አገር ወዳድነት ሲባል ጥልቅና ጥብቅ ትርጉም የሚሰጥ ነው፤ ነፍሳችን ከአገራችን ጋር ያላትን መልከ ብዙ ቁርኝት የሚገልጽና ስሜቱን እንድናጋባው የሚያስገድድም ነው። በእርግጥ ስሜቱ በቃላት የሚገለጽ አይደለም። ይሁንና በግርድፉ ስናየው አገርን መውደድ ማለት ለአገርና ለሕዝብ ታማኝ ሆኖ የቻሉትን ማድረግም ነው። በተለይም ሕዝብንና አገርን ከማገልገል፣ ከመደጋገፍ አንጻር ጎላ ተደርጎ ይታያልም። መከባበርን ማስረጽና ለወገን መቆርቆርም ነው።
አገር ወዳድነት የሌላ አገርን እያዩ ምራቅ መዋጥ፤ አለያም ለመኖር መመኘት ሳይሆን በአገር ላይ ሠርቶ ለመለወጥ ማሰብና ችግሮችን በጋራ ለመፍታት መታተርም ነው። ከራስ ያለፈ ነገር ለወገንና ለአገር ማበርከትም እንደሆነ ብዙዎች ይስማሙበታል።
የአንድ አገር ልጆች በተለያዩ ጉዳዮች መለያየታቸው ተፈጥሯዊ ነው። ይህ ደግሞ በልዩነቶች ውስጥ ያለውን አብሮነት ለማጉላትና አብሮ ለመሥራት ያግዛልና አገር መውደድ ማለት ይህንንም አካቶ መጓዝ እንደሆነ ይታመንበታል። በዚህ መሠረት ላይ ሆኖ መትጋትንም ይይዛል። በተለይም ሙሉ ሰው ያደረጉንና የተገነባንባቸውን ማህበራዊ እሴቶች ጠብቀን ለሌሎች የሚተርፍ ሥራ መሥራት አገር ወዳድ እንደሆንን የምንገልጥበት እንደሆነ ይገለጻልም። እናም ይህንን መነሻ በማድረግ ስለአገራቸው ገዷቸው ጊዜያቸውን፣ ጉልበታቸውንና ሀብታቸውን የሚሰጡና የሚሠሩ በርካቶች መሆናቸው እሙን ነው። ከእነዚህ መካከል ደግሞ ለዛሬው የ‹‹ሀገርኛ›› አምድ ዝግጅታችን ይዘን የቀረብንላችሁ እንግዳ አንዱ ናቸው።
እንግዳችን በሥነምግባር የታነጸ ትውልድ ማፍራት ላይ የተሰማሩ ሲሆኑ፤ በባህላዊና ሃይማኖታዊ እሴቶች ተኮትኩተው የሚያድጉ የነገ አገር ተረካቢዎችን በብዙ መልኩ እየገነቡ ይገኛሉ። በራሳቸው ወጪ ትምህርት ቤት ከፍተው በየአካባቢቸው ስለአገራቸውና ስለወገናቸው እንዲገዳቸውም እያደረጉ ናቸው። ይህ ትምህርትቤት ትውልድን በሥነምግባር ከማነጽ ባሻገር ለወጣቱ የሥራ ዕድል የፈጠረና ለተማሪዎች ደግሞ ጥራት ያለው ትምህርት የሚሰጥ ነው።
የግለሰቡ ጥረት አጥብቀን የምንሻቸውን እሴቶች የሚጠብቅ እና የሚያረጋግጥ ሲሆን፤ የአገር ወዳድነት ባህሪንም በተግባር ያሳየ ነው። ግለሰቡ መምህር አርጋው ጉግሳ ይባላሉ። የቡናፋየር ትምህርትቤት ሥራአስኪያጅና ባለቤት ናቸው። ቀደም ሲል መምህርም ስለነበሩ በትምህርትቤቱ ውስጥ ያስተምራሉ።
