
ድሬዳዋ፡- ለኢንዱስትሪዎች ቀጣይነት ያለው ውጤታማነት አረንጓዴ አሻራን ከኢንዱስትሪ ልማት ጋር አጣምሮ መሥራት እንደሚገባ የኢንዱስትሪ ሚኒስቴር ገለፀ፡፡
የኢንዱስትሪ ሚኒስቴር የ2014 በጀት ዓመት ዕቅድ አፈፃፀም እና የ2015 የዕቅድ መነሻ ውይይት በትናንትናው ዕለት ተጠናቋል፡፡
ሚኒስቴሩ ከክልል እና ከከተማ አስተዳደር ኢንዱስትሪ ቢሮዎች ጋር በመሆን በድሬዳዋ የሚገኙ ኢንዱስትሪዎችን በመጎብኘት በድሬዳዋ ኢንዱስትሪ ፓርክ የአራተኛው አረንጓዴ አሻራ የችግኝ ተከላ መርሃግብር አከናውኗል፡፡
የኢንዱስትሪ ሚኒስቴር ሚኒስትር ዴኤታ አቶ ሽሰማ ገብረሥላሴ፤ አራተኛው የአረንጓዴ አሻራ ፕሮግራም በሁሉም አካባቢዎች ከሁሉም ሥራዎቻችን ጋር አስተሳሰረን የምንፈፀመው ተግባር ነው ብለዋል፡፡ በዘንድሮው ዓመት የአረንጓዴ አሻራ መርሃግብር በአገሪቱ በሚገኙ ኢንዱስትሪ ፓርኮች እና በሌሎችም አካባቢዎች 100 ሺህ ችግኞች ለመትከል አቅደው እየሠሩ መሆኑን ተናግረዋል፡፡
በዚሁ ዓመት የአረንጓዴ አሻራ መርሃግብር በቂሊንጦ ኢንዱስትሪ ፓርክ፤ በደቡብ ክልል ሃድያ ዞን እንዲሁም በትናንትናው ዕለትም ሦስተኛውን ዙር በአዳማ ኢንዱስትሪያል ፓርክ ግቢ ውስጥ ማከናወናቸውን ገልፀው፤ ለኢንዱስትሪዎች ዘላቂነት ያለው ዕድገት ለማምጣት እና በዓየር ንብረት ለውጥ የማይናጋ ኢኮኖሚ ለመፍጠር የአረንጓዴ አሻራ መርሃግብርን መተግበር የውዴታ ግዴታ መሆኑን አብራርተዋል፡፡
አረንጓዴ ልማት ከኢንዱስትሪው ዘርፍ ተነጥሎ የሚታይ አይደለም ያሉት አቶ ሽሰማ፤ አብዛኞቹ ኢንዱስትሪዎች የግብርና ምርትን እንደ ግብዓት የሚጠቀሙ እንደመሆናቸው መጠን በአረንጓዴ አሻራ ላይ የሚሠራው ሥራ ኢንዱስትሪው በቂ ግብዓት እንዲያገኝ እንደሚረዳው ገልፀዋል፡፡
ሌላው የኢንዱስትሪ ሚኒስቴር ሚኒስትር ዴኤታ አቶ ታረቀኝ ቡሉልታ በበኩላቸው፤ የ2014 በጀት ዓመት የኢንዱስትሪ ሚኒስቴር አፈፃፀም የተሻለ እና ተስፋ ሰጪ ጅምሮች የታዩበት ነው፡፡ ይህ ጅምር ቀጣይ ሊሆን የሚችለው ከኢንዱስትሪዎች የሚወጡ በካይ እና ሙቀት አማቂ ጋዞችን መጥጠው የሚያስቀሩ እና የዓየር ንብረት እንዳይዛባ ማድረግ የሚችሉ ዛፎችን ማልማት ስንችል ነው ብለዋል፡፡

ከአረንጓዴ የኢንዱስትሪ ልማት አኳያ የችግኝ ተከላው ትልቅ ትርጉም የሚሰጠው ነው ያሉት አቶ ታረቀኝ፤ ከኢንዱስትሪዎች የሚወጣውን ካርበን መከላከል የሚቻለው ዛፎችን በመትከል ነው፤ በቀጣይም በሁሉም ኢንዱስትሪ ፓርኮች እና ሌሎች አካባቢዎች ጭምር የችግኝ ተከላ መርሃግብር በማካሄድ ዘላቂነት ያለው የኢንዱስትሪ ልማትን ለማረጋገጥ እንሠራለን ሲሉ ገልፀዋል፡፡
የሲዳማ ብሔራዊ ክልላዊ መንግሥት ንግድና ኢንዱስትሪ ቢሮ ኃላፊ አቶ አሻግሬ ጀምበሬ፤ የኢንዱስትሪዎች ቀጣይነት ያለው ውጤታማነትን ለማረጋገጥ የአረንጓዴ አሻራ መርሃግብር ቁልፍ ሚና ይጫወታል ብለዋል፡፡
አረንጓዴ አሻራ ሥራ በአገራችን ፈርጀ ብዙ ጠቀሜታ ያለው ነው የሚሉት አቶ አሻግሬ፤ ኢንዱስትሪዎች በብቁ ሁኔታ አምርተው ውጤታማ የሚሆኑት የተስተካከለ የዓየር ንብረት ሲኖር ነው ሲሉ ገልፀዋል፡፡
እንደ አቶ አሻግሬ ገለፃ፤ ለዓየር ንብረት ለውጥ ተፅዕኖ የማይበገር ኢኮኖሚ ለመገንባትም የአረንጓዴ አሻራ መርሃግብር የማይተካ ሚና ስላለው የኢንዱስትሪ ልማትን ለማፋጠን በሚታሰብበት ጊዜ ሁሉ አረንጓዴ አሻራ ጋር አጣምሮ መሥራት ያስፈልጋል፡፡
ውብሸት ሰንደቁ
አዲስ ዘመን ሐምሌ 13 ቀን 2014 ዓ.ም