
አዲስ አበባ:- የጠቅላይ ሚኒስትር ጽሕፈት ቤት ከተጠሪ ተቋማት ጋር በክረምት የበጎ ፈቃድ አገልግሎት በሻሸመኔ ከተማ የአቅመ ደካሞችን ቤት እድሳት አስጀመረ።
ከሁለት ዓመት በፊት በጠላት ኃይሎች ከፍተኛ ጉዳት ደርሶባት የነበረችው የሻሸመኔ ከተማ አሁን ላይ አንድ ዓመት ባልሞላ ጊዜ ውስጥ ወደነበረችበት ተመልሳለች ሲሉ የሻሸመኔ ከተማ አስተዳደር ከንቲባ ገለጹ።
በጠቅላይ ሚኒስትር ጽሕፈት ቤት የሀገራዊ ፕሮጀክቶች ክትትል ዘርፍ ሚኒስትር ዴኤታ ወርቁ ጓንጉል በመርሐ ግብሩ ላይ እንደገለጹት፤ ሕዝብና መንግሥት ከተባበሩ የማይፈቱት ችግር የለም።
የጠቅላይ ሚኒስትር ጽሕፈት ቤት በዘንድሮው የክረምት በጎ ፈቃድ አገልግሎት በሻሸመኔ ከተማ የ35 አቅመ ደካሞች ቤቶችን በማደስ ለማስረከብ ሥራ ጀምሯል።
በቀጣዮቹ ሁለት ቀናትም በምዕራብ አርሲ ዞን ሁለት ወረዳዎች ድጋፍ ለሚያስፈልጋቸው ወገኖች የሰባት ሚሊዮን ብር የትምህርት መርጃ ቁሳቁስ ድጋፍ እንደሚደረግ ተገልጿል።
በቤት እድሳት ማስጀመር መርሐ ግብሩ ላይ የተገኙት የጠቅላይ ሚኒስትር ጽህፈት ቤት አመራሮች በሰጡት አስተያየት ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አቢይ አህመድ ያስጀመሩትን የአረንጓዴ አሻራና የአቅመ ደካማ ቤቶች እድሳት ለአገር ጠቃሚ የሆነ ፕሮጀክት ነው። የአቅመ ደካማ ቤቶችን ማደስ፣ አብሮነታችንና ህብረ ብሄራዊ አንድነታችን ለማጠናከር ወሳኝ ነው። ይህን በጎ ተግባር አጠናክረን እንቀጥላለን ሲሉ ተናግረዋል።
የሻሸመኔ ከተማ ከንቲባ አቶ ወሾ ከድር በበኩላቸው ፤የፌዴራል ተቋማት አስታዋሽ ላጡና በከፋ ድህነት ውስጥ ለሚገኙ አረጋውያን ቤት ለመስራት ከተማዋን በመምረጣቸውን አመስግነዋል።
ከሶስት ዓመት በፊት በጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር ዐቢይ አህመድ የተጀመረው የበጎ ፈቃድ አገልግሎት ብዙ ጧሪ ያጡ አባቶችና እናቶችን ከመንገድ ላይ በማንሳት የቤት ባለቤት እያደረገ መሆኑን ጠቁመው፤ በተለያዩ ከተሞች በመስጊድ፣ በቤተክርስቲያንና በመንገድ ላይ የሚገኙ በርካታ የሆኑ አቅመ ደካሞች በበጎ ፈቃድ አገልግሎት የመኖሪያ ቤት ተጠቃሚ ሆነዋል። የቤት እድሳት ፕሮግራሙ ሌሎች በርካታ ዜጎችን ለመታደግ ትልቅ የበጎ አድራጎት ጥሪ ነው ሲሉ ከንቲባው ተናግረዋል።
በሌላ በኩልም ከሁለት ዓመት በፊት በጠላት ኃይሎች ከፍተኛ ጉዳት ደርሶባት የነበረችው የሻሸመኔ ከተማ አሁን ላይ አንድ ዓመት ባልሞላ ጊዜ ውስጥ ወደነበረችበት ተመልሳለች ያሉት ከንቲባው፤በህዝብ ተሳትፎ ብቻ 800 ቤቶች በላይ ተመልሰው ተገንብተው አሁን ነዋሪዎቿ በፍቅርና በመቻቻል እየኖሩባት መሆኑን ገልጸዋል።
በወቅቱ እንደ ቢቢሲ ያሉ ዓለም አቀፍ ሚዲያዎች ሳይቀር ከተማዋ ከደረሰባት ውድመት አንጻር ወደ ነበረችበት ለመመለስ ከ50 ዓመት በላይ ይወስዳል ብለው ሲዘግቡ እንደነበር አስታውሰው፣ የሻሸመኔ ከተማ ህዝብና መላ ኢትዮጵያውያን በአጭር ጊዜ ውስጥ ሻሸመኔ ከተማ ወደነበረችበት ለመመለስ ያሳዩት ትብብር ኢትዮጵያዊ አንድነታችን ያሳየ መሆኑን ገልጸዋል።
በቤት እድሳት ማስጀመሩ መርሐግብር የመንግሥት ኮሙዩኒኬሽን አገልግሎት ሚኒስትር ዶክተር ለገሰ ቱሉ፣ የጠቅላይ ሚኒስትር ጽህፈት ቤት አመራሮችና የምዕራብ አርሲ ዞን ዋና አስተዳዳሪና ሌሎች አመራሮች መገኘታቸው ታውቋል።ቤት በማደስ በመርሐ ግብሩ ላይ 16 የፌዴራል ሴክተር መስሪያ ቤቶች እንደሚሳተፉ ተመላክቷል።
ሞገስ ተስፋ
አዲስ ዘመን ሐምሌ 9 ቀን 2014 ዓ.ም