ወቅቱ የ2014/ 2015 የምርት ዘመን የመኸር ግብርና ስራ ርብርብ የሚደርግበት ነው፤ የዘር ወቅት፡፡ በእዚህ ወቅት እንደ ሀገርም አንደ ክልሎችም አብዛኛው ትኩረት ለመኸር እርሻ ስራ ይሰጣል፡፡ በሀገሪቱ በምርት ዘመኑ ከመኸር ወቅት እርሻ 390 ሚሊዮን ኩንታል ለማምረት ታቅዷል፡፡ ክልሎችም የየራሳቸውን እቅድ ይዘው እየሰሩ ናቸው፡፡
በግብርና ስራ ዙሪያ መረጃ ለማግኘት ለአማራ ክልል ግብርና ቢሮ ምክትል ኃላፊ ዶክተር አልማዝ ጊዜው ስልክ ደወልን፡፡ ስልኩን በደወልንበት ወቅት የቢሮ ኃላፊዋ የአርሶ አደሩን የግብርና እንቅስቃሴ ጉብኝተው እየተመለሱ ነበር፡፡ ጥሩ ግጥምጥሞ ሆነ፤ ስለጉብኙቱም ስለአጠቃላይ የክልሉ የምርት ዘመኑ እንቅስቃሴ ገለጹልን፡፡
ዶክተር አልማዝ እንዳሉት፤ የመኸር የግብርና ሥራ የመስክ ቅኝቱ ሐምሌ አንድ የጀመረ ሲሆን፣በዳይሬክተር ደረጃ በሚገኙ የሥራ ኃላፊዎች የሚመራና ስድስት ቀጣናዎችን የሚሸፍን ቅኝት ወይንም ጉብኝት ነው የተካሄደው፡፡
የመስክ ቅኝቱ በሰብል ልማት፣በግብአት ስርጭት፣በአረንጓዴ አሻራ መርሃ ግብር አፈጻጸም ላይ ያተኮረ ነው፤ ዓላማውም በእነዚህ ሶስት ዋና ዋና ተግባራት ላይ ድጋፍና ክትትሉን በማጠናከር የላቀ አፈጻጸም ለማስመዝገብ መሆኑን ነገሩን፡፡
በቅኝቱ ከተለዩት ክፍተቶች አንዱ በክላስተር ማረስ ላይ የታየው ነው፤ ክፍተቱንም እዚያው ለመፍታት ጥረት ተደርጓል፡፡ በወቅቱ ግብአት ያልደረሳቸው አርሶ አደሮችም ምክንያቱን በመለየት እንዲደርሳቸው ተደርጓል፡፡ የመስክ ቅኝቱ ክፍተቶችን መለየት ብቻ ሳይሆን በቦታው ላይ ፈጣን መፍትሄ በመስጠት ችግሩን መፍታት ነው፡፡ ምርት ተሰብስቦ ወደ ጎተራ እስኪ ገባ በዚህ መልኩ የክትትልና ድጋፍ ሥራውን በማጠናከር የምርት ዘመኑን ዕቅድ ለማሳካት ጥረት እንደሚደረግ የቢሮ ኃላፊዋ ይገልጻሉ፡፡
በአሁኑ ጊዜም የመኸር የግብርና ሥራ ቅድመ ዝግጅት ተጠናቅቆ ወደ ዋናው የተግባር ምዕራፍ ሥራ ተገብቷል፡፡ በመጀመሪያው ምዕራፍ የመጀመሪያ የእርሻ ደረጃ የሚባለው ቀድሞ በተያዘው ዕቅድ ልክ መከናወኑ በመስክ ጉብኝቱ ተረጋግጧል፡፡ ወደ ዘር ሥራ ለመሸጋገር እንቅስቀሴዎች ቢኖሩም በአንዳንድ የክልሉ አካባቢዎች ያጋጠመው የዝናብ መቆራረጥ ዘር መዝራቱን በዕቅዱ መሰረት ለማከናወን አላስቻለም፡፡
