ባለፈው እሁድ ኢ ቢ ኤስ ቴሌቪዥን ላይ አንዲት የ13 ዓመት ታዳጊ ልጅ ወልዳ እናት ሆና መታየቷ በማህበራዊ የትስስር ገጾች ሲዘዋወር ነበር። አስገራሚና አሳዛኝ ያደረገው ልጅ መሆኗ ብቻ አይደለም፤ በዚህ ያልጠና ሰውነቷ ያለፍላጎቷ መሆኑ ነው። እናትና አባቷ በፍች በመለያየታቸው ምክንያት መጠጊያ አጣች። ቢያስጠጋኝ ብላ የተጠጋችው ወንድ ነው ለዚህ የዳረጋት።
ሌላኛው አሳዛኙ ነገር ደግሞ ወላጆቿ በሕይወት እያሉ ማገዝ እንኳን ባይችሉ ሞቷን የሚመኙ መሆናቸው ነው።
በዚህ አሳዛኝ ክስተት ምክንያት ብዙዎች ‹‹እንደ ማህበረሰብ ዘቅጠናል›› በሚል ኋላቀርነታችንን እየረገሙ ነው። አዎ! ኋላቀሮች ነን፣ የንቃተ ህሊና ችግር አለብን። መጠጊያ አጥታ የመጣች ገና ምንም የማታውቅ ልጅ ለእንዲህ አይነት ችግር መዳረግ ሰው የመሆን ዝግመተ ለውጥን አለመጨረስ እንጂ ሌላ ምን ይባላል?
በዚሁ ሳምንት አንዲት የ17 ዓመት ታዳጊ በደፋሪዋ ተገድላለች። አስገድዶ በመድፈሩ ለምን ተከሰስኩ ብሎ ነው የገደላት። እንዲህ አይነት አረመኔያዊ ድርጊቶችን እየተላመድናቸው ነው። በየመገናኛ ብዙኃኑ እና በየመድረኩ አንድ ሰሞን ‹‹ጉድ!›› ይባላል በዚያው ይረሳል። የሰዎችን የጭካኔ ድርጊት እናወግዛለን በዚያው ይረሳል፤ ድርጊቶችም ይቀጥላሉ።
እንዲህ አይነት ድርጊቶች በተከሰቱ ቁጥር ማህበረሰብን መርገም ብቻውን መፍትሔ የሚሆን አይመስለኝም። መፍትሔው የንቃተ ህሊና እና የመሰልጠን ባህል እንዲመጣ ማስተማር ነው። የአረመኔዎችን ድርጊት ብቻ ማራገብ ሳይሆን የአስተዋይና የብልህ ሰዎችን ታሪክም ማስተዋወቅ ነው።
የበጎ ሰው ሽልማት ላይ ዲያቆን ዳንኤል ክብረት ሲናገር የሰማሁት አንድ ሀሳብ ነበር። ተደጋጋሚ የትራፊክ አደጋ ያደረሰ ሰው ስሙ በብዙ መዝገቦች ላይ ይገኛል። 30 እና 40 ዓመት ምንም አይነት ግጭት ሳያደርስ ያገለገለ ሾፌር ግን ማንም አያውቀውም። በጎ ነገር ካደረጉት ሰዎች በላይ መጥፎ ነገር ያደረጉት ሰዎች ስም ይነግሳል፤ ችግሩን ግን ሲቀርፍ አይታይም።
የማህበረሰባችንም ነገር ልክ እንደዚሁ ነው። በመራገም ብዛት ለውጥ አይመጣም። ጥቃቅን ሊመስሉን ቢችሉም ማህበረሰባችን ውስጥ በጎ ሰዎችም አሉ። ያንን ውስብስብ ልማድ ጥሰው የሚወጡ ፈላስፎች አሉ። ልጅ እያለሁ በአካባቢዬ የተከሰተ አንድ ታሪክ ልጥቀስ።
በአካባቢው ልማድ ሴት ልጅ ሳታገባ እንኳንስ መውለድ ድንግልናዋን እንኳን ካጣች ትልቅ ነውር ነው። አግብታ ‹‹ክብረ ንጽህናዋ የለም›› ከተባለ ቤተሰቦቿ እንደተዋረዱ ነው የሚቆጠር። በነገራችን ላይ ይሄ ልማድ አሁን ላይ በፊት በነበረው ልክ አይደለም፤ በጊዜ ሂደትና በከተሜነት መስፋፋት አስተሳሰቡ ገጠርም ስለደረሰ እየተሻሻለ መጥቷል።
ወደ ታሪኩ ስመለስ፤ በዚያ ልማድ ውስጥ አንዲት ልጅ ሳታገባ ወለደች። እርግዝናዋ መለየት ከጀመረበት ጊዜ ጀምሮ እናቷ ለወራት ቤት ውስጥ እያዋለች አቆየቻት። ስትወልድ ጭራሹንም እንዳትታይ ጓዳ ውስጥ ተደረገች። ይህን ሁሉ ክስተት አባት ያውቃል። የመደበቁ ተባባሪ ነው።
