የአማርኛው መዝገበ ቃላት አባይን ዋና አባት ሲል ይገልጸዋል። ከዚህ እውነት በመነሳት አባይ ማለት ዋና ማለት እንደሆነና አባት ማለት እንደሆነ እንደርስበታለን። ይህ ስም የስሞች ሁሉ በኩር፣ የክብሮች ሁሉ ቁንጮ ነው። ይህ ስም የእኛ ስም ነው። ይህ ስም የኢትዮጵያውያንን ባህልና ታሪክ ተንተርሶ ነፍስ የዘራ ነው። ይህ ስም እትብቱን ከእትብታችን ቀላቅሎ፣ ጥቁርነትን ለብሶ፣ ታሪክና ስልጣኔአችንን ተጋርቶ ከጉያችን መንጭቶ የሚፈስ ነው።
ታዲያ አባት ቢባል ምን ያንስበታል? አባይ ዋናችን ነው..ከዚህ ውጪ ምንም ሊሆን አይችልም። ለዘመናት በአቅምና በኢኮኖሚ ችግር አባትነቱን ግብጾች ቀምተውን በራሳችን ታሪክ ባይተዋር አድርገውን ነበር። ለዘመናት በእኛ አባትነት ግብጽን ጨምሮ የታችኞቹ ተፋሰስ ሀገራት ሲያጌጡና ከፍ ሲሉ ነበር። ዘመን ተቀይሮ ይሄኛው ትውልድ በአቅምም በኢኮኖሚም በርትቶ አባይን እየገደበው ይገኛል፤ ምን መገደብ ብቻ ሀይል ማመንጨትም ጀምሯል።
በርግጥ ለኛ ኢትዮጵውያን አባይ የጋራ ስማችን ነው…መታወቂያችን። ኢትዮጵያዊነት የወል ስም ካለው አባይ ነው። በብዙ ነገር ተለያይተን በአባይ ጉዳይ ላይ ግን አንድ ነን። ምክንያቱም አባይ በጋራ የጻፍነው የጋራ ታሪካችን ስለሆነ። በኢትዮጵያ ምድር እንደ አባይ በጋራ ጀምረን በጋራ ልንጨርሳቸው የሚገቡ በርካታ ነገሮች አሉ። መለያየት ያበላሻቸው፣ እኔነት ያጸለማቸው በጣም ብዙ ጉዳዮች አሉን። እኚህ ጉዳዮቻችን ተጀምረው እንዲያልቁ፣ ስኬትና ከፍታ፣ እድገትና ስኬት እንዲሆኑን በአንድነት መቆም አለብን።
አባይ የአንድነታችን ውጤት ነው። አለም በተነሳብን ጊዜ፣ ሀያላኖቹ ለግብጽና ሱዳን ወግነው በተነሱብን ጊዜ አንድ ላይ ነበርን። በብዙ ልዩነት ውስጥ አብረን ነበርን። ይሄን ነው የኢትዮጵያዊነት ቀለም የምላችሁ። ይሄን ነው የጋራ ስማችን የምላችሁ። ይሄ አንድነት ዛሬ ላሉብን ችግሮች አስፈላጊ ነው። አባይን በጋራ እንደገነባነው ሁሉ በጋራ የምንወጣቸው በርካታ ሀገራዊ እንከኖች አሉብን። አንድነት ምን ያህል ሀይል እንደሆነ አባይ ምስክራችን ነው። የአባይ ግድብ፣ የአባይ ምስጢሩ የአንድነታችን ውጤት ነው።
በአባይ ጉዳይ ግብጾች ተኝተው አያውቁም። ዛሬም የውሸትና የፖለቲካ ሸሮችን እየጎነጎኑ ተስፋችንን ሊነጥቁን እያሴሩብን ነው። ትውልዱ ግን በአባቱ የማለ፣ በአባቱ ቀልድ የማያውቅ ሆኖ በግብጽና ሱዳንም ጩኸት ውስጥ ታሪክ እየሰራ ይገኛል። ይሄ ትውልድ ከእንግዲህ ወደ ኋላ የማይል ነው። ዋናውንና አባቱን ለባዕድ ሰጥቶ በድህነትና በኋላ ቀርነት መኖር አይፈልግም። አይደለም በአባይ ጉዳይ ወደኋላ ሊል ቀርቶ እነዛ በአቅም ማነስ በግብጾች የበላይነት ያለፉት የአባቶቹ ዘመናት እንኳን የሚያስቆጩት ናቸው።
