ባለፈው ሳምንት ለኢትዮጵያ ሥነጽሑፍ ታላቅ አስተዋፅኦ ስላደረጉት፤ ስለ መምህራቸውና አሻራ አስረካቢያቸው አለቃ ኪዳነ ወልድ ክፍሌ (መጽሐፈ ሰዋስው ወግስ ወመዝገበ ቃላት ሐዲስ) ሕይወትና ስራዎች (በዚሁ ገጽና አምድ ላይ) ማንሳታችን ይታወሳል። በእግረ-መንገዳችን የዛሬው እንግዳችንንም መጥቀሳችን አይረሳም። በመሆኑም፣ ባለፈው ማንሳታችን ለዛሬው እንደ መንደርደሪያችን ይቆጠርልን ዘንድ በማሳሰብ በቀጥታ ወደ አለቃ ደስታ ተክለ ወልድ ሕይወትና ስራዎች እንሄዳለን።
አለቃ ደስታ ተክለ ወልድ
እጅግ ከፍ ያለ ጥረት በታየበት የሕይወት ዘመን ሥራቸው፣ ከ1921 እስከ 1950 ዓ.ም ድረስ ባሉት ሠላሳ ዓመታት ውስጥ የተጠናቀቀው የ‹‹ዐዲስ ያማርኛ መዝገበ ቃላት›› አዘጋጅ በመሆናቸውና በመሳሰሉት ተግባራቸው በኢትዮጵያ የማንነት ድርሳናት ውስጥ ገዝፈው ይታወቃሉ።
ቀለምን ፈጥኖ በመቀበልና በማስተዋል ችሎታቸው የተመሰከረላቸው፤ የመጻሕፍት አንድምታ ትርጓሜን ያጠናቀቁ ዕውቅ የኢትዮጵያ የቤተ ክርስቲያን ሊቅ፤ ከአጥቢያቸው ጀምሮ እስከ ደብረ ሊባኖስ የቅኔና የዜማ ትምህርታቸውን ያጠናቀቁ፤ ቅዱሳት መጻሕፍትን በማረምና በማስተካከል ከ1916 እስከ 1920 ዓ.ም. ድረስ የሠሩ፤ በጊዜው የምስጢር መመራመርና መራቀቅ ምክንያት በጉባኤው ላይ «የቀለም ቀንድ» የሚል ቅጽል ማግኘታቸው እና ሌሎች በርካቶች አለቃ ደስታ ከሌሎች ተለይተው እንዲታወቁ አስተዋፅኦ ያደረጉ ሰብእናዎች ናቸው።
ሰውየው፣ ከመምህራቸው አለቃ ኪዳነወልድ ክፍሌ ‹‹አስተማሪዬ መምህር ክፍለ ጊዮርጊስ የጀመሩትን ግእዝ ዐማርኛ ግስ እንድጨርስ አዘውኝ ነበር፡፡ እነሆ እስከ ዛሬ ደክሜበታለሁ፤ አልተጠናቀቀልኝምና አንተ ተረክበኸኝ ሥራውን ቀጥል፡፡ ዘርሁን፤ ዘር ይውጣልህ›› ተብሎ የተሰጣቸውን አደራ በተሟላ ብቃት ተወጥተዋል። ለኢትዮጵያ ሥነጽሑፍ፣ ባህል፣ ቋንቋና ታሪክ መበልፀግ የግዕዝ መማርያ፣ ‹‹ርባሐ ስም ወአንቀጽ›› (1946 ዓ.ም.)፣ ‹‹ገበታ ሐዋርያት›› (1928 ዓ.ም) … እና የመሳሰሉትን ስራዎች አበርክተዋል። ወደ ድሬዳዋ በመሄድ በአልዓዛር ማተሚያ ቤት ሥራቸውን (ለ16 ዓመት) የቀጠሉበት አጋጣሚ የተፈጠረው ከሊቁ አለቃ ኪዳነ ወልድ ክፍሌ ጋር ለመተዋወቅ የበቁና ስራቸውንም አስቀጥለው ለህትመት ያበቁ ሰው ናቸው።