የአገራቸው የወደፊት ዕጣ ፈንታ በጣም የሚያሳስባቸው ሲሆኑ፤ ይህንን መፍታት የሚቻለው ትምህርት ላይ በመሥራት ነው ብለው በማመን ትምህርትቤት ከፍተው ትውልድን በመቅረጽ ላይ ተሰማርተዋል። ለዚህ ደግሞ መምህር መሆናቸው በእጅጉ እንዳገዛቸው ይናገራሉ።
ለትውልድ መቆርቆራቸውና የሥነምግባር ክፍተቶችን በስፋት ማየታቸው ወደዚህ ተግባር እንደመራቸው ያጫወቱን መምህር አርጋው፤ የአገር ፍቅርን በእያንዳንዱ ዜጋ ላይ ለመዝራት ትምህርት ወሳኝ እንደሆነ ያነሳሉ። ትውልዱን በሥነምግባር ኮትኩቶ ማሳደግ የታለመበትን የአገር እድገት ጉዳይ በአጭር ጊዜ ያሳካል ባይም ናቸው። ትምህርት ቤቶች የአዲሱ ትውልድ መገኛ ቦታዎች እንደመሆናቸው መጠን ሀገር ወዳድ ትውልድን ለመቅረጽ ወሳኝ ስፍራዎች መሆናቸውንም ይገልጻሉ።
በመምህርነት ዘመናቸው ከሚመኙት ነገር አንዱ በሥነ ምግባር የታነጸ፣ የማኅበረሰቡን ወግና ባሕል ያከበረ፣ ታላላቆቹን የሚያዳምጥ፣ ፈጣሪውን የሚፈራ፣ መምህራንን የሚያከብርና ለወላጆቹ የሚታዘዝ፣ በትምህርቱ ጎበዝና አገሩን የሚያስጠራ ተማሪን መመልከት ነበር። ይህ ደግሞ በአሁኑ ጊዜ ለማየት እጅግ አስቸጋሪ ነው። እናም ይህንን ለመፍታት ሥራውን በተግባር የሚፈጽም አካል ያስፈልጋል። ለዚህም ነው ትምህርትቤት መገንባት የሚለውን ሀሳብ ለአዕምሯቸው የነገሩት።
ትምህርት ቤት መገንባት ትልቅ የኢኮኖሚ አቅምን ይጠይቃል።ህልምም በአንድ ጊዜ የሚሳካበት አይደለም የሚሉት ባለታሪካችን፤ ህልማቸውን እውን ለማድረግ ከአስር ዓመታት በላይ ጠብቀዋል። ይሁን እንጂ ትምህርትቤት ሲታሰብ በእርሳቸው አስተሳሰብ ከምንም በፊት ሥነምግባር ይቀድማል ነው።
ለመማር፣ ለመሥራት፣ ነግዶ ለማትረፍ፤ አርሶ ለመብላት ሥነምግባር ግድ እንደሆነ የሚያነሱት መምህሩ፤ በሥነምግባር የታነጸ ትውልድ የሥራ ተነሳሽነት ይኖረዋል ባይ ናቸው። ስለዚህም ትውልድን በሥነምግባር ማነጽ እንዲሠራ ማዘጋጀት፤ የአገሩን ፍቅር እንዲገልጥ ማበርታትና በእርሱ ተግባር የአገር ክብር እንዲጠበቅ ማስቻልም ነው። ስለሆነም ለሥነምግባር ልዩ ትኩረት ሰጥተን በትምህርትቤታችን እንድንሠራ ሆነናልም ብለውናል።
