
አዲስ አበባ፡- የታላቁ ኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ ኃይል ከማመንጨት በላይ ኢትዮጵያውያን እንችላለን የሚለውን የሚያሳይ ነው ሲሉ የኢፌዴሪ ፕሬዚዳንት ሳህለወርቅ ዘውዴ ገለጹ።
የታላቁ ኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ ሶስተኛው ዙር የውሃ ሙሌት ትናንት በስኬት መጠናቀቁን አስመልክቶ በጉባ በተዘጋጀው መርሃግብር ላይ የተገኙት የኢ.ፌ.ዴ.ሪ ፕሬዚዳንት ሳህለወርቅ ዘውዴ፤ የግድቡ ትርጉም ሃይል ከማመንጨት በላይ ኢትዮጵያውያን እንችላለን የሚለውን የሚያሳይ ነው፤ ኢትዮጵያውያን ከተባበርን ብዙ መስራት እንችላለን፤ ዛሬ ያየነው የአሸናፊዋን ኢትዮጵያ ገጽታ ነው ሲሉ ተናግረዋል።
ይህ ፕሮጀክት ከግድብነት ያለፈ ነው ያሉት ፕሬዚዳንቷ፤ ግድቡ የመብራት ሃይል ከማመንጨት ያለፈ ትርጉም እንዳለው፤ ከጭለማ ወደ ብርሃን ከማሸጋገር ያለፈ እንደሆነ፤ ጾታ፣ ሃይማኖት፣ ዘር እንዲሁም የተለየ ቀለም የሌለው ይልቁንም ኢትዮጵያዊ ግድብ መሆኑን ጠቅሰዋል። ኢትዮጵያውያን ከተባበርን ለዚህ መድረስ እንችላለን ብሎ የሚያሳይ እንደሆነም ገልጸዋል።
ፕሬዚዳንቷ፤ “ኢትዮጵያውያን ከተባበርን ብዙ መስራት እንችላለን፤ ዛሬ ያየነው የአሸናፊዋን ኢትዮጵያ ገጽታ ነው። ኢትዮጵያ እንደዚህ ነች፤ ኢትዮጵያን እንደዚህ ነው ማድረግ ያለብን። ኢትዮጵያን ዛሬ የደስታ እንባ እንድታፈስ እናደርጋታለን። ነገር ግን የኀዘን እንባ እንድታፈስ አድርገናታል። ይህንን ማወቅ አለብን ፤ ማመን አለብን” በማለት ከዚህ ለመውጣት መስራት እንደሚገባ ጠቁመዋል።
በሺዎች የሚቆጠሩ ወገኖች ይህንን ግድብ ለዚህ ያበቁት በሀሩር ውስጥ እንደሆነና፤ የውጭ ድርጅቶችም በዚህ ግንባታ መሳተፋቸውን በመጥቀስ፤ “ነገር ግን ከሁሉም በላይ እናንተ ኢትዮጵያውያን በልታችሁ ሳትጠግቡ ፣ ነገ ያልፍልናል ብላችሁ ገንዘብ ያዋጣችሁ፣ እናንተ ኢትዮጵያውያን ለዚህ ግድብ የተረባረባችሁ፤ ሀገር ውስጥም ሆነ በውጭ ሀገር ያላችሁ በእጅጉ ልትመሰገኑ ይገባል” ብለዋል።
ግድቡ አሁን ወደ ልማት ለማተኮር የሚጋብዝ በመሆኑ ይህ ሃይል መንጭቶ ለሕዝቡ በፍትሃዊነትና በዘላቂነት የሚደርስበትን ሁኔታ በማመቻቸት ኢትዮጵያ ወደፊት እንድትራመድ ማድረግ እንደሚገባም አሳስበዋል።
ፕሬዚዳንቷ፤ ላም አለኝ በሰማይ ከሚለው እንድንወጣ እያደረግን ነው በማለት፤ “የኛ ስራ ውይይትን፣ ምክክርን የሚከለከል አይደለም። እንዳውም የዚህ ግንባታ እዚህ መድረስ ለጎረቤት ሀገሮች ከናይል ተፋሰስ ሀገሮች ጋር የበለጠ ትብብር ምክክር እንዲኖረን ከሀገር አልፎ አካባቢውን፣ ከአካባቢ አልፎ አህጉራችንን ለማሳደግ ነው መነሳት ያለብን” ሲሉ ገልጸዋል።
ግድቡ በጋራ ለመስራት የዲፕሎማሲውን በር በሰፊው የሚከፍት እንደሆነ በመግለጽ፤ በርትቶ መሥራት እንደሚገባና የሕዝቡ ድጋፍም ቀጣይነት እንዲኖረው ጥሪ አቅርበዋል።
አዲሱ ገረመው
አዲስ ዘመን ነሐሴ 7 /2014