‹‹አለቃ ኪዳነ ወልድ ብርሃንና ሰላምን ሲጎበኙ ደስታ ተክለ ወልድ የግዕዙን መጽሐፍ ከፍ ባለ ድምፅ ሲያነብቡና ሲያናብቡ ሰምተው ‘ከኔ ጋር ሥራ’ ብለው ጠይቀዋቸው” እንደ ነበር፤ በዚሁ መሰረትም እሳቸው የጀመሩትን ስራ እንዲያጠናቅቁላቸው አደራ ባሏቸው መሰረት፣ ቃል ጠብቀው በ1948 ዓ.ም ‹‹መጽሐፍ ሰዋሰው ወግስ፤ ወመዝገበ ቃላት ሐዲስ›› የተባለውን የመጀመሪያ ታላቅ መዝገበ ቃላት አሳትመዋል፡፡ በ1962 ዓ.ም ደግሞ ”ዐዲስ ያማርኛ መዝገበ ቃላት”ን ለህትመት አብቅተቀዋል።
አለቃ ክፍለ ጊዮርጊስ፣ አላ ኪዳነ ወልድ እና አለቃ ደስታ
‹‹አለቃ ክፍለ በወቅቱ የአገሪቱ የቀለም ሰዎች ከተባሉት አንዱ ነበሩ፡፡ ዘመኑም የአፄ ዮሐንስ ነበር፡፡ የሃይማኖት ክርክሩ ቦሩ ሜዳ ላይ ተነሥቶ አለቃ ክፍሌ በኋላቀር ካህናት ከሃዲ መስለው በመታየታቸውና በአፄ ዮሐንስ ዘንድ እጅግ ፊት በማጣታቸው የሸዋ ንጉሥ የነበሩት ምኒልክ አገር ጥለው እንዲሰደዱ ይመክሩዋቸዋል፡፡ ከዚያም በምድረ ሱዳን አድርገው ግብፅ ቀጥለውም ወደ ኢጣልያ ይሻገራሉ፡፡ እነ አግናጥዮስ ጒይዲንና ሌሎችንም ግእዝ ካማርኛ ያስተምራሉ፡፡ ቀጥሎም እርጅና ሲመጣባቸው ወደ ኢየሩሳሌም ጉዞ ያደርጋሉ፡፡ ከዚያም አለቃ ኪዳነ ወልድን ያገኛሉ፡፡ ያላቸውን ዕውቀት ከውድ መጻሕፍታቸው ጋር ለኪዳነ ወልድ ያስረክባሉ፡፡ በተለይም የግእዝና የአማርኛ መዝገበ ቃላት በውል ተሰናድቶ እንዲታተም ለኪዳነ ወልድ አደራ ይሰጣሉ፡፡ በአገሪቱ ዘመናዊ ማተሚያ ሲቋቋም አለቃ ኪዳነ ወልድ ለመጻሕፍት ትርጓሜ ሥራ ወደ አገራቸው ይጠራሉ፡፡ እሳቸው ከአለቃ ክፍሌ የተቀበሉትን አደራ ለአለቃ ደስታ ተክለ ወልድ ያስረክባሉ፡፡ የዚህ ዐቢይ መዝገበ ቃላት ሥራ መነሻው ይህ ነው (የዛሬ 45 አመት አካባቢ የአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ መምህር የነበሩት የታሪክ ምሁሩ ነፍስ ኄር ዶክተር ብርሃኑ አበበ ስለ አለቃ ክፍሌና ስለ አለቃ ኪዳነ ወልድ ከአዲስ ዘመን ጋዜጣ፣ ‹‹ምን እየሠሩ ነው?›› አምድ አዘጋጅ ካደረገው ቃለመጠይቅ የሪፖርተሩ ያሬድ ጠቅሶት እንዳገኘነው። (ዶክተር ብርሃኑ የሦስቱንም የቀለም ሰዎች ታሪክ በፈረንሣይኛ ቋንቋ አዘጋጅተው ‹‹ሃይማኖተ አበው ቀደምት ወዘደኃርት›› ከተባለው የአለቃ ኪዳነ ወልድ ክፍሌ መጽሐፍ ጋር አዳብለው በ1978 ዓ.ም. በጀርመን ማሳተማቸው በጋዜጣው ተጠቅሷል።))
አለቃ ደስታ ስለ አለቃ ኪዳነ ወልድ
