ባለቅኔውና ወግ ሰላቂው በእውቀቱ ስዩም በፊስ ቡክ ሰሌዳው ላይ ሰሞነኛውን ሟርት በጨዋ ደንብ እውቅና የሰጠ ሌላ ገደምዳሜ ሟርትን ፤ “ታሪክን ወደ ኋላና ወደፊት”በሚል ርዕሰ አስነብቦናል። ለነገሩ ለበእውቀቱ ሟርት ብርቁ አይደለም። ከዚህ ቀደም “ሟርት”የሚል ሟርትም በ”በራሪ ቅጠሎች”አሟርቶልን ያውቃል። ሟርት ይፈራል። ይጠላል ። ደግሞ እንዲህ ያሟርታል ፦
“ያልተበረዘውን የኢትዮጵያ ታሪክ የሚያነብ ሰው ፥ መጀመሪያ የሚመጣለት ስሜት “ ምን ጉድ ነው ?” የሚል ነው ፤ ለምሳሌ ነገስታት አንድ ልማድ ነበራቸው፤ ልክ ዙፋን ላይ ሲወጡ ልጆቻቸውን እና ወንድሞቻቸውን ሰብስበው ከመዲናቸው ራቅ ያለ ማጎርያ ቦታ ያስቀምጧቸዋል ፤ የማጎርያው መልክአምድር ለማምለጥ አይመችም ፤ ከዚያም አልፎም ፤ በንቁና አስፈሪ ዘበኞች ይጠበቃል፤ በአክሱም ዘመን ደብረዳሞ የልኡላን ማጎርያ ሆኖ አገልግሏል ፤ የሸዋ ነገስታት በተራቸው ሲገዙ ፤ ለዚህ ተግባር የመረጡት ቦታ ፥ ወሎ ዛሬ ግሼን ማርያም የምትገኝበትን አምባ ነበር ፤ የጎንደር ነገስታት በበኩላቸው ዘመዶቻቸውን “ወህኒ” ወደ ተባለ ስፍራ ማጋዝ ጀመሩ፤ ወህኒቤት የሚለውን ቃል የወረስነው ከዚህ ስፍራ ነው ፤ ወህኒ በመሰረቱ የፖለቲካ እስር ቤት ሲሆን ፥ የመጀመርያው የፖለቲካ ወንጀል ከንጉስ መወለድ ነበር፤
ንጉሱ ድንገት ወራሹን ሳያሳውቅ በጦር ሜዳ ይገደላል እንበል፥ አንዱ የቤተመንግስት መኮንን ብድግ ይልና አንዱን ልኡል ከማጎርያ ቤት አውርዶ ዙፋን ላይ ያወጣዋል፤ ሌላው የጦር አዝማች ደግሞ የኔን ምርጫ ካላነገስኩ ሞቼ እገኛለሁ ብሎ ይነሳል፤ ባንጋሾች መካከል የሚደረገው ፉክክር መዲናይቱን ባንዴ ወደ ፍርስራሽ እና ያስከሬን ክምር ይቀይራታል::
የቀድሞ ሰዎች እንዲህ አይነቱን ብሄራዊ አደጋ ለመቀነስ የፈጠሩት “ዘዴ “ የንጉስን ሞት መሰወር ነበር ፤ የንጉስ ሞት ቀርቶ ህመሙ እንኳ ለህዘብ ይፋ አይደረግም፤ በዘመነ መሳፍነት ጊዜ ፥ የየጁው ራስ አሊ ሲሞት ፤ አንድ አሳባቂ ( የዘመኑ ፓፓራዚ) ወሬውን አሾለከው፤ ወድያው የረጋው አገር መላወስ ጀመረ፤ ጉዳዩ ያሳሰባት አንዲት አልቃሽ እንዲህ ብላ ገጠመች፥
“ እሻ እሻ ነው እንጂ የእስራኤልን ሞት
እንዲያልቅሰው አሊን ለምን ቀበሩት “
