
- በመጪው ዓመት ማስተማር እንደሚጀምርም አስታውቋልበዚህም
አዲስ አበባ፡- የአዲስ አበባ አመራር አካዳሚ የተሰጠውን ተልዕኮ እውን ለማድረግ ተቋምን፣ ከተማንና አገርን ሊለውጡ የሚችሉ ብቁ አመራሮችንና ባለሙያዎችን ለማፍራት በትኩረት እየሠራ መሆኑን ገለጸ። በ2015 የትምህርት ዘመን ተማሪዎችን ተቀብሎ ለማስተማር ዝግጅት እያደረገ መሆኑንም አስታውቋል።
የአዲስ አበባ አመራር አካዳሚ ዋና ዳይሬክተር ዶክተር ደሳለኝ ጴጥሮስ በከተማ አመራርና አስተዳደር ትምህርት ካሪኩለም ላይ ግብዓት ለመሰብሰብ በተዘጋጀው የምክክር መድረክ ላይ እንደገለጹት፤ አዳሚው ተቋምን፣ ከተማንና አገርን ሊለውጡ የሚችሉ ብቁ አመራሮችንና ባለሙያዎችን እንዲያፈራ የተሰጠውን ተልዕኮ እውን ለማድረግ በትኩረት እየሠራ ነው።
አዲስ አበባ የበርካታ ዓለም አቀፍና አህጉራዊ ተቋማት መቀመጫ ናት ያሉት ዶክተር ደሳለኝ፤ በመሆኑም ይህንን በሚመጥን መልኩ ከተማዋን ሊመራ የሚችል አመራር ምን አይነት ትምህርትና ስልጠና ያስፈልገዋል የሚለውን ለመመለስ እየሠራ ነው ብለዋል።
አዲስ አበባ ከተማ ላይ ያልተመጣጠነ እድገት ይስተዋላል ያሉት ዋና ዳይሬክተሩ፤ ይህን ችግር ለመቅረፍና ከተማዋን የሚመጥን ብቃት ያላቸው ብቁ አመራሮችና ባለሙያዎችን ለማፍራት ዓለም አቀፍ ተሞክሮዎችን ያካተተ የትምህርት ካሪኩለም መቀረጹንም ጠቁመዋል።
በኢትዮጵያ ከ900 በላይ ከተሞች ቢኖሩም ብዙዎቹ በፕላን የሚመሩ አለመሆናቸውን ጠቁመው፤ የአገልግሎት አሰጣጥን ለማዘመንና የሕዝብን ጥያቄ ለመመለስ አመራሩ በክህሎት፣ በእውቀትና በስነምግባር የበለጸገ ሊሆን ይገባል ብለዋል።
ስድስተኛውን አገራዊ ምርጫ ተከትሎ አካዳሚው በአዲስ መልክ መቋቋሙን የጠቆሙት ዋና ዳይሬክተሩ፤ በዚህም በትምህርት፣ በማህበረሰብ አገልግሎት፣ በስልጠናና በማማከር አመራሩና ባለሙያውን እንዲያበቃ ትልቅ ኃላፊነት ተጥሎበታል ሲሉም ተናግረዋል።
ይህን ኃላፊነቱን ለመወጣት የሦስት የትምህርት መስኮች የካሪኩለም ጥናት መከናወኑን ያስታወሱት ዶክተር ደሳለኝ፤ በቀጣይ ጥር ወር በከተማ አመራርና አስተዳደር ትምህርት መስክ በሁለተኛ ዲግሪ ተማሪዎችን ተቀብሎ ለማስተማር ዝግጅት እያደረገ መሆኑን ገልጸዋል።
አካዳሚው በ10 ሺ ካሬ ሜትር ቦታ ላይ እየገነባ ያለው ዘመናዊ ማሰልጠኛ በቅርብ ጊዜ ይጠናቀቃል ተብሎ እንደሚጠበቅ ጠቁመው፤ ግንባታው ሲጠናቀቅ የአካዳሚውን አቅም በእጅጉ ከፍ ያደርገዋል ሲሉም ጠቁመዋል።
የአካዳሚው የትምህርትና ስልጠና ዘርፍ ዋና ዳይሬክተር ዶክተር ለሚ ተስፋ በበኩላቸው፤ አካዳሚው የአጭርና የረጅም ጊዜ ስልጠናዎችን እንዲሰጥና የማማከር አገልግሎት እንዲያከናውን ኃላፊነት ተሰጥቶታል ብለዋል።
አካዳሚው ከተማዋ ላይ ትልቅ የአመራር ክፍተት መኖሩን ለይቷል ያሉት ዶክተር ለሚ፤ ይህን ክፍተት በአጭር ጊዜ ውስጥ በመሙላት የተስተካከለ እድገትና ለነዋሪዎቿ የምትመች ከተማ ለመፍጠር መሥራት ያስፈልጋል ሲሉም ተናግረዋል።
አዲስ አበባ ትልቅ የዲፕሎማሲና ሰፋ ያለ የንግድ እንቅስቃሴ የሚስተዋልባት ከተማ ናት ያሉት ምክትል ዋና ዳይሬክተሩ፤ ከተማዋን ይበልጥ እያሳደጉ ለመሄድ አመራሩ በእውቀት፣ በክህሎትና በሥነ-ምግባር መታነጽ አለበት። ለዚህም ከተማዋ በሁሉም መልኩ ለኑሮ የምትመረጥ ከተማ እንድትሆን አካዳሚው የበኩሉን ሚና ለመወጣት እየሠራ ነው ብለዋል።
ፋንታነሽ ክንዴ
አዲስ ዘመን ሐምሌ 5 ቀን 2014 ዓ.ም