በማህበራዊ ሚዲያዎች እየተሸረሸሩ ያሉ ዕሴቶቻችን
ለብዙዎቻችን መመለስ ከሚከብዱን ጉዳዮች ቀዳሚው ኢትዮጵያዊነት ምንድነው? የሚለው ጥያቄ ነው። ብዙዎች በየዘመናቸው በተረዱበት ልክ ሊያብራሩት ሊገልፁት የሞከሩ ቢሆንም አሁንም ድረስ በቂ የሚባል መልስ ያልተገኘለት፡ ወደፊትም ደግሞ ጥያቄ ሆኖ የሚቀጥል ጉዳይ ነው። ምክንያቱም ኢትዮጵያዊነት ቅኔ ነው በሰም እና ወርቅ የተለበጠ። ብዙ ምርምር የሚጠይቅ በዘመናት ውስጥ አጥጋቢና ቀጥተኛ ምላሽ ያልተገኘለት ስውር ቅኔ። ኢትዮጵያዊነትን እንዴት ትገልፁታላችሁ ተብለን ብንጠየቅ መልሳችን የሚሆነው ረጅም ዝምታ ነው። ምክንያቱም ኢትዮጵያዊነትን ለመግለፅ ቃል ያጥረናል፤ ቋንቋ ይነጥፍብናል።
ኢትዮጵያዊነት ለኛ የምንኖረው ፤ የእለት ተእለት ህይወታችን ፤ ሳቃችን፤ ለቅሷችን፤ ሀዘናችን፤ መፅናናታችን፤ የብዙ ስሜቶች ቅይጥ ነው። ታዲያ ይህን የብዙ ስሜቶች ቅይጥ በቃላት ድርድር ማሳየት በቋንቋ ቅንብር በሙላት መግለጽ አይቻልም። ቢሆንም ግን ስሜትን ለመግለጽ ያህል ትንሽ ነገር ማለት አይከፋምና እንደሚከተለው ልግለፀው።
ኢትዮጵያዊነት የሚኖር እንጂ የሚወራ አይደለም። ኢትዮጵያዊነት የአንዲት ኢትዮጵያ የምትባል አገር ህዝብና አስተዳደር ማንነት ማለት ነው። የኢትዮጵያን ብሄራዊ ቅርፅ የያዘ፣ አቅጣጫና ይዘት የሚነድፍ የሚመራ ፍልስፍና፣ የህዝቧን አንድነት፣ የግዛቷን ሉዓላዊነት፣ የመንግስቷን ቀጣይነት የዜጎቿን እኩልነት፣ የሚሰብክ አንድ የመሆን አስተሳሰብ ነው። ኢትዮጵያዊነት ባህልና ታሪክ ተሳስረው ያቆሙት ማንነት ነው።
ኢትዮጵያዊነት ከግላዊነት የራቀ ማህበራዊ ፍቅር ወይም ከራስ ወዳድነት የተለየ የወገን ተቆርቋሪነት ነው። ቁጥብነትን፤ ጨዋነትንና ግብረ ገብነትን መከተሉ፣ ለቃሉ መታመንና አደራ ጠባቂነትን ማንገሱ ቀናነትንና የልብ ንፅህናን ማክበሩ ልዩ ያደርገዋል። አትዮጵያዊነት ክብር እና ፀጋ ያልተለየው የትህትና መንፈስ ነው። ኢትዮጵያዊነት የሠከነ ስሜት የነቃ ህሊና ነው።
ኢትዮጵያዊነት የማንነት ፍልስፍና ባለፈውን ተንተርሶ ወደፊት የሚመጣውን እጣፈንታ ተስፋ የሚያደርግ ማህበረሰብ፣ ረጅም ርቀት በመጣ ታሪካዊ መስተጋብር ያዳበሩት ቤተሰባዊ ስነልቦና፣ ራሳቸውን ከሌሎች የሚለዩበትና የሚታወቁበት ማህበራዊ እና ህሊናዊ ድንበር ነው። ነገዳዊ፤ እምነታዊ ብሄራዊ የመሳሰሉ…… የተለያዩና የተሳሰሩ ድሮችን አካትቶ በዘመናት የተሸመነ ባለህብረ ቀለም ካባ ነው። የአገር ፍቅር የማንነት ክብር፤ አርበኝነት፤ በሚልም ሊገለጽ ይችላል።