“ እሻ እሻ “ ማለት ዝም በሉ ጸጥ በሉ ማለት ነው፤ በዘመኑ የንጉስ ወገን ነን የሚሉ ሰዎች ዘራቸውን ከሰለሞን ስለሚመዝዙ “ እስራኤል “ በሚል የወል ስም ይታወቃሉ፤
በግጥሙ መስመር ላይ ያለው ህብረቃል “ እንዲያልቅሰው “ የሚል ነው፤ ሰሙ “ እንዲህ አልቅሰው “ ሲሆን ወርቁ “ ሰው እንዲተላለቅ” የሚል ትርጉም አለው ፤ ባጭሩ አልቃሺቱ፥
“ ህዘብ እንዳይተላለቅ የንጉስ ሞት ይደበቅ “ ማለት ነው የፈለገችው ፤ ከጥንት እስከዛሬ አገረ መንግስታችን የሚቆመው ባንድ ሰው ትከሻ ላይ ነው ፤ መሪ ሲታመም አገር ይታመማል፤ መሪ ሲሞት አገር በጥቂቱ ይሞታል፤ ይህንን መለወጥ የሚቻለው እንዴት ነው? የማይሞቱ ተቋሞችን በመገንባት ፤ የማይታመሙ ህጎችን በመመስረት? ወይስ ሌላ መላ አለ? “በማለት ይቋጫል ።
የበእውቄ ይቺ ሾካካ ታሪክ ቀመስ ሟርት ላለፉት አንድና ሁለት ሳምንት በማህበራዊና በመደበኛ ሚዲያው በስፋት ሲነዛ የሰነበተ ሟርት ቅርሻ ናት። ሆኖሞ የዘመነ ጓዴነትና የእውነታ/fact/ጥያቄ ሊነሳባት ይችላል። አይደለም የ18ኛውንና የ19ኛውን መክዘ ዘመነ መሳፍንት ከዛሬው መግስት ጋር ማነጻጸር፤ የመለስን አገዛዝ ከዐቢይ አስተዳደር ለማነጻጸር መሞከር እንኳ ጥያቄ ያስነሳል ። ሁለቱም በዘመናቸው ከነበሩ አቻ ገዢዎችና መሪዎች ጋር ቢነጻጸሩ ይበልጥ አግባብነት ይኖረዋል ።
የእጅ ስልክ ያለው ሕዝበ አዳም ሁሉ መረጃ ነጋሪ በሆነበት ፤ የእጅ ስልክና በይነ መረብ ጓዳ ጉድጓዱን ባዳረሰበት 21ኛው መክዘ አይደለም የሀገር መሪ ህመምና ሞት የእኔ ቢጠው በጉንፋን ቢያዝ ከብርሃን ፈጥኖ ለቢጤው ይደርሰዋል። እውነት እንነጋገር ከተባለ በሀገሪቱ ዘመናዊ ታሪክ ለዛውም ቀውስ እንደ ጫጩት በሚቀፈቀፍበት ሀገር እንደ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ ለተቋማት ግንባታ ትኩረት የሰጠ መሪ የለም ። የኢትዮጵያ ብሔራዊ የምርጫ ቦርድን፤ የኢትዮጵያ ሰብዓዊ መብት ኮሚሽንና ሌሎችን በአብነት ማንሳት ይቻላል። የማንኩሳውን በእውቄ ሟርት ለመንደርደሪያነት ያህል ካነሳሁ ስለሚበቃ ወደ ዋናው ሟርት ልመለስ ።