በክልሉ እየተከናወነ ያለው የግብርና ሥራ በ12 ዋና ዋና የሰብል አይነቶች ላይ ትኩረት አድርጓል፤ በክልሉ ከሚለሙ የሰብል አይነቶች አንዱ በቆሎ ነው፤ በቅድሚያ ይዘራ የነበረውም በቆሎ ነው፡፡ ዝናብ በወቅቱ ባለመጣሉ ሳቢያ በዕቅዱ መሠረት ዘር መዝራት አልተቻለም ይላሉ፡፡ በመሆኑም ከእቅዱ ማከናወን የተቻለው 61 በመቶውን ብቻ መሆኑን ጠቅሰው፣ በዝናብ መቆራረጥ ምክንያት የዘር መዝራት የተስተጓጎለበትን አካባቢ መሬቱ ጾም እንዳያድር ለማካካስ በሌሎች የሰብል አይነቶች እንዲሸፈን በድጋፍና ክትትል ጥረት እየተደረገ መሆኑን ይገልጻሉ፡፡
እንደ ምክትል ቢሮ ኃላፊዋ ገለጻ፤ ምርትና ምርታማነትን በመጨመር የሚታወቀውን ኩታገጠምና በመስማር መዝራት የግብርና ሥራ በመተግበር ረገድም የተጠናከረ ተግባር እየተከናወነ ነው፡፡ እስካሁን በመስመር መዝራት በተከናወነው ሥራም 50 ከመቶ በላይ አፈጻጸም ተመዝግቧል፡፡ ሁለቱንም የግብርና ሥራ ዘዴዎች ጨምሮ ማዳበሪያና የሚያስፈልጉ የግብርና ግብአቶች በወቅቱ ለአርሶአደሩ እንዲደርሱ በዘርፉ በከፍተኛ አመራሮች የሚመራ የአሰራር ሥርአት ተዘርግቶ ስምሪት ተሰጥቶ እየተሰራ ነው፡፡
ግብአት የማዳረስ ሥራ እንደቀጠለ ነው፡፡ በተለይ በዋጋ መወደድና በተለያየ ምክንያት እንደሀገር ያጋጠመውን የማዳበሪያ አቀርቦት እጥረት ክፍተት ለመሸፈን ግብአቱ በብዛት ካለበት ወደሌለበት በማዳረስ፣ ህብረት ሥራ ማህበራት(ዩኒየኖች)ያላቸውን ግብአት ለአርሶ አደሩ እንዲያዳርሱ፣ በተጨማሪም አርሶአደሩ የተፈጥሮ ማዳበሪያ እንዲጠቀም ምክረሀሳብ በመስጠትና ፣ድጋፍና ክትትል በማድረግ ክፍተቱን ለመሙላት እየተሰራ ይገኛል፡፡
ቨርን ኮምፖስትና ኮምፖስት የተበላውን የተፈጥሮ ማዳበሪያ በክልሉ ቀድሞም የመጠቀም ልምዱ ቢኖርም በስፋት እንዲከናወን ግንዛቤ የመፍጠሩ ሥራ ከመቼውም ጊዜ በበለጠ በዚህ አመት እየተሰራ ነው፡፡ በአርሶ አደሩ በኩልም መልካም የሚባል እንቅስቃሴ እየታየ ነው ይላሉ ምክትል የቢሮ ኃላፊው ፡፡
እንደ ዶክተር አልማዝ ማብራሪያ፤ ሌላው በግብርና ሥራው ትኩረት ተሰጥቶ እየተተገበረ ያለው አርሶ አደሩ ሙሉ የግብርና ፓኬጅ የሚባለውን አሰራር እንዲከተል የማድረጉ ስራ ሲሆን፣ ከፓኬጆቹ አንዱ የግብርና ሜካናይዜሽን (የእርሻ መሳሪያዎች) መጠቀም ነው፡፡ በእንስሳት ጉልበት በስፋት የሚከናወነውን የግብርና ሥራ ለማዘመን፣ምርትና ምርታማነትን ለመጨመር፣ የምርት ብክነትን ለመቀነስ፣የአርሶ አደሩን ጊዜ ለመቆጠብና ድካሙን ለመቀነስ በትራክተር ማረስ ተመራጭ እንደሆነ ግንዘቤ በመፍጠርና አቅርቦትን ምቹ ለማድረግ እየተሰራ ይገኛል፡፡
በዚህ ረገድም በመኸር እርሻ የቅድመ ዝግጅት ሥራ ከባለድርሻ አካላት ጋር ውይይትና ስምምነቶች ተደርገዋል፡፡ የክልሉ መንግሥትም በልዩ ትኩረት የሚችለውን ድጋፍ አድርጓል፡፡ በመንግሥት ደረጃ እስከ 30 ሚሊየን ዶላር ተፈቅዶ አራት አቅራቢ ድርጅቶች የአርሻ ትራክተር እንዲያቀርቡ ከባንኮች ጋር በማስተሳሰር አርሶአደሩ ትራክተር ብድር በብድር እንዲያገኝ ሁኔታዎች ተመቻችተዋል፡፡