መምህር አርጋው ህልማቸውን ለማሳካት ሲሉ ከመምህርነት ሙያቸው ጎን ለጎን የተለያዩ ሥራዎች ሞክረዋል። አንዱ እህት ኩባንያ መክፈት ሲሆን፤ ይህም ከቤተሰቦቻቸው የወረሱትና ስኬታማ የሆኑበት ሥራ ነው። ብዙ ገንዘብ እንዲያካብቱበት አምነው ገብተውበታል። እንዲያውም ህልማቸው ስኬት ላይ የደረሰው በእርሱ አማካኝነት እንደሆነ ያስረዳሉ።
ኩባንያቸው ‹‹አርጋው የመለዋወጫ ዕቃ ማከፋፈያ›› የሚባል ሲሆን፤ መጀመሪያ አካባቢ ግማሽ ቀን የሚሠሩበት ነበር። ሆኖም ውጤታማ ሊሆኑ ስላልቻሉ አቁመው የነገ የአገር ተረካቢ ትውልዶችን ለማቆም የሚወዱትን ሙያ ለጊዜው አቋረጡት። ሙሉ ጊዜያቸውን ለኩባንያው ሰጥተውም የገቢ ምንጫቸውን ማካበት ላይ አተኮሩ። በዚህም በላቲንኛ ‹‹ቦናፋይር›› በአማርኛ ‹‹እውነት›› የተሰኘ ስያሜን የያዘ ትምህርትቤታቸውን በእህት ኩባንያቸው ገቢ ገንብተውና እስከ ቅርብ ጊዜ ለሠራተኞች ደመወዝ ከፍለው እርሳቸውንም ተማሪዎችንም አነጹበት።
ከሀዋሳ ከተማ 26 ኪሎሜትር ርቃ በምትገኘው የትውልድ መንደራቸው ለኩ ከተማ ላይ ይህንን ትውልድን በሥነምግባር ማነጽ አለብኝ በሚል ትምህርትቤት ለመክፈት ሞክረው እንደነበር ያጫወቱን መምህር አርጋው፤ ነገሮች ቀላል እንዳልሆነላቸው ያስረዳሉ። ምክንያቱ ደግሞ የገንዘብ እጦት መሆኑን ያነሳሉ።
ያሰቡትን ለማሳካት ተኝተው የማያድሩት መምህር አርጋው፤ የአሁኑን ትምህርትቤታቸውን እንደአገር ተመራጭና ሞዴል አድርገውታል። ለዚህም ማሳያው ደግሞ በአገር ደረጃ በአገር ባለሀብት የተሠራና ሁለቱን ሳይክል ያቀፈ ደረጃ አራት ትምህርትቤት የእርሳቸው ብቻ መሆኑ ነው። እንደ አገር ደረጃ አራት የተሰጣቸው ትምህርትቤቶች ከአምስት አይበልጡም። እነርሱም ቢሆኑ ከአንዱ በስተቀር በውጭ ባለሀብቶች የሚመሩ ናቸው። አንዱ በአገር ሀብት የተሠራ ቢሆንም ከአንደኛ እስከ አራተኛ ክፍልን ብቻ የያዘ ነው። ስለዚህም የእርሳቸው ትምህርትቤት ከሥነምግባር ባለፈ በሞዴል ትምህርትቤትነቱም የታወቀ ነው። ‹‹የአገሩን ሰርዶ በአገሩ በሬ›› የሚለው ብሂል የሚያረጋግጥም ነው።
የትምህርት ሥራ የቢዝነስ ሳይሆን ትውልድን የማፍራትና አገርን የመገንባት ጉዳይ እንደሆነ የሚገልጹት መምህር አርጋው፤ ሥራቸውን በ2009 ዓ.ም መጋቢት ላይ ቦታውን ከግለሰብ በመግዛት ጀምረዋል። ከአራተኛ ክፍል በኋላ ያለውን የመማሪያ ክፍል በየዓመቱ እየገነቡም ነው ስምንተኛ ክፍል የደረሱት።
