ሰኔ ሲመጣ በመንግስት ተቋማት ጎልተው ከሚታዩ ተግባራት መካከል የግዥ ጥድፊያ ዋነኛው ነው። በጀት እንዳይቃጠል በሚል ሰበብ በችኮላ ብዙ ግዥዎች ይፈፀማሉ። በዚህ ሳቢያ የመንግስት ገንዘብ ለብክነት ይጋለጣል። ጊዜው ደረሰ በሚል ሰበብ ጥራታቸውን ያልጠበቁ ግዥዎች ከመከናወናቸው በተጨማሪ የጥቅም ትስስር የሚካሄድበት ሁኔታ ስለሚፈጠር በተለያየ መልኩ ሙስና ይፈፀማል። ይህንን ችግር ለማቃለል ምን እየተሠራ ነው? ከማለት በተጨማሪ ሌሎች ተያያዥ ጥያቄዎችን በመያዝ ወደ መንግስት ግዥና ንብረት ባለስልጣን በማምራት ዋና ዳይሬክተር አቶ ሃጂ ኢብሳን አነጋግረን እንደሚከተለው አቅርበንላችኋል።
አዲስ ዘመን፡- ባለስልጣን መስሪያ ቤቱ እየሠራ ካለው ሥራ እንጀምር፤ ምን እየሠራችሁ ነው?
አቶ ሃጂ፡– የመንግስት ግዥ እና ንብረት ባለስልጣን በዚህ ስም የተሰየመው ካለፈው መስከረም ጀምሮ ነው። ሲሰየም ከዚህ በፊት ከነበረው ኃላፊነት በተጨማሪ ሌሎች ኃላፊነቶችም ተሰጥተውታል። ተጠሪነቱ ለገንዘብ ሚኒስቴር ሲሆን፤ የግድ በዛ መስመር የሚያልፉ ነገሮች ይኖራሉ። አምና ከሃምሌ እስከ መስከረም በወቅቱ ለነበሩት 191 የፌዴራል ተቋማት ሙሉ ስልጠና ስንሰጥ ነበር። በሶስቱ ወራት በአጠቃላይ ግዥ ፣ በመንግስት የኤሌክትሮኒክስ ግዥ፣ በንብረት አያያዝ፣ በኦዲት እና በሌሎችም በመሳሰሉት ጉዳዮች ላይ ሥልጠና ሰጥተናል። ከስልጠና በኋላ ደግሞ በግላችን ስልጠናው ምን ለውጥ አምጥቷል? በሚል የዳሰሳ ጥናት አካሂደናል።
ከዩኒቨርሲቲዎች ጋር ደግሞ ሞዴል ዩኒቨርሲቲዎችን ለመፍጠር በተለየ መንገድ (ሲናሪዮ) ስልጠና ጀምረናል። የዩኒቨርሲቲ ግዥ ንፁህ እንዲሆን ፤ ሙሉ ለሙሉ ንፁህ እንኳን ባይሆን አነስተኛ ክፍተት ብቻ እንዲኖርበት ለማድረግ ጠንካራ ሥራ አከናውነናል። ከ47ቱ ዩኒቨርሲቲዎች መካከል ከ43ቱ ጋር ደብረዘይት ላይ ውይይት አድርገናል። ፎረም በማበጀት በስድስተኛው ወር ላይ ቦንጋ ላይ አካሂደናል። ዩኒቨርሲቲዎችን በሶስት የከፈልን ሲሆን፤ በግዥ ላይ፣ በመንግስት ሃብት እና ንብረት ላይ ከፍተኛ ጉዳት ያስከተሉትን እና ትልቅ ክፍተት ያለባቸውን ‹‹ቀይ›› ብለን ለይተናል።
ጥቃቅን ስህተት ያለባቸውን ‹‹ቢጫ›› ያልን ሲሆን፤ በርካታ ክፍተት የሌለበት እና ወደ ንፁህ የሚጠጋውን ‹‹አረንጓዴ›› ብለን ዩኒቨርሲቲዎቹን ሶስት ቦታ ከፍለናል። የዩኒቨርሲቲ ፕሬዚዳንቶች ባሉበት 43ቱ ዩኒቨርሲቲ ከእያንዳንዱ ሁለት ሁለት ከፕሬዚዳንት እና ከፋይናንስ ዘርፍ ከሚመለከተው ጋር ውይይት አድርገናል። ስለዚህ ባለፈው ስልጠና መሠረት ከአንድ ተቋም በስተቀር ሁሉም የፌዴራል ተቋማት የግዥ ዕቅዳቸውን እንዲያቀርቡ አድርገናል። በ2014 በዕቅዳቸው መሠረት መስራታቸውን እያየን ነው። በ2014 የተሻለ ክትትል አድርገናል ማለት ይቻላል። ነገር ግን በርካታ የሚቀሩ ነገሮች እንዳሉ ማየት ይቻላል።
አዲስ ዘመን፡- ስለዚህ 2014 ላይ ፈተና አላጋጠማችሁም?
