
ዘመን ዘመንኛውን ይመስላል። በዘመኑ የሚኖሩትን ይስተካከላል። ዘመን የአንድነት መንፈስ የሞላበት መተባበርና ፍቅር ያየለበት ከሆነ፤ ያ ዘመን በፍስሀ ይሞላል። ዘመኑ ሰላም የሰፈነበት እና የፍቅር ከሆነ ያንኑ ይመስላል። ዘመኑ ብሩህ ከሆነ ትውልድም የሚደሰትበትና ሀገር የምትለወጥበት ይሆናል። በተቃራኒው ደግሞ የዘመኑ ባለቤቶች ዘመኑን ካበላሹት ያ ዘመን ጭለማ የወረሰው ይሆናል። አልፎ ሲያስቡት የሚቀፍ፣ ሲነግሩት የማይመች ክፉ ዘመን የሚል ስም ይተርፈዋል።
የዚህ ዘመን ትውልዶች የዚህ ዘመን ባለቤቶች ነን። ስለዚህ የዘመኑ ማማርም ሆነ መንተብ ተወቃሾች እኛው ነን። ስለዚህ ዘመኑን ማንፃትና የተዋበም ማድረግ የእኛ ፋንታ ይሆናል። የዚህ ዘመን ዋነኛ ባለቤቱ የዘመኑ ትውልድ፣ በዚህ ወቅት የተገኘን ሁላችንም ነን። በተለይም የዚህ ዘመን ዋነኛ ተዋናይ የሆነው ወጣት፤ ዘመኑ በሰላም እንዲኖር ሊፈቀድለት ይገባል።
አዎን! በተለይ የወጣቱ ውብ ጊዜ በወጉ ሊኖረው ይገባል። የአገሩን አንገት ቀና ለማድረግ በጉልበቱ ሊለፋላት ይገባል፤ ሮጦ ለሀገሩ ለውጥ ሊያመጣ፣ ጥሮ ህዳሴዋን ሊያረጋግጥ ግዴታ አለበት። እናም ዘመኑን እሱ በሚቃኘው በራሱ ልኬት ሊሰምርለት ያስፈልጋል። ይህ ዘመን የዘመኑ ትውልድ ነውና ራሱ በፈቀደው መልክ እንዲኖረው ለእርሱ እንተውለት።
ለፀብና ለእርስ በርስ ቁርሾ ምክንያት ሲሆን የቆየው የፖለቲካ ልምዳችን ዘመኑን አንትቦብናል። እንደ ኢትዮጵያ ትልቅነት ያልተለቀው የፖለቲካ ልምድ ውድ ጊዜያችንን አለዝቦብናል። የማይጨበጥ የከረመ ቅዠት ዘመናችንን አጨፍግጎታል። ለአገርና ለወገን የምንሰራበት ምርጡ ዘመናችንን በከንቱ ባክኗል። ጥሩ ጊዜያችን እንዲነጠቅ አንፈቅድም። እሳቤያቸው ኢትዮጵያ ካልሆነች፤ መዳረሻ ግባቸው ኢትዮጵያን ከፍ ማድረግ ያልሆኑ ሰዎች ከጨዋታው ገልል ይበሉ። አዲሱን ዘመን በአዲስ መንፈስ እንጀምረው።
የሀገራችንን ህዳሴ እንሻለን የኢትዮጵያን ብሩህ መሆን እንመኛለንና፤ አካሄዳችሁ ይገራ። ተማርን የምትሉ ልሂቃን፣ ፖለቲካውን ለኛ ተው እንደ ጉድ እናሾረዋለን የምትሉ የዘርፉ ተዋናዮች እባካችሁ ዘመናችሁን ኖራችሁ ስታበቁ የእኛን ዘመን አትቀሙን። መልካሙን አመላክቱን በስህተት ውስጥ ዘመናት ያለፈችው ኢትዮጵያ ዳግም የስህተት መኖሪያ አታድርጓት።
አዎ! ይህ ዘመን የእኛ ነውና ለእኛ ተውልን። ዘመኑን ኖሮ የሌሎችን ውድ ጊዜ የሚቀማ፤ እሱ የምሩን ኖሮ ሌላውን የውሸት ለማኖር የሚተጋ ለእኛ በጎ አይደለምና እጁን ከላያችን ላይ ያንሳ። ወጣቱ የተዋበ ጊዜው እንዲበላሽ የወደፊት ተስፋው እንዲጨልም አይፈልግም።