ታድያ በፈጣሪ ጸጋ የተሰጠንን ከጥንት ከአባቶቻችን ጀምሮ የተቀበልነውን ክቡሩን ማንነት፤ ውዱን ስነልቦና ዘመናዊነት ይሉት ነገር ባመጣብን ጣጣ አደባባይ ላይ ልናዋርደውና ሸቀጥ ልናደርገው አይገባም። በአሁኑ ወቅት በስርአት፣ በእምነት በባህል ታቅፎ እዚህ የደረሰን ማንነት የሚያጠፋ፣ የሚበርዝ፣ የሚያቃልል አፀያፊ ተግባር በየሶሻል ሚዲያው እያየን እንገኛለን። በቲክቶክ፤ ዩቲዩብ፤ ፌስቡክ፤ ኢንስታግራም በነዚህና በመሳሰሉት ፕላት ፎርሞች የሚታየው ነገር በእውነት ኢትዮጵያዊነትን አይመጥንም።
ሴትነት ክብር አጥቶ፣ ፆታ የሚባለው ነገር ጭራሹኑ ጠፍቶ ሰውነት ቀሎ ነው የምንመለከተው። እንደሚታ ወቀው ሶሻል ሚዲያ የሚጠቀመው አብዛኛው ወጣቱና ታዳጊው የማህበረሰብ ክፍል ነው። እናም በየሶሻል ሚዲያው የሚያጋሩት ምስልም ሆነ ቪድዮ በጣም የሚያሳዝን ከመሆኑም ባሻገር ወዴት እየሄድን ነው፤ ባህል ስርአት ክብር የሚባለው ነገር የት ደረሰ? የሚያሰኝ ነው። ሴቶቹ የሚያሳዩት ምስልና ቪድዮ እርቃናቸውን በጡት መያዣና በፓንት ያልተገቡ እንቅስቃሴዎች እያሳዩ ነው። አንዳንዶቹ የጡት መያዣን ትተውታል። የሴት ልጅ ክብርን በማይመጥን መልኩ ወሲብ ቀስቃሽ እንቅስቃሴዎችን ያደርጋሉ።
ሴቶቹ የጡትና የመቀመጫ ውድድር ያለ እስኪመስል ድረስ እርቃናቸውን የሚያሳይ ቪድዮ ያጋራሉ። እውነቱን ለመናገር በኢትዮጵያዊ ባህል ላደገ ሰው እንደዚህ አይነት ስርአት ያልጠበቀ መረን የለቀቀ ነገር መመልከት የሚከብድ ነው። የወጣቱ እንቅስቃሴው ወሬው ሁሉ ወሲብ ብቻ ሆኗል። በድፍረት መናገር ይቻላል፤ ሴሰኛ ትውልድ እየተፈጠረ ነው። ኢትዮጵያዊነት ጥያቄ ውስጥ ገብቷል። በእውነቱ ከሆነ ሚዲያ ላይ ወጥቶ እርቃንን ማሳየት እውቀትም ጥበብም የሚጠይቅ ጉዳይ አይደለም ፤ ትንሽ ክብርን መጣል ቢጠይቅ እንጂ። ታዲያ ትልቅ ቁምነገር እንደሰራ፣ ለትውልድ የሚጠቅም፣ ለአገር የሚተርፍ ጀብድ እንደፈፀመ ሰው እርቃንን እያሳዩ ቪድዮ በመስራት የሚገኝ ዝናም ሆነ እውቅና የለም። ለሰዎች የጥቂት ቀናት የብልግና ምሳሌ ከመሆን በቀር።
በመሰረቱ ልብስ ያስፈለገው እርቃን መሆን ተገቢም አስፈላጊም ስላልሆነ ነው። የአብዛኞቻችን ኢትዮጵያውያን የህይወት መመሪያ የሆነው መጽሀፍ ቅዱስ ወይም ቁርዓን ሴት ልጅ መከናነብ እንዳለባት ይናገራል። እንደው መከናነቡ ቢቀር እርቃን መሆንን ምን አመጣው። በየሶሻል ሚዲያው ያለውን ቪዲዮ የሚመለከተው ሰው እርቃናቸውን አደባባይ ለሚያሳዩ ሴቶች የሚያድርበት ክብር ሳይሆን ንቀት ነው።