አቶ ሃጂ፡– አጋጥሞናል። አንደኛው ተግዳሮት ልዩ ፍቃድ ነበር። ከጥቅምት ጀምሮ በነበረው ጦርነት ምክንያት ልዩ ፍቃድ ይበዛል። ለምሳሌ መከላከያ የሚገዛቸው ብዙ ነገሮች ይኖራሉ። እነዛ ሁሉ ግዥያቸው የሚከናወነው በልዩ ፍቃድ ነው። የአገር ጉዳይ እና ጦርነት በመሆኑ ወደ ጨረታ መሔድ አይቻልም። ከዛ ውጪ ለምሳሌ በሰሜኑ አካባቢ ቁስለኞችን ሰብስበው የሚያክሙ ፣ የሚያበሉ እና የሚያጠጡ በርካታ ሆስፒታሎች ልዩ ፍቃድ ተሰጥቷቸዋል። እዛ ብቻ ሳይሆን አዲስ አበባም ጦር ሃይሎች እና የመከላከያ መምሪያም ልዩ ፍቃድ ነበራቸው።
ጦርነቱም ትንሽ መለስ ካለ በኋላ በርካታ ዩኒቨርሲቲዎች ሙሉ ለሙሉ ውድመት አጋጥሟቸው ነበር። ለምሳሌ ወልዲያ እና ወሎ ዩኒቨርሲቲዎች ሙሉ ለሙሉ ወድመው ነበር። ደብረብርሃን ዩኒቨርሲቲ ካምፕ ሆኖ ነበር። ፍራሽ፣ ወንበር፣ በርና ሌሎችም መጠቀሚያዎች ተሰባብረው ነበር። ወያኔ ደብረሲና ሲደርስ ካምፕ ለሠፈሩት የሠራዊቱ አባላት ምግብ መቻል የግድ ያስፈልግ ነበር። ይህ ትልቅ ፈተና ነበር። ለፌዴራል ፖሊስም ሙሉ ለሙሉ ልዩ ፍቃድ ሲሰጥ ነበር። ካቀድነው የተለየብን ይህ ነው።
ተቋማት በዕቅዳቸው መሠረት እንዲሠሩ አቅደን ነበር። በእርግጥ በግዥ ህግም ልዩ ፈቃድ ተቀምጧል። ነገር ግን በህጉም ልዩ ፍቃድ ተብሎ የወጣው ከአቅም በላይ ሲያጋጥም ፍቃድ ለማግኘት ነው። በዚህ ምክንያት ተለዋዋጭ ነገር አጋጥሟል። በበርካታ ዩኒቨርሲቲዎች ጉድለት ታይቷል። ኦዲትም የማናደርጋቸው ዩኒቨርሲቲዎችም አጋጥመዋል። ለምሳሌ ቡሌሆራ ላይ በኦሮሚያ ካለው የሸኔ እንቅስቃሴ ጋር ተያይዞ ኦዲት ማድረግም ሆነ መቆጣጠር እና መከታተል አይቻልም። አማራ ክልል ላይ ከላይ የጠቀስኳቸውን ዩኒቨርሲቲዎች ጨምሮ ደባርቅ ዩኒቨርሲቲ እና አራት አምስት ዩኒቨርሲቲዎች ከአቅም በላይ ችግር ያጋጠማቸው አሉ።
ሰላማዊ አካባቢ የተባለው ደብረማርቆስ ዩኒቨርሲቲ ራሱ ካምፕ ሆኖ ስለነበር እና ቁስለኛ ያስተናግዱ ስለነበር በግዥ ህጉ እንዳንሔድ ወደ ልዩ ፍቃድ የምንሔድበት አግባብ ላይ ደርሰናል። ይህ ማለት እኛ ተጠናክሮ እንዲቀጥል የምንፈልገው ግዥ የጨረታ ነው። ጨረታ ሁሉም የንግዱ ማህበረሰብ የሚወዳደርበት ነው። ከውድድር ደግሞ መንግስት ትርፍ ያገኛል። ሃያ ሰላሳ ተወዳዳሪዎች ቢኖሩ እና በቴክኒክ የተወሰኑት አልፈው በፋይናንስ ሲወዳደሩ ዝቅተኛ ያቀረበው ያሸነፋል። በዛ ትርፍ መንግስት ይጠቀማል።
ያለ ጨረታ ግዥ ሲፈቀድ አንደኛ የመልካም አስተዳደር ችግር ይፈጠራል። ሁለተኛ ልዩ ፍቃዱ በመሰጠቱ የማቅረብ ዕድሉን ለአንዱ ሲሰጥ ጎረቤትየው ለኔ ለምን አልተሰጠም? ይላል። ለምሳሌ ተቋሙ ‹‹ከአንዱ ካምፓኒ ለሠራዊቱ ጫማ እገዛለሁ›› ካለ አትግዛ ተብሎ አይከለከልም። ይፈቃዳል። ሌላ ካምፓኒ ደግሞ ለምን ከኔ ጫማ አልተገዛም? ብሎ አቤቱታ ሊያቀርብ ይችላል። ስለዚህ እንደዚህ አይነት ነገር ተግዳሮት ሆኖብናል። ባሰብነው ልክ በዕቅድ ለመሔድ አዳግቶናል። ይሔ በፌዴራል ተቋማትም ሆነ በዩኒቨርሲቲዎች አጋጥሞናል።
አዲስ ዘመን፡- ሌላስ ያጋጠማችሁ ችግር ምን ነበር?