ለአገራቸው የራሳቸውን አሻራ ማኖር እንዳለባቸው አምነው ወደዚህ ዘርፍ የገቡት ባለታሪካችን፤ ለተግባሩ ብዙ ዋጋ መክፈላቸው ምንም እንደማይመስላቸው ያነሳሉ። ግዴታቸው እንደነበርም ይናገራሉ። ዛሬ ላይ ቢሆንም እንዲህ ዓይነት ፈተና ቢገጥማቸው እንደሚያደርጉት ያስረዳሉ። ምክንያቱም ትውልዱን ከመታደግ የሚበልጥ አንድም ነገር እንደሌለ ያምናሉ። የትውልድ ሞራል ላይ እየሠሩ በመሆናቸውም ደስተኛ ናቸው።
እርሳቸው መምህር መሆናቸው የተማሪ ጉዳይ እጅጉን ያሳስባቸዋል። ከምን አንጻር ከተባለ መልኩ ብዙ ነው። የመጀመሪያው የሥነምግባር ጉዳይ ሲሆን፤ ሁለተኛው የትምህርት ጥራት ነው። አንዳንዴም በሙያው የሚሠራ ሰው በብዛት አለማየታቸው ሌላው ጉዳይ ነው።እናም ‹‹የእኔ ድርሻ ምንድነው›› እንዲሉ አድርጓቸዋል።
‹‹ሙያን ማፍቀር ህልምን መውደድ ነው።ህልም ያለው ሰው ደግሞ በትውልድ ላይ ሲሠራ አገራዊ እሴቱን ያሰፋል። አሻራውንም የጸደቀ ተክል ያደርገዋል። ለዚህ ስኬቱ ደግሞ የማይቆፍረው ድንጋይ አይኖርም›› የሚሉት መምህር አርጋው፤ ትምህርትቤቱን እንዲከፍቱ ብርታት የሰጣቸው በሥራና በተግባር ያዩት ልምዳቸው እንዲሁም የልጆቻቸው ማረፊያ ማጣት እንደሆነ ይናገራሉ።
አገርን ማየት የሚቻለው በሚፈጠረው ዜጋ ማንነት ልክ ነው። ማንነትን ከመሥራት አኳያ ደግሞ ትምህርትቤቶች የሚኖራቸው ሚና ላቅ ያለ ነው።ከዚህ አኳያ ትውልድ ላይ ሠርቻለሁና በጥቂቱም ቢሆን አበርክቶዬን አይቻለሁም ይላሉ።
እርስ በእርስ መተጋገዝ ብዙ ሰዎችን በብዙ ተግባር ማሻገር ይቻላል። ለምሳሌ፡- ትምህርትቤቱ ከመማር ማስተማሩ ባሻገር አንባቢ ትውልድ ለመፍጠር ተማሪዎች እቤታቸው በየሳምንቱ አንድ መጸሐፍ ይዘው እየሄዱ እንዲያነቡ ያደርጋል። በክፍል ኃላፊዎቻቸው በኩልም ቸክ ሊስት እየተሞላ ጭምር የሚገመገሙበት ሥርዓት ፈጥሯልም። ሌላው ‹‹ጆርናል ራይቲንግ›› የሚባል ተግባርን በመፍጠር ጸሐፊ የሚሆኑበት ሥርዓት ዘርግቷል።በተመሳሳይ ‹‹ኦፕን ሀውስ›› የወላጅ መምህራን መገናኛ ቀንም ፈጥሮ የውይይት ባህል እንዲዳብርም እየተደረገ ነው።
ሌላው የሚደንቀው የወዳጅ ኅብረት የሚባል በመፍጠርም ወላጆች በራሳቸው ተነሳሽነት መምህራንን ጭምር ስፖንሰር አድርገው እንዲሠሩም ዕድል ተፈጥሯል። ይህ የሚያሳየው ደግሞ የእርስ በእርስ ትስስሩን በማስፋት ምንምን ተግባራት መከወን እንደሚቻል ነው። ይህንን መተጋገዝ ደግሞ ተማሪዎች እንዲኖሩትና እንዲያዩት ይደረጋልም።ከዚያ ነገ ተግባሪዎቹ እነርሱ ይሆናሉም ይላሉ።
