት ልጆቿ እምነታቸው ከራስ ያለፈ፣ በወገን ፍቅር ልባቸው የነደደ፣ የዜግነት ኃላፊነታቸውን ለመወጣት ሹመትም ሆነ ሽልማት የማይጠብቁ፣ ጎሽታም ሆነ እሶሶ የማይጠይቁ የተግባር ሰዎች ናቸው። የክፉ ቀን አለኝታ የሆኑት እነዚህ የሀገር ጌጦች፤ ቀዳሚው ህልማቸውና ርዕያቸው የሀገራቸው ከፍታና የሕዝባቸው እፎይታ ነው።
የሚነጉደው እድሜያቸውና የምድር ጉዟቸውን ሲያጠናቅቁ የሚያሸልበው ሥጋቸውና ትዳራቸው እያጓጓቸውና እያሳሳቸው “ከራስ በላይ ነፋስ” በማለት አያላዝኑም። ልባቸውን አሳብጠውና ስሜታቸውን አስብተውም “ከእኔ ወዲያ ላሳር” እያሉ አይፏልሉም። ሀገራቸውን በወርቃማ ትከሻቸው ላይ ተሸክመው የሚያከብሯት አማላይ ጉርስም ሆነ ውርስ ስለሚፈልጉ አይደለም። ተግባራቸው እንጂ ስማቸው እንዲጮኽና አዋጅ እንዲለፍፍም አይፈልጉም። ሃሳቡን በተጨባጭ ማሳያ እናጎላምሰው።
ሀገርን ለመታደግ ከግፈኛው ወራሪ ኃይል ከአሸባሪ ሕወሓት ጋር እየተፋለሙ ያሉትን አናብስት የጥምር ጦሩን ጀግኖቻችንንና በተለየ “ንስር ዐይኑ” ለሉዓላዊነታችን ክብር በተጠንቀቅ ዘብ የቆመልንን የመከላከያ ሠራዊታችንን ለአንድ አፍታ በዐይነ ህሊናችን አቅርበን እናስተውላቸው። ደምና ላባቸውን፣ ዕድሜያቸውንና ቤተሰቦቻቸውን ለመስዋዕትነት አቅርበው ጠላትን እየጣሉ የሚወድቁት ለግል ጥቅማቸው ሲሉ ሳይሆን ኢትዮጵያን ላለማስደፈር የገቡትን የቃል ኪዳን መሃላ የሙጥኝ ብለው ስለሚጠብቁ ነው። ኪዳናቸውን በዝማሬ የሚገልጹትም፡-
”አጥንቴም ይከስከስ፤ ደሜም ይፍሰስላት፣
ይህቺን ሀገሬን ፍጹም አይደፍራትም ጠላት።‘
እያሉ ነው።
አንዱ በመስዋዕትነት ሲወድቅ ሌላው እየተቀባበለ ኢትዮጵያ አብራቸው እንዳትወድቅ ቀን ከሌት የሚፋለሙትም ከራሳቸው በላይ የሀገራቸው ክብር ነፍሳቸውንና ማንነታቸውን ጢም አድርጎ ስለሞላው ነው። እንዲያማ ባይሆን ኖሮ ሕወሓት የሰሜን ዕዝ ጀግኖችን በከዳበትና ሀገር መከራ ላይ በወደቀችበት ጊዜ “ኢትዮጵያን በጫንቃቸው ላይ ተሸክመው” ነፍሳቸውን ለውርርድ በማቅረብ መራር ዋጋ ባይከፍሉ ኖሮ ዛሬ “እምዬ” ምን ልትመስል እንደምትችል መገመቱ አይከብደም። ክብርና ሞገስ ለጀግናው መከላከያችን፣ ለፀጥታ ክፍሎችና ለሕዝባዊ ሠራዊቶቻችን ይድረስልን።
በወታደራዊ መስክ ብቻ ሳይሆን በሕዝብ አስተዳደር፣ በፖለቲካ አመራር፣ በግብርና፣ በትምህርት፣ በንግድና በኢንቨስትመንት፣ በሕግና በሰላም ማስከበር፣ በሳይንስና ቴክኖሎጂ በሚዲያውና በኪነ ጥበቡ መስክ ወዘተ. ወርቃማውን ጫንቃቸውን ዝቅ አድርገው ኢትዮጵያን በመሸከም ከፍ ላደረጓት ልጆቿ በሙሉ ክብርና ሞገስ ይሁንላቸው።
