
አዲስ አበባ፡- በኮቪድ የተቀዛቀዘው የሆቴል ዘርፍ በመንግሥት ጥረት መነቃቃት እየታየበት መሆኑን የአዲስ አበባ ከተማ የባህልና ኪነጥበብ ቱሪዝም ቢሮ አስታወቀ። በግራንድ ኤልያና ሆቴል የተዘጋጀውና ለሁለት ቀናት የሚቆይ ባዛር በኤልያና ሆቴል ተከፍቷል።
የአዲስ አበባ ከተማ የባህልና ኪነጥበብ ቱሪዝም ቢሮ ኃላፊ ዶክተር ሂሩት ካሳው የሆቴል ግብአት አቅራቢዎች ባዛር ትናንት ሲከፈት እንደገለፁት፤ በኮቪድ 19 ወረርሽኝ ምክንያት መቀዛቀዝ የታየበት የሆቴል ቱሪዝም ዘርፍ መንግሥት ባደረገው ያላሰለሰ ጥረት በዘርፉ ሕይወት መዝራት ተችሏል።
ባለፉት አስር ዓመታት የሆቴል ቱሪዝም ዘርፉ ከፍተኛ እድገት ማሳየቱን ያወሱት ኃላፊዋ፤ በተቃራኒው ባለፉት ሁለት ዓመታት ዘርፉ በኮቪድ 19 ወረርሽኝ ምክንያት መቀዛቀዝ ቢያሳይም መንግሥት የተለያዩ መውጫ መንገዶችን በመፈለግና በመተግበር የሆቴል ዘርፉ በአጭር ጊዜ መነቃቃት ማሳየት መቻሉን ገልጸዋል።
የሆቴል ግብአት አቅራቢዎች ባዛርና ኤክስፖዎች በሆቴልና ቱሪዝም ዘርፉ ላይ አዲስ አበባን የቱሪስት መዳረሻ በማድረግ ሂደት ላይ ሚናቸው የጎላ ነው ሲሉም ዶክተር ሂሩት ተናግረዋል።

የግራንድ ኤልያና ሆቴል የሰው ኃይል አስተዳደር የሆኑት ወይዘሮ ምሥራቅ ሞገስ በበኩላቸው እንደገለፁት፤ ባዛሩ በኮቪድ 19 ወረርሽኝ ምክንያት የተቀዛቀዘውን የሆቴል ቱሪዝም ዘርፍ ለማሳደግና ለማነቃቃት ከፍተኛ አስተዋጽኦ አለው። ባዛሩ የኅብረተሰቡን አቅም ባገናዘበ ሁኔታ ምርት እና አገልግሎትን በአንድ ቦታ እንዲያገኙ በማድረግ አቅራቢውን እና ሸማቹን በቀላሉ የሚያገናኝ ነው።
በዓለማችን የሚገኙ ሆቴሎች ለተለያዩ ሥራዎች የሚሆኑ አልግሎቶችን እና ግብአቶችን ከፍተኛ የውጭ ምንዛሪን በማውጣት አገርን በተለያየ አላስፈጊ ወጪ እንደሚዳረጉ የገለፁት ወይዘሮ ምሥራቅ፤ ባዛሩ አገር ውስጥ ያሉ የሆቴል አቅራቢዎችን ከሆቴሎች ጋር በማገናኘት እየባከነ ያለውን ምንዛሬ ከመተካት አንፃር ጉልህ ሚና የሚጫወት እንደሆነም ገልፀዋል።
ባዛሩ የሆቴል ግብአት አቅራቢዎች፣ የንግዱ ማኅበረሰብ፣ ባለድርሻ አካላትና ከፍተኛ የመንግሥት የሥራ ኃላፊዎች በተገኙበት ተከፍቷል። ግራንድ ኤልያና ሆቴል በከተማችን ካሉ ባለ አራት ኮከብ ሆቴሎች አንዱ ሲሆን የቱሪዝም እድገትን እያሳደጉ ከሚገኙ ሆቴሎች መካከል ሰፊውን ድርሻ ይዞ በመሥራት ላይ እንደሚገኝ በመድረኩ ተመላክቷል።
ዳግማዊት ግርማ
አዲስ ዘመን ሐምሌ 13 ቀን 2014 ዓ.ም