
አዲስ አበባ፡- ሁሌም ኢትዮጵያ ውስጥ ከሚከሰቱ ጥፋቶች ጀርባ ህወሓት ይጠፋል ብለን አናምንም ሲሉ የትግራይ ዲሞክራሲ ፓርቲ የህዝብ ግንኙነት ኃላፊ ተናገሩ። ትግራይን መልሶ ለመገንባት የተያዘውን በጀት ህወሓት ለራሱ እኩይ አላማ እንዳያውለው ጥንቃቄ ማድረግ እንደሚገባም አሳስበዋል።
የትግራይ ዲሞክራሲ ፓርቲ የህዝብ ግንኙነት ኃላፊ አቶ ሙሉብርሃን ኃይሌ በተለይ ለኢትዮጵያ ፕሬስ ድርጅት እንደገለጹት፤ አሸባሪው ህወሓት በለውጥ ተቃራኒ መጓዝ ከጀመረ ጊዜ ጀምሮ በኢትዮጵያ በርካታ ግጭቶችን ፈጥሯል፤ አገርን የማፍረስ ሙከራዎችንም አድርጓል።
ህወሓት በአገር ውስጥና ከአገር ውጭ ሆነው ሀሳቡን ከሚደግፉ ኃይሎች ጋር በመተባበርና በማስተባበር ግጭቶችን ሲመራና ሲያስተባብር ነበር ያሉት አቶ ሙሉብርሃን፤ ሁሌም ኢትዮጵያ ውስጥ ከሚከሰቱ ጥፋቶች ጀርባ ህወሓት ይጠፋል ብለን አናምንም ብለዋል።
ወደ ኋላ መለስ ብለን ስናይ ህወሓት ከሸኔ ጋር በይፋ ለመስራት መግለጫ ሲያወጡ ነበር ያሉት ኃላፊው፤ ሰሞኑን ባሉ ግጭቶችም ህወሓት ከበስተጀርባ እንዳለበት መገመት ይቻላል ብለዋል።
እንደ አቶ ሙሉብርሃን ገለጻ፤ ቡድኑ ወደ መቀሌ ከገባ በኋላ በርካታ የሽብር ሥራዎችን ሲሰራ እንደነበር ማስታወስ ይቻላል። ሼኔን ጨምሮ ከበርካታ የሽብር ቡድኖች ጋር በጋራ ሲሰራ ነበር፤ መስራት ብቻ ሳይሆን መቀሌ ላይ ቢሮ ከፍቶላቸው ሲንቀሳቀሱ
ነበር። በቅርቡም አላማውን የሚደግፉ በርካታ የሽብር ቡድኖችን እንዳሰለጠነ መረጃዎች አለን፤ የሚመስሉትን በማስተባበር አገር ለማተራመስ እየሰራ ነው።
ሰላምና ድርድር ከህወሓት ተፈጥሮአዊ ባህሪ ጋር የማይሄዱና ለጊዜ መግዣነት የሚጠቀማቸው ስልቶቹ ናቸው ያሉት አቶ ሙሉብርሃን፤ ችግሮችን በድርድር የመፍታት ባህሪ ህወሓት የለውም፤ ችግሮችን በድርድር መፍታት የሚችል ቢሆን ኖሮ ጦርነት የሚያስገባው ጉዳይ ሳይኖር ጦርነት አይጀምርም ነበር ብለዋል።
አቶ ሙሉብርሃን እንደተናገሩት ህወሓት ፍላጎቱ አንድ ነው፤ እሱም በጉልበት ስልጣን መያዝ ነው። በጉልበት ኢትዮጵያን የማይመራ ከሆነ ደግሞ ማፍረስ ተቀዳሚ አላማው በመሆኑ በየቦታው ግጭቶችን እየፈጠረ ይገኛል።
“አገር የሚገነባው በኢኮኖሚ ብቻ አይደለም፤ የዳበረ አዕምሮና አስተሳሰብ ከሌለ ትርጉም የለውም” ያሉት አቶ ሙሉብርሃን፤ የህወሓት አመለካከትና አስተሳሰብ አውዳሚ ነው ሲሉም ገልጸዋል።
ኃላፊው እንደተናገሩት፤ ትግራይ ውስጥ የነበሩ መሰረተ ልማቶችን ያፈረሳቸው ህወሓት ነው። በዚህ ሁኔታ ትግራይን መልሶ መገንባት ይቻላል ብለን አናምንም። ይህ አሸባሪ እስካለ ድረስ ትግራይን መልሶ ለማቋቋም የተያዘው 300 ሚሊዮን ዶላር በጀትም በጥንቃቄ ለህዝቡ ጥቅም እንዲውል ካልተደረገ ህወሓት ለራሱ እኩይ አላማ እንደሚያውለው ግልጽ ነው ብለዋል።
በትግራይ ክልል በትክክል የመልሶ ግንባታ ሥራ ለመስራት፣ ሰላም፣ ዲሞክራሲ፣ ፍትህና እኩልነት እንዲሰፍን ከተፈለገ የህወሓት ኃይል ከክልሉ መውጣት መቻል አለበት። ካልሆነ ግን በጀቱ ለመሰረተ ልማት ግንባታ ሳይሆን ለህወሓት አላማ መጠቀሚያ ይሆናል፤ እንዲሁም ዘላቂ ልማትና መልሶ ግንባታ ይመጣል ተብሎ አይታሰብም። ልማት ያለው የለማ አስተሳሰብ ላይ ነው፤ ህወሓት ደግሞ ሰላምና ልማት የሚባሉ ነገሮች የሉትም። አሁንም በማሸነፍና በመሸነፍ ትርክት ውስጥ ያለ ቡድን ነው፤ ስልጠናዎችን በማዘጋጀት ተጨማሪ ችግሮችን ለመፍጠር እየተዘጋጀ ያለ ኃይል በመሆኑ ይህ ኃይል እስካለ ድረስ ትግራይን ወደ ልማት መመለስ አይታሰብም ብለዋል።
ሞገስ ጸጋዬ
አዲስ ዘመን ሐምሌ 9 ቀን 2014 ዓ.ም