
ከሁለት ዓመት በፊት ለመስክ ሥራ ወደ አንድ ክልል እየተጓዝን የተነሳ ክርክር ትዝ አለኝ። በዚህ ሆድ በባሰው የብሔር ፖለቲካ የአካባቢውን ስም ልተወውና፤ ሜዳ ተራራውን እያቆራረጥን ለምንም ያልዋለ ብዙ ባዶ መሬት አየን። ከመንገዱ ዳር ያሉ አንዳንድ ለምግብነት የሚውሉ የአትክልትና ፍራፍሬ አይነቶችን አይተን ‹‹እንዲህ የሚያምር ከሆነ ለምን ባዶ ማሳውን ሁሉ አልተከሉትም›› እያልን ሀሳብ ተለዋወጥን።
ውይይታችን ግን ወዲያውኑ የፖለቲካ መልክ ያዘ። የፖለቲካ መልክ የያዘበት ምክንያት አካባቢውን ምርታማ ለማድረግ አስተዳደር ያስፈልጋል፣ ቆራጥ አመራር ያስፈልጋል፣ የሚሉ ምክንያቶች ተነስተው ነው። የአካባቢው ነዋሪዎች ከዚያ ለም መሬት ላይ ሆነው የሚለምኑ አሉ። ልጆቻቸውም አዲስ አበባ መጥተው ከልመና ጀምሮ በተለያዩ አስቸጋሪ እና ውጤታማ በማያደርጉ ሥራዎች ላይ ተሰማርተዋል። የአካባቢው ለምርት ምቹነት ግን ሙሉ ኢትዮጵያን ይመግብ ነበር።
የአካባቢውንና የፌዴራሉን የመንግሥት አመራሮች ስንወቅስ ቆይተን ወደ ተቃዋሚ ፓርቲዎች ሄድን። የአካባቢውን ተቃዋሚ ፖለቲከኞች በስም እያነሳን፤ እቆረቆርለታለሁ የሚለው ሕዝብ እንዲህ ለም መሬት እንዳለው ያውቅ ይሆን? የአካባቢው ልጆች በአዲስ አበባ ጎዳናዎች ላይ ለአደንዛዥ ሱሶች ተዳርገው አስፋልት ላይ ተኝተው እንደሚውሉ ያውቅ ይሆን? እያልን ተጨዋወትን።
ይህን ያልንበት ምክንያት በተለያየ አካባቢ ያሉ ተቃዋሚ ፖለቲከኞችም በመገናኛ ብዙኃንም ሆነ በፖለቲካ መድረኮች የሚያወሩት ስለአካባቢው ኢኮኖሚያዊ ሁኔታ ሳይሆን፤ ስለ ቋንቋ፣ ከመቶ እና ሺህ ዓመታት በፊት እገሌ ብሔር ይጨቁነን ነበር፣ ይሄ ባህል የእገሌ ነበር፣ ይሄኛው የእንትና ነበር…. የሚሉ ለዛሬ እና ለነገ የማይሆኑ ሙግቶችን ነው።
በዚህ ሁሉ ውስጥ ግን በተለያየ የአገሪቱ ክፍል ያሉ ዜጎች ለኑሮ ጉስቁልና ወደተለያዩ አገራት እየተሰደዱ ነው። ኢትዮጵያ አፈሯ ለም፣ መሬቷ ለምለም፣ የውሃ እናት… የሆነች አገር ነበረች። የድህነታችን ምክንያቱ ምንድነው ከተባለ ደካማ የፖለቲካ አስተዳደርና የማህበረሰብ ንቃተ ህሊና አለመኖር ነው። የፖለቲካ ባህል አለመሰልጠን ነው።
ይህን ሀሳብ ያስታወሰኝ ዛሬ ጳጉሜን 2 የአምራችነት ቀን ተብሎ መሰየሙ ነው። ስለ ምርት በመንግሥት ደረጃ ብዙ ተብሏል። ‹‹ምግቤን ከጓሮዬ፣ የከተማ ግብርና፣ የበጋ መስኖ ስንዴ…›› በመንግሥት ሲሰሩና ሲነገሩ የቆዩ አጀንዳዎች ናቸው። በመንግሥት ኮሙዩኒኬሽን በተሰጠ መግለጫ ዛሬ የአምራችነት ቀን ሆኖ አምራችነት እንድታወስ ተደርጓል።
