ንቅሳት ድሮ ድሮ የገጠር ሴቶች ማጌጫ፣ ውበትን አጉልቶ ማሳያና የተለያዩ አካባቢዎች ባህላዊ ጌጥ ነበር። በገጠር ለኮረዳዎች የሚደረገው ንቅሳት እድሜ ልክ የማይጠፋ ኪንና ስን የታከለበት ማጌጪያ ነው። በእንቆቅልሽም ‹‹ስኖርም ስሞትም የማይለየኝ ጌጤ›› ተብሎ የሚጠየቀው ንቅሳት ዕድሜ ዘመን የማይጠፋ መሆኑን ለማመላከት ነው። ‹ንቅስ ያለች› ሲባልም ቆንጆ ለማለት ነው። ንቅሳት በፈረንጆች ታቱ ተብሎ ይጠራል። ስያሜው ከፓሲፊክ ውቅያኖስ የታሂቲ ደሴት ነዋሪዎች የመጣ መሆኑም ይነገራል። ንቅሳት የሰዎችን የሰውነት አካል በስዕል፣ በፊደልና ሌሎችም ነገሮች የማስዋብ ጥበብ ነው። ማንም ሰው ዘው ብሎ ሊገባበት የሚችል ሙያም አይደለም። ነቃሽ ለመሆን የስዕል ዝንባሌ ሊኖር ይገባል።
ባህላዊው ንቅሳት ፤ ኩል፤ የወይራ ጭስና ኑግ ተወቅጦ በአጠፋሪስ ቅጠል ጭማቂ ተለውሶ ይዘጋጃል። ከዛም በአጋም እሾህ ፣ መርፌ፣ ወይም ወስፌ ወይዛዝርት ይነቀሱታል። የአገራችን ጥንታዊ ስነ ግጥሞችም ይህንኑ ይገልፃሉ፡-
ተነቀሽ ተነቀሽ ተነቀሽ በሾክ፣
ትሆኝ እንደሆን የእናትሽ ምትክ።
ንቅሳትሽማ መቁጠርያ የሚመስለው፣
ያን ውበትሽን አስበለጠው ከሰው።
ኮረዳዎቹ ሲነቀሱት ለህመማቸው ማስታገሻ አስካሪ መጠጥ ጠጥተው እንዲደነዝዙ ተደርጎ ነው። በተነቀሱበት አካላቸውም ላይ ስስ ሻሽ ተከናንበው ሦስት ቀን ከበዛም ሳምንትም ይቆዩበታል። ይህም እንዳይደማ፣ቁስሉ እንዲደርቅና ንቅሳቱ እንዳይጠፋ ለማድረግ መሆኑን እናቶች ይናገራሉ።
በገጠር በእግር፣ በደረት፣ በግንባር ፣ በአንገት ፣ በእጅ (አይበሉባ)፣ በባት፣ በድድና በክንድ፣ እንዲሁም በአገጭና በጉንጭ ላይ ንቅሳት ሊሰራ ይችላል። በተጠቀሱት አካላት የሚነቀሱ እንዳሉ ሁሉ ፤ በአንድ ወይ ሁለት ቦታ የሚነቀሱ ወይዛዝርትም አይጠፉም። በግንባር ላይ የመስቀል፣ የክብና የኮኮብ ምልክት መነቀስ የተለመደ ነው። በአንገት እና በአገጭ ላይ መሰላል ወይም ሀዲድ መሳይ ስዕልን ለጌጥን ብዙ ወይዛዝርት ተነቅሰውም ማየት የተለመደ ነው። ንቅሳታቸውን ብቻ በማየት የየት አካባቢ ነዋሪ እንደሆኑ የሚለዩም አሉ።
በሰሜኑ የኢትዮጵያ አንዳንድ አካባቢ መበጣት እንደ ንቅሳት ይታያል። ንቅሳት ውበትን እምነትን፣ ጀግንነትን፣ ፍቅርን ቅጣትን እንዲሁም ከለላን አመላካች ሆኖ ለበርካታ ዘመናት ማገልገሉ ይገለጻል። ቀደም ብሎም ንቅሳት የባሮችና የእስረኞች መለያ ሆኖ ማገልገሉን አንዳንድ ጽሁፎች ያሳያሉ።
