
አዲስ አበባ፡- በአዲስ አበባ በበጀት ዓመቱ ለ19 ሺህ 207 ኢንተርፕራይዞች የስምንት ቢሊዮን ብር የገበያ ትስስር መፈጠሩን የከተማዋ ከንቲባ ከንቲባ አዳነች አቤቤ ገለጹ። በከተማዋ በበጀት ዓመቱ ለ405 ሺህ 536 ዜጎች የሥራ እድል መፈጠሩን ተመልክቷል።
በሀገር ውስጥና የውጭ ሀገር የገበያ ትስስር መፍጠርን በተመለከተ ለ21 ሺህ 62 ኢንተርፕራይዞች 6 ነጥብ 5 ቢሊዮን ብር የገበያ ትስስር ለመፍጠር ታቅዶ፣ ለ19 ሺህ 207 ኢንተርፕራይዞች የ8 ቢሊዮን ብር የገበያ ትስስር ተፈጥሯልም ነው ያሉት።
የአካል ጉዳተኛ አ\sንቀሳቃሾችን በገበያ ትስስር ተጠቃሚ ለማድረግ ለ320 አንቀሳቃሾች የገበያ ትስስር ለመፍጠር የታቀደ ሲሆን፣ ለ378 የ10 ሚሊዮን ብር የገበያ ትስስር መፍጠር መቻሉን ከንቲባ አዳነች ጠቁመዋል።
ከ9 ሺህ 947 ኢንተርፕራይዞች ውስጥ 8 ሺህ 323 ኢንተርፕራይዞች ወደሚቀጥለው ደረጃ እንዲሸጋገሩ መደረጉን ተገልጧል።
ከንቲባዋ የሥራ እድል ፈጠራን አስመልክቶ ባደረጉት ንግግር ፣ በበጀት ዓመቱ ለ350 ሺህ ዜጎች አዳዲስ አማራጭ የሥራ ዕድል መስኮችን ለመለየት ታቅዶ፣ ከ391 ሺህ በላይ (112 በመቶ) የሥራ እድል መፍጠር የሚያስችሉ ልዩ ልዩ የሥራ መስኮች መለየታቸውን ገልጸዋል።
ለ350 ሺህ ሥራ ፈላጊዎች የሥራ እድል ለመፍጠር በተደረገው ርብርብ 405 ሺህ 536 ዜጎች ሥራ ማግኘታቸውን ነው የተናገሩት።
ከነዚህ ውስጥ 380 ሺህ 720 ቋሚ የሥራ እድል ሲሆን ፣ 24 ሺህ 811 ጊዜያዊ የሥራ እድል የተፈጠረላቸው ናቸው ብለዋል።

በተጨማሪም ለ597 አካል ጉዳተኞችና ለ820 ከስደት ተመላሾች የሥራ እድል ተፈጥሮላቸዋል ያሉት ከንቲባዋ ፣ የሥራ እድል ከተፈጠረላቸው መካከል 54 በመቶ የሚሆኑት ሴቶች ሲሆኑ ፤ 76 በመቶ ወጣቶች፣ 16 በመቶ ከዩኒቨርሲቲና ቴክኒክና ሙያ የተመረቁ መሆናቸውን ጠቅሰዋል።
በተጨማሪም ተኪ ምርት የሚያመርቱ አምራች ኢንዱስትሪዎችን 568 ለማድረስ ታቅዶ፣ 831 ማድረስ መቻሉንም ነው ያስረዱት።
ከንቲባዋ አክለውም ፣ በሁለተኛው ዙር በምግብ ዋስትናና በልማታዊ ሴፍቲኔት መርሐ ግብር በመዲናዋ ለተለያዩ ማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ ችግሮች የተጋለጡ የህብረተሰብ ክፍሎችን በመለየት 109 ሺህ 918 ዜጎች ተጠቃሚ እንዲሆኑ መደረጉን ከከንቲባ ጽህፈት ቤት ያገኘነው መረጃ ያመለክታል።
በአንድ በኩል በከተማዋ ነዋሪዎች ላይ የኑሮ ውድነት ያስከተለውን ጫና ለመቅረፍ፣ በሌላ በኩል የሥራ አጥነትን ችግር ለመቀነስ የሚያስችል ሥራ ከመሰራት በተጨማሪ የሥራ ባህልን ለማጐልበት ጉልህ አስተዋፅኦ ያለው ተግባር ተከናውኗል ብለዋል ከንቲባ አዳነች።
በጋዜጣው ሪፖርተር
አዲስ ዘመን ሐምሌ 9 ቀን 2014 ዓ.ም