አሁን አሁን ብሔራዊ ፈተናዎች ሲታሰቡ በየጊዜው ሁሉም አዕምሮ ውስጥ ብቅ ማለት የሚጀምረው የፈተና መስረቅና መኮራረጅ ጉዳይ ነው። ከዚህ ጋር ተያይዞም በርካታ ተማሪዎች ተጎድተዋል። በማለፍና በመውደቅ ማለት ነው። ሳያውቅ ዩኒቨርሲቲ የገባው ከአቅሙ በላይ ትምህርት ስለሚገጥመው በጭንቀት እንዲዋዥቅ ይሆናል። አቅሙ ኖሮት ደግሞ በፈተናው መሰረቅ ምክንያት ውጤት ዝቅ ያለበት ሲቆጭ ይኖራል። ሁለቱም የተጎዱበት ይህ የፈተና ጉዳይ መሰረታዊ ችግሩ ምንድነው ከተባለ ሁለት ምክንያቶችን መጥቀስ እንችላለን። መስረቅና የእርማት ስህተት ናቸው። በዚህ ውስጥም ሁለት ነገሮች ተፈጥረዋል።
የመጀመሪያው በስርቆት ፈተናው የደረሰው ተማሪ አቅሙ ሳይኖረው በገፍ ዩኒቨርሲቲን እንዲቀላቀል መሆኑ ሲሆን፤ ሁለተኛው በገፍ የመጣው ውጤት ጎበዞቹን ተማሪዎች ከቤት ማስቀረቱ ነው። ምክንያቱም ውጤት ይሰቀልና ለእነርሱ የሚሆን ቦታ ይጠፋል። እናም የስነልቦና ስብራት ሁለቱም ላይ እንዲገጥም ያስገድዳል። ለዚህ ደግሞ ካቻምና የሆነውን ብቻ መጥቀስ በቂ ነው። ፈተናው ተሰርቋል፤ የእርማትም ስህተት ነበረበት። በዚህም ብዙዎች ዩኒቨርሲቲ የመግባት እድላቸው ከሽፏል። ከእነዚህ መካከል በአንድ ወቅት ኢንተርቪው ያደረግነው በአማራ ክልል ሰሜን ወሎ ዞን መቄት ወረዳ የፍላቂት ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤት ተማሪ ሳሙኤል ጸጋዬ አንዱ ነው።
እርሱ እንደሚለው፤ ቤተሰቦቹና መምህራኑ ብቻ ሳይሆኑ ዞኑ ጭምር ይጠብቀው ነበር። ሆኖም በፈተናው መሰረቅና በእርማት ስህተት የተነሳ ውጤቱ ሞልቶለት መግባት አልቻለም። የአስተራረም ችግሩን በተደጋጋሚ ቢገልጽም ማንም ቦታ ሊሰጠው አልፈቀደም። ይህ ነገር ደግሞ የእርሱ ብቻ ሳሆን የሌሎች ጓደኞቹም ችግር ነበር። ስለዚህም እርሱና እኩዮቹ ውጤታማ ቢሆኑም ከቤታቸው ቀርተዋል። መንግስት በእኛ ይብቃና እዚህ ላይ ልዩ ትኩረት መስጠት አለበትም ባይ ነው።
እርሱና መሰሎቹ በጦርነቱ ምክንያት ዳግም እድሉን እንዳገኙ የሚያስረዳው ተማሪው፤ አሁን በሚደረገው ፈተና በሚገባም ራሳቸውን ለማሳየት እንደሚሞክሩ ይገልጻል። ለዚህም ክረምቱን ሙሉ በመረዳዳት ውስጥ እንዳሳለፉ ያነሳል። እናም ምን ያህል ብቁ እንደሆኑ ለማሳየት ቋምጠዋል። ነገር ግን አሁንም ቢሆን አንድ ነገር ያሳስባል። ይህም የአስተራረሙ ጉዳይ ሲሆን፤ የፈተና ስርቆቱም ቢሆን ዩኒቨርሲቲ መፈተኑ ብቻ ያቆመዋል የሚል እምነት የለውም። ስለሆነም ጥብቅ ክትትል እንዲደረግበት ያስገነዝባል።