አለቃ ኪዳነ ወልድ የተጣለባቸውን አደራ ለመወጣት በመምህር ክፍለ ጊዮርጊስ የተፃፈውን ጅምር መዝገበ ቃላት ስራውን ጀመር፡፡ ይህንን ትጋታቸውን አለቃ ደስታ ሲያስታውሱ፤ “በሥራ ውለው ማታ ንፋስ በመቀበል ጊዜ አንድ ሃሳብ ቢያገኙ በማስታወሻ ለመፃፍ ከውጭ ወደ ቤት ይመለሳሉ፡፡ በምሳ ወይም በእራት ጊዜ አንድ ትርጓሜ ቢታሰባቸው ምግቡን ትተው ብድግ ይላሉ፡፡ ሌሊትም ተኝተው ሳሉ አንድ ምስጢር ቢገጥማቸው ከመኝታቸው ተነስተው መብራት አብርተው ይጽፋሉ” በማለት ተናግረዋል፡፡
አለቃ ኪዳነ ወልድ ክፍሌ ለበርካታ ዓመታት በዚህ ሁኔታ ቢሰሩም መዝገበ ቃላቱን ከፍፃሜ ለማድረስ እድሜ እንደሚገድባቸው ስለተረዱት አለቃ ደስታን ለደቀ መዝሙርነት መረጡ፡፡ ጊዜ ሞታቸው ሲቃረብም ከመምህር ክፍለ ጊዮርጊስ በጅምር የተቀበሉትንና እርሳቸው ያስፋፉትን የግእዝ መዝገበ ቃላት ሥራ በተራቸው ለአለቃ ደስታ ተክለወልድ አስተላልፈው አረፉ፡፡ በመሆኑም የሁለት ቀደምት ሊቃውንት ልፋትና ድካም በአለቃ ደስታ ተክለወልድ ፍፃሜ አግኝቶ “መጽሐፈ ስዋስው ወግሥ ወመዝገበ ቃላት ሐዲስ” በሚል መጠሪያ ለመገለጥ በቃ፡፡
ሁለቱን በተመለከከተም “አለቃ ደስታ በተፈሪ መኮንን ማተሚያ ቤት በሚሰሩበት ጊዜ ከአንጋፋው የግዕዝ ሊቅ አለቃ ኪዳነ ወልድ ጋር ለመተዋወቅ ቻሉ፡፡ በተፈሪ መኮንን ማተሚያ ቤት የተወጠነው ምሁራዊ ጓደኝነት” ድሬዳዋ በሚገኘው በቅዱስ ዐልአዛር የላዛሪስት ማተሚያ ቤትም ቀጥሎ ሁለቱ በእውቀት ሰንሰለት የተሳሰሩት ሰዎች ለአስራ ስድስት አመት አብረው ሰርተዋል፡፡ በማለት በዓሉን የሚጠቅሰው ያሬድ ያስነብባል። በዓሉ “የግዕዝን መሰረት ያወቅሁት ከአለቃ ኪዳነ ወልድ ነው፤ አሁን ያዘጋጀሁትን ሰፊ ያማርኛ መዝገበ ቃላት ለመፃፍ የበቃሁት ከርሳቸው ባገኘሁት ትምህርትና እውቀት ነው” ሲልም የአለቃ ደስታን ምስክርነት አስታውሷል።
መዝገበ ቃላቱ
እርግጥ ነው፣ በቂ የሆነ የመዝገበ ቃላት ጥናት የለንም። ይሁን እንጂ አንዳንድ ግርድፍ መረጃዎች ግን አሉ። ሆኖም፣ የአለቃ ደስታን ብቃትና ድካም ለማሳየት የሚከተለው በቂ ነው።
ዐዲስ ያማርኛ መዝገበ ቃላት 1ሺ 248 ገጽ ያለው ሲሆን፤ ከቃላት ፍችው በፊት አምስት ክፍሎች አሉት፡፡ በመጀመሪያው ክፍል የቋንቋው ታሪክ፣ ፊደልና የፊደል ነገር፣ እንዲሁም የንግግር ክፍሎች፤ ልዩ ልዩ ርባታዎችና የግዕዝ ጉዳዮች አሉበት፡፡