በዘመናችን በከተሞች አካባቢ በሴቶች ዘንድ ባህላዊው የመነቀስ ልምድ እየቀነሰ መምጣቱን የሚናገሩ ቢኖሩም ቀድሞም ከገጠር ተነቅሰው የመጡ እንጂ በከተሞች ንቅሳት እንዳልነበረ የሚናገሩ አልጠፉም። አሁን አሁን ግን መልኩን ቀየረ እንጂ በተለያዩ ከተሞች ንቅሳት በዘመናዊ መልኩ በወጣቶች ላይ በስፋት እየታየ ነው። ከድሮው በተለየም ወንዱም ሴቱም እንደ ፋሽን ወደ ንቅሳቱ ጠጋ ጠጋ እያለ መሆኑን ማስተዋል ይቻላል።
አሁን አሁን በመላው ዓለም ሊባል በሚችል ደረጃ ንቅሳት እንደ ዘመናዊና ፋሽን ተከታይነት ሲቆተር ይታያል። በተለይም በስፖርተኞች፣ በተዋንያን በታዋቂ ሰዎች ዘንድ በስፋት ይስተዋላል። በሀገራችንም የነዚህን ዝነኛ ሰዎች ንቅሳት በማየት በከተሜው ወጣቶች ዘንድ ፋሽኑን የመከተል ባህል እየሰፋ ይገኛል። ንቅሳት መነሻው ከአፍሪካ ቢሆንም ምንጩ ግን መበጣትም (ውቅራት) ሆነ ንቅሳት በኢትዮዽያ መሆኑን የሚናገሩ አሉ።
ሰውነትን በንቅሳት ማስዋብ ከቅርብ ጊዜ ወዲህ በዘመናዊ መልኩ እንደፋሽን በበርካታ የዓለማችን ክፍሎች እንደተስፋፋ ጽሁፎች ያመለክታሉ። በተለይ በአሜሪካ፣ በጃፓን፣ በአውሮፓ ተወዳጅ ሆኗል። የንቅሳት ባህል እንደ ፋሽን ሊስፋፋ የቻለው የቴክኒክ እና የስነ-ጥበብ ስልጠና ያላቸው አዳዲስ ባለሞያዎች ወደ ዘርፉ በመግባታቸው ነው ተብሎ ይታመናል። በተጨማሪም የሚነቀሱ ዝነኛና ተፅእኖ ፈጣሪ ሰዎች በቴሊቪዥንና በፊልም ወይም በፎቶ ሲታዩ ንቅሳታቸውም ጭምር መካተቱ በከተሞች መነቀስን በርካቶች እንደፋሽን እንዲከተሉ ተፅዕኖ ማሳደሩ ይታመናል።
ዘመናዊ የንቅሳት ቀለም እና መሣሪያ በየግዜው መሻሻሉም ለጥበቡ ማደግ አስተዋጽኦ አድርጎል። በመዲናችን ወጣቶች ከሚስተዋሉ የንቅሳት አይነቶች መካከል ሃይማታዊ ምስሎች፣እርግብ አእዋፍትና ሌሎች እንስሳቶችን በስፋት ማየት ይቻላል።
በአዲስ ከተማ አብነት አካባቢ ዘመናዊ ንቅሳት የሚሰራው ወጣት ሚኪያስ አሸናፊ ወደ ሙያው የገባው ከስምንት ዓመት በፊት ተማሪ እያለ መሆኑን ይናገራል። ሙያውን በአካባቢው ንቅሳት ከሚሠሩ ሰዎች የለመደው ሲሆን ራሱ ላይ ሞክሮ ጓደኞቹን መንቀስ እንደጀመረ ያስታውሳል። በማኅበራዊ ገፆች በሚለቃቸው ምስሎች እንዲሁም የተነቀሱ ሰዎችን በማየት ወጣት ወንዶችና ሴቶች ለመነቀስ እሱ ጋር እንደሚመጡ ይናገራል።