ግብጾች የነጠቁንን አባታችንን ማስመለስ የዚህ ትውልድ የቤት ስራው ነው። ለዘመናት በአባታችን በአባይ ግብጽ ስታጌጥ ኖራለች። ከእንግዲህ አባይ የእኛ ነው። ካባ ለብሶ፣ ዘውድ ጭኖ ትንሳኤውን ሊያሳየን እነሆ ከአፋፍ ደርሷል። ኢትዮጵያውያን በአንድ ያዜምንለት፣ በአንድ የዘፈንለት አባይ ሊሞሸር ዋዜማ ላይ ነው። ጨለማዎቻችን ሊነጉ፣ ተስፋዎቻችን ብርሀን ሊያዩ…ኢትዮጵያ ልትስቅ እንሆ ትንሽ ብቻ ይቀራል።
አባይ የገነት መቀነት ነው። ወገቧን ሸብ ያደረገችበት። ገነት ያጌጠችው አባይን ተደግፋ፣ አባይን ጠምጥማ ነው። አባይ የኤዶም ገነት ክንብንብ ነው…አንገቷ ላይ ጣል ያደረገችው። አባይ እምነታችን፣ ጽናታችን፣ የአንድነታችን ክር ነው። አባይ ተስፋችን፣ ትንሳኤአችን፣ የከፍታችን ማማ ነው። በአባይ ግድብ ተስፋን የሰነቁ፣ ነገን አሻቅበው የሚያዩ ነፍሶች በኢትዮጵያ ምድር አሉ። እኚህ ነፍሶች እኔና እናንተ ነን። እኚህ ነፍሶች መጪው ትውልዶች ናቸው። ከምንበላው ላይ ቀንሰን፣ ከሌለን ላይ ገምሰን ነው ከዘመናት ኩብለላው የመለስነው። አባይ በተፈጥሮ ውልደት ከከበቡንና ታሪክና ባህላችንን ከወረሱ እሴቶቻችን አንዱና ዋነኛው ነው።
በዚህ ርስታችን ማጌጥ አለብን። ከዚህ ህብስታችን መብላት አለብን። ኢትዮጵያውያን ክፉዎች አይደለንም። እውነትን ሽተው ለተጠጉን ካለን ላይ ማካፈል የለመድን ህዝቦች ነን። እኛ አብረን እንብላ ስንል ግብጽና ሱዳን ለብቻችን ካልበላን እያሉ ነው። ይሄ ትውልድ ርስቱን አሳልፎ መስጠት አይፈልግም። ከበሉ አብረውን ይብሉ ካልበሉ ግን በርስታችን ላይ የመጠቀም ሙሉ መብት አለን፤ አባይን ገድበን የመጠቀምና የመልማት መብት።
ሱዳንና ግብጽ የከፉብንን ያህል እኛ ለነሱ ከፍተን አናውቅም። ከትናንት እስከዛሬ አብረን እንልማ፣ አብረን እንደግ እንዳልን ነው። ነገር ግን ወልደው ባሳደጉት የክፋት ሃሳቦቻቸው ከጀመርነው የእድገት ጎዳና ሊያደናቅፉን ብዙ ለፍተዋል አሁንም እየለፉ ነው። በተለይ አባይን ለመገደብ በተነሳንበት ሰሞን ከግብጽና ከወዳጆቿ እንዲሁም ከአለም አቀፉ ማህበረሰብ የደረሰብን ጫና ቀላል የሚባል አልነበረም።
አሁንም አልተኙም…የተሳሳተ መረጃዎችን በማሰራጨት፣ በአባይ ጉዳይ ያለንን አንድነት ለማላላት በርካታ ሴራዎችን በመጎንጎን ላይ ናቸው። እኛ ግን አሁንም በአባይ ጉዳይ ላይ አልቆምንም፤ አልተለያየንም፣ አንድ ላይ ነን። በተለይ የመጀመሪያውን የውሃ ሙሌት በጀመርን ሰሞን፣ በተለይ ሁለተኛውን የውሃ ሙሌት ጀምረን ሀይል ማመንጨት ስንጀምር የሆኑት መሆን እንዲህ በቀላሉ የሚገለጽ አልነበረም። አሁንም የተሳሳተ መረጃዎችን በማሰራጨት ከምዕራባውያን ወዳጆቻቸው ጋር እያሴሩብን ነው።
