
አዲስ አበባ፡- አማራ ክልል ከ200 ቢሊዮን ብር በላይ ካፒታል ያስመዘገቡ ኩባንያዎች በማዕድን ኢንቨስትመንት ዘርፍ የምርመራና ማምረት ስራ ፈቃድ ወስደው እየሰሩ መሆናቸውን የክልሉ ማዕድን ሀብት ልማት ቢሮ አስታወቀ።
የቢሮው ኃላፊ አቶ ኃይሌ አበበ እንደገለጹት፤ በክልሉ ያለውን ዕምቅ የማዕድን ሀብት በአግባቡ አልምቶ ጥቅም ላይ ለማዋል ቢሮው በትኩረት እየሰራ ነው። ባለፈው አንድ ዓመት ተኩል ብቻ ከ200 ቢሊዮን ብር በላይ ካፒታል ያስመዘገቡ 102 ኩባንያዎች በማዕድን ዘርፍ የምርመራና ማምረት ስራ ፈቃድ ወስደው እየሰሩ ይገኛሉ።
የተለያዩ ፋብሪካዎች ለወለል ንጣፍ፣ ለደረጃና ሌሎች አገልግሎቶች የሚውሉ ግራናይት፣ ማርብልና ጂብሰም እያመረቱ እንደሚገኙ ጠቁመዋል።
ኩባንያዎቹ በዓመት እስከ 130 ሺህ ቶን ግራናይት ማርብልና ጅብሰም አምርተው ለሀገር ውስጥ ገበያ ማቅረብ መጀመራቸውን አመልክተው፤ ከውጭ ይገቡ የነበሩ ምርቶችን በሀገር ውስጥ ምርቶች የመተካት ስራ እየተከናወነ ነው ብለዋል።
የምርመራ ፈቃድ ከወሰዱ ሰባት የሲሚንቶና 30 የድንጋይ ከሰል ኩባንያዎች 3ቱ የምርመራ ስራቸውን ማጠናቀቃቸውን ገልጸው፤ የማምረት ፈቃድ ወስደው ወደ ሥራ መግባታቸውን አመልክተዋል።
በማዕድን ዘርፍ የምርመራና የማምረት ፈቃድ የወሰዱት ኩባንያዎች ከ23 ሺህ ለሚበልጡ ዜጎች ቋሚና ጊዜያዊ የስራ ዕድል መፍጠራቸውንም አቶ ኃይሌ አስታውቀዋል።
“ሀገሪቱ በ10 ዓመቱ የልማት ዕቅድ ወደ ከፍታ ከምትወጣባቸው የኢኮኖሚ ዘርፎች አንዱ ማዕድን ነው” ያሉት አቶ ኃይሌ፤ የክልሉ መንግስትም ለዘርፉ ዕድገት ልዩ ትኩረት ሰጥቶ እየሰራ ይገኛል ብለዋል።
የቤአይካ ጄኔራል ቢዝነስ ዋና ስራ አስፈፃሚ አቶ ካሳሁን ምስጋናው በበኩላቸው፤ ኩባንያቸው 10 ቢሊዮን ብር በሚጠጋ ካፒታል በንግድ፣ ኢንዱስትሪ፣ እርሻና ኮንስትራክሽን ዘርፎች ተሰማርቶ እየሰራ መሆኑን ገልጸዋል።
በተለይ በማዕድን ዘርፍ ለኮንስትራክሽን ግብዓት የሚውሉ ግራናይት፣ ማርብል፣ ታይልስና ካልሽየም በሀገር ውስጥ ጥሬ ዕቃ መቶ በመቶ እያመረቱ መሆኑን አስረድተዋል።
አሁን ላይ ግራናይት 3 ሺህ 500 ካሬ፣ ማርብል 1 ሺህ ካሬ፣ ታየርስ 2 ሺህ 500 ካሬ፣ ቀለም 100 ሺህ ሊትር በቀን በማምረት በሁሉም የሀገሪቱ አካባቢዎች ምርቱን ተደራሽ እያደረገ ይገኛል ብለዋል።
በሀገር ውስጥ ያለውን ከፍተኛ ፍላጎት ለማሟላት እየተሰራ መሆኑን ጠቁመው፤ ከመጪው ጥቅምት ወር ጀምሮ የግራናይት ምርትን በሶስት ዕጥፍ፣ የማርብል ምርትን ደግሞ በሁለት ዕጥፍ የሚያሳድጉ ተጨማሪ ፋብሪካዎችን ለመትከል የተገዙ ማሽነሪዎችን እያጓጓዙ መሆኑን ኢዜአ ዘግቧል።
ለኤክስፖርት ብቻ የሚሆን የግራናይት ምርት የሚያመርት ግዙፍ ፋብሪካ ጥሬ ዕቃው በሚገኝበት በምዕራብ ጎጃም ቡሬ አካባቢ ለመትከል ቅድመ ዝግጅት እየተደረገ መሆኑን ጠቁመዋል።
“መንግስትም 24 ሰዓት ፋብሪካዎቻችን ስራቸውን ሳያቋርጡ እንዲያከናውኑ በቂ የኤሌክትሪክ ኃይል ከማቅረብ ጀምሮ የተለያዩ ድጋፎች እያደረገልን ነው” ብለዋል።
ኩባንያው በተሰማራባቸው የኢንቨስትመንት ዘርፎች ለ7 ሺህ ዜጎች ቋሚና ጊዜያዊ የሥራ ዕድል መፍጠሩን ጠቅሰው፤ ከዚህ ውስጥ 40 በመቶው በማዕድን ዘርፍ የተፈጠረ ነው ብለዋል።
በአማራ ክልል ለኢንዱስትሪ፣ ለኮንስትራክሽን፣ ለብረት፣ ለኃይል አቅርቦትና ለጌጣጌጥ የሚውሉ 35 አይነት ማዕድናት እንደሚገኙ በጥናት መረጋገጡን ከቢሮው የተገኘ መረጃ ያመላክታል።
በጋዜጣው ሪፖርተር
አዲስ ዘመን ሐምሌ 5 ቀን 2014 ዓ.ም