ብሩህ ነገር ሊያይ የተዋበ ነገር ሊያይም የሚያስችለው በጎ አስተሳሰብ መውረስ ይፈልጋል። የተሻለ ዘመን እንዲቀርበው መልካም ጊዜ እንዲመጣለት አጥብቆ ይመኛል። ውብ ጊዜ በጥላቻ ትርክት ማጣት በእርስ በርስ ግጭት ማበላሸትን አይፈቅድም። የሚነገረው በጎ፤ የሚወራለት በጎ መሆን ይገባዋል። ተነስ በታሪክ የከበረችው ሀገርህን ለውጥ እንጂ ተነስ የተከፋችውን ሀገርህ አፍርስ የሚል አይፈልግም። ዘመንህን አጨልም የሚል ጨለምተኛ ሀሳብ ሊቀርብለት አይገባም።
የትውልዱን ውብ ጊዜው ለመቀማት፣ ውድ የሆነውን ዘመኑን ለመንጠቅ የሚሞክር ፖለቲከኛ የራሱን ዘመን አበላሽቶ የዚህ ዘመን ፍካት ላጠልሽ የሚል ስግብግብ ሊቆጠብ ይገባል። ወጣቱ አገሩ በልፅጋ፣ ህዝብ ተለውጦ ማየትን ይመኛል። ለዚህ ምኞቱ መሳካት ለመልካም ሀሳቡ ሙሉ መሆን ደግሞ አብሮነት ሊሰበክ አንድነት ጠቀሜታው ሊነገረው ይገባል።
በኢትዮጵያ ፖለቲካ ውስጥ ዋናውን ሚና የሚጫወቱት ኤሊቶች፤ ለዘመኑ ባለቤት ወጣት መልካምን ማመላከት ለጥሩ ነገር መጣራት አብሮነትን መስበክ ሲገባቸው በተቃራኒው ሊያቆሙት ሲሞክሩ ይታያል። የሀገር ግንባታ ዋንኛ ተዋናዩን ወጣት አስበው የእርሱን ዘመን ለራሱ በሚሆን መልኩ እንዲኖረው መፍቀድን አለመዱም። ባለፈ ታሪክ የሚጋጭ፣ ባልኖረበት ዘመን የሚጠየቅ ፣ በማያውቀው የሚሳቀቅ ለማድረግ በብርቱ ይሰራሉ።
ይህ መንገድ የተሳሳተ ዘመኑና ባለዘመኑን ትወልድ የማይመጥን ነውና የወጣቱን ዘመን መቀማቱ የተዋበ ጊዜውን መንጠቁ ሊያቆሙ ይገባል። ትውልዱ አብሮነት ገብቶት፣ ተከባብሮና ተማምኖ የሚኖር ጥላቻን ንቆ ፍቅርን አንግሶ ዘመኑን በሰላም የሚያሳልፍ ውብ ጊዜውን በራሱ ቅኝት የሚራመድ መሆኑ ሊታወቅለት ግድ ይላል። ሁሉም የራሱ የሚለው ውድ ጊዜ የኔ የሚለው ዘመን አለው። ወጣቱም እራሱና አገሩ የሚለውጥበት ትኩስ ጉልበቱ ሳይባክን ውጤታማ በሆነ ጉዳይ የሚያውልበት የእድሜው ዋንኛው ክፍል ነውና ዘመኑን ይኑረው።
ሀገር የምትገነባበት ህዝብ የሚለወጥበት መንገድ ማመላከት የወደፊቱ ዘመን ብሩህ እንዲሆን መስራት ሲገባቸው የወጣቱን ዘመን የሚያጨልሙ መልካም ጊዜውን የሚነጥቁት ማነሳሻዎች በርክተዋል። የተሻለች አገር መስርቶ የእራሱ የሆነውን ምቹ ሁኔታ የሚፈጥር ትወልድ፤ ለእነሱ ጉዳይ ሳይሆን መሰላል የፍላጎታቸው ማሟያ ለማድረግ ይጥራሉ። ለወጣቱ የሚሆን ብሩህ ጊዜውን በሰላም የሚኖርበት እድሉን የሚነጥቁት ሀሳቦች እንዲላበስ አጉል እኔ ላንተ ተቆርቋሪ ነኝ፤ ስላንተ እኔ ተሟጋች ነኝ የሚል ማታለያ ያቀርቡለታል።
