
ፈረንጆች መጥፎ ማስታወቂያ የለም ይላሉ። ይህን የፈጠረው ዘመን ነው። ድሮ ሰዎች ለስማቸው ይጠነቀቁ ነበር። በክፉ ለመነሳት አይሹም። በበጎ ለመነሳትም የአቅማቸውን ጥረት ያደርጋሉ። በዚህም የተነሳ በሚያመርቱት ምርትም ሆነ በሚሠሩት ሥራ ላይ ከፍተኛውን ጥንቃቄ ይወስዳሉ። ከትርፍ እኩል በጎ ስም እንደ ትርፍ ይታይ ነበር። በዘመነ ካፒታሊዝም ይህ ተቀይሯል። በዚህ ዘመን መታወቅ ከፍተኛ ዋጋ አለው። መታወቁ ከተቻለ በበጎ ቢሆን ይመረጣል። ካልሆነ ግን በመጥፎም ቢሆን መታወቅ ይፈለጋል። በጭራሽ የማይፈለገው ነገር አለመታወቅ ነው። ስለዚህም በየጊዜው የሰውን ትኩረት ለማግኘት ብዙ ለየት ያሉ፤ አወዛጋቢ፤ አናዳጅ የማስታወቂያ መንገዶችን በቀጥታውም በዘወርዋራውም ይጠቀማሉ።
የሆነ ሆኖ ይህን ሁሉ ያወራሁት ስለ ማስታወቂያ ሳይንስ ለማውራት አይደለም። ይልቁንም ሰሞኑን በማህበራዊ ሚዲያ የማያቸው አጀንዳዎች ከእነዚህ የማስታወቂያ መንገዶች ጋር ስለተመሳሰሉብኝ ነው። ሁላችሁም እንደምታዩት ሰሞኑን እና ከቅርብ ጊዜያት ወዲህ ሰዎች ከስውር ዓለም አሠራር ጋር በተያያዘ ብዙ ትንታኔ እየሰጡ ነው። ብዙ ውይይቶች እና ክርክሮችም ከዚህ ጋር የተያያዙ ሆነዋል። ክርክሮቹ ብዙውን ጊዜ ይህ ስውር ዓለም እና የክፉ መንፈስ አሠራር ዓለምን እየገዛ እንደሆነ እና ሁሉም ሰው ከዚህ ሊጠነቀቅ እንደሚገባ የሚያሳስብ ነው።
ነገሩ እውነት ነው ወይስ ውሸት ነው ወደሚል ክርክር አልገባም። ነገር ግን ብዙ ሰዎች በዚህ ንድፈ ሃሳብ(ቲዎሪ) እጅጉን ስለተመሰጡ ብዙውን ጊዜያቸውን ስለሱ በማሰብ እና ይህን የተመለከተ መረጃ በመሰብሰብ ነው የሚያሳልፉት። በዚህም የተነሳ አሁን ላይ ብዙዎቹ በዚህ ጉዳይ ላይ ኤክስፐርት ሆነው እያንዳንዱን ባለሀብት፤ አርቲስት፤ ዝነኛ ሰው ኢሉሚናቲ(የምስጢራዊ ማህበረሰብ አባል) ነው ወይም አይደለም የሚል ምደባ የመስጠት ደረጃ ላይ ሁሉ ደርሰዋል። በማህበራዊ ሚዲያ ላይም በዚህ ዙሪያ ትንታኔ ሲሰጥ ነው የሚዋለው። እርግጥ ነው ዓላማቸው ሕዝብን መጥፎ ከሚሉት ነገር ማስጣል ነው። ነገር ግን አንዳንዴ ስለ አንዳንድ ነገሮች ብዙ ባወራን ቁጥር ለዚያ ነገር የማያስፈልገው ትኩረት እንዲያገኝ ሰዎችም ወደዚያ ነገር እንዲሳቡ እያደረግን መሆኑን እንዴት ዘነጋን?
ከላይ እንደጠቀስነው በዚህ ዘመን ማስታወቂያ መልኩ ብዙ ነው። ስለዚህም ስለ አንድ ነገር በመጥፎ መልኩ በትኩረት እንዲወራ ማድረግም የማስታወቂያ መንገድ ነው ማለት ነው። እንደ እኔ ግምት አንድን መጥፎ ነገር መጥፎ ነው ብለን መናገር ጠቃሚ ቢሆንም አንዳንዴ ግን ጭራሽ እንዳይወራ ማድረግ ደግሞ የተሻለው መንገድ ይሆናል። ማህበረሰባችንም ነውር (ታቡ) የሚላቸውን ነገሮች በዚህ መልኩ አጀንዳ እንዳይሆኑ በማድረግ ነው የማስታወቂያ ግብአት ከመሆን ራሱን ጠብቆ የኖረው። አለማውራት ቀድሞውንም የማያውቁት ሰዎች ሳያውቁት እንዲቀሩ የሚያውቁትም እንዲዘነጉት ብሎም እንዳይለማመዱት (ኖርማላይዝ እንዳያደርጉት) ያደርጋል። ማውራቱ ግን ጭራሽ የማያውቁትም እንዲያውቁት የሚያውቁትም እንዳይረሱት እና የተለመደ ነው ብለው እንዲያስቡት ያደርጋል። እንዳይታወቅ እና እንዳይስፋፋ የምትፈልገውን ነገር ደጋግመው ካወራህለት አንተ ለእሱ ውለታ እየዋልክለት ነው ማለት ነው። ምክንያቱም የእሱን የመታወቅ እና የመስፋፋት ፍላጎት ነውና እየፈጸምክ ያለከው።