ተማሪው ያለውን የስርቆት ጉዳይ ለማስቀረት ሰሞኑን ለጋዜጠኞች በተሰጠ መግለጫ እንደተባለው ትምህርት ሚኒስቴር ትልቅ ትኩረት ሰጥቷል። አንዱ አዲስ ፕሮጀክት ነድፎ መንቀሳቀሱ ነው። ከፈተና መስጫ ቦታ ጀምሮ የተለየ እንቅስቃሴ ማድረግ ጀምሯል። በዩኒቨርሲቲዎች ፈተናው እንዲሰጥ ማድረጉ አንዱ ሲሆን፤ በዙሪያው የሚደረጉ ማንኛውም የፈተና ሒደቶችም በጥብቅ ዲሲፕሊን የሚከናወኑ እንደሆኑ ተገልጿል።
ቀደም ሲል በፈተና ወቅት በሚደረግ ጉዞ ፈተናዎች የመዘረፍ ዕድላቸው ሰፊ ነበር። አዲሱ አሰራር ግን ይህንን እንደሚያስቀር እምነት ተጥሎበታል። ምክንያቱም አብዛኞቹ ዩኒቨርሲቲዎች የሚገኙት የአየር ማረፊያ ያለባቸው በመሆኑ ፈተናዎች በአውሮፕላን ስለሚጓጓዙ የመሰረቅ አጋጣሚያቸው ይቀንሳል። በተጨማሪም የሚጎዳ ሰውም እንዳይኖር ያደርጋል። የትምህርት ሚኒስትሩ ፕሮፌሰር ብርሃኑ ነጋ እንዳሉት፤ ባለፈው ዓመት በነበረው ፈተና 13 የሚሆኑ የፌደራል ፖሊስ አባላት ሞተዋል። ስለዚህም ይህ እንዳይሆን የአሁኑ አሰራር በብዙ መንገድ ያግዛል።
አዲሱ አሰራር ፈታኞች በምንም መልኩ ከተማሪዎች ጋር እንዳይታወቁ የሚደረግበት አሰራር ተዘርግቷል። ይህ ደግሞ የእርስ በእርስ መጠቃቀም እንዳይኖር ያስችላል። ሌላው ኤሌክትሮኒክስ መሳሪያዎች ማለትም እንደ ሞባይል፤ ታብሌትና መገናኛ መሳሪያዎች በምንም ተአምር ወደ ፈተና አካባቢ እንዳይደርሱ መደረጉ ሲሆን፤ ፈተናውን ተማሪዎች በራሳቸው ብቃት እንዲሰሩ ያስችላቸዋል። ከዚህ ጋር ተያይዞ ክልከላው ለተማሪዎች ብቻ ሳይሆን ለፈታኞችና ለሌሎች አካላትም ነው። አንድ ተማሪ ከፈተና በኋላም ቢሆን ወጥቶ ሞባይል ይዞ በቅጥር ግቢ ውስጥ ቢገኝ በምንም አይነት መልኩ ዳግም ወደ ፈተና መግባት እንደማይችልም ተወስኗል። እናም ተማሪዎች ሕይወታችሁ እንዳታበላሹ በዚህ አጋጣሚ ለመግለጽ እንወዳለን።