እኛ ግን ያው እንደ ትናንቱ ነን። የግብጽን የሀሰት ወሬ ችላ ብለን ስለ አባይ ጎንበስ ቀና እያልን ነው። እኛና ግብጽ አይሁድንና ክርስቶስን ነን። በዛ በጎለጎታ፤ በርባን ተፈቶ ክርስቶስ ሲሰቀል ብዙዎች ደስ ብሏቸው ነበር። አሁንም የግብጽ ወዳጆች ኢትዮጵያ ከስራ ግብጽ እንድታተርፍ የሚፈልጉ ናቸው። ይሄ ግን አይሆንም፤ ምክንያቱም ትውልዱ ትንታግ ትውልድ ነው። በዚያ ጊዜ ከአይሁድ ጫጫታ ይልቅ ጲላጦስን ያስፈራው የክርስቶስ ዝምታ ነበር። እኛም የግብጾች ጩኸት ምናችንም ነው። እንደ ክርስቶስ ዝም ብለን የተደቀኑብንን መሰናክሎች ተረማምደን ትንሳኤአችንን እናያለን።
አባይ አባታችን ነው፤ እናቱ ደግሞ ኢትዮጵያ ናት። ከአብራኳ ወጥቶ፣ በአብራኳ አድጎ የበለጸገ ልጇ። ታዲያ አባዬ ብለን ብንጠራው ማን ምን ያገባዋል? ዛሬም ነገም መቼም አባይ የእኛ ነው። ለሚወዱን በፍቅር ለተጠጉን እናጋራዋለን። አባይን ከመገደብና በአባይ ላይ ከመጠቀም የሚያግደን ምንም ምድራዊ ሀይል የለም።
አንዳንድ ውሸቶች ሲቆዩ ወደ እውነት ይቀየራሉ። በተለይ ውሸት ፈጣሪ ግለሰቦችና ፖለቲከኞች ሲኖሩ እውነት ክብር ያጣል። የአባይ ጉዳይ በግብጽ ላይ እንደዚህ ነው። ለዘመናት ያለማንም ከልካይ ተጠቀሙበት፤ ከዛም የእኛ ብቻ ነው፣ የሚመነጨውም ከግብጽ ምድር ነው ሲሉ ማመን ጀመሩ። ማመን ብቻ አይደለም ያላመኑትን ማሳመን ጀመሩ። ትውልዱ እውነትን ሽሮ አባይ የግብጻውያን እንደሆነ አምኖ እንዲቀበል ብዙ ለፉ። ለልጆቻቸውም ስለ አባይ ውሸት ነገሩ።
በዚህ አላበቁም፤ በአባይ ጉዳይ ላይ የትምህርት ስርዐት ገንብተው ልጆቻቸውን ስለአባይ ውሸት ማስተማር ጀመሩ፤ አባይ የእኛ ነው ሲሉ። አሁን ለግብጻውያን አባይ ማለት ከግብጽ የሚመነጭ፣ ለግብጽ ህልውና የተሰጠ አምላካዊ ስጦታ ነው። ይሄ በዘመናት የውሸት አሉባልታ ውስጥ የተፈጠረ እውነት ነው።
አባይ የኢትዮጵያውያን ነው። ውልደቱ፣ እድገቱ ከሰከላ ማህጸን ነው። አሁን ትግላችን በግብጻውያን ልብ ውስጥ የታተመውን የውሸት እውነት ፍቆ አባይ የሀገራቱ ህዝቦች የጋራ ሀብት እንደሆነ ማሳየት ፤ አባይን በጋራ እንድንጠቀመው ማድረግ ነው።
በግብጽ ምድር ለአባይ የተዘፈነውን ያህል ለማንም አልተዘፈነም። ዛሬም ድረስ የጉዳያቸው አንደኛ ነው። ብሄራዊ ክብራቸው፣ ታሪካዊ ህልውናቸው አድርገውት ለዘመናት ኖረዋል። ይሄ የውሸት ትርክት በዚህ በእኔና በእናንተ ተሽሮ አባይ የጋራ ነው ስንል ተነስተናል። ትግላችንም ፍሬያማ ሆኖ ለጋራ ተጠቃሚነት እየገደብነው ብቻ ሳይሆን ብርሃኑንም እያየነው ነው። የጊዜ ጉዳይ ካልሆነ በስተቀር የቀረን ትልቁ ነገር በአንድነት የገነባነውን፣ በአንድነት የደከምንለትን የህዳሴ ግድባችንን ማጠናቀቅ ነው። ይሄም ከሁለት አመት ብዙም የሚዘል አይሆንም። የሚቀረን በጋራ ትንሳኤአችንን ማጣጣም ነው። የሚቀረን እንደ ህዳሴ አይነት ሌሎች ግድቦችን መስራት ነው።