ይህ ነገር የሚታየው በኢሉሚናቲው ጉዳይ ብቻ አይደለም፤ በብዙ ጉዳዮች ላይም ይታያል። ለምሳሌ በአገሪቱ ብሔርተኝነት ተስፋፍቷል የሚሉ ሰዎች ብዙውን ሰዓታቸውን የሚያሳልፉት ስለ ብሔር ፖለቲካ የሰላ ትችት በመስጠት ነው። በተቃራኒው ያለፈው ሥርዓት ጎድቶናል የሚሉ ሰዎችም ቀኑን በሙሉ የሚያሳልፉት ያለፈውን ሥርዓት በመራገም ነው። ሁለቱም ስለሚደግፉት ሀሳብ በጎነት ከመናገር ይልቅ ስለሚቃወሙት ሀሳብ አደገኝነት በመስበክ ተጠምደዋል። ይህ ሁኔታ አንዳቸው ከሌላቸው ወገን በሀሳባቸው ተማርኮ ወደ እነሱ የሚመጣ ሰው ከማግኘት ይልቅ ጭራሽ ከእነሱ በተቃራኒ ወገን ያለው ኃይል የባሰ እያከረረ እንዲሄድ ነው ያደረገው። በዚህም የተነሳ ዛሬ ላይ ሁለቱ ጽንፎች ሊገናኝ በማይችል መልኩ ተራርቀው ተቀምጠዋል። የፌዴራሊስት እና የአሀዳዊነት ጽንፍ የተፈጠረው አሁን ባይሆንም ነገር ግን አሁን ላይ አንዳቸው ስለሌላቸው አትኩረው በማውራታቸው የተነሳ ሀሳቡ በብዙዎች ዘንድ ጽንፍ ስለረገጠ ነው።
በክልሎች ደረጃ ይህ ሁኔታ ባህል ሆኖ አሁን ላይ የአንዱ ክልል አክቲቪስቶች በሌላው ክልል ላይ ያለውን ችግር በስፋት ሲተነትኑ ይውላሉ። በክልላቸው ስላለው ልማት ወይም መሠራት ስላለበት ሥራ ከመናገር ይልቅ ያኛው ክልል ላይ የተከናወነው ልማት እና ጥፋትን በስፋት ያብራራሉ። ይህ አካሄድ በክልሉ ነዋሪዎች መካከል መቆራቆስን ፈጥሯል። ከዚህ በተጨማሪ ግን አንዳቸው በሌላቸው ላይ የሚያደርጉት የፕሮፓጋንዳ ዘመቻ ቀስ በቀስ ራስን ተበዳይ እና ተጠቂ በማድረግ በመሆኑ የበታችነት ስሜት እንዲፈጠር እያደረገ ነው። ዛሬ ላይ ከሚሰጥባቸው የሰላ ትችት የተነሳ ዝነኛ የሆኑ አመራሮች ተፈጥረዋል።
በሃይማኖት ጉዳይ ላይም ተመሳሳይ ነው። የራሳቸውን ሃይማኖት ሀሳቦች ከማስተማር ይልቅ በሌላው ሃይማኖት ላይ ያለውን ችግር በማጋለጥ እና በመተንተን ላይ የተሰማሩ ሰዎች ቁጥር እየተበራከተ ነው። ይህ ሁኔታም ቀስ በቀስ ቀድሞ የነበረውን መከባበር እያጠፋው በገሀድ መዘላለፍ ፋሽን እንዲሆን አድርጓል። ይህም በሂደት ስንፈራው እና ስንታገለው የነበረው ጽንፈኝነት እንዲወለድ እና መሠረት እንዲይዝ እያደረገ ነው። ስለዚህም አንዳቸው በሌላቸው ላይ የሚለቁት ፕሮፓጋንዳ የጠቀመው ሁለቱንም ሳይሆን ጽንፈኝነትን ነው። ጽንፈኝነት ያልከፈለበት ማስታወቂያ ተሠርቶለታል።
ከሁሉም የሚያስገርመው በኪነ ጥበቡ ዘርፍ ያለው ልማድ ነው። ብዙው ሰው መጥፎ ነው ብሎ የሚያስበውን ከያኒ የሰላ ትችት ይሰነዝርበታል። ሌሎችም ይከተሉታል። ከዚያም ብዙ ሰው መጥፎ ነው የተባለው ሥራ ምን ዓይነት ቢሆን ነው በሚል ወደ ዩቲዩብ ሄዶ ያየዋል። ያ ለሚተቸው ሰው ብዙውን ጊዜ ጠቃሚ ይሆናል። አሁን ላይ ብዙ የኪነ ጥበብ ባለሙያዎች በዚህ መልኩ ከሥራቸው ይልቅ በሚደርስባቸው ትችት የተነሳ ዝነኛ ሆነዋል። በኪነ ጥበቡም ገፍተውበታል። ነገር ግን መሆን የነበረበት የቀረበው ሥራ አይመጥንም ተብሎ ከታመነ ሥራውን አለማየት ወይም ትችትም ካለ አንድ ጊዜ ብቻ መስጠት ይበቃ ነበር። በቋሚነት ስለ እነሱ የምታወራ ከሆነ ግን በማስታወቂያ ሥራ እያገዝካቸው ነው ማለት ነው። ሲጠቃለል ዋነኛ መልዕክት አንዳንዴ ሕዝብን እናስተምራለን ብለን የምንናገረው ነገር የምንቃወመውን ነገር ማስታወቂያ እንዳይሆን እንጠንቀቅ የሚል ነው።
አቤል ገ/ኪዳን
አዲስ ዘመን መስከረም 9 ቀን 2015 ዓ.ም