
አዲስ አበባ፡- የብሄራዊ የመንገድ ደህንነት ስትራቴጂ በትራፊክ አደጋ የሚደርሰውን ሞት በግማሽ የመቀነስ ግብ እንዳለው የኢፌዴሪ ትራንስፖርት እና ሎጀስቲክስ ሚኒስቴር ገለጸ።
ሚኒስቴር መስሪያ ቤቱ ከብሉምበርግ ኢኒሼዬቲቭ ፎር ግሎባል ሮድ ሴፍቲ ጋር በመተባበር እ.ኤ.አ. ከ2021 እስከ 2030 ተግባራዊ እንዲሆን ያዘጋጀውን የመንገድ ደህንነት ስትራቴጂ በትላንትናው እለት ይፋ አድርጓል።
ትራንስፖርት እና ሎጀስቲክስ ሚኒስትሯ ወይዘሮ ዳግማዊት ሞገስ እንደገለጹት፤ የብሄራዊ የመንገድ ደህንነት ስትራቴጂ በትራፊክ አደጋ የሚደርሰውን ሞት በግማሽ የመቀነስ ግብ አለው።
የአገራት ልምድ እንደሚያሳየው የመንገድ ደህንነት ስትራቴጂን ተግባራዊ በማድረግ በትራፊክ አደጋ የሚደርሰውን ሞት እና የከባድ አካል ጉዳት ትርጉም ባለው መልኩ መቀነስ ችለዋል ያሉት ሚኒስትሯ፤ ኢትዮጵያም ውጤታማ የብሄራዊ የመንገድ ደህንነት ስትራቴጂን ተግባራዊ በማድረግ በትራፊክ አደጋ የሚደርሰውን ሞት በግማሽ የመቀነስ ግብ ተይዟል ብለዋል።
የትራፊክ ግጭት ዋነኛ የዓለም አቀፍ ማህበራዊ፣ ኢኮኖሚያዊ እና የጤና ችግር እንደሆነም ቀጥሏል ያሉት ሚኒስትሯ፤ ከፍጥነት ወሰን በላይ ማሽከርከር፣ ጠጥቶ ማሽከርከር፣ ሄልሜት (የደህንነት ቆብ) አለማድረግ እና የደህንነት ቀበቶ ወይም የህጸናት ግጭት መከላከያ ማቀፊያ አለመጠቀም ቁልፍ የመንገድ ትራፊክ መንስኤዎች እንደሆኑ ጥናቶች እንደሚያመለክቱም ገልጸዋል።
ስትራቴጂውን ተግባራዊ ለማድረግ እና አንግቦ የተነሳውን ግብ ለማሳካት የመንገድ ደህንነት ተቋማዊ ብቃት እና የአስተዳደር ዘዴ፤ ደህንነቱ የተጠበቀ ፍጥነት፣ ደህንነቱ የተጠበቀ የመንገድ መሰረተ ልማት፣ ደህንነቱ የተጠበቀ ተሽከርካሪ፣ ደህንነቱ የተጠበቀ የመንገድ ተጠቃሚ፤ ድህረ አደጋ የህክምና አገልግሎት መስጠት የተሰኙ ስድስት የመንገድ ደህንነት ምሶሶዎች እንዳሉት ጠቅሰዋል።
“የስትራቴጂው ዋና ዋና ምሰሶዎች ከዓለም አቀፍ ምርጥ ተሞክሮዎች፣ እስታንዳርዶች እና ከገባናቸው ስምምነቶች እንዲሁም ከሀገራችን ተጨባጭ ሁኔታ ጋር እንዲናበቡ ተደርገው ውጤት በሚያመጡ መልኩ የተቀረፁ ናቸው። ” ያሉት ሚኒስትሯ ስትራቴጂው ደህንነቱ የተጠበቀ የመንገድ ደህንነት ስርዓት መዘረጋትን እና ለመንገድ ትራፊክ ጉዳት ተጋላጭ የሆኑ መንገድ ተጠቃሚዎችን ከግምት ውስጥ ያስገባ ታሳቢ በማድረግ የተዘጋጀ ነው ብለዋል።
የትራፊክ አደጋን ለመከላከል ለተወሰኑ ተቋማት ብቻ የሚተው ሳይሆን የሁሉንም ባለድርሻ አካላት እና አጋር ድርጅት ቅንጅታዊ ሥራ የሚጠይቅ ነው ያሉት ሚኒስትሯ ፤ ስትራቴጂውን ተግባራዊ በማድረጉ ሂደትም የህብረተሰቡ ተሳትፎም ወሳኝ ነው ሲሉ ገልጸዋል።
የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት የመንገድ ደህንነት ልዩ መልእክተኛው ሚስተር ዣን ቴድ በበኩላቸው፤ የትራንስፖርትና ሎጂስቲክስ ሚኒስቴር የመንገድ ደህንነትን ለማስጠበቅ የሰራቸውን ተግባራት በማድነቅ በቀጣይም ለሚከወኑት ሥራዎች ከኢትዮጵያ ጎን እንደሚቆሙም ቃል ገብተዋል።
ከፌዴራል ፖሊስ ኮሚሽን የተገኘ የትፊክ አደጋ መረጃ እንደሚያሳየው በአገር ደረጃ በመንገድ ትራፊክ ግጭት ሳቢያ በየቀኑ በአማካይ ከ11 የማያንሱ ሰዎች ሕይወት የሚቀጠፍ ሲሆን በ2013 በጀት ዓመት አራት ሺህ 161 ሰዎች በትራፊክ አደጋ ሕይወታቸውን ማጣታቸው ይታወቃል።
ዳግማዊት ግርማ
አዲስ ዘመን ሐምሌ 9 ቀን 2014 ዓ.ም