አቶ ሃጂ፡- እኛ የምንሠራው ሌላም አለ። ኦዲት ሥራ ላይ አንዱ የገጠመን ችግር ብዙ ጥቆማዎች ይመጣሉ። በዚህ ተቋም ላይ ሙስና አለ። ሌብነት አለ ይባላል። በማወቅ፣ በመተዋወቅ፣ በወዳጅነት እየሠሩ ነው ይባላል። ጥቆማውን ተከትሎ ግዥውን በማስቆም ኦዲት ይደረጋል። ኦዲት ሲደረግ ጥቆማው ትክክል ከሆነ ግዥው ይሠረዛል። የተጠቆመው ጥቆማ ደግሞ ስህተት ከሆነ ግዥው እንዲቀጥል ይደረጋል።
በተጨማሪ አቤቱታ እና ጥፋተኝነት የሚል ዳይሬክቶሬት አለ። ይህ ክፍል የከፊል ዳኝነት ሥራን ይሠራል። በእዚህ ውስጥ ከ70 በመቶ በላይ ተቀጣሪዎቹ ህግ የተማሩ ዳኞች ናቸው። የፍትሓ ብሔርም ሆነ የወንጀል ህጎችን አጣቅሰው ውሳኔ ያስተላልፋሉ። አቅራቢ እና ተቀባይ ሁለት ተቋማት ይካሰሳሉ። ማንኛውም የፌዴራል ተቋምም ሆነ አቅራቢ ይከሳል፤ በሌላ በኩል ሌላኛው ደግሞ ይከሳል። በሚካሰሱበት ጊዜ ወደ ፍርድ ቤት ሳይሆን ወደ እኛ ይመጣሉ። እንደማንኛውም የፍርድ ቤት መስመር ህግን ተከትለን መረጃዎችን እና ማስረጃዎችን ይዘን እንመረምራለን።
በገንዘብ ሚኒስቴር የሚመራ አምስት አባል ያለው ቦርድ አለ። ከምርመራው በኋላ ለእርሱ ይቀርብና ቦርዱ አይቶ ወሳኔ ያሳልፋል። ውሳኔ እኛ ካሳለፍን በኋላ ውሳኔው ትክክል አይደለም ብሎ የሚቀጥል አካል ካለ ወደ ፍርድ ቤት ይቀጥላል። ፍርድ ቤት ድረስ እስከ ሰበር መቀጠል ይችላል። ለምሳሌ የደብረማርቆስ ዩኒቨርሲቲ ጉዳይ መጀመሪያ ቦርዱ ለዩኒቨርስቲ ወሰነ፤ አቅራቢው ትክክል አይደለም ብሎ ፍርድ ቤት ሔደ። ፍርድ ቤት ደግሞ ለአቅራቢው ወሰነ፤ እያለ ቀጠለ፤ መጨረሻ ላይ ሰበር ሰሚ ችሎቱ ቦርዱ የወሰነውን አፀና፤ ዩኒቨርሲቲው አሸነፈ። ስለዚህ የምንሰራው ከፊል ዳኝነት ነው።
ከዛ ውጪ አስቸግሮን የቆየው ጨረታ ላይ ዋጋ ሰብሮ መግባት ነው። ለምሳሌ ባህርዳር ዩኒቨርሲቲ ላይ የእንጀራ ገበያ ሽያጭን በሚመለከት በ6 ብር የሆነውን በ4 ብር አቀርባለሁ ብሎ ያሸንፋል፤ ይገባል። ሁለት ጊዜ አቅርቦ ዋጋ አስተካክሉ ይላል። ከዛ ወደ ጭቅጭቅ ይገባል። በሌሎች ሥራዎች ላይም ዋጋ ሰብሮ መግባት ከፍተኛ ችግር እየፈጠረ ነው። ቴክኒክን ያልፋሉ፤ ዋጋ ሰብረው ገብተው ሥራውን አያጠናቅቁም። ከአራት ከአምስት ወር በኋላ ብረት ጨምሯል፤ ሚስማር ጨምሯል ብለው ይጨቃጨቃሉ።
