
‹‹ወያኔ ዛፍ››ን በግብዓትነት የሚጠቀም ፋብሪካ ወደሥራ ገብቷል
አዲስ አበባ፡- እንቦጭን በመመገብ ማጥፋት የሚችል የእንጉዳይ ዝርያ በምርምር መገኘቱን የኢትዮጵያ ደን ልማት አስታወቀ፡፡
በተለምዶ የወያኔ ዛፍ የሚሰኘውንና በሳይንሳዊ አጠራሩ ‹‹ፕሮሶፒስ›› የተባለውን የዕፅዋት ዝርያ ለጣውላ፣ ለፐርኬ፣ ለቤት ግንባታና ለተለያዩ አገልግሎቶች እንዲውል የሚያግዝ ፋብሪካ ሥራ መጀመሩን ተቋሙ አስታውቋል።
በኢትዮጵያ ደን ልማት የደን ውጤቶችና ኢኖቬሽን ዳይሬክቶሬት ዳይሬክተር አቶ ዳንኤል ገበየሁ በተለይ ለኢትዮጵያ ፕሬስ ድርጅት እንደገለፁት፤ እንቦጭ አረምን ለማጥፋት ብዙ ጥረትና ምርምር ሲደረግ ቆይቷል። በአሁኑ ወቅት እንቦጭን በመመገብ የሚያጠፋ እንጉዳይ ዝርያ በምርምር ተገኝቷል፡፡ የምርምር ውጤቱ የእንቦጭ አረምን ለማጥፋት ይረዳሉ ተብለው ለመፍትሔነት ከቀረቡ አማራጮች መካከል አንዱ ነው።
በምርምሩ መሠረት እንቦጭ ያለበት ቦታ ላይ እንጉዳዩ እንዲዘራ ይደረጋል ያሉት ዳይሬክተሩ፤ እንጉዳዩ ሲበቅል እንቦጭን እንደ ምግብ በመጠቀም የሚያድግ ይሆናል፤ በዚህ ሂደት እንጉዳዩ ለሰው ልጆች ምግብነት የሚውል ሲሆን፤ እንቦጩ ደግሞ እየጠፋ ይሄዳል ብለዋል፡፡

ተቋሙ የእንጉዳይ ምርት ላይ የተለያዩ ምርምሮችን እያደረገ መሆኑን አቶ ዳንኤል ገልጸው፤ በቀጣይ ጊዜያትም የሚገኙ የምርምር ውጤቶችን በሰፊው ጥቅም ላይ ለማዋል ጥረት እንደሚያደርግ ጠቁመዋል።
ከዚህ ባለፈ ተቋሙ መጤ አረሞችን ወደ ጥቅም ሰጪ ነገር ለመቀየር የተለያዩ ምርምሮችንና የቴክኖሎጂ አማራጮችን ጥቅም ላይ ለማዋል እየሠራ እንደሚገኝ ተናግረዋል፡፡
አቶ ዳንኤል እንዳስታወቁት፤ የወያኔ ተክል በአፋርና ሱማሌ ክልሎች አንድ ነጥብ ሁለት ሚሊዮን ሄክታር መሬት ላይ ተንሰራፍቷል። ስርጭቱን ሙሉ ለሙሉ መግታት ወይንም ደግሞ ስርጭቱን በሂደት ማቆም ያስፈልጋል፡፡
ይህ የዛፍ ዝርያ በአርብቶ አደርነት የሚተዳደረውንና የአፋር እና ሱማሌ ክልል ማኅበረሰብ ላይ ከፍተኛ ተፅዕኖ እየፈጠረ ሲሆን፣ በወተትና ሥጋ ምርት ላይም አሉታዊ ጫና አሳድሯል፡፡ በእነዚህ አካባቢዎች የሳር ግጦሽ ወሳኝ ሲሆን፤ ይህ አረም ግን ሳር፣ ቅጠላ ቅጠልና ሌሎች የዕፅዋት ዝርያዎች እንዲጠፉ እያደረገ ነው ብለዋል፡፡
ከዚህም በተጨማሪ የከርሰ ምድር ውሃን በከፍተኛ ሁኔታ ስለሚመጥና ከፍተኛ ትነት በመኖሩ የሥነ-ምህዳር መዛባትን እያስከተለ መሆኑን አስረድተዋል፡፡
የወያኔ ተክልን እየተጠቀሙ ማጥፋት የሚለው መርህ ትኩረት ተደርጓል ያሉት አቶ ዳንኤል፤ አረሙን ሙሉ ለሙሉ ለማጥፋት ባይቻልም እንኳን ባለበት ለመቆጣጠር ተክሉን ለጣውላ ምርትነትና ለከሰል ምርት ለማዋል የሚደረገውን ጥረት ተቋሙ እየደገፈ መሆኑን ገልጸዋል።
በተለያዩ አካባቢዎች እየተስፋፋ የመጣውን በተለምዶ “ወያኔ” ዛፍ የሚባለውን በሳይንሳዊ አጠራሩ ‹‹ፕሮሶፒስ›› የተሰኘውን ተክል ለፋብሪካ ግብዓት እንዲውል ተደርጓል።
ወያኔ ዛፍን ለጣውላ፣ ለቤት ግንባታና ለተለያዩ አገልግሎቶች እንዲውል የሚያደርግ ፋብሪካ ሥራ ጀምሯል።
የወያኔን ዛፍ በዘመናዊ መንገድ ወደ ከሰልና አማራጭ ኢነርጂ በመቀየርም ጥቅም ላይ ማዋል ይቻላል ያሉት አቶ ዳንኤል፤ ለዚህም በአፋር ክልል አሚባራ ወረዳ ፋብሪካ ተቋቁሞ ወጣቶችም ተደራጅተውና ስልጠና ወስደው ወደ ሥራ መግባታቸውን አረጋግጠዋል፡፡
ክፍለዮሐንስ አንበርብር
አዲስ ዘመን ሐምሌ 13 ቀን 2014 ዓ.ም