
ሰሞኑን በማህበራዊ ሚዲያው አማካኝነት አጀንዳ ሆኖ ብዙኃኑን ሲያነጋግር ከከረሙ ርዕሰ ጉዳዮች አንዱ የአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ጤና ሳይንስ ኮሌጅ ተማሪው ቢኒያም ኢሳያስ ጉዳይ ነው።
አካል ጉዳተኞችን መደገፍና ማበረታት እንጂ ሕልማቸው ማቀጨጭ አይገባም በሚል I stand with Biniyam!! የሚል የማህበራዊ ሚዲያ ንቅናቄ በማድረግ የተማሪ ቢኒያምን ጉዳይ ሰዎች እዚያና እዚህኛው ጫፍ ላይ ሆነው ሲከራከሩበት ከርመዋል።
የህግ ባለሙያዎችና የአካል ጉዳተኞች ጉዳይ ይመለከተናል ያሉ ሰዎች በሙሉ ጉዳዩን አንስተው ብዙ ብለውለታል። የአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የጤና ሳይንስ ኮሌጁም ጋዜጠኞችን ጠርቶ በተማሪ ቢኒያም ጉዳይ ኃላፊነቱን እንደሚወስድ መግለጹም የሚታወስ ነው።
ለመሆኑ ተማሪ ቢኒያም ማን ነው ?፤ ወጣት ቢኒያም ኢሳያስ በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ በጥቁር አንበሳ ስፔሻላይዝድ ሆስፒታል የ5ኛ ዓመት የሕክምና ትምህርት ክፍል ተማሪ ነው። ከልጅነቱም ጀምሮ ሐኪም የመሆን ሕልም የነበረውና በትምህርቱ ጎበዝና መልካም ስብዕና ያለው መሆኑን በቅርብ የሚያውቁት ጓደኞቹና መምህራኑ ይመሰክራሉ።
ተማሪ ቢኒያም በተፈጥሮ ምክንያት አካል ጉዳተኛ ቢሆንም፤ ብዙዎች በሙሉ አካል የሚከብዳቸውን የሕክምና ትምህርትም እስከ 5ኛ ዓመት በትጋት ከመማሩም ባሻገር በትምህርት ውጤቱም ሶስት ነጥብ ስምንት በማምጣት ጉብዝናውን ማስመስከር የቻለ ተማሪ ነው።
ነገር ግን ሊመረቅ ሁለት ዓመት የማይሞላ ጊዜ ሲቀረኝ በአካል ጉዳተኝነቴ ምክንያት ሐኪም መሆን አትችልም ተብዬ ትምህርቴን እንዳቋርጥና ሌላ ትምህርት እንድትጀምር የሚል አስደንጋጭ ውሳኔ ተላልፎብኛል የሚለው ወጣት ቢኒያም፤ ይህ በደል በእኔ ላይ መተላለፉ አግባብ አይደለም ሲል ዩኒቨርሲቲውን በአደባባይ ሞግቷል።
በዚህ ወቅት ነበር አካል ጉዳተኛነቱ ሳይበግረው ተምሮ ጥሩ ውጤት ሲያመጣ የከረመን ልጅ በዚህ መልኩ ከትምህርቱ ማራቅ ተገቢ አይደለም የሚሉ ድምፆች ከተለያዩ አቅጣጫዎች መሰማት የጀመሩት።
የኢትዮጵያ ፕሬስ ድርጅትም የተማሪ ቢኒያምን ጉዳይ ምን ትላላችሁ ሲል ዩኒቨርሲቲውን ጠይቆ ነበር፤ ዩኒቨርሲቲው አመራሮችም በበኩላቸው ተማሪ ቢኒያም ጉዳይ ሕግና አሰራር እስከሚፈቅድ ድረስ መጓዙንና ላለፉት ስምንት ወራት ሲመለከቱ መቆየታቸውን ይገልጻሉ።
የአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የጤና ሳይንስ ኮሌጅ ዋና ዳይሬክተር ዶክተር አንዱአለም ደነቀ የትምህርት ተቋሙን በመወከል በሰጡት ምላሽ መሰረትም ተማሪ ቢኒያም የአራተኛ ዓመት ተማሪ እያለ የግራ እጁ ላይ በተፈጥሮ የአካል ጉዳት ያለበት መሆኑ በመምህራን መለየቱን ያስታውሳሉ። ከዚህ በኋላ ይህ ጉዳት በህክምና ትምህርቱ ላይ ያለው ተፅዕኖ እንዲለይ በሚል ጉዳዩ ወደ ዲን ጽህፈት ቤት ተመርቶት ነበር ይላሉ።
ቢያንስ አንድ የህክምና ትምህርት ተማሪ መለስተኛ ቁስል መስፋት፣ የቆመ የልብ ምት ማስነሳት፣ ኦክሲጅን መስጠት፣ ቱቦ በሰውነት ውስጥ ማስገባት እንዲሁም ወሊድ የመሳሰሉትን ሕክምናዎች መስጠት ግዴታ መሆኑንም ዶክተር አንዷለም ይናገራሉ።