ትክክለኛውን ዋጋ ያቀረበው ሰው የመውደቅ ዕድል ያጋጥመዋል። ትምህርት ቤትም ሆነ የጤና ተቋማት እንዲሁም ማንኛውም የሚገነባው ለሕዝብ እስከሆነ ድረስ ዋጋ ሠብሮ ገብቶ ፤ ሌላ ክስ እና ጭቅጭቅ ውስጥ ከመግባት ፤ ባሻገር ፕሮጀክቱ ይዘገያል። የሁለት ዓመቱ ፕሮጀክት አራት ዓመት ይፈጃል። የአራት ዓመቱ ፕሮጀክት ስምንት ዓመት ሲፈጅ ሌላ ተጨማሪ ወጪ ያስከትላል፤ መንግስትንም ይጎዳል።
ገንዘብ ሚኒስቴር ሆኜ በተደረገው ጥናት የመንግስት ፕሮጀክቶች ከአምስት እስከ አስር ዓመት በመዘግየታቸው ምክንያት እስከ 43 ቢሊዮን ብር መንግስት ለተጨማሪ ወጪ ይጋለጣል። በወቅቱ ቢጠናቀቁ ግን ይህ 43 ቢሊዮን ብር ለሌላ የልማት ተግባር ይውል ነበር። ስለዚህ ፕሮጀክቶች ላይ ከፍተኛ ክፍተት የሚፈጠረው አንድም በደንብ አይጠናም፤ በደንብ ሳይጠና በትዕዛዝ ይጀመራል። ዋጋ ሰብሮ መግባት ታክሎበት መሃል ላይ ሲደርስ ፕሮጀክቱ ይቆማል።
በተጨማሪ ለዛ ፕሮጀክት የሚበቃ በጀት ከገንዘብ ሚኒስቴር ጋር የፕሮጀክት ጥናት ይጠናል። በፕላን ሚኒስቴር በኩል ለፓርላማ ቀርቦ ፓርላማ ላይ ከፀደቀ በኋላ፤ እያንዳንዱ አዲስ የፀደቀው ፕሮጀክት በጀት መኖሩ ተረጋግጦለት መቼ እንደሚጀምር፣ ማን እንደሚሠራ፣ ይህንን ሥራ ላይ ያላዋለ የመንግስት አካልም ይሁን ሌላ በህግ እንደሚቀጣ ተለይቶ መግባባት ላይ አይደረስም፤ ስለዚህ ፕሮጀክት ይዘገያል።
አዲስ ዘመን፡- እዚህ ላይ የአገር ውስጥ ብቻ ሳይሆን የዓለም የገበያ ሁኔታ ራሱ በፍጥነት እየተለዋወጠ ከመሆኑ አንፃር ፕሮጀክቶች ቀድሞ ከተያዘላቸው ገንዘብ በላይ የሚያስፈልግበት ሁኔታ ሊፈጠር ይችላል? እዚህ ላይ ምን ይላሉ?
አቶ ሃጂ፡– ልክ ነው፤ ሁሉ ነገር ተገለባብጧል። ትናንት የነበረ ዛሬ የለም። ከዓመት በፊት ውል የገባ ኮንትራክተር ዛሬ በዛ ጊዜ ዋጋ ጨርስ ማለት ያስቸግራል።
አዲስ ዘመን፡- አዎ! ይህንን ጉዳይ እንዴት እያስተካከላችሁት ነው?