ዐዲስ ያማርኛ መዝገበ ቃላት “አ”ን አጋፋሪ አድርጐ ገጽ 69 ላይ ይጀምርና በ”ተ” ፊደል በገጽ 1ሺ284 ላይ ይፈፀማል፡፡ መዝገበ ቃላቱ በውስጡ 523 አስረጂ ሥዕሎች (Illustrations)ንም ይዟል፡፡
ሁለተኛው ክፍል አገባብ (ሰዋሰው)፣ ሦስተኛው ያማርኛ ሰምና ወርቅ፣ አራተኛው ምክር በሁለት የግጥም አይነቶች፤ የመጨረሻው አምስተኛው ክፍል ግስን ይዟል፡፡ የአለቃ ደስታ እጅግ ከፍ ያለ ጥረት የታየበትና የሕይወት ዘመን ሥራ የሆነው ይህ መዝገበ ቃላት በታተመ በዓመቱ የቀዳማዊ ኃይለ ሥላሴ ሽልማት ድርጅት ተሸላሚ አድርጓቸዋል፡፡
ከሰባት አመት በፊት ዳግመኛ የታተመው ‹‹ዐዲስ ያማርኛ መዝገበ ቃላት በካህናትና በሀገረሰብ ቋንቋ ተጻፈ ከደስታ ተክለ ወልድ ዘሀገረ ወግዳ የፊደሉ ተራ አቡጊዳ›› የመሸጫ ዋጋ 800 ብር ሲሆን፤ የመጀመሪያው እትም 27 ብር ነበር።
በዓሉ ግርማ (መስከረም ወር 1962 ዓ.ም ታትሞ ለሚወጣው መነን መጽሔት) አንጋፋው ደራሲንና የ68 አመቱን አዛውንቱን አለቃ ደስታ ተክለ ወልድን እንግዳ አድርጎ ቃለ መጠይቅ አድርጓል።
ሪፖርተሩ ያሬድ ሄኖክ እንደነገረን ከሆነ በዓሉ በቀጠሮው እለት ሲደርስ አለቃ ቢሯቸው ውስጥ በስራ ተጠምደው ነበር፡፡ በወቅቱ የ29 ዓመት ጐልማሳ ሳሉ የጀመሩትንና 30 አመት የለፉበትን የአማርኛ መዝገበ ቃላት ለማሳተም በመዘጋጀት ላይ የነበሩበት ጊዜ ሲሆን፤ ቃለ ምልልሱ በተደረገበት ወቅት የረቂቁ መጽሐፍ ገጽ 2ሺ 978 ላይ ደርሷል፡፡ በዓሉ ግርማ አለቃ ደስታ ተክለወልድን ሲያነጋግራቸው፤ ከ1938 ዓ.ም ጀምሮ ባገለገሉበት የአርቲስቲክ ማተሚያ ቤት የሙሉ ጊዜ የእርማት ሠራተኛ ነበሩ፡፡
”የአርቲስቲክ ማተሚያ ቤት ባለቤት የነበሩት ሙሴ ጆርጅ ጄራህያን በጊዜው ስለ አለቃ ደስታ ሲናገሩ፤ ከምድብ ሥራቸው አንዲት ደቂቃ እንኳን ዝንፍ የማይሉ ብርቱ፣ ታታሪና ኃይለኛ ሠራተኛ መሆናቸውን ገልፀው፤ የእርማቱን ሥራ ጨርሰው ትተው ሙሉ ጊዜያቸውን የሚያሳልፉት አዲስ በሚያዘጋጁት መዝገበ ቃላት ላይ” መሆኑ ለበዓሉ ተነግሮታል። ሙሴ ጆርጅ ”አለቃ ደስታ በእርምት ሥራቸው ችላ ብለው የሚያልፉት ቃል ቀርቶ ፊደል ስለሌለ “የአለቃ እርምት ከባድ ነው፤ የእርሳቸውን እርምት የተከተልን እንደሆን በሳምንት የሚያልቀው ሥራ በወር እንኳ አይገባደድም፤ በዚህ የተነሳ እርምት እንዳይሰሩ ከልክለናል” በማለት ለበአሉ መንገራቸውም በበአሉ አርቲክል ላይ ሰፍሮ ለታሪክ በቅቷል።