በነገራችን ላይ ግብጻውያን አባይን የህልውናቸው መሰረት ያደረጉበትን ብዙ ማስረጃዎችን ማየት እንችላለን። ግብጽ ውስጥ በአባይ የሚምሉ አሉ። ግብጽ በየአመቱ ከአምስት ሺ በላይ የሶስተኛ ዲግሪ ተማሪዎችን ታስመርቃለች፤ በጣም የሚገርመው ደግሞ እነኚህ ሁሉ ተማሪዎች የመመረቂያ ጽሁፋቸውን የሚሰሩት በአባይ ወንዝ ላይ መሆኑ ነው። ግብጽ ውስጥ አባይ ለብዙ ተማሪዎች የመመረቂያ ጽሁፍ ሃሳብ ነው። ይሄ ማለት ግብጾች በአባይ ዙሪያ ምን ያህል ርቀት እንደተራመዱ የሚያሳይ ነው። አሁን ጊዜው የእኛና የአባይ ነው። በአባይ ላይ የግብጽ የበላይነት አክትሟል። አባይ ወደ እናቱ ተመልሷል።
በየትኛውም መስፈርት ቢታይ የኢትዮጵያ ታላቁ ህዳሴ ግድብ መስራት ግብጽና ሱዳንን አይጎዳም ይጠቅማቸዋል እንጂ፤ ግን ውስጣቸው ያስቀመጡት የኔነትና የብቻ ሃሳብ ስላለ አባይን መጋራት አይፈልጉም።
ይሄ ሃሳብ ምን ያህል እውነት እንደሆነ ለማየት ጥቂት ምሳሌዎችን ላስቀምጥ። ካቻምና የመጀመሪያ የውሃ ሙሌት ስናከናውን ካጠቃላዩ የውሃ ይዘት 4 በመቶ ብቻ ነበር የተጠቀምነው። ቀጥለን በአመቱ አምና ማለት ነው 13 በመቶ ብቻ ነው ለሙሌት የተጠቀምነው፤ ይሄ ማለት በመጀመሪያው ሙሌት 96 በመቶው በሁለተኛው ሙሌት ደግሞ 87 በመቶው ውሃ ወደ ግብጽና ሱዳን ፈሷል ማለት ነው። ከዚህ እውነት በመነሳት የውሃ እጥረት ይፈጠራል፣ የተፋሰሱ ሀገራት ይራባሉ የሚሉት የግብጽና የሱዳን አሉባልታዎች ውሸት መሆናቸውን እንደርስበታለን።
የግብጽና ሱዳን ስጋት የኢትዮጵያን ብልጽግና ከመፍራት የመነጨ ነው። ኢትዮጵያን ከመፍራት፣ ብልጽግናዋን ከመስጋት የመነጨ ስሜት ነው። ኢትዮጵያ ሀገራችን ከህዳሴ ግድባችንና ከዚህ በኋላም በምትገነባቸው ግድቦች የምታገኘው የሀይል፣ የኢኮኖሚ፣ የፖለቲካ፣ የስልጣኔ፣ የዘመናዊነት ጸጋ ስጋት ሆኗቸው ነው ዛሬ ላይ ይሄን ሁሉ ችግር እየፈጠሩ ያሉት።
የህዳሴ ግድባችን ከሃሳባችን ያልወጣ፣ ከሃሳባችን የማይወጣ የህልውናችን ማህተም ነው። ጠላት ያው ጠላት ነው፤ ጥሩ ነገር አያወራም። ገና ከዚህ በኋላም የተለያዩ የውሸት ወሬዎችን እንሰማለን። ከእኛ የሚጠበቀው እንደ ክርስቶስ ዝም ብለን እየሰራን ወደ ትንሳኤአችን መጓዝ ነው።
አባይ አባታችን ነው፤ ከግንባታው የሚያስቆመን ማንም የለም። የግብጾች ህልውና እንደመሆኑ ለእኛም ህልውናችን ነው። በአባይ ግድብ ላይ መቶ ሃያ ሚሊዮን ድሀ ህዝቦች ተስፋን ሰንቀዋል። እምነትን ጥለዋል። በአባይ ግድብ ላይ መጪው ትውልድ ኩራትና ብኩርናን በዛሬዎቹ እኛ ላይ ጥሏል። ታዲያ አባይ እህል ውሃችን ቢሆን ምን ይገርማል?::
በትረ ሙሴ መልከ (ኢትዮጵ)
አዲስ ዘመን ነሐሴ 6 /2014