አቶ ሃጂ፡– ሁሉም ነገር ጥቅም እና ጉዳት አለው። አሁን ለምሳሌ ከዚህ በፊት በነበረው ልማድ የአፍሪካ እና የዓለም ዋጋ በተረጋጋበት ሰዓት ውል ይታደሳል፤ የሚል ነገር አልነበረም። ምክንያቱም ሽርክና የሚፈጠርበት ሁኔታ ይኖራል በማለት ፕሮጀክቱ አምስት ዓመት ይፈጃል ከተባለ አቅራቢው ወይም ገንቢው በአምስት ዓመት ውስጥ የምጨርስበትን ሁኔታ እፈጥራለሁ ይላል። አሁን ግን ውሉ እንደአስፈላጊነቱ የሚታደስበት ሁኔታ እናስገባለን። በተለይ የዓለም ገበያ እስከሚረጋጋ ድረስ ይህን መከተል የግድ ነው።
ምክንያቱም ሲሚንቶ ከአንድ ዓመት በፊት አራት መቶ እና አምስት መቶ ብር ነበር። አሁን ግን ስምንት መቶ እና አንድ ሺህ ብር ገብቷል። ስለዚህ ሲሚንቶ አራት መቶ ብር በሆነበት ጊዜ ኮንትራት የወሰደ ሰው ሲሚንቶ አንድ ሺህ ሆኖበት በዚህ ጨርስ ማለት ጫና መፍጠር ነው። ነገር ግን አንዳንድ ጊዜ በዚህች ቀዳዳም አላግባብ መንግስት እንዳይጎዳ ማሰብ የግድ ነው።
መንግስት ከህዝብ ያገኛትን ትንሷን ገንዘብ ይዞ የሚያስተዳድር በመሆኑ በጣም በጥንቃቄ መሠራት እንዳለበት ሊረሳ አይገባም። ውሉ ይሻሻላል ተብሎ ቢቀመጥም፤ ምን ሲሆን ይሻሻላል? የሚለው በጥንቃቄ በግልፅ መቀመጥ አለበት። በቅርቡ ገንዘብ ሚኒስቴር ከኮንስትራክሽን ሚኒስቴር ጋር በመተባበር በተለይ ነባር ፕሮጀክቶች ውላቸው በወቅታዊ ዋጋ እንዲስተካከል እና ገበያውንም ማዕከላዊ ስታቲስቲክስ ባጠናው መሠረት እንዲስተካከል የማድረግ ሥራ እየተሠራ ነው።
በሌላ በኩል ዩኒቨርስቲዎች ላይ የተማሪ ቀለብ ላይ ጤፍ ሶስት ሺህ በነበረበት ጊዜ ኮንትራቱን የወሰደ አካል አሁንም በዛው ዋጋ አቅርብ ማለት አይቻልም። ስለዚህ ማዕከላዊ ስታቲስቲክስ በሚያጠናው መሠረት አስተካክሉ እያልን ነው። ምክንያቱም ዩኒቨርስቲዎች ተማሪ ይዘው መሰቃየት ስለሌለባቸው ውሉ ላይ ባይኖርም በፍጥነት ከማዕከላዊ ስታትስቲክስ ጋር እየሰሩ ወዲያው እኛን እያሳወቁ በጋራ እንዲሰሩ እየተደረገ ነው።
ለእያንዳንዱ ዩኒቨርሲቲ እና ለእያንዳንዱ ተቋማት ሳይሆን ተመሳሳይ አካባቢዎች በምስራቅ ፣ በምዕራብ እና በሌሎችም አካባቢዎች ያለውን ዋጋ ማዕከላዊ ስታቲስቲክስ በ27 ቅርንጫፎቹ እያጠና ዋጋውን ይገልፃል። በዛ መሠረት ማሻሻያ ያደርጋሉ። በተለይ ለተማሪዎች በዚህ መልኩ የምግብ ዋጋ እየተስተካከለ ነው።
አዲስ ዘመን፡- ሌላ ከስልጠናው ባሻገር የምትሠሩት ምንድን ነው? የሰኔ ግዥን በሚመለከትስ ምን ይላሉ?
አቶ ሃጂ፡– አሁንም ስልጠና መስጠታችንን እንቀጥላለን። አምና ስንሰራ እንደክፍተት ያየነው አንድ ተቋም ያምጣ እንጂ የሚፈፀሙት ግዥዎች በዕቅድ ውስጥ የተካተቱ ናቸው ወይስ አይደሉም? የሚለው አይታይም ነበር። የሰው ሃይልም አልነበረም። አሁን ግን እንከታተላለን። አንድ ተቋም ዕቅድ ሲያመጣ ለመግዛት ያሰበው ምንድን ነው? የሚገዛው መቼ ነው? የሚለውን እንከታተላለን። ይህንን ያደረግነው የሰኔ ላይ ግዥን ሙሉ ለሙሉ ለመከላከል ነው።
ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር ዐቢይ አህመድም ከግንቦት ጀምሮ ግዥ ይቁም ብለዋል። እኛም ሚያዚያ ላይ ልዩ ፍቃድ እና ልዩ ግዥ የሚባል ሙሉ ለሙሉ እንዲቆም አቅጣጫ አስቀምጠናል። ገንዘብ ሚኒስቴርም ግዥ እንዲቆም ብሏል። ነገር ግን አሁንም ልዩ ፍቃዱ ቀጥሏል። አንዳንዴ ግን ቢከለከልም የሚያሳምን ፈቃድ የሚያስፈልገው ያጋጥማል። ለምሳሌ የወረርሽኝ በሽታ ቢያጋጥም አንዴ ግዥ ከልክያለሁ እና አልፈቅድም ማለት አይቻልም። በእርግጥ ትንንሽ ግዥዎች እስከ ሰኔ 30ም ሊያጋጥሙ ይችላሉ።