መሸፈን የሚገባውን ነገር፤ በጣም ግላዊ የሆነውን ነገር ለአደባባይ ማቅረብ ለሸቀጥ፤ ለሽያጭ ማቅረብ ማለት ነው። ገበያ የወጣ ነገር ደግሞ የፈለገው ሁሉ በገንዘብ ይገዛዋል። እንደፍላጎቱ ያደርገዋል። እነሱ ክብሬን አልፈልገውም ቢሉ እንዴት ለቤተሰባቸው ማሰብ ያቅታቸዋል? ። ቤተሰብ ሲመሰርቱ ለልጆቻቸው የሚያስቀምጡት ታሪክስ ምንድነው? ምስል፤ ቪዲዮ ታሪክ ነው ፋይል ተደርጎ ነው የሚቀመጠው። ይህንን አርቆ ማሰብ እንዴት ያቅታል። አሁን እያደረጉት ያለው ነገር ከሆነ ወቅት በኋላ ሲያዩት ሊፀፀቱ እንደሚችሉ እርግጠኛ ነኝ። የእውነት በጣም አሳፋሪ ነገር ነው። ምንም ያህል ዘመንን ብንል መጨረሻ ላይ ኢትዮጵያውያን ነን። በባህል ድር እና በእምነት ማግ ታስረን ያደግን የኖርን።
ሊሸፈኑ የሚገባቸው የሰውነት ክፍሎቻቸው ላይ ንቅሳቶችን በማድረግ ከእኛ ባህልና ወግ ውጪ የሆኑ ድርጊቶችን የሚፈጽሙ ወጣቶች ተፈጥረዋል። በዚህ ግዜ ስማርት ስልክ የማይጠቀም ታዳጊ የለም። ሶሻል ሚዲያ የማይጠቀም ወጣት የለም። በመሆኑም ይህ ከባህልም፣ ከእምነትም፣ ከኢትዮጵያዊነትም ያፈነገጠ ስራቸው እነዚህ ታዳጊዎችን እየመረዘ ነው ያለው። እነዚህ ወጣቶች ቪዲዮውን በተደጋጋሚ በሚያዩበት ወቅት እንደዛ የማድረግ ፍላጎት ውስጥ ይገባሉ ትክክለኛ አግባብ (ኖርማል) ነገር ይመስላቸዋል። እለት እለት የሚያዩት ነገር በመሆኑ ትልቅ ተጽእኖ ውስጥ ነው የሚገቡት። ከባህላቸው ከማንነታቸው ያወጣቸዋል።
እነዚህ ሰዎች በኢትዮጵያ ባህል፡ ነውር፣ የማይገቡ የምንላቸው ነገሮችን አቅልለው ማቅረብ (normalize) እያደረጉ ነው ያሉት። ከትንሽ ጊዜ በኋላ እርቃን መሆን የተለመደ (normal) ይሆናል። ሴሰኝነት ይነግሳል። ይኼነው እንግዲህ ትልቁ ኪሳራ። ይህ የጥቂት ወጣቶች ጉዳይ ብቻ አይደለም፤ ይህ የትውልድ መጥፋት ጉዳይ ነው። ይህ የነገዋ ኢትዮጵያ ጉዳይ ነው። እንግዲህ አገር የሚረከበው ይሄ ትውልድ ነው። በሴሰኝነት ልቡ የናወዘ በሱስ አእምሮውን የሣተ ትውልድ።
በሶሻል ሚዲያው ሴቶቹ በእርቃንነት አባዜ ሲናውዙ፣ ወንዶቹ ደግሞ የተለያዩ ሱሶችን ፕሮሞት (ማስተዋወቂያ) አድርገውታል። ጭሣጭሶችን መጠቀም እንደዘመናዊነት ተቆጥሯል። ግብረገብነት የሚባል ነገር ጠፍቷል፣ ከሰዎች ጋር የሚኖረንን ግንኙነት ስርአት የሌለው ክብር የጎደለው የሚያደርግ አስተምህሮ ይዘው መጥተዋል። ሌላው ደግሞ በተለይ በአሁኑ ሰአት በጣም እየጎላ እና እየገነነ የመጣው በተለይ ደግሞ በሶሻል ሚዲያው በስፋት ለማንፀባረቅ እየተሞከረ ያለው። የግብረሰዶማውያን ተግባር ነው።
ኢትዮጵያውያን ናቸው ወይ በሚያስብል ደረጃ ግብረሰዶማዊነት ሲያስፋፉ፣ ሲደግፉ አልፎም ተርፎም የግብረሰዶማውያን መብት ተሟጋቾች ነን የሚሉ አካላት ተነስተዋል። ከአለምአቀፍ ድርጅቶች ጋር በመሆን እንዴት ግብረሰዶማዊነትን ኢትዮጵያ ውስጥ ህጋዊ ማድረግ እንደሚችሉ በግልጽ ይወያያሉ። የበለጠ የሚያሳዝነው ደግሞ እዚሁ ኢትዮጵያ ውስጥ የሚኖሩ ግብረሰዶማውያን ቪድዮ እየሰሩ በነጻነት ነው የሚለቁት። የግብረሰዶማውያን