ፋሽን ዛሬ የገዘፈ ኢኮኖሚያዊ ጠቀሜታ የሚያስገኝ ዘርፍ በመሆኑ ብዙ አገራት ትኩረት ሰጥተው ይሰሩበታል። በዚህም የፋሽን ኢንዱስትሪዎቻቸው ትልቅ የሆነ ኢኮኖሚያዊ አድገት አስገኝቶላቸዋል። አገራዊ ገቢያቸውንም አሳድገውበታል። ሰፊ የስራ እድል ፈጥረውበታል። በዚህም በዘርፉም የሚፈልጉትን ማሳካት ችለዋል። ነገር ግን እነዚህ በፋሽን ኢንዱስትሪው ርቀው ሄዱ አገራት ውስጥ ፋሽን በራሱ የፈጠራቸው አሉታዊ ተፅኖዎች መከሰታቸው አልቀረም።
በእርግጥ ፋሽን መከተል ቁመና እንደሚያሳምርና በራስ የመተማመን ስሜት እንደሚያዳብር ምንም ጥርጥር የለውም። ሰዎች በምርጫቸው የሚፈልጉትን አልያም የሚያምርባቸው አልባሳት መልበስ ይወዳሉ። በዚህም አምረውና ደምቀው ይታያሉ። ፋሽን መከተላቸው የነበራቸውን ውበት ሊያጎላና ተጨማሪ ውበት ሊያላብሳቸው ይችላል። በዚህም ሌሎች ሰዎች ዘንድ ጥሩ አመለካከት እንዲኖራቸውም ሊያደርግ ይችላል።
ፋሽን አዎንታዊም ሆነ አሉታዊ ገጽታ እንዳለው ግልጽ ነው። መሠረታዊ የሆነውን አምሮ የመታየትንና አዲስ ልብስ የመልበስን ሰብዓዊ ፍላጎት ያሟላል። ይሁን እንጂ ቅጥ ያጡ ፋሽኖችን መከተል መጥፎ ስም ሊያሰጠን ይችላል። ነገር ግን ይህ በጎ ገፅታን የሚያላብሰው ፋሽን በሰዎች ላይ አሉታዊ ተፅዕኖም ሊኖረው ይችላል። ተፅዕኖው ማሕበራዊ አልያም ኢኮኖሚያዊ ሊሆን ይችላል። ይህ ተፅዕኖ ፋሽን ተከታዮች ባላቸው ልምድ አልያም በሚከተሉት ፋሽን ምክንያት የሚፈጠርባቸው ነው።
የፋሽን ተከታዮች ኢኮኖሚያዊ ተፅዕኖ
ብዙውን ጊዜ ፋሽን ተከታዮች አዳዲስ ምርቶች በመከታተል የራሳቸው ለማድረግ ሲጥሩ ይታያል። እነዚህ የፋሽን ተከታዮች የፋሽን ቁስ ወይም ልብስ በመግዛት ማለቂያ የሌለው ሽክርክሪት ውስጥ ሊገቡ ይችላሉ። በአንፃፉ ደግሞ የፋሽኑ ኢንዱስትሪው አዳዲስ ዲዛይኖችም ማውጣት የሁልጊዜ ተግባሩ ነው። ምክንያቱም ፋሽኖች ጊዜያቸው ቶሎ ባለፈ መጠን ፋሽን አውጪዎችና ልብስ ነጋዴዎች የሚያጋብሱት ትርፍ የዚያኑ ያህል ይበልጥ ይጨምራል።
እዚህ ላይ እውቁ ፈረንሳዊ የፋሽን ዲዛይነር ጋብርኤሌ ቻነል ፋሽን የሚወጣው እንዴት እንደሚያልፍበትም ታስቦበት መሆኑን ይናገራል። ስለዚህም የፋሽን ኢንዱስትሪዎች ለፋሽን ተከታዮች የሚያቀርቡት ቁስ ወይም አልባሳት ወቅታዊ አልያም በሁኔታዎች ውስጥ ቶሎ ተለምዶ በፍጥነት የሚቀየር ነው። አዳዲስ ፋሽኖች ይመጣሉ፣ ይሄዳሉ። እንዲያውም አንዳንዶቹ ከጥቂት ወራት ያለፈ ዕድሜ አይኖራቸውም። ጀማሪው አንድ የታወቀ ሙዚቀኛ ወይም ሌላ ታዋቂ ሰው ሊሆን ይችላል። ጥቂት ፋሽኖች ግን ዘላቂ ሆነው ይቀራሉ።
ስለዚህ ጥንቁቅ ያልሆነና በእቅድ የማይመራ ሸማች ከጊዜው ጋር እኩል ለመራመድ ሲል ብቻ አዳዲስ ልብሶችን መግዛት እንደሚኖርበት ይሰማዋል። የፋሽን ኩባንያዎች ብዙውን ጊዜ የሚያመርቱት ቁስ አልያም አልባሳት ለማስተዋወቅ እና ሰዎች እንዲመርጡት ለማድረግ ለሚያሰሩት ማስታወቂያዎች በሚሊዮን የሚቆጠር ገንዘብ ያጠፋሉ።