አንድ ሃላፊ ጉዞ እየሔደ ጎማው ቢበር አይገዛም ለማለት ይከብዳል። ነገር ግን ሰኔ ላይ በጅምላ እና በብዛት ግዢዎችን ማካሔድ አይቻልም። በዚህ ዓመት የምንሠራው የተለየ ሥራ እያንዳንዱ ተቋም አቅዶ ከመጣ በኋላ ለዕቅዱ ምላሽ መስጠት፤ ተቋማቱ ለግዥ እኛን የሚጠይቁን ነገሮች በሙሉ በዕቅድ ውስጥ የተካተተ መሆኑን እናያለን። ብዙ ተቋማት ትኩረት አይሰጡም። የአምናውን ወይም የካቻምናውን ገልብጠው ያመጣሉ። እኛም አይተን አንተችም፤ እንዲሁ እናስቀምጣለን። ተቋማቱም ዕቅዳቸው ውስጥ የሌለ ግዥን ይጠይቃሉ። ተከታትሎ የሚያመሳክር አልነበረም። አሁን ግን ፋይሉን አስወጥተን እንጠይቃለን።
ግዥ በጣም አድካሚ ሥራ ነው። አንደኛ የውስጥ ድክመት አለ። የግዥ ሥርዓቱ ላይ በተለያየ መልኩ የተለመዱ ነገሮች አሉ። እነዛን ልማዶች በአንድ ጊዜ ጠራርጎ ማጥፋት አይቻልም። ሽርክና ይኖራል። ለምሳሌ የጨረታ ግዢ አራት ወር ይፈጃል። ስለዚህ ለአስቸኳይ ጉዳዮች የለቀማ ግዢ እና ውስን ግዢ ይፈቀዳል። በዛ ጊዜ አምስት አቅራቢ ቢወዳደር እነማን እንደሆኑ የሚያውቀው አንድ አምላክ ነው። መቀራረብ እና አብሮ መስራት ይኖራል።
አዲስ ዘመን፡- ዩኒቨርሲቲዎችን ጨምሮ ወደ ሁለት መቶ የሚጠጉ የመንግስት ተቋማትን ግዥ ለመቆጣጠርና የሚፈፀሙ ወንጀሎችን ለመከታተል የባለስልጣን መስሪያ ቤቱ አቅም ምን ያህል ነው?
አቶ ሃጂ፡- ሙሉ በሙሉ የመንግስት ተቋማትን ግዥ ለመቆጣጠር የሚያስችል አቅም አለን አልልም። የሰው ሃይል ብዛት ሳይሆን ጥራት ያስፈልጋል። ለምሳሌ አጠቃላይ የአገሪቷን የግዥ ሥርዓት የሚመራ የግዥ ዳይሬክቶሬት አለ። ይህንን የግዥ ሥርዓት የሚመራ ሰው በዕውቀትም ሆነ በልምድ ትልቅ ዓቅም ያለው ጠንካራ ሰው መሆን አለበት። እንደዚህ ዓይነት ሰው ለመያዝ ደግሞ ደመወዝ ይፈልጋል። ጥራት ያለው የሰው ሃይል ለማግኘት ጥራት ያለው ክፍያ ይፈልጋል።
የውስጥ ግዥ ዳይሬክተር እና የአጠቃላይ ግዥ ዳይሬክተር ደመወዛቸው አንድ ዓይነት ነው። ከገበያ የማገኘው ከማንኛውም የግዥ ዳይሬክተር የበለጠ አቅም ያለው መቅጠር አይቻልም። ይህንን ለማስተካከል ከሲቪል ሰርቪስ ኮሚሽን ጋር በደንብ ተነጋግረናል። በደመወዝም በጥቅማጥቅምም ሆነ በሥራ ልምድ የበለጠ መሆን እንዳለበት መግባባት ላይ ተደርሷል። የዩኒቨርስቲ ፕሬዚዳንትን ለማነጋገር የሚመጥን ላፊ መኖር አለበት፤ ተባብለን ተነጋግረናል።
አቤቱታ እና ማጣራትም በተመሳሳይ መልኩ ዳኝነት ነው። የዳኞች ደመወዝ የተሻለ ነው። ስለዚህ ከእኛ እየለቀቁ ወደ እዛ ይገባሉ። ምክንያቱም የቤት አበልን ጨምሮ ብዙ የደመወዝም ሆነ የሌሎች ጥቅማጥቅሞች ልዩነት ያለበት በመሆኑ ከእኛ ለቅቀው ወደ እዛ ይገባሉ። ከእኛ ለቅቀው አምስት እና ስድስት የሚሆኑ የህግ ባለሞያዎች ዳኛ ሆነዋል። ኦዲትም በተመሳሳይ መልኩ ሌላ ቦታ የተሻለ ደሞዝ ሲያገኙ ይለቃሉ። ስለዚህ በተለይ ሶስቱ ዋና ዋናዎቹ ላይ ከሲቪል ሰርቪስ ኮሚሽን ጋር ተስማምተናል። ነገር ግን ፀድቆ አልመጣልንም ይፀድቃል ብለን እናስባለን። ስለዚህ ትንሽ የተሻለ ክፍያ ፈፅመን የተሻለ ሥራ የምንሠራበት ሁኔታ ይኖራል። በ2015 የተሻለ ነገር እንጠብቃለን።
አዲስ ዘመን፡- ባለፈው ዓመት አሠልጥነናል ብላችኋል። ስልጠናዎችን ሰጥታችሁ በትክክል ውጤት መምጣቱን ትከታተላላችሁ?
