
አዲስ አበባ፡- በቴሌብርና በአጭር የጽሁፍ መልዕክት አማካኝነት በኢትዮጵያ የመጀመሪያው ሕጋዊ የዲጂታል ሎተሪ ገበያ ላይ መዋሉን ኢትዮ ቴሌኮምና የብሔራዊ ሎተሪ አስተዳደር አስታወቁ።
ኢትዮ ቴሌኮምና የብሔራዊ ሎተሪ አስተዳደር የሎተሪ ትኬት በዲጂታል አማራጭ ለማቅረብ የሚያስችል ስምምነት ትናንትና አድርገዋል።
በወቅቱ ስምምነቱን የፈረሙት የኢትዮ ቴሌኮም ሥራ አስፈጻሚ ወይዘሪት ፍሬህይወት ታምሩ እንዳስታወቁት፤ ከብሔራዊ ሎተሪ ጋር በተደረገ ስምምነት በቴሌብርና በአጭር የጽሁፍ መልዕክት አማካኝነት ሎተሪ መቁረጥ የሚያስችል ዲጂታል ሥራ ተጀምሯል።
ዲጂታል ሎተሪው “አድማስ” የተሰኘ መሆኑን ጠቁመው፤ ደንበኞች በቴሌ ብር አማካኝነት ሎተሪውን ለመቁረጥ ሲፈልጉ *127# በመደወል ከሚመጡ ዝርዝሮች መካከል 7 ቁጥርን በመምረጥ የብሔራዊ ሎተሪን አገልግሎት ማግኘትና የሎተሪ ክፍያ መፈጸም እንደሚችሉ ገልጸዋል።
በተጨማሪ በ605 አጭር የጽሑፍ መልዕክት ላይ A አሊያም የሚፈልጉትን ፊደል በመላክ ከተመዘገቡ በኋላ የሎተሪ ዕጣ ቁጥር ማግኘት ይቻላል ያሉት ወይዘሪት ፍሬ ሕይወት፤ ዲጂታል ሎተሪው ዘመናዊ እንዲሁም ወጪና ጊዜ ቆጣቢ በመሆኑ እንደአገር አዋጭ መሆኑን ተናግረዋል።
ኢትዮ ቴሌኮም አሰራሩን በማዘመን ከተለያዩ ተቋማት ጋር በመጣመር በርካታ አገልግሎቶችን በቴሌብር አማካኝነት እያቀረበ ይገኛል። ቀደም ብሎ ግብር ክፍያና የትራፊክ ህግ መተላለፍ ቅጣትን በቴሌብር አማካኝነት መክፈል የሚያስችል አሰራር ተግባራዊ ተደርጓል። አሁን ደግሞ ሎተሪን በቀላል መንገድ ማግኘት የሚቻልበት አሰራር በእያንዳንድ የእጅ ስልክ ላይ በመቅረቡ ለአገልግሎቱን ፈላጊ ህብረተሰብ ምቹ ሁኔታ ተፈጥሯል ብለዋል።
የብሔራዊ ሎተሪ አስተዳደር ዋና ዳይሬክተር አቶ ገረመው ጋርጄ በበኩላቸው፤ ዲጂታል ሎተሪ አገልግሎቱን ለማስጀመር ከኢትዮ ቴሌኮም ጋር ለረጅም ዓመታት ውይይት ሲደረግ መቆየቱን አስታውሰዋል።
አሁን ላይ ያሉት የቴሌ አመራሮች ለዲጂታል ኢኮኖሚ ያላቸው መልካም አስተሳሰብና ጥረት ለአገልግሎቱ ዕውን መሆን ከፍተኛ አስተዋጽኦ በማድረጋቸው ምስጋና ይገባቸዋል ሲሉ ተናግረዋል።
ከኢትዮ ቴሌኮም ጋር በመተባበር ተግባራዊ በሆነው የዲጂታል ሎተሪ አገልግሎት በርካታ ደንበኞች እንደሚገኙ ይጠበቃል ያሉት ዋና ዳይሬክተሩ፤ ዲጂታል ሎተሪ አገልግሎቱን በአጭር ጊዜ በሚሊዮን የሚቆጠሩ ዜጎች ዘንድ እንዲዳረስ ጥረት እንደሚደረግ ጠቁመዋል።
የብሔራዊ ሎተሪ አስተዳደር 14 ዓይነት የሎተሪ ዕጣዎች እንዳሉት የገለጹት አቶ ገረመው፤ አድማስ የተሰኘው ዲጂታል ሎተሪ 15ኛ የሎተሪ አይነት ሆኖ መቅረቡን አስታውቀዋል።
እንደ ዋና ዳይሬክተሩ ገለጻ፤ ዲጂታል ሎተሪው ተግባራዊ ቢደረግም በሎተሪ አዟሪዎች አማካኝነት ደንበኞች ጋር የሚደርሱ የወረቀት ሎተሪዎች እንደከዚህ ቀደሙ ሁሉ ገበያ ላይ እንዲውሉ ይደረጋል።
በመሆኑም በቀጣይ ዓመታት የህትመት ወጪን ለመቀነስ የዲጂታል ሎተሪዎች የወረቀት ሎተሪዎችን እንዲተኩ መደረጉ ስለማይቀር ሎተሪ አዟሪዎች ከወዲሁ ሌሎች የሥራ አማራጮችን ማሰብ ይኖርባቸዋል ሲሉ ዋና ዳይሬክተሩ መልዕክት አስተላልፈዋል።
በ1954 ዓ.ም በ50 ሺህ ብር መደበኛ ዕጣ ሥራውን የጀመረው የብሔራዊ ሎተሪ አስተዳደር ከአጠቃላይ ገቢው 10 በመቶ ለሎተሪ ህትመት ወጪ እንደሚያውል አስታውቋል።
ከኢትዮ ቴሌኮም ጋር በመተባበር የሚቀርበው የዲጂታል ሎተሪ ዕጣ የህትመትና የአገልግሎት ወጪ ስለሌለው ተመሳሳይ ዲጂታል ሎተሪዎችን እያስፋፋ እንደሚሄድ ብሔራዊ ሎተሪ አስተዳደሩ ጠቁሟል።
ጌትነት ተስፋማርያም
አዲስ ዘመን ሐምሌ 9 ቀን 2014 ዓ.ም