መገናኛ 24 ተብሎ የሚጠራው አካባቢ ያለው ኮከብ ሕንጻ ነበር ጉዳዬ፡፡ አካባቢውን እንጂ ሕንጻውን አላውቀውም ነበር፡፡ ዳሩ ግን ማንንም መጠየቅ ሳያስፈልገኝ የሄድኩበትን ጉዳይ የሚያመለክት ምልክት ማየት የጀመርኩት ከሕንጻው ከብዙ ርቀት ነው፡፡
የሄድኩበት ጉዳይ ሔዋን የፋሽን ዲዛይን፣ የፀጉር፣ የሜካፕ እና ዲኮር ማሰልጠኛ ተማሪዎችን ስለሚያስመርቅ ለመታደም ነበር፡፡ ገና ከርቀት ጋወን የለበሱ ተማሪዎችን አየሁ፡፡ ሌላ የሚያስመርቅ ዩኒቨርሲቲ ወይም ኮሌጅ አለ ይሆን ተጠራጠርኩ፡፡ ዳሩ ግን የአንዳንዶች አለባበስ እንዳልጠራጠር አደረገኝ፡፡ ፋሽን ተኮር ነው፡፡ ጋዎን የለበሱትን የደረታቸውን ማዕረግ ጠጋ ብየ ሳይ ‹‹የፋሽን ዲዛይን….››› ሙሉውን ለማየት ያልቋጨሁት ጽሑፍ አየሁ፡፡
ቀጥታ ወደ አዳራሹ ገባሁ፡፡ የተለያየ አይነት ዲዛይን የለበሱ ቆነጃጂት ይታያሉ፡፡ አብዛኞቹ ግን የለበሱት የተማሪዎቹን የምርቃት ጋዎን ነው፡፡
ወዲያውኑ የፋሽን ሾው ተጀመረ፡፡ የተለያየ አይነት ዲዛይንና ፈጠራ ይታያል፡፡ በነገራችን ላይ እነዚህ ፈጠራዎች የውስጥን ምንነት የሚያሳዩ ናቸው፡፡ ምክንያቱም ፋሽን የውስጥ ስሜት ነው፡፡ ፋሽን ፍልስፍናም ነው፡፡ ፋሽን ፈጠራ ነው፡፡
በመድረኩ ላይ በነበረው ትዕይንት የተለያዩ ፈጠራዎች ታይተዋል፡፡ ከላባ የተሰሩ የዲዛይን አይነቶች፣ ከቃጫ የተሰሩ የዲዛይን አይነቶች አሉ፡፡ ከተለያዩ ልብ ከማንላቸውና ትኩረት ከማንሰጣቸው ነገሮች የተሰሩ ብዙ አይነት ዲዛይኖች አሉ፡፡
እነዚህን በአካባቢያችን ያሉ እና ልብ ያላልናቸውን ነገሮች ትኩረት ሰጥቶ እንደዚያ አይነት ማራኪ ዲዛይን መሥራት ጥበብ ይጠይቃል፡፡
የፋሽን ፍልስፍና የውስጥን እውነታ ለውጭ ማሳየት ነው፡፡ የውስጥ እውነታ ማለት በዲዛይነሯ ውስጥ የተፈጠረው ስሜት ወይም ዕይታ ማለት ነው፡፡ ያንን የውስጥ ዕይታ አውጥታ በልብስ መልክ ለውጭው ታሳያለች፡፡ ይህ ነው የፋሽን ፍልስፍና የሚባለው፡፡
እንዲህ አይነት የፈጠራ ባለቤት የሆኑ ባለሙያዎችን ነው ሔዋን የፋሽን ዲዛይን፣ የፀጉር፣ የሜካፕ እና ዲኮር ማሰልጠኛ ባለፈው እሁድ ያስመረቀው፡፡