በሠርክ ጸሎታቸው/ዱአቸው እና በጾማቸው ሥጋቸውን እያረቁ በመቃተት ተንበርክከውና ዝቅ ብለው ኢትዮጵያን ወደ ፈጣሪ ዙፋን ለማቅረብ ሌት ተቀን ለሚቃትቱ የሃይማኖት አባቶች፣ መምህራንና ርህሩህ እናቶችና ዜጎች የኢትዮጵያ አምላክ ዘላለማዊ ክብር ያዋርሳቸው። ሀገራቸው በክብር ጸንታ የኖረችውና ዛሬም ተከብራ ያለቸው የእነርሱን ወርቃማ ጫንቃ መንበር አድርጋ ስለሆነ ኩራትም ክብርም ሊሰማቸው ይገባል።
ኢትዮጵያ የተሸከመቻቸው ወበከንቱዎች፤
“ጽድቁ ቀርቶ…” እንዲሉ ኢትዮጵያን መሸከሙ ቢቀር እንኳን በእርሷ ላይ ተንጠልጥለው የተጣቧት በመዥገር የሚመሰሉ የልጅ ጠላቶቿ አደብ ቢገዙ ባልከፋ ነበር። ቀደም ሲል ስንኞቹን የተዋስነው ገጣሚ ካሳተመው የመጽሐፉ ገጾች ውስጥ “የመጻተኛ ሀገር” በሚል ርዕስ በአራት ሀረጋት ቀምሮ ያቀረበልን አንድ ግጥም ከዚህ ንዑስ ርዕስ ጋር የሚጎዳኝ ስለመሰለን ደራሲው ባየበት ዕይታ ሳይሆን ይህ ጸሐፊ በገባው መልኩ እንደሚከተለው ለሃሳባችን ማጎልበቻነት ተጠቅመንበታል።
“ሀገር ድንኳን ትሁን፤ ጠቅልዬ የማዝላት፣
ስገፋ እንድነቅላት፤ ስረጋ እንድተክላት።”
ኢትዮጵያን ለማስከበር ሳይታክቱ ዋጋ እየከፈሉ ያሉ ልጆቿ የመኖራቸውን ያህል በአንጻሩም “ሆድ አደርነትን” መለያ በማድረግ ኅሊናቸውን ለክፋትና ለጥፋት እየቸረቸሩ ያሉ “የሀገር ጉዶች” መኖራቸውንም በብዙ መልኩ እያየንና እየታዘብን ነው። እንደነዚህ ዓይነት የቁም ሙቶች የሚኖሩት ለዜግነታቸው ክብር “ዘብ በመቆም” ሳይሆን በእኔነታቸው ታዛ ሥር ተጠልለውና አድበተው በሙት ኅሊናቸው እየተነፈሱ፣ በበድን ማንነታቸው እየተኩራሩና “እኔ ከሞትኩ…” አለችው ከምትባለው እንስሳ ጋር አብረው እያፋሸኩ ነው።
ለእነርሱ የሚታያቸው ኢትዮጵያ የጀግኖች ልጆቿን ጫንቃ እንደ አእማድ አጽንታ በክብር መቆሟ ሳይሆን ሲቃዡ የሚያድሩት “የሰሜን ነፋስ” ካስማውን በቀላሉ ነቃቅሎ እንደሚያፈራርሰው ተራ ድንኳን ነው። ድንኳኑን የተሸከመው ደግሞ የእነርሱ ጎባጣ ወገብ እንደሆነ ሲፎክሩ መታየታቸው ሌላው መገለጫቸው ነው።
“ሲፋጅ በማንኪያ፤ ሲቀዘቅዝ በእጅ” እንዲሉ በውስጣቸው የሰረጸው ፍልስፍና ከላይ በሁለት ስንኝ ውስጥ የተጠቀሰው መልእክት ነው። ሀገር ስትረጋጋ ሊኖሩባት፤ “መከራ ሲገጥማት” ጥለው እብስ ሊሉ በቋፍ ላይ መሆናቸው የኅሊና ቢስነታቸው አድማስ ጥግ ነው።