አሰራሩም አነስተኛ አቅም ያላቸውንም እርሶአደሮች ተጠቃሚ እንደሚያደርግ ነው የተናገሩት፡፡ በዚሁ መሠረትም 136 ትራክተሮች በብደር በማቅረብ አርሶአደሩ በአስር አመት ጊዜ ውስጥ ብድሩን እንዲያጠናቅቅ ከባንክ ጋር የማስተሳሰር ሥራ ተሰርቷል ይላሉ፡፡ ክልሉ እስከ አንድ ሺ ትራክተሮችን ለማቅረብ በእቅድ የያዘ ሲሆን፣አቅርቦቱ በኪራይም እንዲኖር ለማድረግ ጥረት እየተደረገ መሆኑን አስታውቀዋል፡፡
የኩታ ገጠም የግብርና ሥራም የሚበረታታው በትራክተር ሲታረስ መሆኑን ጠቅሰው፣ ይህ ስራ ተጠናክሮ ይቀጥላል ነው ያሉት፡፡ የክልሉ መሬት 40 በመቶ የሚሆነው በትራክተር ለማረስ ምቹ ነው፡፡ በዚህ ረገድ የክልሉ መንግሥት ከሚያደርገው ድጋፍ በተጨማሪ አቅሙ ያላቸው በትራክተር እንዲያርሱ ይበረታታሉ፡፡ ክልሉ ቢያንስ 15 ነጥብ ሰባት በመቶ የሚሆነው መሬት በትራክተር እንዲታረስ የማድረግ ዕቅድ ተይዞ እየተሰራ ነው ሲሉ ያብራራሉ፡፡
እንደ ምክትል ቢሮ ኃላፊዋ ገለጻ፤ ከመኸር ግብርና ሥራው ጎን ለጎን የአረንጓዴ አሻራ መርሃ ግብርን በማጠናከር እየተሰራ ነው፡፡ መርሃ ግብሩ የአትክልትና ፍራፍሬ ልማትን የሚያካትት በመሆኑ በኩታገጠም የልማት ሥራ እንዲከናወንም ልዩ ትኩረት ተሰጥቶታል፡፡ በክልሉ የአቮካዶና የቡና ልማት ውጤቶችን ለውጭ ገበያ የማቅረብ ጅማሮ በመኖሩ በ2014_2015 የምርት ዘመን አጠናክሮ ለመቀጠል ልማቱን በክላስተር ለማከናወን ነው በትኩረት እየተሰራ ያለው፡፡
ክልሉ በምርት ዘመኑ አራት ነጥብ ስምንት ሚሊየን ሄክታር መሬት በማረስ በተለያየ ሰብል በመሸፈን ምርትና ምርታማነትን ለማሳደግ አቅዶ በመስራት ላይ ይገኛል፡፡ እቅዱን ለማስፈጸምም ከቅድመ ዝግጅት ጀምሮ በክትትልና ቁጥጥር እየተሰራ ነው፡፡ የሚታረሰው የእርሻ መሬት ከ2013_2014ዓም የምርት ዘመን በ20 በመቶ ጭማሪ አለው፡፡ ክልሉ በምርት ዘመኑ ከ143ሚሊየን ኩንታል በላይ ሰብል ለመሰብሰብ ታቅዷል፡፡
የቤንሻንጉል ጉሙዝ ክልልን የመኸር የግብርና ሥራ በተመለከተ የክልሉን ግብርናና የተፈጥሮ ሀብት ቢሮ ኃላፊ አቶ ባብከር ከሊፋን አነጋግረናቸዋል፡፡ የክልሉ የተወሰኑ አካባቢዎች ከፀጥታ ስጋት ነፃ ባለመሆናቸው በእርሻ ሥራ እንቅስቃሴው ላይ ያለውን ስጋታችንንም አንስተንላቸዋል፡፡