ሌላው እንደ ሕግ የተቀመጠው ነገር ማንኛውም ተማሪ የአንገት ሐብል፣ የጸጉር ጌጥ፣ የጆሮ ጌጥ፣ የጣት ቀለበት ከጋብቻ ቀለበት በስተቀር ይዞ መገኘት አይችልም የሚለው ነው። የጦር መሳሪያና ፎቶ አንሺ መሳሪያዎች እንዲሁም የድምጽና መሰል መቅጃዎችም ይዞ መግባትም አይቻልም። ማንኛውንም አደንዛዥ እጽ መጠቀምም ሆነ ይዞ መግባት የተከለከለ ነው። በዩኒቨርሲቲዎች ውስጥ በሚቆይባቸው ጊዜያት ምንም አይነት ጮክ ያለ ድምጽ ማሰማትም አይቻልም። ይህንን ሁሉ መመሪያ የሚያስፈጽሙት ደግሞ ወደ 8 ሺ የሚጠጉ የፌደራል ፖሊሶች እንደሆኑም ፕሮፌሰሩ ተናግረዋል።
በዘንድሮው ማለትም በ2015 ዓ.ም የሚፈተኑት ተማሪዎች በ2014 የነበሩት ሲሆኑ፤ በሁለት ዙሮች ፈተናቸውን ይወስዳሉ። የመጀመሪያውን ፈተና የሚወስዱት ማለትም ዛሬ ለፈተና የቀረቡት የማህበራዊ ሳይንስ ተፈታኞች ሲሆኑ፤ በሁለተኛ ዙር ደግሞ የሚፈተኑት የተፈጥሮ ሳይንስ ተማሪዎች ናቸው። ፈተናውን የሚወስዱበት ቀን ጥቅምት ስምንት ጀምሮ ሲሆን፤ በዩኒቨርሲቲው ቅጥር ግቢ ውስጥ ከጥቅምት አምስት ጀምሮ መግባት አለባቸው። በሁለቱም ዙር ከዘጠኝ መቶ ሺህ በላይ ተማሪዎች ይፈተናሉ። በተለያዩ ችግሮች ምክንያት የማይፈተኑ 56ሺህ ተማሪዎችም አሉ። ከወር ቆይታ በኋላ ፈተናውን እንደሚወስዱም ሚኒስትሩ አስረድተዋል።
ተፈታኞቹ እንደተለመደው ፈተናውን የሚ ወስዱት በወረቀት ሲሆን፤ ከባለፉት ዓመታት የሚለየው በዩኒቨርሲቲ የሚፈተኑ መሆናቸውና 11 ኮዶች ተሰጥተውት መፈተናቸው ነው። ይህ ደግሞ ኩረጃን ከመቀነሱም በላይ ተማሪዎች ሌሎች ጎበዝ ተማሪዎችን አስበው እንዳይገቡ ያደርጋቸዋል። በራሳቸው አቅም ሰርተው የት ላይ እንዳሉም ለመለየት ያስችላቸዋል። ለመሆኑ ይህንን አዲስ የፈተና ስርዓት ለመተግበር ዩኒቨርሲቲዎች በምን ያህል ተዘጋጅተዋል ስንልም የተወሰኑ ዩኒቨርሲቲዎች ፕሬዚዳንቶችን ማነጋገር ችለናል። በተለይም የስጋት ቀጠና ናቸው የተባሉት ልዩ ትኩረታችን ናቸው።
የጸጥታ ችግር ተማሪዎችን ሳይረብሽ በተረጋጋ መንፈስ እንዲፈተኑ ከማድረግ አንጻር ዩኒቨርሲቲዎች ውስጥ ምንም ሳይጎልባቸው እንዲፈተኑ ከማድረግ አኳያ ምን ያህል ዝግጁ ናችሁ ካልናቸው መካከል የደብረታቦር ዩኒቨርሲቲ አንዱ ሲሆን፤ የአካዳሚክ ጉዳዮች ምክትል ፕሬዚዳንት ዶክተር ክንዴ ገበየሁ በጉዳዩ ላይ ሀሳባቸውን አጋርተውናል። እርሳቸው እንደሚሉትም፤ ዩኒቨርስቲው በአማራ ክልል ባለው ጦርነት ከባድ ችግሮችን አሳልፏል። ሆኖም የ12ኛ ክፍል ፈተና አገርን የማዳን ጉዳይ ነውና ችግርን ተጋፍጦ መልካም ነገሮችን ለማምጣት የተቻለውን እያደረገ ነው። በቂ ዝግጅት አድርጓልም። ይህ ዝግጅቱ ብዙ መሥራትን ያስተማረው ነው። ዩኒቨርሲቲው አንዱ የመፈተኛ ተቋም ተደርጎ በመመረጡ ያሉትን ሃብቶች አብቃቅቶ መጠቀም እንዴት እንደሚቻልም ተምሮበታል። ማለትም በእከዛሬው ቆይታ 190 የሚሆነውን ክፍል ብቻ ይጠቀማል። አሁን ግን ነገሮች ሲከብዱና ከሚቀበላቸው ተማሪዎች በላይ እንዲፈትን ሲገደድ ወደ 500 የሚደርስ የመፈተኛ ክፍል ማዘጋጀት ችሏል። የጸጥታ ችግሩ ብዙ ንብረቶችን ቢያወድምበትም እነዚያን ለመተካት የተለያዩ አማራጮችን ተጠቅሟል። ለአብነት ለመፈተኛ የሚሆኑ ወንበሮችን ከመጠገን ባለፈ ከኮሌጆች ጭምር በማምጣት ለመሙላት ጥረት አድርጓል።
የደብረ ታቦር ዩኒቨርሲቲ ዛሬ በሚጀምረው ፈተና ከ17 ሺህ በላይ ተማሪዎችን ተቀብለው ያስተናግዳል። በቀጣዩ ዙርም ከዚህ ያልተናነሰ ተማሪ ያስፈትናል። ይህ ደግሞ ለቀጣይ የዩኒቨርሲቲ ተማሪዎች ቅበላ ዩኒቨርሲቲው አቅሙን የሚያሳይበት ይላሉ የአካዳሚክ ጉዳዮች ምክትል ፕሬዚዳንቱ ዶክተር ክንዴ ገበየሁ።
የጸጥታ ስጋቱን በተመለከተ ከከተማ አስተዳደሩና ከዞን ጋር እየሰሩ መሆኑን የሚናገሩት ምክትል ፕሬዚዳንቱ፤ እንደ ፌደራል እስከ አሁን ከ60 በላይ የፌደራል ፖሊሶች ገብተው ሥራ ጀምረዋል። ተጨማሪ የጸጥታ አካላትም ይኖራሉ። ስለሆነም ችግር ይገጥማል ተብሎ አይታሰብም። ክልሉም ቢሆን የጸጥታውን ጉዳይ በስፋት ትኩረት አድርጎ እየተንቀሳቀሰበት ነው። ከፍተሻ እስከ ፈተና ቆይታቸው ድረስ ተማሪዎች ተረጋግተው እንዲፈተኑ ያደርጋል። ማህበረሰቡ ጭምር ለዚህ የፈተና ዝግጅት የበኩሉን እንዲያደርግ ስምምነት ላይ ተደርሷል። ይህ ደግሞ መጨረሻው ባይታወቅም ጅማሮው ግን ስኬታማ ነው ለማለት ያስችላል ይላሉ።
የደንቢዶሎ ዩኒቨርሲቲ ፕሬዚዳንት ዶክተር ለታ ተስፋዬ በበኩላቸው እንደገለጹት፤ አካባቢው የስጋት ቀጠና ተደርጎ ቢወሰድም ከተለያዩ አካባቢዎች ወደ ዩኒቨርሲቲው ተመድበው የመጡትን 4000 ተማሪዎች እስካሁን በነበረው ጊዜ ተቀብለን ስናስተናግድ ነበር። ይህ ሁኔታ ደግሞ ዩኒቨርሲቲያችን ጸጥታና መረጋጋት ያለበት እንደሆነ አረጋግጦልናል። የቀጣዩን ስራ እንዲሰጠንም አድርጎናል። በቂ ዝግጅት ያደረግንበት ነው ብለዋል።