መምህር አርጋው ከትምህርት ሥራው ባሻገርም አገራዊ ኃላፊነታቸውን በተለያየ መልኩ ይወጣሉ።አንዱ ከእነርሱ ያነሱ ትምህርትቤቶችን ማገዝ ሲሆን፤ በቋሚነት የሚያግዟቸው ትምህርትቤቶችም አሉ። አንዱ በሐዋሳ ከተማ የሚገኘው አዲስ አለም ትምህርትቤት ነውም። መጀመሪያ በቴክኒክ ደግፈውታል። ከዚያም በመቀጠል በቁሳቁስ ብዙ ነገር አድርገዋል። አሁንም ቢሆን ይህ እገዛቸው እንደሚቀጥል ነግረውናል። ከዚያ በተጓዳኝ ተሞክሯቸውን ማካፈል ላይ ይሠራሉ። ማንኛውም ትምህርትቤት ልምዳችሁን ልቅሰም ካላቸው በራቸው ክፍት መሆኑንም አጫውተውናል።
ሌላው የሚሠሩት ነገር ማኅበረሰቡን በቻሉት ልክ ማገዝ ሲሆን፤ በኮቪድ ጊዜ በትምህርትቤቱ አቅራቢያ ላሉ ችግረኛ ሰዎች በገንዘብና በቁሳቁስ ደራሽ ነበሩ። ለመከላከያም እንደተቋም ያደረጉት ነገርም ነበር። በተጨማሪም አሁንም ቀበሌው በሚያዛቸው ሁኔታ ላይ ችግረኛን ከማገዝ ወደኋላ አላሉም።
በትምህርት ቤት ውስጥ የሚያስተምሩ መምህራን ልጆቻቸውን ለማስተማር ከሚከፈላቸው ደመወዝ አንጻር እንደሚከብዳቸው ያውቃሉና አንድ ተማሪ በነፃ እንዲያስተምሩም ዕድሉን ፈጥረዋል። ወላጅ ከሁሉ በላይ ለልጆቹ መስጠት ያለበት ገንዘብ ሳይሆን እውቀትን ነው። ለዚህ ደግሞ በክፍያ ጉዳይ መደራደር የለበትም። በእርግጥ ተገቢ ያልሆነ ክፍያ የሚጠይቁ አሉ። እነርሱ ግን የአገር ጉዳይ የሚያሳስባቸው ናቸው ለማለት ያስቸግራል። ስለሆነም ለአገር ክብር ብላችሁ ሥሩ ሲሉ ይመክራሉ። አቅም የሌለው ብዙ ሰዎች መኖሩ አይካድምና ትምህርትቤቶች ይህንን አስበው ማገዝ ይኖርባቸዋልም ይላሉ። የእነርሱም ትምህርትቤት ከተመሠረተ ጥቂት ዓመታት ያለፉት ቢሆንም የቀጣይ እቅዱ ግን ችግረኛ ተማሪዎችን ማስተማር እንደሚሆን ይናገራሉ።
ዜጋውን ዜጋ በማድረግና ለአገሩ ምንም የሚሰስተው ነገር ሳይኖር እንዲሠራ ካደረግነው ከመሬት ከምናወጣውና ከተፈጥሮ ከምናገኘው ሀብት የበለጠ መጠቀም እንችላለን። ለዚህ ደግሞ ትምህርት ቤቶች የላቀ ድርሻ አላቸው። እናም ያንን እናድርግ መልዕክታቸው ነው። እኛም አርአያነት ያለው ተግባር የሚፈጽሙ የአገር ፈርጦችን እንከተላቸው በማለት ለዛሬ አበቃን። ሰላም!!
ጽጌረዳ ጫንያለው
አዲስ ዘመን ሰኔ 17/2014