
ሀዋሳ፡- በረቀቀ የስዕል እና የጥበብ ሥራዎቻቸው የሚታወቁት እጅግ የተከበሩ የዓለም ሎሬት ሜትር አርቲስት አፈወርቅ ተክሌ መኖሪያ ቤት የነበረውና በአሁኑ ወቅት አቶ ጥላሁን ሽፈራው በተባሉ የግል ባለሀብት ባለቤትነት በግዢ የተዛወረው የቪላ አልፋ እንግዳ ማረፊያ በ220 ሚሊዮን ብር ወጪ እድሳት ተከናውኖለት አገልግሎት መስጠት መጀመሩ ተገለጸ፡፡
የሐዋሳ ከተማ አስተዳደር ከንቲባ ረ/ፕሮፌሰር ፀጋዬ ቱኬ በከተማዋ በግሉ ዘርፍ በመከናወን ላይ ያሉ የኢንቨስትመንት እንቅስቃሴዎችን ተዟዙረው ከተመለከቱ በኋላ እንደገለጹት፤በግሉ ዘርፍ እንቅስቃሴዎች የቱሪዝምና የኢንቨስትመንት መነቃቃት በከፍተኛ ደረጃ እያደገ ይገኛል፡፡
በግሉ ዘርፍ እንቅስቃሴዎች የቱሪዝምና የኢንቨስትመንት መነቃቃት እንደ ከተማ በከፍተኛ ደረጃ እያደገ እንደሚገኝ የገለፁት ረ/ፕሮፌሰር ፀጋዬ ቱኬ ከተማ አስተዳደሩ ለኢንቨስተሮች ምቹ ሁኔታዎችን የመፍጠር የመደገፍና የመከታተል ስራውን ትኩረት ሰጥቶ እየሠራ እንደሚገኝ ጨምረው ገልፀዋል፡፡
ይህ ታሪካዊ ስፍራ በተገቢው ሁኔታ ታድሶ እና ተገንብቶ አገልግሎት መስጠት መጀመሩ ለሐዋሳ ከተማ ኢንቨስትመንት እና የቱሪዝም እንቅስቃሴ ተጨማሪ አቅም የሚፈጥር መሆኑን ወ/ሮ ደርጊቱ ጫሊ የሀዋሳ ከተማ አስተዳደር ባህል፣ ቱሪዝምና ስፖርት መምሪያ ኃላፊ ገልፀዋል፡፡
ቪላ አልፋ እንግዳ ማረፊያ ታሪካዊ ይዘቱን ሳይለቅ በተዋቡ እና የተገልጋይ ፍላጎትን ማዕከል ባደረጉ እንዲሁም ደረጃቸውን በጠበቁ ቁሳቁሶች የተገነባ መሆኑን የገለፁት የእንግዳ ማረፊያው ባለቤት አቶ ጥላሁን ሽፈራው በእንግዳ ማረፊያው ግንባታና እድሳት ሂደት እጅግ የተከበሩ የዓለም ሎሬት ሜትር አርቲስት አፈወርቅ ተክሌ ታሪክና ስም ማስቀጠል የሚያስችሉ ሥራዎችን ለማከናወን እቅድ ተይዞ በትኩረት እየተሠራ እንደሚገኝም ጨምረው ገልፀዋል፡፡
ለእንግዳ ማረፊያው ግንባታ ከ220 ሚሊዮን ብር በላይ ወጪ መደረጉን የገለፁት አቶ ጥላሁን እንግዳ ማረፊያው ሙሉ በሙሉ ወደ ሥራ ሳይገባ ከ80 በላይ ቋሚ እና ጊዜያዊ የሥራ እድል ከመፍጠሩም በተጨማሪ በሚሰጠው አገልግሎት ለሐዋሳ ከተማ ተጨማሪ ውበት የሚፈጥር የቱሪዝም መዳረሻ እንደሆነም መግለጻቸውን የዘገበው የሃዋሳ ከተማ አስተዳደር የመንግሥት ኮሙኒኬሽን ጉዳዮች መምሪያ ነው።
በጋዜጣው ሪፖርተር
አዲስ ዘመን ሐምሌ 28 ቀን 2014 ዓ.ም