የቀለበት ስነስርአት ሁሉ በቪዲዮ ማየት ደረጃ ላይ ደርሰናል። ይህ የማንነት ዝቅጠት የስነልቡና ቀውስ ነው። ለወንድ ባህሪ የሚገባው ሴት ናት፤ ለሴት ባህሪ ደግሞ የሚገባው ወንድ ነው። ይህንን የተፈጥሮ ህግ በመጣስ ለባህሪያቸው የማይገባውን ነገር ማድረጋቸው ሳያንስ ይህንን ድርጊታቸውን ደግሞ በሚዲያ ያሳዩናል አስተሳሰባቸውን ሊጭኑብን ጥረት እያደረጉ ነው።
በአሁኑ ሰአት ከመደበኛ ሚዲያው ይልቅ በእጅ ስልኮቻችን ላይ በምናገኘው ሶሻል ሚዲያ ሁሉንም ነገር ይፋ ወጥቷል። ከተፈጥሮም፤ ከሀይማኖትም፤ ከባህልም ውጪ የሆነ ነገር በመሆኑ መቼም ልንቀበለው እንደማንችልና፣ እንደማይገባ ግንዛቤ ማስጨበጥ የሚገባበት ጊዜ አሁን ነው።
ቲክቶክ የሚባለው ፕላትፎርም ላይ ላይቭ ስትሪም (የቀጥታ ስርጭት) የሚባል ፕሮግራም አለ። ሰዎች ተሰባስበው የተለያዩ ጉዳዮችን እያነሱ የሚወያዩበት ፕሮግራም ነው። መልካም እና ገንቢ የሆኑ ሀሳቦችን እያነሱ የሚወያዩ ሰዎች ቢኖሩም፣ አብዛኛውን ጊዜ ለዛ ቢስ የሆኑ ጨዋታዎችን የሚጫወቱበት፣ ጥያቄ ተጠያይቀው ትእዛዝ መታዘዝ ነው። ትእዛዙ ደግሞ መረን የለቀቀ አፀያፊ፣ ይሉኝታ፣ ክብር የሚባለውን ነገር አሽቀንጥሮ የጣለ ነገር ነው የሚያደርጉት። አንዲት በውጪ አገር የምትኖር የሶሻል ሚዲያ ተጽእኖ ፈጣሪ (influencer) የሆነች ሴት (እናት) በአንድ ቡድን ቀጥታ ፕሮግራም ላይ ተገኝታ ስትናገር የነበረው ነገር በጣም አሳዛኝ ነበር። ቪድዮው የግብረሰዶማውያን አባላት በቀጥታ ስርጭት ተሰባስበው፣ መብታችን ነው የሚሉትን ነገር እንዴት ማስፋፋት እንደሚችሉ፣ የሚወያዩበት ፕሮግራም ነበር ።
ይህቺ ሴት በቀጥታ ስርጭት ገብታ የምትናገረው ከአንዲት ኢትዮጵያዊ ሴት አንደበት የሚወጣ አይመስልም። ስለስነምግባር፤ ስለልጆች የወደፊት ህይወት ብሎም ስለ ቀጣይ የአገሪቱ መጻኢ ዕድል የምትጨነቅ ሴት አይደለችም። በጓዳ የሚነገረውን ሁሉ በአደባባይ እንደመጣላት ትዘረግፈዋለች። ይባሱን ብሎም የተሰበሰቡትን ወጣቶች በሷ ጋጠ ወጥ መንገድ እንዲጓዙ ትመክራለች፤ ታበረታታለች።
ከአንዲት ኢትዮጵያዊት እናት እንደዚህ አይነት ንግግር መስማት እጅግ ከባድ ነው። በጣም የሚከፋው ደግሞ ይቺ ሴት ሌሎችም ማህበራዊ፤ ፖለቲካዊ፤ ሀይማኖታዊ እና በማናቸውም ወቅታዊ ጉዳዮች ላይ አስተያየት የምትሰጥ፤ ሀሳቦችን የምታነሳ፤ በብዙዎች የምትታወቅ፤ ብዙ ተከታዮች ያሏት መሆኗ ነው።
ሶሻል ሚዲያ ያላመጣብን ነገር የለም። በነገሬ ላይ ሶሻል ሚዲያውን ለበጎ ተግባር፣ ለቅዱስ አላማ የሚያውሉ፣ ቢዝነስ አድርገውት ብዙ ስራዎችን እየሰሩ: በኢኮኖሚ ከቤተሰብ ተላቀው ራሳቸውን ለመቻል ጥረት የሚያደርጉ ልጆችን፣ ሰዎችን ሳላመሰግን እና ሳላከብር አላልፍም። ነገር ግን የዚህ ፅሁፍ አላማ ሶሻል ሚዲያውን ለእኩይ አላማ የሚጠቀሙትን መገሰጽ እና በዚህ አጀንዳ ዙሪያ ግንዛቤ መስጠት ነው።