ኃላፊው አቶ ባብከር እንዳስረዱት፤ በምርት ዘመኑ 34 ሚሊየን ኩንታል ሰብል ለመሰብሰብ እቅድ በመያዝ ነው ወደ ሥራ የተገባው፡፡ በዚህ ወቅትም በተለይ በአሶሳና በመተከል ዞኖች የግብርና ሥራው በስፋት በመከናወን ላይ ይገኛል፡፡ በዞኖቹ አንጻራዊ የሆነ ሰላም በመኖሩ ህብረተሰቡ በእርሻ ሥራው ላይ ትኩረት አድርጎ እያከናወነ ይገኛል፡፡ ቢሮው የክትትልና ድጋፍ ሥራውን ቀድሞ በመጀመሩ እያያዙ ጥሩ ሆኖ ይታያል፡፡
እስካሁን በተሰራው የግብርና ሥራም 50 በመቶ ያህል ማከናወን ተችሏል ይላሉ የቢሮ ኃላፊው፡፡ በክልሉ የፀጥታ ስጋት የፀጥታ ስጋት ካለባቸው አካባቢዎች መካከል የካማሺ ዞን አምስት ወረዳዎች እንዲሁም ማኦኮሞ ልዩ ወረዳ መሆናቸውን ይገልጻሉ፡፡አካባቢዎቹ ከፀጥታ ስጋት ነጻ ሆነው የግብርና ሥራው እንዲከናወን በመንግሥት ጥረት እየተደረገ መሆኑን ጠቁመዋል፡፡ ችግሩ ተቀርፎ ህብረተሰቡ ወደ ግብርና ሥራው ይገባል የሚል ተስፋ እንዳለና በቢሮው በኩል አስፈላጊው ዝግጅት ተደርጓል ይላሉ፡፡
በእነዚህ የፀጥታ ችግር ያለባቸው አካባቢዎች በፀጥታ መደፍረስ ባለፈውም የምርት ዘመን የግብርና ሥራ ባለመከናወኑ የአካባቢው ማህበረሰብ ተረጂ መሆኑን ጠቅሰው፣አሁንም ይህ እንዳይደገም የመንግሥት አካል ፀጥታ በማስፈን ላይ ከፍተኛ ሥራ እንደሚሰራ ይጠበቃል ብለዋል፡፡
ለምርት ዘመኑ የሚያስፈልገው የግብአት አቅርቦት የግብርና ሥራው በሚከናወንባቸው የክልሉ አካባቢዎች እንዲደርስ በመደረግ ላይ መሆኑን ጠቅሰው፣ ዩሪያም ማዳበሪያም 75 በመቶ ያህል ተደራሽ ሆኗል ይላሉ፡፡ ቀሪው የማዳረስ ሥራ እየተከናወነ ጎን ለጎንም አርሶ አደሩ የተፈጥሮ ማዳበሪያ በማዘጋጀት እንዲጠቀም በድጋፍና ክትትል ይጠናከራል ሲሉ ነው የገለጹት፡፡
እንደ ቢሮ ኃላፊው ማብራሪያ፤ አርሶ አደሩ የኩታገጠም የግብርና ዘዴ በመጠቀም አበረታች እንቅስቃሴ በማድረግ ላይ በመሆኑ ቢሮው ከመኸር እርሻው የተሻለ አፈጻጸም ይጠብቃል፡፡ የግብርና ሥራውን ለማዘመንም በተለይም በትራክተር የእርሻ ሥራ እንዲከናወን ጥረት እየተደረገ ሲሆን፣ የክልሉ መንግሥት 34 ትራክተሮችን ገዝቶ በማቅረብ ድጋፍ አድርጓል፡፡
በተለይ በአሶሳና መተከል ዞኖች ላይ ወደ ተግባራዊ ሥራ ተገብቷል ያሉት ኃላፊው፣ በዞኖቹ በእርሻ ሥራ የሚንቀሳቀሱ ባለሀብቶች በመኖራቸው የሚያግዙበት ሁኔታ ስለሚኖር በትራክተር የመጠቀሙ ሁኔታ በተሻለ ይጠበቃል ብለዋል፡፡ እስካሁን ወደ 200 ሺ ሄክታር የሚሆነው መሬት በትራክተር ታርሶ ለሰብል ልማቱ ዝግጁ መደረጉንም አብራርተዋል፡፡
በአሁኑ ጊዜ በክልሉ በስፋት የግብርና ሥራ በሚከናወንባቸው በአሶሳና በመተከል ዞኖች ሥራው የሚገኝበትን ደረጃ በተመለከተም አቶ ባብከር እንዳስረዱት፤ ወደ 547ሺ ሄክታር መሬት ታርሶ ለሰብል ዘር ዝግጁ ተደርጓል ሲሉ ገልጸው፣ ከዚህ ውስጥም እስከ ባለፈው ሳምንት ድረስ ወደ 400 ሺ ሄክታር የሚሆነው በተለያየ የሰብል ዘር ተሸፍኗል፡፡