ይህን ስል ጠቅላይ ሚንስትር ዐቢይ ፍጹም ናቸው፤ በፕሬዚዳንትነት የሚመሩትና የመሠረቱት ብልጽግና ሙሉኡ በኩልሄ ነው እያልሁ አይደለም። የማይታረቁ ቅራኔዎች ፣ እልፍ አእላፍ ፍላጎቶችና መሳሳቦች ፣ ለግማሽ ክፍለ ዘመን ልዩነት ተቋማዊና መዋቅራዊ ሆኖ በተነዛበትና የጋራ አካፋይ በሌለበት ሀገር ይቅርና በአንጻራዊነት አልጋ በአልጋ በሆነበት ሀገርም ስህተትና ቀውስ ይፈጠራል ። እንኳን ትላንት የተመሠረተው ብልጽግና ዲሞክራት ይሁን ሪፐብሊካን፣ ሌበር ይሁን ቶሪ ፣ 100 አመትን የተሻገረው የደቡብ አፍሪካው ኤኤንሲ ፣ አልያም ወደ 70 አመት የተጠጋው የጃፓኑ ኤልዲፒ ይሁን የቻይናው ፓርቲ ከስህተትና ከቀውስ አምልጠው አያውቁም ። ሀቁ ይህ ሆኖ ሳለ ብልጽግናንም ሆነ ፕሬዚዳንቱን ወይም ጠቅላይ ሚንስትሩ በሀሳብ መሞገትና መተቸት ከፍ ሲልም አማራጭ የፓሊሲ ሀሳብ አቅርቦ መቃወም እየተቻለ ሟርትን ምን አመጣው ።
በእኛ፣ በቤተሰባችን፣ በጓደኛችን በዘመድ አዝማዳችን እንዲደርስ የማንፈልገውን ሞት በእሳቸው እንዲደርስ እንዴት እናሟርታለን ፤ ታላቁ መጽሐፍስ፦” እንግዲህ ሰዎች ሊያደርጉላችሁ የምትወዱትን ሁሉ እናንተ ደግሞ እንዲሁ አድርጉላቸው ፤ ሕግም ነቢያትም ይህ ነውና።” ( የማቲ ወን 7 ÷ 12) አይደል የሚለው ፤ ሶስቱ አብርሀማዊ ዕምነቶችን ካስተሳሰሩ ትዕምርቶች አንዱ ፤
“ በራስህ ላይ እንዲደረግ የማትፈልገውን፤ በሌሎች ላይ አታድርግ ፤”አይደለምን የሚለው !?
ቁጥራቸው ቀላል ያልሆኑ የግል መደበኛ ሚዲያዎችና ብዙ ተከታይ ያላቸው አንቂ ተብየዎችና ዩቲውበሮች ፤ የተቃዋሚ ፓለቲካ አመራሮች ሳይቀሩ ነጋ ጠባ ሲሰልቁትና ሲያነሱ ሲጥሉት የሰነበተው ሟርታ የጠቅላይ ሚንስትር ዐቢይ አሕመድን መጥፋት ነው። በተለያዩ አጋጣሚዎችና ሁነቶች ቶሎ ቶሎ በሚዲያ ሲታዩ የማይንበለበል የትችት ፍላጻ የለም። እንደ እዚያ ሰሞን ከካሜራ እይታ ዘወር ሲሉ ደግሞ አንድ ጊዜ ታመው ነው ፣ ሌላ ጊዜ ሞተው ነው በሚል ሟርት አየሩንና መልካውን ይቆጣጠሩታል ።
የዚህን ሟርት መነሻም ሆነ የሟርተኞችን ግብ ከተለያየ ማዕዘን መተንተንና መበየን ቢቻልም የሟርቱ ዋና ዛቢያና ማጠንጠኛ ግን ራሱን በጠላትነትነት ያሰለፈ ኃይል ጠላቴ ብሎ ለፈረጃቸው ጠቅላይ ሚንስትር ያለውን ክፉ ምኞት የገለጸበት ነው ። በዚህ ቀውጢ ሰዓት በእሳቸው ላይ የሚሟረት ሟርት በኢትዮጵያና በመላው ኢትዮጵያዊ ላይ የተሟረተ መሆኑን ይሄ ክፉ ኃይል አልተረዳም ። ቢረዳም ለሀገርና ለዜጋ ግድ እንደሌለው አረጋግጦልናል ።
