
አዲስ አበባ፡- በፌዴሬሽን ምክር ቤት የፀደቀው ደንብ ከፌዴራል መንግስቱ የሚሰጡ ድጎማዎች ለምዝበራና ብልሹ አሰራሮች እንዳይዳረጉ እንደሚረዳ ተገለጸ። መሠረተ ልማት ስርጭቶች ፍትሐዊነትና ግልፀኝነት እንዲኖራቸው ጉልህ ሚና እንዳለው ተመልክቷል።
ውስን ዓላማ ያላቸው የድጎማ በጀትና የፌዴራል መሠረተ ልማት ስርጭት ፍትሐዊነት የክትትል ሥርዓትን ለማስፈጸም የተዘጋጀ ረቂቅ ደንብ የፌዴሬሽን ምክር ቤት ትናንት አፅድቋል።
የፌዴሬሽን ምክር ቤት ስድስተኛ የፓርላማ ዘመን 1ኛ ዓመት የሥራ ጊዜ 2ኛ መደበኛ ስብሰባውን ባደረገበት ወቅት ውስን ዓላማ ያላቸው የድጎማ በጀትና የፌዴራል መሠረተ ልማት ስርጭት ፍትሐዊነት የክትትል ሥርዓትን ለማስፈጸም የተዘጋጀ ረቂቅ ደንብ ላይ ሰፋ ያለ ውይይት አድርጓል።
ከዚህ በፊት በተለያዩ ምክንያቶች ከፌዴራል መንግሥቱ የሚሰጡ ልዩ አላማ ያላቸው ድጎማዎች ለምዝበራና ብልሹ አሰራሮች የተጋለጡ በመሆናቸው ግልፅ የሆነ አሰራር ሊበጅላቸው የሚገባ መሆኑን የምክር ቤቱ አባላት ተናግረዋል።
ደንቡም ከፌዴራል መንግሥት የሚሰጠው ልዩ ዓላማ ያላቸው ድጎማዎች የፌዴራል መሠረተ ልማቶች በፍትሐዊነት እንዲከፋፈል እንዲሁም ግልጽና ፍትሐዊ አሰራር እንዲሰፍን የሚያደርግ መሆኑን የምክር ቤቱ አባላት አመልክተዋል።
በሙሉ ድምፅ የፀደቀው ደንብ በክልሎች መካከል የሚስተዋለውን ኢፍትሐዊነት የመልማት ጥያቄ በዘለቄታነት የሚፈታ ደንብ መሆኑና የተመጣጠነ ልማትና መንግሥታዊ አገልግሎት እንዲኖር ያደርጋልም ተብሏል።
በሌላ በኩል ምክር ቤቱ በሕገ መንግሥት ጉዳዮች አጣሪ ጉባዔ ለሕገ መንግሥት ትርጉም የቀረቡ የውሳኔ ሃሳቦች ላይ ተወያይቶ ውሳኔ አስተላልፏል።
የምክር ቤቱ የህገ መንግሥት ትርጉም ክትትልና ውሳኔ አፈፃፀም ቋሚ ኮሚቴ ሰብሳቢ የሆኑት ዶክተር ሰማ ጥሩነህ እንደገለጹት፤ ዜጎች በየደረጃው ባሉ ፍርድ ቤቶች የተሰጡ ውሳኔዎች ህግ መንግሥቱን መሰረት ተደርገው የተሰጡ ውሳኔዎች አይደሉም። የፌዴሬሽን ምክር ቤት የህገ መንግሥት ትርጉም ሊሰጠው ይገባል በሚል 87 የሚደርሱ ጉዳዮች ለቋሚ ኮሚቴው መቅረቡን አንስተው፣ ጉዳዮቹ በየደረጃው ባሉ ፍርድ ቤቶች በቂ ክርክር ተደርጎባቸው ዜጎች በዚህ ውሳኔ ባለመርካት የተለያዩ አንቀፆችን በመጥቀስ ህገ መንግሥታዊ አይደሉም ብለው ያቀረቧቸው መሆናቸውን አንስተዋል።
በዚህም መሰረት በሕገ መንግሥት ጉዳዮች አጣሪ ጉባኤ አማካኝነት የታዩና ለህገ መንግሥት ትርጉም ክትትልና ውሳኔ አፈፃፀም ቋሚ ኮሚቴ የቀረቡ ሰባት ርዕሰ ጉዳዮች ለምክር ቤቱ በዝርዝር ቀርበው ውይይት ተደርጎባቸዋል።
ለምክር ቤቱ ከቀረቡ ሰባት ዝርዝር ጉዳዮች ውስጥም ስድስቱ የሕገ መንግሥት ትርጉም እንደማያስፈልጋቸው እና አንድ ጉዳይ ደግሞ የሕገ-መንግሥት ትርጉም ያስፈልገዋል የሚለውን የቋሚ ኮሚቴን የውሳኔ ሀሳብ ምክር ቤቱ በአብላጫ ድምፅ አፅድቋል።
ፍቃዱ ዴሬሳ
አዲስ ዘመን ሐምሌ 9 ቀን 2014 ዓ.ም