ወጣቱ እኔ በዘመኔ በፍቅር ማደር በወቅቴ ተስማምቶ መኖር እሻለሁና አስማሙኝ፣ ጥንት አባቶች የነበሩበት አንድነት አብረው ያደሩበት መቻቻል አስተምሩኝ ሊል ነው የሚገባው። እነሱ በተቃራኒው የሚነግሩት አሉታዊ ነገር የሚያስረዱት የተዛባ ሆኗል። ወጣት ሆይ ከዛሬ ምናምን አመት በፊት እነ እንትና አባቶችህ በድለዋልና ተነስ ተዋጋ፤ ወገኔ ሆይ እነ እንትና ሊያጠቁህ ከጫፍ ደርሰዋልና ጠላት ሁናቸው የሚሉ ማታለያዎች አይፈልግም።
ይህ ዘመን መልካም አስተሳሰብ የሚያሸንፍበት የማያሻግር አመለካከት የሚከስምበት ነው። አዎን ይህ ዘመን ዋንኛ ባለቤቱ የዘመኑ ትወልድ ዋንኛ ተዋናዩም የዛሬው በፍቅር ያመነ ዜጋ ነው። ይህ ፈፅሞ ሊቀማ አይገባውም። ወጣቱ ስለ አገሩ መልካም መሆን በርትቶ የሚሰራበት ቀድማ ጀምራ ኋላ የቀረችው አገሩ ወደፊት እንድትራመድ ትኩስ ጉልበቱ ሳይሰስት የሚሰዋበት ዘመኑ ነውና ይህ ዘመን ሊቀማ አይገባም።
የዚህ ዘመን ትውልድ የራሱ የሆነ ጊዜው በፍቅር ያመነ በአንድነት የፀና ሆኖ እንዲያሳልፈው የምትሰብኩት ፍቅር የምትነግሩት ደግሞ አብሮነት መሆን ይገባዋል። ድንቅ የሆነ ዘመኑ ተቀምቶ ባልኖረበት ዘመን ታሪክ የሚጋደል ባላየው ሁነት የሚጋጭ መሆን ከቶም የለበትም። ለዚህ ትውልድ ይህ ዘመን ምትክ የሌለው የተዋበ መልካም ነገሮችን የሚያልምበት ተስፋው እንዲሳካ የሚታትርበት ነውና ዘመኑ ለራሱ ለባለቤቱ ይተውለት። የተሳሳተ ትርክት በማንሳት አትለዩት።
የራሳቸውን አበላሽተው ሲያበቁ የወጣቱ ዘመን ቀምተው መጠለያ ለመስራት የሚያስቡት ፖለቲከኞቻችን ሊያውቁት የሚገባው ትልቅ ቁም ነገር አለ። ዘመኑን የዋጀ የፖለቲካ እሳቤና በአንድነት ቆሞ ጠንካራ ማድረግ የሚችል ሀሳብ እንጂ ወጣቱን ነጣጥሎ በተለያየ ጎራ ሆኖ የሚናቆርበት ሊሆን አይገባም። ከዚህ በተለየ መልኩ የእርስ በርስ ወዳጅነቱ እንዲጠነክር አብሮነቱ እንድጎለብት ሊነግሩት ሊያስተምሩትም ቢጥሩ ለእነሱም እረፍት ለአገሪቱም ብስራት ይሆናል።
የወጣትነት ውብ ጊዜን የሚያጨልሙ ትርክቶችን ማጥፋት የእርስ በርስ ግጭቶችን የሚፈጥሩ ንግግሮችን ማስቆም ይገባል። የወጣቱን ዘመን ለመቀማት የምትፈልጉ የእናንተን በመንገር የእሱን ለመውሰድ ያቀዳችሁ ተግባራችሁ ሊገራ ሀሳባችሁ ሊታደስ ይገባዋል። ወጣቱን ገርታችሁ በአንድነት እንዲቆም፤ አስተካክላችሁ አብሮነቱ እንዲያጠናክር መንገር ከእናንተ ይጠበቃል። ሀገሩን የሚለውጥበት ትኩስ ጉልበቱ በአግባቡ እንዲጠቀምበት፤ይህች ከእርሱ ብዙ የምትጠብቀው እናት ምድሩን እንዲያፀናት ደግፉት። እንዲወዳት አድርጉት። መልካምን በመንገር መልካም ዘመኑን እንዲያቀና ፍቀዱለት።
ተገኝ ብሩ
አዲስ ዘመን መስከረም 4/2015 ዓ.ም