ለጆርጅ ውሳኔ የአለቃ ደስታ መልስ “ማንም ሰው ግዕዝን ጠንቅቆ ካላወቀ አማርኛን ሊያውቅ አይችልም፤ ፊደሉንም አነጋገሩንም ስህተት ያደርጋል፡፡ የኔ አረም ለዘመኑ ሰው ሁሉ አይስማማም፡፡ ከግዕዝና ካማርኛ ሕግ ውጪ ተጽፎ የመጣውን ሁሉ አልቀበልም፡፡ ቋንቋዬን ስለማውቀው ማክበር አለብኝ፡፡ እንደ’ኔ ከሆነ “ዦሮ” ነው እንጂ “ጆሮ” አይባልም፡፡ እንዲሁም ባንድ “ሀ” “ዐ” “አ” እንጠቀም ከሚሉ ሰዎች ጋር አልስማማም፡፡ ያማርኛ አባት ማን ሆነና! ይህ ሁሉ ስህተት የሚመጣው ግዕዝን ጠንቅቆ ካለማወቅ ነው” የሚል እንደ ነበርም ከበዓሉ ግርማ ብዕር አላመለጠም። (አለቃ ደስታ “በኢትዮጵያችን የፊደል መጀመሪያ ’አ’ መሆኑ ቀርቶ ’ሀ’ የሆነው በአራተኛው መቶ ክፍለ ዘመን ነው፤ ይህ ፈፅሞ ስህተት ነው፡፡” እንዲሁም ”የጥንቱ ፊደል ተራ አበገደ ነበር፡፡ የዓለም ፊደል ሁሉ የሚጀምረው በ”አ” ነው፡፡ እኔ በአበገደ ጽፌዋለሁ፤ አለቃ ኪዳነ ወልድን ተከትዬ”። በዚህ መሰረት “ሀ” አምስተኛ ፊደል እንዲሁም “ለ” ሠላሳኛ ፊደል ሲሆን የመጨረሻው ፊደል ደግሞ “ተ” ይሆናል ማለት ነው፡” ማለታቸውንም ልብ ይሏል።)
በዓሉም ”በአለቃ ደስታ የቢሮ ጠረጴዛ ላይ ቀይና ጥቁር ቀለም የያዙ ልዩ ልዩ ቅርፅ ያላቸው ብልቃጦች ተደርድረው ይታያሉ፡፡ ልዩ ልዩ የብረት ብርዖች የመስቀል ችቦ መስለው ተከምረዋል፡፡ የሚጽፉት በእጃቸው ሲሆን አንዴ ቀይ አንዴ ጥቁር እያጠቀሱ ያዘጋጁት መዝገበ ቃላት ላይ ይወርዱበታል፡፡ በቀይ የሚጽፉት አውራ ቃል ሲሆን በጥቁር የሚጽፉት ደግሞ ትርጓሜው ይሆናል፡፡” በማለት በመነን ላይ ምልከታውን አስፍሯል። “ውቅያኖሰን በማንኪያ እየጨለፈ ለመጨረስ ታጥቆ የተነሳ ሰው ይመስላሉ፤ ትዕግስታቸው ትዕግስት ያሳጣል” ሲልም፣ በአይኑ ያየውን፣ የታዘበና ተመለከተውን የአለቃ ደስታን፣ መሰረቱን በትእግስት ላይ ያደረገውን ሁለንተናዊ ብቃት አስምሮበታል።
አለቃ ደስታ ተክለወልድ ዐዲስ ያማርኛ መዝገበ ቃላት፤ አርቲስቲክ ማተሚያ ቤት ፲፱፻፷፪ ዓ.ም፤ መዝገበ ፊደል (ቋንቋ)፤ አቡጊዳ (ቋንቋ)፤ ገበታ ሐዋሪያ (ቋንቋ) እና ገበታዋሪያ (ቋንቋ /1928/)ን የመሳሰሉ እውቅ ስራዎች ያሏቸው ሲሆን ሌሎችም በርካታ ለህትመት የበቁና ያልበቁ ስራዎችም አሏቸው።