ክልሉ የተለያዩ የሰብል አይነቶችን የሚያመርት ቢሆንም በአንደኛ ደረጃ በስፋት የሚለማው በቆሎ ነው ያሉት ኃላፊው፣ በሁለተኛ ደረጃ ደግሞ ማሽላ እንደሚለማ ይጠቁማሉ፡፡ ልማቱም እንደ ስነምህዳሩ ውጤታማ የሚሆንባቸው ከአካባቢ አካባቢ ይለያያል፡፡ በተለይም መተከል ወንበራ ተብሎ የሚጠራው አካባቢ ስንዴ፣ዳጉሳ፣ጤፍ ይመረታል፡፡አሶሳ ዞን ላይ ደግሞ አኩሪ አተር በስፋት ይመረታል ሲሉ ያብራራሉ፡፡
እንደ አቶ ባብከር ማብራራያ፤ እስካሁን በዝናብ ስርጭት በኩል አስቸጋሪ ሁኔታ አልገጠመም፡፡ እንደውም አንድ ሁለት ቀን ፋታ በመስጠትና በተከታታይ በመዝነብ ለእርሻ ሥራው ተስማሚ የሆነ የዝናብ መጠን ማግኘት ተችሏል፡፡
እንደ ክፍተት የሚጠቀሰው አካባቢው ላይ ያጋጠመው የፀጥታ ስጋት በተለይ የግብርና ባለሙያው ተረጋግቶ እንዲሰራ እያደረገው አለመሆኑ መሆኑን ይጠቁማሉ፡፡ በዚህ የተነሳም አርሶ አደሩን በተለያየ የግብርና ሥራ ሙያ የሚያግዝ ባለሙያ ማግኘት አስቸጋሪ ሆኗል ነው የሚሉት፡፡
የግብርና ቴክኖሎጂን ለአርሶአደሩ ተደራሽ ለማድረግ የባለሙያ መኖርና እገዛ ከፍተኛ ነው ያሉት ኃላፊው፣ ከፍተኛ የፀጥታ ስጋት ባለባቸው አካባቢዎች የግብርና ባለሙያዎች አሉ ለማለት እንደማያስደፍር ነው የተናገሩት፡፡
በጥንካሬ የወሰዱት ደግሞ መተከል ዞን ውስጥ የሚገኙ ሁለት ወረዳዎች ነው፡፡ ወረዳዎቹ ለሁለት የምርት ዘመን በማምረት ሂደት ውስጥ እንዳልነበሩ በዚህም በጣም ተጎጂ እንደነበሩ አስታውሰው፣ የአካበቢው የፀጥታ ሁኔታ ተሻሽሎ ነዋሪው የግብርና ሥራውን በእንስሳት ጉልበትና በትራክተር ታግዞ ወደ ማልማት ፊቱን ማዞሩን ተናግረዋል፡፡ ይህም ተስፋ ሰጭ መሆኑን ጠቅሰው፣ ነዋሪው ወደ ምርት ሥራ መግባቱ ከተረጂነት እንዲላቀቅ ያስችለዋል ይላሉ፡፡
እንደ እሳቸው ገለጻ በቤኒሻንገጉል ጉሙዝ ክልል አምና መተከል ውስጥ የግብርና ሥራው የተከናወነው በከፊል ነበር፡፡ በክልሉ በ2014_2015 የምርት ዘመን በነበረው ፀጥታ ችግር የምርት መቃጠልም አጋጥሞ ስለነበር ችግሩ ውስብስብ ነበር፡፡ ዘንድሮ ግን መተከልና አሶሳ ዞኖች ላይ ሙሉ ለሙሉ በሚባል ደረጃ እየተሰራ በመሆኑ የተሻለ ውጤት ይጠበቃል፡፡
ከሁለቱ የሥራ ኃላፊዎች መገንዘብ እንደቻልነው የግብርና ሥራው በክትትልና ድጋፍ ተጠናክሯል፡፡ የተለየ ነገር ካላጋጠመ እነርሱ እንዳሉት በምርት ዘመኑ ከክልሎቹ ጥሩ ውጤት ይጠበቃል፡፡
ለምለም መንግሥቱ
አዲስ ዘመን ሐምሌ 11/2014