ጉዳዩን ማለባበስ ከመባባስ፣ ከመስፋፋት አላገደውም። በዚህ አጀንዳ ላይ በተለይ ደግሞ ቤተ-እምነቶች ላይ ትልቅ ስራ ሊሰራ ይገባል። ሁሉም ቤተ- እምነቶች ይህንን የተወገዘና ርኩስ፣ ከተፈጥሮ ውጪ የሆነ ድርጊት ማውገዝ አቋማቸውንም ማሳወቅ አለባቸው። ምን ያህል ከእምነትም ከተፈጥሮም ውጪ የሆነ ተግባር እንደሆነ ተከታዮቻቸውን ማስረዳት አላባቸው። የዚህ ምግባር ባለቤቶችም የራሳቸው የሆነ ምልክት፣ በአለባበሳቸው፣ ሰውነታቸው ላይ በሚያደርጓቸው ነገሮች፣ እንቅስቃሴዎች ማወቅ እንደሚቻልና ከነዚህ ሰዎች ራሳችንን የመጠበቅን አስፈላጊነት በአጽንኦት ማስተማር ይገባቸዋል።
እዚህ አጀንዳ ውስጥ የሚገቡ ሰዎች በማወቅም ይሁን ባለማወቅ ይሆናልና፣ ከገቡበት የማንነት ቀውስ እንዲወጡ አካላዊ ህክምናም ይሁን የስነልቦና ህክምና የሚያገኙበትን መንገድ ማመቻቸት ትክክለኛ ወደሆነው ማንነታቸው እንዲመለሱ መርዳት ይገባናል። የጤና ባለሙያዎችም በዚህ አጀንዳ ላይ ትልቅ ድርሻ ሊኖራቸው ይገባል። በጤና ላይ ስለሚያመጣቸው አካላዊና ስነልቦናዊ ችግሮች ማስተማር ተገቢ ነገር ነው።
ማህበራዊ ሚዲያ በአገራችን ብጥብጥና ሁከት እንዲፈጠር ዋነኛ መሳርያ እየሆነ ከመምጣቱም በሻገር አገራዊ ዕሴቶቻችንም እያጠፋና በምትኩም ፀያፍ የሆኑ መጤ ባህሎችን እያስፋፋ ይገኛል። ማህበራዊ ሚዲያ ምን ያህል ትውልድን የመቅጨት ኃይል እንዳለው እያየን እንገኛለን። በመሆኑም የሚመለከተው ሁሉ በዚህ ጉዳይ ላይ የአቅሙን ብቻ ሳይሆን ከአቅሙ በላይ የሆነውን ሁሉ ማድረግ አለበት ምክንያቱም ይህ የማንነት ጉዳይ ፤ ሰው የመሆን ጥያቄ ነው።
ኢትዮጵያዊነት ርኩሰት የሌለበት ቅድስና ነው። ሀበሻ ትክክል የመሆን ፍቅር ልበ ሰፊነት፣ ለትኩረት፤ አንክሮና ተዘክሮ ያለው ልዩ ቦታ፤ የነግ በኔ ፍቅሩ ፤ አስተዋይነቱና ፤ አርቆ አሳቢነቱ ናቸው መገለጫዎቹ። በመሆኑም እኛ ስንኖር ኢትዮጵያዊ ስንሞት ኢትዮጵያ ነን። ሌላ የምናመጣው ማንነት የምንጨምረው ትርክት የለንም። የኢትዮጵያ ህዝብ ክርስቲያኑም ሙስሊሙም ሌላውም የስልጣን ምንጭ የመኖር ፀጋ ባለቤት፤ እንደየባህሉ እንደየቋንቋው በሰጠው ስም እግዚአብሄር መሆኑን ያምናል። በመሆኑም ፈጣሪ የሰጠንን ተፈጥሮም ጾታም አክብረን ወደን የምንኖር ፈሪሀ እግዚአብሔር ያለን ጨዋ ህዝቦች ነን። በዚህ ጉዳይ ላይ ያለንን ተቃውሞ በምንኖርበት ቦታ፡ በስራ አከባቢያችን፡ በቤተ እምነታችን ልናሰማና ልናወግዘው ይገባል። ሰላም
በአክበረት ታደለ
አዲስ ዘመን ሐምሌ 22/2022