ላለፉት አራት አመታት ከታሪካዊ ጠላቶቻችን ጋር ግንባር ገጥሞ በሀሰተኛ መረጃ ፣ ሕዝብ እንዲነሳባቸው ሌት ተቀን በመቀስቀስ ፣ በብልጽግና መካከል መከፋፈል በመፍጠር ፣ መከላከያን በብሔርና በሀይማኖት በመለያየት ፣ ኢኮኖሚውን በማሻጠር ፣ የእርስ በርስ ጦርነት በመቀስቀስ ፣ በውክልና ጦርነት፣ ነፍጥ በማንሳት ፣ በግድያ ሙከራ፣ ወዘተረፈ ሊያጠፋቸው ያልፈነቀለው ድንጋይ ባይኖርም ሊሳካለት ስላልቻለ ወደ ሟርተኛነት ወርዷል ። ወደ የሟርትና የጥንቆላ ፓለቲካ ዘቅጧል ።
ይህ የሟርተኛና የጠንቋይ ስብስብ ያልተረዳው ሀቅ በዚህ ቀውጢ ሰዓት ለዛውም ተቋማት ገና ዳዴ ዳዴ እያሉ ባለበት ሁኔታ የአመራር ክፍተት ተፈጠረ ማለት ሀገርን ወደለየለት ቀውስ የማንደርደር ሲከፋም ሀገርን ለውጭ ወረራና ለእርስ በርስ ጦርነት የመዳረግ እምቅ አደጋ መኖሩ ነው። በተዘዋዋሪ እነዚህ ሟርተኞችና ጠንቋዮች ኢትዮጵያ እንድትታመምና እንድትሞት ነው እያሟረቱ ያሉት። አሁን ባለንበት ተጨባጭ ሁኔታ መሪ ቢሄድ መሪ ይመጣል የሚያስብል ዋስትናም ነባራዊ ሁኔታም የለም ። ሌላው ይቅርና በገዥው ፓርቲ ብልጽግና ያለውን መሳሳብና መወነጃጀል የምናውቀው ነው። የፓርቲው ውስጠ አካላቱ እንደ ሌሎች ተቋማት ገና አልጸናም። ተሰርቶ አላለቀም። የፓርቲ ፓለቲካችን የተቋማት ግንባታው አካል መሆኑም ሊዘነጋ አይገባም ።
የሀገራችን የፓርቲ ፓለቲካ ገና ጨቅላ ነው። ያልበሰለ ጮርቃ ነው ። በእድሜም በአስተሳሰብም ለጋ ነው ። ብዙ ይቀረዋል። በ1960ዎቹ በተማሪ ንቅናቄ የተሟሸና የተጋገረ ነው። ገና ከ70 አመት ያልዘለለ ሩጦና ዘሎ ያልጠገበ ጉብል ህጻን ነው። ለሀገርና ለፓርቲ ሲሆን 70 አመት 7 አመት ነው የሚል ዕምነት አለኝ። የአልበርት አነስታይንን የአንጻራዊነት ቀመር እዚህ ላይ ያስታውሷል ። የሀገረ መንግስትና የፓለቲካ ታሪክ የሰው ልጅ እድሜ እንደሚሰላው አይሰላም። ከፍ ብሎ ለመግለጽ እንደተሞከረው የሀገራችን ዘመናዊ የፓለቲካ ታሪክ መነሻው የተማሪዎች ዕንቅስቃሴ ነው።