የማሰልጠኛው መሥራችና ባለቤት ወይዘሮ ሔዋን ቀለመወርቅ በእለቱ እንደገለጹት፤ በፋሽን፣ በፀጉር፣ በዲኮር፣ በሜክአፕ፣ በጥልፍ እና በሌሎችም ዘርፎች ሲሰለጥኑ የቆዩ ተማሪዎች ስልጠናቸውን በብቃት አጠናቀው ተመርቀዋል፡፡ በዕለቱ ምርቃቱ ላይ ብዙ የፈጠራ ሥራዎች ታይተዋል፤ እነዚያን ሥራዎች የሰሯቸው እዚሁ ማሰልጠኛ ውስጥ ሆነው ነው፡፡
ማሰልጠኛ ተቋሙ እነዚህን ባለሙያዎች ማሰልጠን ከጀመረ ሰባት ዓመታት ሆነውታል፡፡ ሔዋን የፋሽን ዲዛይን፣ የፀጉር፣ የሜካፕ እና ዲኮር ማሰልጠኛ ተቋም ባለፈው ሳምንት እሁድ ያስመረቃቸው ተማሪዎቹ 15ኛ ዙር ሰልጣኞች መሆናቸውን የማሰልጠኛው መሥራችና ባለቤት ገልጸዋል፡፡
በ2007 ዓ.ም ስልጠና መስጠት የጀመረው ማሰልጠኛ ተቋሙ፤ ከአመት አመት የሚቀበላቸው ተማሪዎች ቁጥር እየጨመረ መጥቷል፤ በዚህም ምክንያት ተማሪዎቹን በዓመት ሁለት ጊዜ የሚያስመርቅ መሆኑንም ወይዘሮ ሔዋን ገልጸዋል።
እንደ ወይዘሮ ሔዋን ገለጻ፤ ከማሰልጠኛው ተመርቀው የሚወጡ አብዛኛዎቹ ተማሪዎች የራሳቸውን የሥራ ዕድል ፈጥረው በግል እና በማህበር እየተደራጁ የሚሰሩ መሆን ችለዋል፡፡
ማሰልጠኛው በቀጣይ ሌሎች ተጨማሪ የሙያ ዘርፎችን መጨመር እና ማሳደግ ላይ ይሰራል ያሉት ወይዘሮ ሔዋን፤ በመንግሥት የተያዘውን በክህሎት የዳበረና የሠለጠነ ወጣት በማፍራት ለሥራ እድል ፈጠራ መስፋፋት የበኩሉን ሚና ለማበርከት ጥረት እንደሚያደርግም አስታውቀዋል።
የፋሽን ኢንዱስትሪ በዓለም አቀፍ ደረጃ አንድ የሚመሰገንበት ነገር አለው፡፡ ይሄውም የአየር ብክለትን ማስቀረቱ ነው፡፡ ከወዳደቁ ነገሮች ዲዛይን የሚሰሩ ዲዛይነሮች አሉ፡፡ እነዚህ ዲዛይነሮች ለአየር ብክለት ምክንያት የሚሆኑ ቁሶችን ወደ ጠቃሚ ምርት ይቀይሯቸዋል ማለት ነው፡፡
በፋሽን ኢንዱስትሪው ውስጥ ዘላቂነት ያለው እና ጊዜያዊ የሚባል አለ፡፡ ጊዜያዊ የሚባለው ቶሎ ሊበላሽ ስለሚችል ከጊዜ በኋላ የሚጣል ሊሆን ይችላል፡፡ ዘላቂው ግን በዘላቂነት የአየር ብክለትን ይቀንሳል ማለት ነው፡፡
የዘላቂ ፋሽንን ጽንሰ ሀሳብ የመጣው በሎንዶን ውስጥ የዘላቂነት ዲዛይን እና ፋሽን ፕሮፌሰር ኬት ፍሌቸር በአውሮፓውያኑ 2007 በፈጠረው ፈጠራ ነው ፡፡ ይህ ሃሳብ እንደሚለው በሚያመርተው ምርት ውስጥ አካባቢን በሚያከብሩ የማኑፋክቸሪንግ ምርቶች ላይ እንዲሁም አንድ ልብስ ለሸማቾች በማምጣት ላይ ባሉት ሁሉም ሂደቶች ውስጥ ብክለት የሌለበት መሆን እንዳለበት ነው፡፡