እንደ ዶክተር አንዷለም ገለጻ፤ ኮሌጁ ባዋቀረው ኮሚቴ በቀረበለት ምክረ ሀሳብ መሰረት ተማሪ ቢኒያም ከጤና ትምህርት ጋር ተያያዥነት ያላቸው ትምህርቶችን እንዲማር ወስኗል። በህክምና ፋርማሲ፣ በህክምና ላብራቶሪ ሳይንስ እንዲሁም በህክምና ላቦራቶሪ በመረጠው ዘርፍ እንዲማርና ተጨማሪ ትምህርት ሳይማር ባችለር ኦፍ ባዮሜዲካል ሳይንስ እንዲሰጠው የሚል ውሳኔ እንደተላለፈም ያስታውሳሉ።
ተማሪው የአካል ጉዳት እያለበት ለህክምና ትምህርት ዘርፍ በመመደቡና ለደረሰው ችግር ዋነኛ ምክንያት የህክምና ኮሌጁ ተማሪዎችን ራሱ መመልመል ያለመቻሉ ነው ያሉት ዶክተር አንዷለም፤ የህክምና ኮሌጁ በተማሪ ቢኒያም ላይ ለተከሰተው ችግር ኃላፊነት እንደሚወስድ ገልጸው ነበር።
ከዚህ ጋር ተያይዞ በቀጣይ የሚገቡ ተማሪዎች በቅበላ ጊዜ ሙሉ ምርመራ እያደረገ ለማስገባት እንደሚሰራም ነው የሚጠቁሙት።
የሆነ ሆኖ ተማሪ ቢኒያም ዩኒቨርሲቲው ባችለር ኦፍ ባዮሜዲካል ሳይንስ ዲግሪው ይሰጠው በሚል ባስተላለፈው ውሳኔ እንደማይስማማ በመግለጽ፤ የሕክምና ዶክትሬት ትምህርቱን ሙሉ በሙሉ ማጠናቀቅ እንደሚፈልግ በግልጽ ነበር የተናገረው።
አዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ በትላንትናው ዕለት በድጋሚ ባወጣው መግለጫ ደግሞ የተማሪ ቢኒያምን ዳግም ቅሬታ በመቀበል ውሳኔውንም መቀየሩንም ይፋ አድርጓል።
የተማሪ ቢኒያም ኢሳያስን ትምህርት በተመለከተ የአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ጤና ሳይንስ ኮሌጅ እና የሕክምና ትምህርት ቤት ለተማሪው የትምህርት ሂደት ይረዳሉ ያሏቸውን አማራጮች ማቅረባቸው ይታወሳል። ሆኖም ተማሪ ቢኒያም ብቸኛ ፍላጎቱ የሕክምና ትምህርትን መማር እንደሆነ በመግለጹ የሕክምና ትምህርቱን እንዲቀጥል መወሰኑን ነው ያሳወቀው።
ከዚህ ባለፈም እስካሁን የተቋረጡ ትምህርቶችንም በማካካስ ትምህርቱን ካቆመበት እንዲቀጥል ሲል ዩኒቨርሲቲው ምላሹን ሰጥቷል።
የኢትዮጵያ ፕሬስ ድርጅት የህግ ባለሙያው አቶ ገመቺስ መኮንንን ስለ ተማሪ ቢኒያም ኢሳያስ ምን ይላሉ ሲል አነጋግሯል።
የህግ ባለሙያው እንደሚሉት ፤ ይህ አይነቱ ችግር መጀመሪያም እንዳይፈጠር ጥንቃቄ መደረግ ነበረበት። አምስት ዓመታት ተገቢውን ክትትል ባለማድረግ ወይም በቸልተኝነት ተማሪው የህክምና ትምህርቱን እንዲከታተል ተደርጎ በመሃል አቋርጥ መባሉ ከመነሻው ሂደቱ ችግር እንዳለበት ነው የሚያሳየው።
ይህን አይነት መሰል ችግሮች ቀድሞውኑ የመከታተል ኃላፊነት ያለበት የመንግሥት አካል አለ፤ በተለይ በትምህርት ሚኒስቴርም ሆነ በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ጤና ሳይንስ ኮሌጅ የሚገኙ ጉዳዩ የሚመለከታቸው አካላት
ተማሪው ላይ ያለውን ጉዳት በተመለከተ ቀድሞውኑ ክትትል ሳያደርጉ ለደረሰው መጉላላት ተጠያቂ መሆን አለባቸው፤ ለደረሰው ችግር እነዚሁ አካላት ኃላፊነት አለባቸው ይላሉ።
ከህግ አንጻር መመልከት ቢቻል ሕገ መንግስቱን እንዲሁም የፍትሐ ብሔር ሕጉ በመንግሥት የተጣለበትን ኃላፊነት ያልተወጣ አካል ተጠያቂ ማድረግ እንደሚቻል፣ ጉዳት የደረሰበት አካል ጉዳዩን የዳኝነት ስልጣን ላለው አካል የማቅረብ እና ፍትህ የማግኘት መብት እንዳለው ይደነግጋሉ።
ዳግማዊት ግርማ
አዲስ ዘመን ሐምሌ 9 ቀን 2014 ዓ.ም