
አዲስ አበባ፡- በዘንድሮው ክረምት ወቅት አዋሽ ተፋሰስን ይዞ አፋር፣ ስምጥ ሸለቆ፣ ምሥራቃዊ የአገሪቱ ክፍሎች፣ በሰሜን ተከዜና ጣና፣ ጋምቤላ ባሮ አኮቦ አካባቢዎች የጎርፍ አደጋ የመከሰት ዕድሉ ሰፊ መሆኑን የኢትዮጵያ ሜትሮሎጂ ኢንስቲትዩት አስታወቀ፡፡ ከደቡብ አትላንቲክ እና ሕንድ ወደ አገራችን የሚገባ እርጥበታማ አየር በተጠናከረ መልኩ በሐምሌና ነሐሴ ወራቶች እንደሚቀጥልም ተመልክቷል፡፡
በኢትዮጵያ ሜትሮሎጂ ኢንስቲትዩት የአየር ትንቢያ እና ማስጠንቀቂያ ዳይሬክተር ወይዘሮ ጫሊ ደበሌ ለኢትዮጵያ ፕሬስ ድርጅት እንደገለጹት፤ ኢንስቲትዩቱ በተያዘው ክረምት ሊከሰት ከሚችል ጎርፍ አደጋ ኅብረተሰቡን ለመከላከል ከሚመለከታቸው ባለ ድርሻ አካላት ጋር በቅንጅት በመሥራት ላይ ይገኛል፡፡
በተያዘው ክረምትም በመጠንም በስፋት በተለያዩ አካባቢዎች መደበኛና ኢመደበኛ የሆነ ዝናብ ስለሚጠበቅ ኅብረተሰቡ ከጎርፍ አደጋ ራሱን መጠበቅ ይኖርበታል ብለዋል፡፡
ኢንስቲትዩቱ ክረምት ከመግባቱ በፊት ጀምሮ ኅብረተሰቡ ከጎርፍ አደጋ ጥንቃቄ እንዲያደርግ የአየር ሁኔታ ትንበያ መረጃዎችን ሲሰጥ መቆየቱን አውስተው፤ በአሁኑ ጊዜም ከኢንስቲትዩቱ በተሰጠው አየር ትንቢያ መረጃ መሠረት ረጅም ሰዓታት እና ሙሉ ቀን የዝናብ መጠን በተለያዩ ቦታዎች እየተስተዋለ ነው ሲሉም ተናግረዋል፡፡ ሐምሌን ወር ጨምሮ በቀጣይ ሁለት ወራትም በተመሳሳይ ሁኔታ እንደሚቀጥል ገልጸዋል፡፡
እንደ ወይዘሮ ጫሊ ገለጻ፤ ከደቡብ አትላንቲክ እና ሕንድ ወደ አገራችን የሚገባ እርጥበታማ አየር በተጠናከረ መልኩ እንደሚቀጥል ይጠበቃል፡፡ ይህን ተከትሎ ከፍተኛ ዝናብ ሊኖር እንደሚችል የአየር ትንበያው ያሳያል፡፡ ከዚህ አኳያ ኅብረተሰቡ ጎርፍ ሊከሰትባቸው የሚችሉ መንገዶችን ተረድቶ አስፈላጊውን ጥንቃቄ ማድረግ አለበት፡፡
በተለይ በምሥራቅ አማራና በመካከለኛው ኦሮሚያ የሚዘንበው ዝናብ ወደ አዋሽ ወንዝ ስለሚገባ በአካባቢው የሚኖሩ ኅብረተሰብ ክፍሎች ጎርፍ መከላከያ ቦዮችን በመሥራትና ከባለሙያ በሚሰጠው ምክር መሠረት ጥንቃቄ እንዲያድርጉ መክረዋል፡፡
በተለይ፤ በወንዞችና በተዳፋትና ገደላማ አካባቢዎች የሚኖሩ ዜጎች ጥንቃቄ እንዲያደርጉ አሳስበዋል፡፡
በዘንድሮው ክረምት መደበኛና ኢመደበኛ የዝናብ መጠን እንደሚኖር ጠቁመው፤ እስከ አሁን ባለው አየር ሁኔታ ትንቢያ መሠረት በአብዛኛው የአገሪቱ ክፍሎች መደበኛ እና ኢመደበኛ ዝናብ ተጠናክሮ ስለሚቀጥል ኅብረተሰቡ ከኢንስቲትዩቱ የሚሰጡትን መረጃዎች በመከታተል ከጎርፍ አደጋ አስፈላጊውን ጥንቃቄ እንዲያደርግ መክረዋል፡፡
ገመቹ ከድር
አዲስ ዘመን ሐምሌ 12 ቀን 2014 ዓ.ም