‹‹አንባቢ ሆይ ያማርኛ ቋንቋ ይህ ብቻ እንዳይመስልህ ከዚህ የቀረውን የእንስሳትንና የአራዊትን የአዕዋፍን፣ የዓሣትን፣ የዕፅዋትን፣ ያገርንና የሰውን ስም አምልተን፣ አስፍተን፣ ከነትርጓሜው ለማሳየት ሐሳብ አለን፤ ለዚሁም ያምላካችን ፈቃዱ ይሁን፤›› ብለው በመዝገበ ቃላቱ ላይ ማስፈራቸውና እስካሁንም ድረስ በዚህ አስተሳሰባቸው በመስኩ ምሁራን ዘንድ ምስጋናን ማግኘታቸው ሌላው የአለቃ ደስታ ማንነት ማሳያ ሆኖ እያገለገለ ይገኛል።
እንደሚታወቀው የመዝገበ ቃላት አዘገጃጀት በአንድ ሰው ብቻ ሊከናወን የሚችል አይደለም። ዝግጅቱ የሚመለከታቸው አካላት ስራ ሁሉ ነው። ለዚህ ”በመላው ዓለም የሚኖሩ የአሦራውያንን ባሕልና ቋንቋ የሚያጠኑ ምሁራን ለዚህ ሥራ አስተዋጽኦ አድርገዋል።” የተባለለትን፤ በ1921 ተጀምሮ አጠቃላይ ዝግጅቱ 90 አመታትን የፈጀው፤ 26 ጥራዞች፣ ከ9ሺህ 700 በላይ ገጾች ያሉትን ”የአሦር ቋንቋ መዝገበ ቃላት” ማስታወሱ፤ እንዲሁም፣ የእነ ዌብስተር፣ ኦክስፎርድ … መዝገበ ቃላትን ገለጥ ገለጥ አድርጎ እንዴትና በ’ነማን እንደተዘአጋጁ ማየቱ ብቻ በቂ ነው። ይሁን እንጂ ይህ ሁሉ ወደ እነ ኪዳነ ወልድም ሆነ አለቃ ደስታ ሲመጣ ዋጋ ቢስ ሆኖ ይገኛል። የዚህ ምክንያቱ ደግሞ የአዘጋጆቹ ባለ አምስት አይናነት ሲሆን፤ እራሳቸውም እንዳሉት የእግዚአብሔር ረዳትነት መኖሩ ነው። በሪፖርተር ላይም፤
”መዝገበ ቃላት ማደራጀትን የመሰለ ግዙፍ ተግባር ያለረዳት ለብቻ ያውም በእጅ እየጻፉ ማዘጋጀትን እንዳ’ለቃ ደስታ ተክለወልድ ያለ መንፈሰ ጠንካራ ሰው ካልሆነ በስተቀር ተራና ተርታው ሰው የሚደፍረው ተግባር አይሆንም ነበር፡፡” በሚል የሰፈረው ከዚሁ አኳያ ነውና እዚህ ሊጠቀስ የግድ ይሆናል። ”ይሄው መዝገበ ቃላት በታተመበት ተመሳሳይ ጊዜ የታተመውና 1ሺህ 390 ገፆች ያሉት (The Collins Dictionary of the English Language) ለማዘጋጀት 13 የእንግሊዝኛ ምሁራን የተሳተፉ ሲሆን ቃላት ለመሰብሰብና ለመተየብ ዘመናዊ መሳሪያዎችን እንደተጠቀሙ ሲታወስ የአለቃ ደስታን ድካም አጉልቶ ለማሳየት ይረዳል፡፡” የሚል መስፈሩም ከዚሁ አኳያ ነው።
በመጨረሻም፣ በዚህ ፅሁፍ የጠቀስናቸውን ጨምሮ በርካቶች በዛሬዋ ኢትዮጵያ እውቀት እዚህ ደረጃ ይደርስ ዘንድ ከፍተኛ አስተዋጽኦ አድርገዋል። አለቃ ደስታ ተክለ ወልድም አንዱና ዋናው ሲሆኑ፤ ለዛሬው የእለት ተእለት ተግባር እያገለገለ የሚገኘው ”ዐዲስ ያማርኛ መዝገበ ቃላት” ደግሞ ለዚህ ዋናው ምስክር ነውና ስለ ውለታቸው አሁንም ባርኔጣችንን እናነሳለን።
ግርማ መንግሥቴ
አዲስ ዘመን ሰኔ 15/2014