የፋሽን ሥነ ልቦናዊ ተጽዕኖ ፋሽን
የጠቀሜታውን ያህል በማሕበረሰብ ውስጥ አሉታዊ የሆነ የሥነ ልቦና ተፅዕኖ ሊፈጥር ይችላል። የፋሽን ኢንዱስትሪው ሰፊና ግዙፍ በመሆኑ በማስታወቂያ በኩል ሰፊውን ቦታ ይወስዳል። ማሕበረሰቡም ማስታወቂያዎቹ ለሚያሳድሩት ጫና ይጋለጣል። በተለይ ፋሽን በአፍላ ወጣቶች ላይ የሚያሳድረው ተፅዕኖ ቀላል አይደለም። ሕፃናትና ወጣቶች በሚያዩት ማስታወቂያ እና አዲስ አልባሳት ይማረካሉ። በሌላ በኩል ደግሞ ሕፃናቱ ጓደኞቻቸው ያንን ልብስ ወይም አልባሳት ሲያደርጉ አይተው እነሱ መልበስ አለመቻላቸውን ሲያስቡ ሥነ ልቦናዊ ተፅዕኖ ሊፈጠርባቸው ይችላል። በስፔን የሚኖር አንድ መምህር “ለወጣቶች በወቅቱ ተወዳጅ የሆነውን ጫማ ለማድረግ አለመቻልን ያህል ቅስማቸውን የሚሰብር ነገር የለም” ብለዋል።
አንዳንድ ቡድኖች አንድን ዓይነት አለባበስ የሚመርጡት ማንነታቸውን ለማሳየት ነው። የሚለብሱት ልብስ የማሕበረሰቡ ተቃዋሚዎች፣ ልቅ የሆነ አኗኗር የሚከተሉ፣ ሌላው ቀርቶ ዓመጸኞች ወይም ዘረኞች መሆናቸውን ሊያመለክት ይችላል። ከእነዚህ አለባበሶች አንዳንዶቹ በጣም ቅጥ ያጡና የማሕበረሰቡ ባህል የሚፃረሩ ሊሆኑ ይችላሉ።
በተጨማሪም ለፋሽን ትልቅ ቦታ የሚሰጡ ሰዎች ስለ መልካቸውና ስለ ቁመናቸው ከሚገባው በላይ መጨነቅ ሊጀምሩ ይችላሉ። የፋሽን አስተዋዋቂዎች አብዛኛውን ጊዜ ለግላጋና ቀጭኖች ሲሆኑ ቁመናቸውንና መልካቸውን በያለንበት እንድናይ እንደረጋለን። “ትክክለኛ” እንደሆነ ተደርጎ የሚታየው ቁመና ከመኪና እስከ ከረሜላ የሚደርሱ የተለያዩ ሸቀጦችን ለማሻሻጥ ይውላል። ይህ በራሱ እንደ ማሕበረሰብ የሚፈጥረው ሥነ ልቦናዊ ጫና ቀላል አይደለም። ይህ ዓይነቱ የማስታወቂያ ውርጅብኝ ጉዳት ሊያስከትል ይችላል። ለምሳሌ ያህል በአሜሪካ በኒውስዊክ መጽሔት ላይ የወጣ አንድ ጥናት ከወጣቶች መካከል 90 በመቶ የሚሆኑት በመልካቸውና በቁመናቸው እንደማይደሰቱ አመልክቷል።
ከእነዚህ መካከል አንዳንዶቹ መልካቸውንና ቁመናቸውን ለማስተካከል የቻሉትን ሁሉ ያደርጋሉ። በተለይ ወጣቶቹ በመገናኛ ብዙኃን የሚወደሰው የክብደትና የቁመት መጠን ላይ የሚደርሱት 5 በመቶ የሚሆኑት ብቻ ናቸው። ይሁን እንጂ እነዚህ ማስታወቂያዎች በፈጠሩት ተፅዕኖ ምክንያት ለቀጫጭን ሴቶች ከፍተኛ አድናቆት መሰጠቱ በሚሊዮን የሚቆጠሩ ሴቶችን ለሥነ ልቦና ጉዳት ዳርጓቸዋል። አንዳንዶቹ ለመክሳት በሚያደርጉት ጥረት ምክንያት ለአመጋገብ ሥርዓት ቀውስ ተዳርገዋል።
እኛ ሰዎች ለመልካችንና ለቁመናችን ከመጠን በላይ የምንጨነቅ ከሆነ ማንነታችን በውስጣዊ ባሕርያችን ሳይሆን በውጪያዊ ገጽታችን ላይ የተመካ ነው ብለን እንደምናምን ሊያደርገን ይችላል። ነገር ግን አንድ ሰው ውጪያዊ መልክና ቁመና ብቻ ሳይሆን ለችሎታውና ለውስጣዊ ማንነቱ የበለጠ ዋጋ መስጠት ይኖርበታል። ይህንን መረጃ ስናዘጋጅ ልዩ ልዩ የድህረ ገፅ መረጃዎች ተጠቅመናል።
ተገኝ ብሩ
አዲስ ዘመን ነሃሴ 23/2014