አቶ ሃጂ፡- ስልጠና ከባድ ነው። ስልጠና አልጋ ላይ ተኝቶ አበል ወስዶ መምጣት አይደለም። አሰልጥኖ አብቅቶ ውጤት ማምጣት መቻል የግድ ነው። በምንፈልገው ደረጃ ላይ አልደረስንም። ለዳይሬክተር ለተዘጋጀው ስልጠና ተቋማት ጀማሪ ባለሙያ ይልካሉ። ቡድን መሪ ተጠርቶ ጥበቃ ይልካሉ። የግዥ ባለሙያ እየተባለ የአይ ቲ ባለሙያ ይልካሉ።
ካለፈው ዓመት ስልጠና ምን ተገኘ? ከተባለ አርባ ምንጭ ዩኒቨርሲቲ ከባድ ደረጃ ላይ ደርሶ ነበር። በመገናኛ ብዙሃን ሳይቀር ቀርቦ ሲተች ነበር። በኋላ ይሔንን ተከታትለን የእኛን ኦዲተር ልከን ስናጣራ ነገሩ በሙሉ የተበላሸ ነበር። የፋይናንሱን ዘርፍ የሚመራ ምክትል ፕሬዚዳንት ልዩ ፍቃድ የሚሰጥ እርሱ ነበር። ዋጋ የሚያስተካክል እርሱ ነው። ሁሉን ከማድረግ ባሻገር እርሱ ከሌለ እርሱን ተክታ የምትሠራው ፀሃፊው ነበረች።
‹‹ዩኒቨርስቲው አደጋ ላይ ነው›› ብለን ቀይ ከሰጠነው በኋላ ለዩኒቨርስቲዎች በሙሉ ስልጠና ተሰጠ። የግዥ ዳይሬክተር የተቋቋመው ለግዥ ነው። ጨረታ ማውጣት ያለበት ማን ነው? ይህ ሁሉ ሥራ ሲሰራ ፋይናንሱ፣ ኦዲቱ፣ የስነምግባር ክፍሉ ሁሉም ምን እየሠራ ነበር? ብለን ፕሬዚዳንቱም ማየት እንደነበረበት ታምኖ ግለሰቡ ከቦታው እንዲነሳ ተደረገ። በቀላሉ በዛ ዩኒቨርሲቲ ለውጥ አምጥተናል።
አዲስ ዘመን፡- ያልተገባ ግዥ ሲያጋጥም ምን ታደርጋላችሁ?