መደበኛ ተማሪዎቹ አሁን የትምህርት ዘመኑን ፈተና ስላጠናቀቁ መውጣት ጀምረዋል የሚሉት ዶክተር ለታ፤ ምንም ችግር ሳይደርስባቸው ወደየቤተሰባቸው እንዲሄዱ ከማድረግ አኳያ ከኮማንድ ፖስቱ ጋር በመቀናጀት የዩኒቨርሲቲውን 10 የሚሆኑ ሰርቢሶች በማዘጋጀት ጉዞ እንዲጀምሩ አድርገናል። በምትኩ የ12ኛ ክፍል ተፈታኞች የሚገቡበት ይሆናልም። ለዚህ ደግሞ በዩኒቨርሲቲው እስከዛሬ ተቀብለን የምናስተምራቸው ተማሪዎች ሰባት ሺህ ብቻ በመሆናቸው ለፈተና የተሰጡን 6500 ተማሪዎች አይከብዱንም ብለውናልም።
በመጀመሪያው ዙር 3200 ተማሪዎችን እንደሚያስተናግዱ የጠቆሙት ፕሬዚዳንቱ፤ በሁለተኛው ዙር 3300 ተማሪዎችን ያስፈትናሉ። ለዚህም በተለይ ተማሪዎች ምንም አይነት የኤሌክትሮኒክስ መሳሪያ ይዘው ስለማይገቡ ችግር እንዳይገጥማቸው ከማድረግ አንጻር ዩኒቨርሲቲው ሁሉንም ነገር አሟልቶ ይጠብቃቸዋል። በተመሳሳይ መመገቢያና መሰል የተማሪዎች አገልግሎቶችን በበቂ ሁኔታ እንዲያገኙ ማድረጉንም ተናግረዋል።
ለፈተና በአንድ ክፍል ቢበዛ 30 ተማሪ እንዲፈተን ይደረጋል በሚል 250 ክፍሎችን በማዘጋጀት እየጠበቁ እንደሆነ የገለጹት ፕሬዚዳንቱ፤ በጸጥታ ጉዳይም ተማሪው ብቻ ሳይሆን ቤተሰብ ጭምር ስጋት እንዳይገጥመው ጥብቅ ክትትልና ቅንጅት እየተደረገ ነው። ለዚህ ደግሞ ከፌደራል ጭምር የመጡ ፖሊሶችና የጸጥታ አካላት አሉ። እንደ ክልልም ቦታው የስጋት ቀጠና በመሆኑ ልዩ ትኩረት ተደርጎ እየተሰራበት እንደሆነም አንስተዋል።
የሰመራ ዩኒቨርሲቲ ፕሬዚዳንት ዶክተር መሃመድ ኦስማን በበኩላቸው እንዳሉት፤ ዩኒቨርሲቲው ይህ ዕድል የተሰጠው ለመጀመሪያ ጊዜ በመሆኑ ደስተኛ ነው። ተማሪዎቹን በተረጋጋና በተሻለ መንገድ እንዲፈተኑ ለማድረግም የተቻለውን ሁሉ ያደርጋል። የዝግጅት ሥራውን የጀመረው ከሁለት ወር በፊት ሲሆን፤ በተለይም በአፋር ቴሌቪዥንና ሌሎች ሚዲያዎችን በመጠቀም ተማሪዎች ተረጋግተው እንዲፈተኑ ለማድረግ የግንዛቤ ማስጨበጥ ሥራ ሲሰራ ቆይቷል።
አፋር የስጋት ቀጠና በመሆኑ ተማሪዎች ብቻ ሳይሆኑ ቤተሰብ ጭምር ይጨነቃል። ጉዞ ላይ ችግር ይገጥማቸዋልም የሚል ስጋት ያደረባቸውም አሉ። እናም ዳሎልና መሰል የጦርነት አካባቢዎች ላይ ያሉ ተፈታኝ ተማሪዎችን የክልሉ ትምህርት ቢሮ፤ የክልሉ መስተዳደርና ዩኒቨርሲቲው በመደጋገፍ ተማሪዎቹ ቀድመው ወደ ከተማው በመምጣት ለፈተናው ልዩ ዝግጅት እንዲያደርጉ እየታገዙ ነው። ዩኒቨርሲቲው ከተፈቀደለት አካልና ጊዜ ውጪ ማንም መግባት ስለማይችል በተለያዩ ኮሌጆች ውስጥ ተረጋግተው የሚፈልጉት ነገር ተሟልቶላቸው እንዲቀመጡ ተደርገዋልም ብለዋል።