በነገራችን ላይ እንዲህ አይነት የአከባበር ቀኖችን በራስ መሰየም መለማመድ አለብን። ብዙ የምናከብራቸው ነገሮች ‹‹በዓለም ይህን ያህል በአገራችን ደግሞ….›› ሲባል እንሰማለን። ይሄ ማለት ሌላው ዓለም ሲያከብር አይተን ነው ያከበርነው ማለት ነው።
መከበርና መታወስ ያለባቸውን ነገሮች በራሳችን መሰየማችን ግን የሚከበረውም ነገር ዓውዳዊ እንዲሆን ያደርገዋል። ከታሪካችን፣ ባህልና ወጋችን፣ ተፈጥሯዊ ሁኔታችን ጋር የሚሄድ ያደርገዋል።
ምንም እንኳን ቀኑን ማክበር ብቻውን ምርታማ ባያደርግም ሀሳቡን ግን አጀንዳ ያደርገዋል። አንዱ የተቸገርነው ከኢኮኖሚያዊ ጉዳይ በላይ የሚወራው ፖለቲካ ሆኖ ነው። የአንዲት አገር ዕድገት፣ ሥልጣኔም ሆነ ኃያልነት በኢኮኖሚ አቅም እንጂ በፓርቲ ብዛት ወይም በፖለቲከኞች ብዛት አይደለም። ከአገራችን ነባራዊ ሁኔታ አንፃር ለኢኮኖሚ ዕድገት ደግሞ ወሳኙ ግብርና ነክ አምራችነት ነው።
የአምራችነት ቀን በሚታወስበት በዚህ ዕለት ስለምርት፣ ምርታማነትና አምራችነት የምጠቁመው አንድ ትዝብት ቢኖር የሚከተለው ነው።
ገበሬው ብልህ ነው። በዘመናት ያካበተው ልምድ አለው። ይህን የገበሬውን ልምድ ዘመናዊና በቴክኖሎጂ የታገዘ ለማድረግ መንግሥት በተገቢው መንገድ አልተጠቀመበትም። በተገቢው መንገድ ለመጠቀም የየአካባቢውን ነባራዊ ሁኔታ የሚያውቁ የግብርና ባለሙያዎች መኖር አለባቸው። የሚሄዱበት ገበሬ በሚያውቀው ቋንቋና ዓውድ ማስረዳት የሚችሉ ባለሙያዎች መኖር አለባቸው። እነዚህ ባለሙያዎች የአካባቢውን ሁኔታና ተፈጥሮ የሚያውቁ ከሆነ ከገበሬው ጋር ሀሳብ ይለዋወጣሉ፤ ባለሙያዎችም ከገበሬው ይማራሉ ማለት ነው። ያንን ከገበሬው ያገኙትን ልምድ ወስደው በዘመናዊ መንገድ ይሞክሩታል፤ ውጤታም ሆኖ ከተገኘ ከገበሬው የቴክኖሎጂ ግብዓት ተገኘ ማለት ነው።
የግብርና ባለሙያዎች ገበሬዎች ሲሄዱ ያጋጥማቸው የነበረውን ችግር አስታውሳለሁ። አንዱ ችግር ከገበሬው ጋር በቋንቋ አለመግባባት ነው። ቋንቋ ሲባል የግድ ሌላ ቋንቋ እና ሌላ ቋንቋ ማለት አይደለም። ለምሳሌ በአማርኛ አፉን የፈታ እና አማርኛ የሚናገር ገበሬ ባለሙያዎች የሚያወሩት አማርኛ አይገባውም። ግማሽ በግማሽ እንግሊዘኛ ነው የሚያወሩ፤ ያሉት የአማርኛ ቃላትም ሙያዊ ስለሆኑ ገበሬው አይረዳም።