አቶ ሃጂ፡- እኛ እኮ ዳኛ አይደለንም። የከፊል ዳኝነት ሥራንም የምንሠራው ተቋማት እና አቅራቢ ሲካሰሱ ብቻ ነው። ኦዲት አድርገን ከሙስና ጋር የተያያዘ ግኝት ካጋጠመ ሰነዱን ለመርማሪ ፖሊስ በመስጠት ሃፊነታችንን እንወጣለን። መርማሪ ፖሊሱ ክብደቱን አይቶ ራሱ ምርመራ አካሂዶ ፍርድ ቤት ይሔዳል። ፍርድ ቤት ደግሞ በራሱ ሲቀጥል እኛን እንደምስክር ወስዶ ውሳኔውን ያሳልፋል። ለዩኒቨርሲቲዎች ትምህርት ሚኒስቴር እርምጃ ይወስዳል፤ እኛ በጀት ከመከልከል ውጪ ምንም ማድረግ አንችልም። ለምሳሌ ጥፋት ላለበት ዩኒቨርሲቲ ማስተካከል ያለብህን ካላስተካከልክ ለአንድ ወር በጀት አንሰጥም እንላለን። ምክንያቱም ከድሃ ጉሮሮ በተሰበሰበ ገንዘብ እንደፈለጉ ማድረግ አይቻልም። ከዛ በኋላ ወዲያው ማስተካከል ያለበትን ያስተካክላል።
የተሳሳተ ጨረታ ወጣ ተብሎ ጥቆማ ከመጣ፤ እናስቆማለን። ነገር ግን የሚወጣውን ጨረታ በሙሉ መቆጣጠር አንችልም። በአንድ ተቋም ተቆጣጥሮም አይቻልም። በየተቋሙ ያሉ የመንግስት ሃላፊዎች ግዴታውን መወጣት አለበት። የእያንዳንዱ ተቋም ሃላፊ የህዝብን ገንዘብ በጥንቃቄ ከጨረታ ጀምሮ እስከ ውስን ግዢ ሃላፊነት በተሞላበት መልኩ መካሔዱን ማረጋገጥ አለበት። አንዳንዴ እኛ ጋር ጥቆማ መጥቶ ኃላፊዎች የማይሰሙበት ሁኔታ አለ።
20 ሚኒስቴር መስሪያ ቤቶች እንከን የለሽ ግዥ መፈፀም ከቻሉ፤ ዩኒቨርሲቲዎችም ተመሳሳይ በሆነ መልኩ የጠራ ግዥን ከፈፀሙ 50 በመቶ የአገሪቷ ግዥ የተጣራ ይሆናል። ነገር ግን ይህንን በአንድ ጊዜ ማምጣት አይቻልም። በፍፁም አልሠርቅም የሚል ዜጋ መፈጠር አለበት። በ2015/በ2014 ያልተሳካውን እናሳካለን ብለን እናስባለን።
አዲስ ዘመን፡- በኦዲት ግኝታችሁ መሠረት ምርመራ ተካሂዶ ክስ እንዲመሠረት የመራችኋቸው ጉዳዮች ፍርድ ቤት ቀርበው ውሳኔ ይተላለፍላቸዋል ወይስ እንዴት ነው? ቀይ ነው ብላችሁ እንዳለፋችኋቸው ይቀራሉ ወይስ ምን ታደርጋላችሁ?
አቶ ሃጂ፡- ቀይ ያልናቸው፤ ቀይ እንደሆኑ እንዲቀጥሉ አንፈልግም። ለምሳሌ የአርባ ምንጭ ዩኒቨርሲቲ ላይ ያጋጠመንን ችግር ለማቃለል ሰውየው ከኃላፊነት እንዲነሳ ማድረግ ተቻለ። እርሱን የተካው ሰው ተመሳሳይ ሥራ እንዳይሠራ እየተከታተልን ሌሎቹንም ሠራተኞች ለማብቃት ጥረት አድርገናል። ሌላው የፍርድ ቤት ሒደት ይታወቃል። አንድ ጉዳይን ወደ ፍርድ ቤት ለማድረስ አራት እና አምስት ወራትን ሊፈጅ ይችላል። መርማሪው ፖሊስ ራሱ ለመመርመር ጊዜ ይወስዳል። በዛ ላይ ከጦርነቱ ጋር ተያይዞ ሰፋፊ ወንጀሎች አሉ። ስራ ሊበዛ ይችላል። ሌሎችም ወንጀሎች ሊኖሩ ይችላሉ፤ ስለዚህ ወዲያው በአንድ ዓመት ይሔ ተሰራልኝ ለማለት አንችልም። ነገር ግን በስምምነት እየሰራን ነው።
አዲስ ዘመን፡- ጥቆማ ትቀበላላችሁ? ጥቆማ ከተቀበላችሁ በኋላስ ምን ያህል ትሠሩበታላችሁ?
አቶ ሃጂ፡- በዚህ ዓመት ከሃምሳ በላይ ጥቆማ ተቀብለናል። ሁሉንም አጣርተን ከሃያ በመቶ በላይ ሙሉ ለሙሉ እንዲቆሙ አድርገናል። ዋናው ወደ ከፋ ወንጀል እንዳይሔዱ እናደርጋለን። ነገር ግን በጥቆማ መሠረት ጨረታ እንዲስተካከል ወይም እንዲሠረዝ የምናደርጋቸው በርካታ ነገሮች አሉ። ካላስተካከለ አስተዳደራዊ እርምጃዎችን እንወስዳለን። አሁን ለምሳሌ ሚዛን ቴፒ ዩኒቨርስሲቲ ላይ በርካታ ጥቆማዎች ይቀርባሉ። ጉዳዮችን እያየን እየፈታን እንሔዳለን።
አዲስ ዘመን፡- ስለነበረን ቆይታ አመሠግናለሁ።
አቶ ሃጂ፡- እኔም አመሰግናለሁ።
ምሕረት ሞገስ
አዲስ ዘመን ሰኔ 15/2014