
አዲስ አበባ፡- የኢትዮጵያን ሁለንተናዊ ብልጽግና ለማረጋገጥ ኢኮኖሚያዊ አቅማችንን በዘላቂነት ማጠናከር እንደሚገባ የሥራና ክህሎት ሚኒስትር ወይዘሮ ሙፈሪሃት ካሚል ገለጹ፡፡
ወይዘሮ ሙፈሪሃት ካሚል የኢትዮጵያ ፕሬስ ድርጅት በጅማ ከተማ ባዘጋጀው ‹‹ስለኢትዮጵያ›› የውይይት መድረክ ላይ እንደገለጹት፤ ኢትዮጵያ ለዘመናት ነፃነቷ አስከብራ ኖራለች፡፡ ነፃነቷ የተሟላ እንዲሆን ደግሞ ኢኮኖሚያችንን በዘላቂነት አሳድገን መጓዝ ይኖርብናል።
ኢትዮጵያ ጠንካራ ኢኮኖሚዊ አቅም እንዲኖራት ስለሥራ፣ ብሩህ ሀሳብና ክሒሎት እንዲሁም ስለምርታማነት ይበልጥ ማሰብ ይገባናል ያሉት ሚኒስትሯ፤ የኢኮኖሚ ነፃነቱ ስር እንዲሰድ በልቶ ከማደር የሚሻገር ጠንካራ ሥራ ይጠይቀናል ሲሉ ተናግረዋል።
ኢትዮጵያን ዓለም ላይ ካሉ 20 ባለጠንካራ ኢኮኖሚ አገራት ውስጥ እንድትገባ የማድረግ የረጅም ጊዜ ትልም እንዳለ አስታውሰው፤ ለዚህም የአገር በቀል ኢኮኖሚን በተከተለ መንገድ በግሉና በመንግሥት ተሳትፎ ኢንቨስትመንትን የማስፋፋትና የሥራ ዕድል ፈጠራን የማሳደግ ተግባራት እየተከናወኑ መሆኑን ጠቁመዋል።
ኢትዮጵያ በተለያዩ ፈተናዎች ውስጥ ብትሆንም ጥቅም ላይ ያልዋሉ ዕምቅ ሀብትና የኢኮኖሚ አማራጮች እንዳሏት የጠቆሙት ሚኒስትሯ፤ ዕምቅ ሀብታችንን ተገቢው ጥቅም ላይ በማዋል በዘላቂነት የኢኮኖሚ ገቢያችንን ማሳደግ ይገባል ብለዋል።
ኢኮኖሚው ትልቅ አገራዊ፣ ቀጣናዊና ዓለም አቀፋዊ ዕድሎች እንዳሉት አመልክተው፤ ዕድሎቹን አሟጦ በመጠቀም በኩል ግን ያሉትን ክፍተቶች ማስተካከል እንደሚገባ ተናግረዋል፡፡
ለአብነት የግብርናው ክፍለ ኢኮኖሚ 44 በመቶ የሥራ ዕድል እንዲፈጥር ቢጠበቅም የእስካሁን አፈጻጸሙ
ግን ከ26 በመቶ ያልዘለለ ነው፡፡ ኢንዱስትሪውም ከ50 በመቶ በታች በሆነ አቅም እያመረተ ነው ብለዋል፡፡
በመሆኑም ዕድሎችን በአግባቡ ለመጠቅምና አገራዊ ትልሞችን ለማሳካት ተጨማሪ ጥረት እንደሚያስፈልግ ጠቁመዋል።
በተጨማሪ ኢኮኖሚያዊ ነፃነታችንን ዘላቂነት እንዲኖረው በሕግ የታገዘና የሠራተኛን አቅም የሚያሳድግ አሠራር መፍጠር ይኖርብናል ሲሉ ገልጸዋል።
አሁን ላይ ግን ሕጎቻችን ጉልበታቸው የሚለካው በመቆለፍ አቅማቸው እንጂ ምቹ ሁኔታ በመፍጠር አይደለም ያሉት ወይዘሮ ሙፈሪሃት፤ ይህንን ለመፍታትና አዳዲስ ሥራ ፈጣሪዎችን ወደ ገበያው ለማስገባት የሚረዳ የሕግ ዝግጅት መደረጉን ጠቁመዋል።
ከዚህ ባለፈ ኢኮኖሚው በዘላቂነት እንዲያድግ የአምራች ኃይሉን አቅም ማጠናከር ይገባል፤ በዚህ ረገድ መንግሥት ትኩረት አድርጓል ሲሉ ተናግረዋል።
በተለያዩ ያደጉ አገራት የአብዛኛው ዜጎቻቸው ዕድሜ የገፋ መሆን ፈተና ሆኖባቸዋል ያሉት ሚኒስትሯ፤ ኢትዮጵያ 70 በመቶ የሚሆነው ዜጋዋ ወጣት ነው፡፡ ይህም ትልቅ የመወዳደሪያ አቅም ስለሆነ ብቃት ባለው ሥርዓተ ስልጠና በመደገፍ ወደ ውጤት ለመቀየር እየተሠራ መሆኑን አስረድተዋል፡፡
እንደ ሚኒስትሯ ገለጻ፤ ሥራን በአግባቡ የሚመራ ኃይል ያስፈልገናል። በተለይ በአስተሳሰቡ፣ በስብዕናውና በአገር ወዳድነቱ ልቆ የድህነት ታሪካችንን ለመቀየር የሚታትር ወጣት ማፍራት የሁላችንም የቤት ሥራ ሊሆን ይገባል።
ባለፉት ጊዜያት የነበረን የታሪክ ውጣውረድ አወንታዊም አሉታዊም ጎኖች አሉት፡፡ ከትውልድ ትውልድ እየተወራረሱ መቀጠል የሌለባቸውን ልማዶች ማስቆም እንዲሁም ጠንካራ የሥራ ልምዶችን ደግሞ ማጎልበት ይጠበቅብናል ብለዋል።
እንደአጠቃላይ ለአገራዊ የኢኮኖሚ መጠናከር ከግለሰብ ጀምሮ በየደረጃው ያሉ ሁሉም ባለድርሻ አካላት ሚናቸውን ለመወጣት መዘጋጀት እንዳለባቸው ወይዘሮ ሙፈሪሃት አሳስበዋል።
ፋንታነሽ ክንዴ
አዲስ ዘመን ሐምሌ 13 ቀን 2014 ዓ.ም