የሀገርን መከራ ለጥቅማቸው፣ ክፉ ወቅትን ለመክበሪያቸው ለመጠቀም ሌት ሲቃዡ፣ ቀን ሲባትቱና ሲወራጩ የሚሉ ዜጎች ቁጥር በስታትስቲክ ቀመር ቢገለጽ መልካም በሆነ ነበር። እንደነዚህ ዓይነት ዜጎች ባህርያቸውም ሆነ ስልታቸው የረቀቀ ነው። ሀገር ለእነርሱ “የነፍስና የሥጋቸው መጦሪያ” እንጂ የክብር ጌጥና ውበት አይደለችም። በንሰሃ ለመመለስም ድፍን አእምሯቸው፣ የደነደነው ልባቸውና የማይረካው ፍላጎታቸው ልቅ ሆነው እንዲጋልቡ ብርታት ሆኗቸዋል።
ለዚህ እውነታ በጥሩ ማሳያነት የሚጠቀሱት ደግመን ደጋግመን እንደገለጽነው የሕወሓት መሪ ተብዬ “የቁም ሙቶች” ናቸው። እነዚህ ጥቂትና በጣት የሚቆጠሩት ግለሰቦች እንኳን ኢትዮጵያን በትከሻቸው ላይ ሊሸከሙ ቀርቶ “ጠረኗን” ሳይቀር ተጠይፈው የኖሩ ጉዶች ናቸው። በሥልጣን ላይ ተፈናጠው የኖሩበትን ዘመን ያገባደዱት እንደ መዥገር ኢትዮጵያ ላይ ተጣብቀው ግቷንና ደሟን እየመጠጡ ነበር። የሃያ ሰባቱ ዓመታት መከራ የሚገለጸው “ዘረፋ” በሚለው ቃል ሳይሆን የሀገሪቱን ሥጋና አጥንት እየጋጡ ነበር ማለቱ ይቀላል።
አበላላቸው አንድም የጅብ፣ አንድም የቅልጥም ሰባሪ ጆፌ አሞራ ዓይነት ነበር። የላይ ላዩን ሥጋ ብቻ ሳይሆን የአጥንቷ ውስጥ መቅኒም አልቀራቸውም። ይህ ማለት የዘረፋ መረባቸው የተዘረጋው ከተራ ኪዮስክ እስከ የከርሰ ምድር ሀብት ድረስ መዝለቁን ለማሳየት ነው። የዱር አውሬዎች እንኳን ያደኑትን የሚመገቡት ከራሳቸው የቡድን ሠራዊት ጋር በመጋራት ነው። ሕወሓት ይሉት የዘመናችን ሰብዓዊ ደም መጣጭ ቢያንስ ስሙን ተሸክሞ “የእኔ ብቻ” እያለ ለሚሸነግለው የተከበረው የትግራይ ሕዝብ አንዳች የበጎነት ተግባር ቢፈጽም ባልከፋ ነበር። የመሪዎቹ ዋና ግብ ሥጋቸውና ቤተሰባቸው ብቻ ስለሆነ ዘረፋው ለራስ ጓዳና ለራስ ወገን ብቻ ነበር።
ኢትዮጵያ አልተፈተነችም ማለት አይደለም። በውስጥ በእንግዴ ልጆቿ፣ በውጭ በታሪካዊ ጠላቶቿ ተጠቅታለች፣ ተጎድታለች ታማለች። ቢሆንም ግን የተሸከሟት ባለወርቃማ ትከሻ ልጆቿ ለጠላቶቿ መቅሰፍት፣ ለጥቃቷ አለኝታ፣ ለህመሟ ፈውስ ሆነው ስለተሸከሟት የተንገዳገደች ትምሰል እንጂ አትወድቅም፤ የዛለች ትምሰል እንጂ አትሰነካከልም። እናት ዓለም በተሸከሙት ልጆችሽ ጫንቃ ላይ ከፍ ብለሽ ግነኚ፣ ደምቀሽ አብሪ፣ በጠላቶች ፊት ድልን፣ በወደረኞች ፊት ሞገስን ይስጥሽ። ሰላም ይሁን!
በ(ጌታቸው በለጠ /ዳግላስ ጴጥሮስ)
gechoseni@gmail.com
አዲስ ዘመን ጥቅምት 12/2015