በቋንቋው እንደምንም ተግባቡ እንበል። ሌላኛው ችግር ደግሞ ሀሳቡን ተቀበል አልቀበልም ነው። እንደ ማዳበሪያ፣ ፀረ አረም መድሃኒትና ሌሎች የግብርና ግብዓቶች ላይ ገበሬው የራሱ አመለካከት አለው። ባለሙያዎች ደግሞ ገበሬው ምንም ስለማያውቅ ነው የማይቀበል በማለት በሚሊሻ እያስገደዱ በግድ ለመጫን ይሞክራሉ። ገበሬውም በግድ ይጠቀመውና ነገርየው ውጤታማ ሳይሆን ይቀራል።
እዚህ ላይ እንግዲህ መሆን የነበረበት ውይይት ነው። ገበሬው ‹‹አልጠቀምም›› ሲል ‹‹ለምንድነው የማትጠቀመው?›› ብሎ ምክንያቱን መጠየቅ። ያ የተናገረው ምክንያት አሳማኝ መሆን አለመሆኑን ማረጋገጥ።
ለምሳሌ፤ ገበሬው የአካባቢውን የእርሻ ማሳ የአፈር ባህሪ በልምድ ያውቀዋል። ምን አይነት ሰብል እንደሚሆን፣ በየትኛው ወቅት መዘራት እንዳለበት፣ የተፈጥሮ ማዳበሪያ (ፍግ) ያለውና የሌለው መሆኑን፣ ምን አይነት እንክብካቤ እንደሚያስፈልገው በልምድ ያውቁታል። ማዳበሪያ አንጠቀምም የሚሉትም የተፈጥሮ ማዳበሪያ ካለው ጋር ይጋጭብናል በሚል ፍራቻ ነው።
ስለዚህ ባለሙያዎች እነዚህን ነገሮች ጊዜ ወስደው ቢያጠኑ ከባህላዊ መንገድ ለቴክኖሎጂ ግብዓት የሚሆን ያገኛሉ ማለት ነው።
እርግጥ ነው ገበሬው ለቴክኖሎጂ አዲስ ስለሆነ ቶሎ አይቀበልም። ይህን ግን እንደ ኋላቀርነት ብቻ ከማየት ከባህላዊ ልማዶች የተገኙ ውጤቶችንም መመርመር ለዘመናዊ ተመራማሪዎች ግብዓት ይሆናል። ወይም አዳዲስ ዝርያዎችን ለማዳቀል ያመቻቸዋል።
ለምሳሌ፤ ገበሬዎች በልምድ እንደሚያውቁት ዝናብ አጠር በሆነ አካባቢ ጤፍ ውጤታማ አይሆንም። ጤፍ ለም መሬት እና ጭቃ ይፈልጋል። የሚታረሰውም ዝናብ በሚገባ መዝነብ ሲጀምር ነው።
የጤፍ ለብዙ ሰው ግልጽ ስለሆነ ባለሙያዎች ይረዱት ይሆናል፤ ዳሩ ግን ገበሬዎች ብቻ የሚያውቁት የተለያዩ የጥራጥሬና የቅባት እህሎች ባህሪ አለ። ተራራ ላይ ምን መዘራት እንዳለበት፣ ዝናብ አጠር የሆነ አካባቢ ላይ ምን መዘራት እንዳለበት፣ ውሃ የሚቋጥር ማሳ ላይ ምን መዘራት እንዳለበት፣ ዋናው የበልግ ወቅት ካለፈ በኋላ ምን መዘራት እንዳለበት፣ የተለያየ የአፈር አይነት (ጥቁር፣ ቀይ፣ ነጭ…) ላይ ምን መዘራት እንዳለበት በልማድ ያውቁታል።
እነዚህን በልማድ የተገኙ አሰራሮች በገበሬዎች ጋር መሆን ማጥናትና ወደ ዘመናዊ አሰራር ማምጣት ምርታማ ያደርጋል። ስለዚህ መንግሥት ለያዘው የምርታማነት ዕቅድ ባለሙያዎችን በማሰማራት ከአምራቹ አካል ጋር በመሆን ይስራ የሚል መልዕክት እናስተላልፋለን።
ዋለልኝ አየለ
አዲስ ዘመን ጳጉሜን 2/2014