ጸጥታ ችግር ያለባቸው አካባቢዎች ላይ ለፈተና የሚዘጋጁ ተማሪዎች የስነልቦና ጫና ጭምር ያጋጥማቸዋል። ስለሆነም ችግር እንዳይገጥማቸው ከማድረግ አንጻር እንደ ዩኒቨርሲቲ የሥነልቦና መምህራን በማዘጋጀት የሚያግዙበትን መንገድ አመቻችቷል የሚሉት ዶክተር መሀመድ፤ በሁለቱም ዙሮች ከስምንት ሺህ በላይ ተማሪዎችን ተቀብለው እንደሚያስፈትኑ ይናገራሉ። ለዚህም በቂ ዝግጅት መደረጉን ያነሳሉ። በተለይ አካባቢው በሙቀት የሚታወቅ በመሆኑ ከውሃ፣ ከኤሌክትሪክ ጋር የሚያጋጥሙ ችግሮች እንዳይኖሩ ከወዲሁ መዘጋጀታቸውንም ገልጸዋል። መተፋፈግ እንዳይኖርም በአንድ ክፍል ውስጥ ከ25 በላይ ተማሪዎችን ለመፈተን መወሰኑን አስረድተዋል።
የጸጥታ ጉዳይን በተመለከተ ከክልል እስከ ፌደራል ድረስ በጥብቅ ክትትልና ቅንጅት እየተሰራ መሆኑን የሚጠቁሙት ፕሬዚዳንቱ፤ አካባቢው በሦስተኛ ዙር ጭምር ጦርነት ውስጥ ያለ በመሆኑ ይህንን ትልቅ መዋዕለንዋይ የፈሰሰበትን የፈተና ጉዳይ በቀላሉ የሚያየው አይሆንም። ስለዚህም ማህበረሰቡን ጭምር በማሳተፍ የሚሰራ ይሆናል። ከወዲሁ ትልቅ ሥራ እየተከናወነም ነው። ከዚያም ባሻገር የክልሉ የጸጥታ ኃይልና የፌደራል ፖሊስም በሙሉ አቅማቸው በመስራት ላይ ናቸው። እንደውም ከጸጥታ አኳያም ሆነ በሌሎች ጉዳዮች ዙሪያ ወልዲያና ሌሎች አጎራባች ከተሞች ጭምር ሄዶ በማገዝ ላይ እንደሆኑ አንስተዋል።
ይህ ፈተና ብዙ ተስፋ የተጣለበት ነው። ለተማሪውም ሆነ ለአገር አበርክቶ ያላቸውን ተማሪዎች በብቃት ለማውጣት ያለመም ነው። ስለሆነም ከእስከዛሬው በተለየ መንገድ እንዲሰራበት እንደመንግስት አቅጣጫ ወርዷል። ይህንን ደግሞ የማስፈጸም ኃላፊነቱ የሁሉም ማህበረሰብ መሆን አለበት። ጉዳዩ ለትምህርት ማህበረሰቡ ብቻም የሚተው አይደለም። በተለይም የጸጥታ ችግር ያለባቸው አካባቢዎች ላይ ሁሉም ካልተረባረበ ፈተናው የሚጠበቅበትን ውጤት ሊያመጣ አይችልም። ጠላት ደግሞ ይህንን ይፈልገዋል። እናም ለአገር ሲባል ይህንን ፈተና ተደጋግፎ በሰላም ማጠናቀቅ እንደሚያስፈልግም አስረድተዋል። እኛም ምክራቸው ተገቢ ነውና ሁላችንም ልዩ ትኩረት በመስጠት ሰላማዊ ፈተና እንዲሆን የበኩላችንን እናበርክት በማለት ተሰናበትን። ሰላም!!
ጽጌረዳ ጫንያለው
አዲስ ዘመን ሰኞ መስከረም 30 ቀን 2015 ዓ.ም