የጎረቤት ሰዎች ‹‹የት ሄዳ ነው አይተናት አናውቅም›› ሲሉ ራቅ ያለ አካባቢ ያሉ ዘመዶችን በመጥራት ‹‹እነ እገሌ ጋ ሄዳ ነው›› ይላሉ። እዚያው ቤት ውስጥ ለማንኛውም ወላድ የሚደረገውን እንክብካቤ ተደርጎላት ወራት ተቆጠሩ።
እንዲህ እንዲህ እያለ ሹክሹክታው መሰማት ጀመረ። ጉድ የሚለው ጉድ ብሎ፣ በምን መንገድ እንደወለደች ግራ የተጋባውም ግራ እንደተጋባ ነገሩ እየተለመደ ሄደ። ወላጆቿም ‹‹ ማን ማባቱ ምን አገባው!›› በማለት የሚጠይቀውን ሁሉ አፍ በማስያዝ ኩም ማድረግ ጀመሩ። ልጅቷ እንደማንኛውም ሰው አግብታ ሕይወቷን ስትመራ ቆይታ ካለፈው ሕይወቷ ጋር በማይገናኝ ህመም ሕይወቷ አለፈ።
የእነዚህ ወላጆች ታሪክ ከተማ ለኖረ ሰው ምንም ላይገርም ይችላል፤ የሚገርመው የአካባቢውን መጥፎ ልማድ ለሚያውቅ ሰው ነው። ልጃቸው ከጋብቻ ውጭ ካረገዘች ቢያንስ ቢያንስ ትገረፋለች፣ ሲከፋ ደግሞ ለስነ ልቦና ቀውስ የሚዳርግ ማግለል ይደርስባትና በባህላዊ መንገድ ለማስወረድ ስትሞክር ሕይወቷ ያልፋል፤ እነርሱ ግን አንዴ የሆነው ሆኗል ብለው ምንም እንዳይደርስባት ነው ያደረጉት። የእንዲህ አይነት ሰዎች ታሪክ ለብዙዎች ትምህርት ይሆናል።
ይህ ማለት ግን ልጆች ልቅ እንዲሆኑ ይፈቀድላቸው ማለት አይደለም። ዳሩ ግን የስነ ልቦና ቀውስ የሚያስከትል ማስፈራራት በማድረግ ሳይሆን በማስተማርና በምክር ነው። ራሳቸውን ችለው እንዲያውቁ በማድረግ ነው። ከዚህ ሁሉ አልፎ የመጣ ስህተት ካለ ግን እንዳይደገም ማስጠንቀቅ እንጂ ልጅቷን ‹‹እንዳላይሽ!›› ማለት ቀጣይ ሕይወቷም የተመሰቃቀለ እንዲሆን ያደርጋል።
ማህበረሰባችን ውስጥ ያለውን መጥፎ ልማድ ስናወግዝ በጎ እሴቱን ግን በተገቢው መንገድ አላስተዋወቅንም። የባልና ሚስት ፍቺ አጀንዳ የሚሆነውን ያህል 50 እና 60 ዓመታት በትዳር የቆዩ ሰዎች ፍቅር አጀንዳ አይሆንም። ‹‹የዘመኑ ትዳር በሳምንቱ ይፈርሳል›› ያልነውን ያህል በደሳሳ ጎጆ ውስጥ ስላለው ፍቅር አናወራም። አንድን ነገር በመጥፎነቱ አጀንዳ ባደረግነው ቁጥር የመለመድ ዕድል ይኖረዋል።
የተማረ የሚባለው ክፍል አሳዛኝ ድርጊቶች ሲከሰቱ ነገሩን ከማራገብና ከመራገም ያሳደገውን ማህበረሰብ ማስተማር ይሻላል። ችግሩ ግን የተማረ የሚባለውም የሚያጠፋው ጥፋት ያልተማረ ከሚባለው የባሰ መሆኑ ነው። ትልልቅ የትምህርት ደረጃ በያዙ ሰዎች ሳይቀር ነው የአስገድዶ መድፈር ወንጀል የሚፈፀመው። ማህበረሰብን ይለውጣል የተባለው ሰውየ ራሱ መካሪና ተቆጪ የሚያስፈልገው ሆነ ማለት ነው። እንዲህ አይነቱን የሚቀጣው ተገቢውን የህግ እርምጃ መውሰድ ነው።
እንደ ማህበረሰብ ላለብን ችግር ግን በመንግሥትም ሆነ በግለሰብ ደረጃ ኃላፊነታችንን ልንወጣ ይገባል። ትንሽ ቀለም የቆጠርን ሰዎች በየአካባቢያችን የግንዛቤ ለውጥ እንዲመጣ ልንሰራ ይገባል። ከገጠሩ የአገሪቱ ክፍል የመጡ በአዲስ አበባ ጎዳናዎች ላይ ለልመና የተዳረጉ እናቶችንና ሕጻናትን እናያለን። የመጡት ለም መሬት እና የደለበ በሬ ጥለው ነው፤ ምክንያቶቹ በንቃተ ህሊና አለመኖር የሚፈጠሩ ናቸው።
ስለዚህ በየአካባቢው ያሉ ብልህ ሰዎችን አርዓያ በማድረግ የማህበረሰብ የአስተሳሰብ ለውጥ ልናመጣ ይገባል።
ዋለልኝ አየለ
አዲስ ዘመን መስከረም 25/2015