በከተሞች እንደፋሽን ወጣት ወንዶችና ሴቶች በስፋት እንደሚነቀሱ የሚናገረው ወጣት ሚኪያስ፤ መንቀሻ መሣሪያው ከውጪ አገር እንደሚመጣና በአገር ውስጥም ተመሳስሎ የሚሰራ እንዳለ ያስረዳል። የመነቀሻ መርፌዎችን እንዲሁም ቀለሞችን አንድ ሰው ከተነቀሰባቸው በኋላ ሌላ ሰው እንደማይጠቀምባቸው የሚናገረው ሚኪያስ፣ ይህም የደንበኞችን ጤንነት ለመጠበቅ ሲባል እንደሚደረግ ያብራራል። ‹‹ሰው እንደየፍላጎቱ ይነቀሳል›› የሚለው ወጣት ሚኪያስ የሌሎችን አይተው የሚነቀሱ እንዳሉ ሁሉ እሱ በሚያቀርብላቸው ምርጫ የሚነቀሱም እንዳሉ ይናገራል።
እንደ ሚኪያስ ገለፃ ክንዳቸው ላይ፣ጀርባቸው ላይ፣ ደረት አካባቢ፣ ከጡታቸው ከፍ ብሎ የሚነቀሱ ወጣቶች አሉ። በአንገት ጎን የሚነቀሱ ወንዶች ፤ ከጆሮ ጀርባ በኩል መስቀል ፣ኮከብ ነገሮች የሚነቀሱ ሴቶችም አሉ። የወዳጃቸውን ወይም የፍቅር አጋራቸውን ስም የሚነቀሱም አሉ። አበባ፣ የሃይማት ምስሎችንና እንስሳትን መነቀስም የተለመደ ነው። መነቀስ ሕመም ቢኖረውም ሰዎች ችለው ከመነቀስ ወደ ኋላ እንደማይሉም ወጣት ሚኪያስ ይናገራል። ሰዎች ሲነቀሱ በሚፈጠርባቸው ሕመም የሚያሳዩት የተለያየ ስሜት አለ። መጮኽም፣ መወራጨትም፣ አንዳንዴ ማልቀስም ይኖራል።
እጅዋን አበባ ስትነቀስ ያገኘኋት ሰሎሜ ሚደቅሳ ፤የጓደኛዋ ሜሮን ግደይ ንቅሳትን በማየት በበጎ ቅናት ለመነቀስ እንደወሰነች ትናገራለች። ሜሮን በበኩሏ በክንዷ ላይ የሃይማኖታዊ ምስልና በእጃ ላይ ደግሞ የእንቡጥ አበባ ምስል ተነቅሳለች። ‹‹መነቀስ ፈልጎ ሕመምን መሸሽ አይሆንም›› ትላለች። ‹‹የምትነቀሰው በመርፌ እየተወጋህ ስለሆነ መታገስ ግድ ነው›› በማለትም ያለውን ስሜት ትናገራለች።
የሙያው ባለቤት ሚኪያስ ፤ ሰዎች የሚነቀሱት የእረፍት ጊዜ ሲኖራቸው መሆኑን ይናገራል። ሰዎች ንቅሳትን የሚጠቀሙት እንደፋሽንና ቆዳን ለማስዋብ ከመሆኑ በተጨማሪ ጠባሳ ነገር ያለባቸውም ጠባሳቸውን ለመሸፈን ብለው እንደሚነቀሱ ያስረዳል። ‹‹ክረምት ላይ ብዙም የሚነቀስ የለም፣ ንቅሳቱም ሕመም ነገር ስላለው ሰዎች ከመስከረም በኋላ ያለውን ጊዜ ይመርጡታል›› ይላል።
ኃይለማርያም ወንድሙ
አዲስ ዘመን ነሐሴ 16 ቀን 2014 ዓ.ም