በተማሪዎች የ1960ዎች ዕንቅስቃሴና በፓለቲከኛነት ስማቸው ቀድሞ የሚነሳው እነ ኃይሌ ፊዳ ፣ ተስፋዬ ደበሳይ፣ ብርሀነመስቀል ረዳ፣ ግርማቸው ለማ ፣ መለስ ተክሌ ( የቀድሞው ጠ/ሚ መለስ ዜናዊ ስሙን የወረሱት)፣ ሰለሞን ዋዳ ፣ ጥላሁን ግዛውና ዋለልኝ መኮነን ለፓርቲ ፓለቲካ መሠረት ከጣሉት ይገኙበታል። ኢህአፓም ሆነ መኢሶን ወይም በዘመኑ እንደ አሸን ፈልተው የነበሩ የፓለቲካ ፓርቲዎች መሠረት የሀገር ቤትና የውጭም ተማሪዎች ንቅናቄዎች ናቸው ። የሁሉም ፓርቲዎች ርዕዮተ አለም ከሞላ ጎደል ሶሻሊዝም መሆኑና ከሀገሪቱ ነባራዊ ሁኔታ ጋር የማይጣጣምና እንዳለ ከውጭ የተገለበጠ መሆኑ ዛሬ ለምንገኝበት ምስቅልቅል ዳርጎናል። መውጫ አሳጥቶናል ። ፓለቲካችንን ወደ ሟርት ፣ ጥንቆላ፣ አስማት፣ ምቀኝነት ፣ ቅናት ፣ መጠላለፍ ፣ መበላላት ፣ አሉባልታ ፣ ውሸት ፣ ወዘተረፈ አውርዶታል።
በፈጠራ ትርክትና በግልብ ትንተና መታገያና ማታገያ ሆኖ የመጣው የብሔር ጥያቄ ሀገራችን ዛሬ ድረስ ለምትገኝበት ምስቅልቅል እና አጣብቂኝ መግፍኤ ከመሆኑ ባሻጋር ፤ ሀገር ፣ ሕዝብና የባህር በር አሳጥቶናል። ከዚያን ጊዜ አንስቶ ልሒቃኑን በሁለት ጎራ ከፍሎ እያባላና እያጨቃጨቀ ይገኛል። በሀገራችን ተንሰራፍቶ የነበረው ጭቆና የመደብ ነው አይደለም የብሔር ጭቆና ነው በሚሉ ሁለት የማይታረቁ ቅራኔዎች ተጠምዷል። የብሔር ጭቆና በተጠየቃዊነት በምክንያታዊነት የሚተነተን ሳይሆን በማንነት በስሜት የሚቀነቀን የሚራገብ መሆኑ ልዩነቱን የማጥበብ ሂደቱን አዳጋች አድርጎታል ።
እዚህ ላይ በህወሓት ፣ በኦነግ እና ኢትዮጵያዊ ብሔርተኝነትን በሚያራምዱ ወገኖች መካከል ያለውን ልዩነት በአብነት ማንሳት ይቻላል ። ሆኖም የተማሪዎች እንቅስቃሴ ለትህነግ ፣ ለኦነግና ለሌሎች የብሔር ድርጅቶች መፈጠር እርሾ ሆኖ ማገልገሉ አይካድም ። የጋራ ሀገር ፣ ታሪክና ጀግና እንዳይኖረን አድርጓል ። ጥላቻ ፣ ልዩነትና ጎሰኝነት እንዲጎነቁል ለም አፈር ሁኗል ። የሀብት ብሔርተኝነትን ተክሏል። ጦዞ ጦዞ ፣ ጉኖ ጉኖ ፣ አርጦ አርጦ መጨረሻው ሟርትና ጥንቆላ መሆኑ ሳያንስ ምትክና ቅያሬ የሌላትን ሀገር ለማፍረስ ጎዝጉዞ እያሟረተ ይገኛል ። ቁርጡን ይወቅ ፤ በሟርት ሀገር አይፈርስም ። ስልጣን አይገኝም። ሀገራችን ኢትዮጵያ ከሟርት በላይ ናት ።
ሀገራችን ኢትዮጵያ በጀግኖች ልጇቿ ታፍራና ተከብራ ለዘላለም ትኖራለች !
በቁምላቸው አበበ ይማም (ሞሼ ዳያን)
fenote1971@gmail.com
አዲስ ዘመን ነሐሴ 10 /2014