
- አዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ 5 ሺህ 58 ተማሪዎች አስመረቀ
አዲስ አበባ፡- አገር በለውጥ ጉዳና እንድትጓዝ በማድረግ ሕዝባችንን ከችግር ለማውጣት መቻቻል፣ መነጋገርና መደማመጥ አለብን ሲሉ የኢፌዴሪ ፕሬዚዳንት ሳህለወርቅ ዘውዴ አስታወቁ።
የኢፌዴሪ ፕሬዚዳንት ሳህለወርቅ ዘውዴ ትናንት በተካሄደው የአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የተማሪዎች ምረቃ ሥነ ሥርዓት ላይ ተገኝተው እንደገለጹት፣ ተመራቂ ተማሪዎች ማሕበራዊ፣ አካዳሚያዊና ፖለቲካዊ ፈተናዎችን አልፋችሁ ዩኒቨርሲቲ የገባችሁበትን ዓላማ ማሳካት በመቻላችሁ እንኳን ደስ አላችሁ። አገራችን በልማት፣ በመልካም አስተዳደር፣ በዴሞክራሲ፣ በፍትህና በሰላም ጎዳና እንድትጓዝ ለማድረግ የሁላችንንም ርብርብ ይጠይቃል፤ በተለይ በእውቀት የታነጸ ወጣት ኃላፊነቱ ጉልህ ነው ብለዋል።
አገር በለውጥ ጎዳና እንድትጓዝ በማድረግ ሕዝባችንን ከችግር ለማውጣት መቻቻል፣ መነጋገርና መደማመጥ አለብን ያሉት ፕሬዚዳንቷ፤ የተማረ ሰው የአገሩን ችግር እንዴት እንደሚፈታ ይመራመራል፤ በችግር ውስጥ ያሉትን የወገኖችን ስቃይ ይረዳል። ከችግር ለማውጣት እንደሚተጋ ገልጸዋል።

ተመራቂዎች በተመረቃችሁበት የትምህርት ዘርፍ ወደ ተግባር በመቀየር ለቤተሰብና፤ ለወገንና ለአገር አገልጋይ መሆን እንደሚጠበቅባቸው ገልጸው፤ መማር
ማለት ግንዛቤን ማሳደግና የእይታ ከፍታን ማምጣት፤ በችግር ወቅት ከዳር ሁኖ ተመልካች መሆን ሳይሆን መሆን የሌለበት ጉዳይ ሲከሰት አይሆንም ማለት መቻል መሆኑን አብራርተዋል።
እንደ ፕሬዚዳንቷ ገለጻ፤ ሕብረተሰቡ የተሟላ ሆስፒታል፣ ትምህርት ቤት፣ ውሃ፣ እና ሌሎች መሰረት ልማት ስለሚያስፈልጉት መረባረብ ያስፈልጋል። ተመራቂ ተማሪዎች በትምህርት ያገኙትን እውቀትና ክህሎት ተጠቅመው ኢትዮጵያ ካለችበት ችግር እንድትወጣ የሚያስችሉ የመፍትሔ ሃሳቦችን ማፍለቅ ይጠበቅባቸዋል።
ኢትዮጵያ በበርካታ ችግሮች ውስጥ እያለፈች በመሆኑ በእውቀትና በክሕሎት የዳበረ ወጣት ትፈልጋለች ያሉት ፕሬዚዳንት ሳህለወርቅ፤ በተለይ ባለፉት ሁለት ዓመታት የታየው ደግሞ ፈጽሞ መፈጸም የለሌበት ድርጊት ነው። ደሃ ሕዝባችንን ካለበት ሁኔታ ለማውጣትና አገር ለማሳደግ መረባበርብ ሲገባን የበርካታ ዜጎቻችን ደም እንዲፈስ ተደርጓል። በርካታ አገሮች ከአገራቸው ወጥተው ዓለም አቀፍ አስተሳሰብ ላይ ባተኮሩበት ወቅት እኛ በቋንቋ፣ ብሔር ማንነት፣ በሃይማኖትና በሌሎች ተከፋፍለን ዜጎች በአሰቃቂ ሁኔታ እየተገደሉ መሆናቸው የሚያሳዝን መሆኑን ተናግረዋል።
መማር ማለት እያየን እንዳላየን መሆን አይደለም፤ ማሳለፍ የሌለብንን ዝም ብለን ማሳለፍ አይደለም ያሉት ፕሬዚዳንት ሳህለወርቅ፤ ተመራቂዎች ባሉበት ቦታ ሁነው ለአገር አንድነት፣ እድገትና ለውጥ እንዲሰሩ ጥሪ አስተላልፈዋል። መንግሥት ለተመራቂ ተማሪዎች የስራ እድል ለመፍጠር ጠንክሮ እንደሚሰራም ገልጸዋል።
የአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ፕሬዚዳንት ፕሮፌሰር ጣሰው ወልደሃና በበኩላቸው፤ ኢትዮጵያ ከውስጥና ከውጭ ጠላት በበዛባት ወቅት የተመረቃች በመሆኑ በዘርና በጎሳ ከመከፋፈል ወጥታችሁ ሀገራችሁን በጥናትና ምርምር መርዳት አለባችሁ ብለዋል።
እንደ ፕሬዚዳንቱ ገለጻ፤ ዩኒቨርሲቲው ለ73ኛ ጊዜ በተለያዩ የትምህርት መስኮች ያስተማራቸውን 5 ሺህ 58 ተማሪዎች አስመርቋል። ከተመራቂዎቹ መካከል 2 ሺህ 420 በመጀመሪያ ዲግሪ እንዲሁም 2 ሺህ 438 ያህሉ ደግሞ በድህረ ምረቃ መርሐ ግብር ትምህርታቸውን የተከታተሉ ናቸው። ከድህረ ምረቃ ተመራቂዎች መካከል 131 ያህሉ በሦስተኛ ዲግሪ እንዲሁም 239 ያህሉ ደግሞ በስፔሻሊቲ መሆኑን ታውቋል።
ሞገስ ጸጋዬ
አዲስ ዘመን ሐምሌ 10 ቀን 2014 ዓ.ም