ትላልቅ የኢንዱስትሪ የፋሽን ኩባንያዎች ብዙውን ጊዜ የደህንነት መመዘኛዎች ባልተሟሉባቸው ሀገሮች ውስጥ ሁሉ ይሰራሉ፡፡ በእነዚህ ሁኔታዎች ታዲያ ዘላቂ የሆኑ የፋሽን ብራንዶች የሚዘጋጁት በአዘጋጆቹ ጥንቃቄና ጥሬ ዕቃዎችን በኃላፊነትና በአግባቡ በመጠቀም ነው፡፡
ሰናይት ማሪዎ የተባለች ፋሽን ዲዛይነር በአንድ ወቅት ከሪፖርተር ጋዜጣ ጋር ባደረገችው ቆይታ እንደገለጸችው፤ ፋሽን የሚያድገው በግለሰብ ብቻ አይደለም፡፡ ለዚህም እምቅ ችሎታ ያላቸው ወጣት ዲዛይነሮች አሉ፡፡ ለእነርሱ ደግሞ ዕድል መስጠትና መድረክ መፍጠር ኢንዱስትሪውን ከሚያሳድጉት መካከል አንዱና ዋነኛ ነው፡፡ በሌላ በኩል እነዚህ ዲዛይነሮች በየአካባቢው እየዞሩ የአገራቸውን የባህል አልባሳት ምቹ አድርገው ለገበያ በማቅረብና ራሳቸውን ኢንተርናሽናል ዲዛይነር ለማድረግ ነው ጥረት የሚደረገው፡፡
የኢትዮጵያ አልባሳት በአብዛኛው የሚሠሩት በጥጥ በመሆኑ ለበጋም ሆነ ለክረምት ምቹና ጤናማ በመሆኑ ቀልብ የሚስብ ነው፡፡ ለዚህም ነው አብዛኛዎቹ የዓለም አገሮች ዲዛይነሮች ጥሬ ዕቃ ከዚህ ወስደው መልሰው የሚሸጡልን፡፡ ታዲያ እንደዚህ ዓይነት መድረኮችን በመፍጠር ዲዛይነሮችን በማበረታታት ከአገራቸው አልፈው አህጉራቸው፣ ከዚያም ዓለም አቀፍ ብራንድ እንዲኖራቸው ነው የምንሠራው ብላለች፡፡
በተዘዋወረችባቸው የዓለም አገራት እንደታዘበችው የኢትዮጵያ የፋሽን ኢንዱስትሪ አላደገም፡፡ አገራት የየራሳቸውን መገለጫ ሲለብሱ ኢትዮጵያውያን ግን የሌሎችን አገራት ነው የሚለብሱት፡፡ በመሆኑም የኢትዮጵያ የፋሽን ኢንዱስትሪ ማደግ እንዳለበት ታሳስባለች፡፡
የፋሽን ኢንዱስትሪ ጥቅምን ለማወቅ ያደጉ አገሮችን ማየት ብቻ በቂ ነው፡፡ ለምሳሌ ወደ ኢትዮጵያ የሚገቡ ምርቶችን በአገር ምርት ቢተካ አንደኛው ጥቅም ነው፡፡ በሌላ በኩል ፋሽን እያደገ ሲመጣ የተለያዩ የዓለም ዲዛይነሮች፣ ሞዴሎች፣ ፋሽን ተከታዮች ወደ ኢትዮጵያ ይዘው የሚመጡት የውጭ ምንዛሪ አለ፡፡ በተጨማሪም በሆቴል ይጠቀማሉ፣ ይዝናናሉ፣ የተለያዩ ዕቃዎችን ይሸምታሉ፣ ከፍ ሲል እዚሁ የመሥራት ፍላጎት ሊኖራቸው ይችላል፡፡ ስለዚህ የፋሽን ኢንዱስትሪ አገሪቷን ሊደግፍና ሊያቀና የሚችል ኢንዱስትሪ ነው፡፡
እነዚህ ነገሮች ይሆኑ ዘንድ ደግሞ የፋሽንና ዲዛይን ማሰልጠኛዎች ሊጠናከሩ ይገባል!
ዋለልኝ አየለ
አዲስ ዘመን ነሃሴ 9/2014