ምንም ይሁን ምን፤ መልኩ የፈለገ ይዥጎርጎር፤ ፍልስፍናው ሊብራልም ይሁን ፀረ-ሊብራል፤ ከፈጣሪ ቀጥሎ ዓለም የምትመራው በሕግና በሕግ ብቻ ነው። ያ ማለት የበላይነቱ የሕግ እንጂ አገዛዝ የበላይ ሆኖ ሕጋዊነት ሊጨፈልቀው አይገባም ማለት ነው። ያ ከሆነ ጉዳዩ ሌላ ነው ማለት ነውና እዚህ መነጋገሩ ሁሉ ላያስፈልግ ይችላል።
ነገር ግን፣ ዓለም የምትመራው፣ ኢትዮጵያም የዓለም አካል ነችና፣ ልትመራ የሚገባው በሕግ የበላይነት (Rule of law) እንጂ በአገዛዝ (Rule by law) አይደለም ተብሎ ስለሚታሰብ እዚህ መነጋገሩ አስፈላጊ ሆኖ ተገኝቷል። በመሆኑም፣ ያለንበትን ወቅታዊ ሁኔታ በተንተራሰ መልኩ የሕግ የበላይነት መከበርን፤ ወይም፣ በሌላና ወቅታዊው አገላለፅ “ሕግ የማስከበር እንቅስቃሴ” ን (ካስፈለገ የ “ሕግ ማስከበር ዘመቻ” ውንም እዚህ ጋር ማስገባት ይቻላል) በተመለከተ አንዳንድ ሃሳብ ለመለዋወጥ ወደ’ዚህ ገጽ ብቅ ለማለት ተሞክሯል።
እርግጥ ነው፣ (በአንዳንድ አገራት) ሕግ እየተናደና በኢ- ሕጋዊነት እየተተካ፣ አጉራ ዘለልነት እየተንሰራፋ፣ ጋጠ ወጥነት ነባሩን የሥነ ምግባር እሴት እየተፈታተነ (ነቅሎ እየጣለ ማለትም ይቻላል)፤ የሰዎች (ዜጎች) ሰብአዊ፣ ዴሞክራሲያዊ፣ ፖለቲካዊ … መብቶች በአደባባይ፣ በጠራራ ፀሐይ እየተጨፈለቁ፤ ንፁሃን ያለ ሃጢያታቸው በሃጢያተኞች በሕይወት የመኖር መብታቸውን ሲነጠቁ፤ ሀብትና ንብረት እንደ ቤተክርስቲያን ጧፍ ቀን ከሌት ሲንቀለቀል፤ እናቶች ከእናትነት መንበራቸው ወርደው በድውያን ሲደፈሩ፣ ወጥቶ መግባት ብርቅ እየሆነ፣ ለመግባቢያነት የተፈጠረው ቋንቋ ዋጋ እያስከፈለ፣ ሕፃናት ያለ ሃጢያታቸው በሀጥአን ሲሰቃዩ፤ የእምነት ተቋማት ዶጋ’መድ ሲሆኑ፤ … (ተዘርዝሮ አያልቅም) እየታየ ያለው እዚህ ብቻ ሳይሆን የትም ሊሆን ይችላል። ይኑር እንጂ፣ ኢትዮጵያ ሆኖ፣ ሰላማዊ ሕዝብን በሰላም ማኖር አቅቶ፣ የሕግ የበላይነትን ማስከበር ተስኖ፤ በየመንደሩ የነገሠን ንጉሥ “ኃይ” ማለት አቅቶ …. ቀጥሎ ያሉትን አገራት በምሳሌነት እየጠሩ ለመፅናናት መሞከር እዳው ገብስ ስላልሆነ፤ በግልፅ ለመነጋገር መንግሥት ሊያስብበት፣ በጉዳዩም ላይ እንቅልፍ ሊያጣ ይገባዋል።
ይህ
ሳይሆን
ቀርቶ፣
ጉዳዩ
ሌላ
ከመሆኑ
በፊት
ሁላችንም
“እንደ
ርዋንዳ
ከተላለቅን
በኋላ
አስታራቂ
ምን
ሊበጀን?”፤ ልንል
ይገባል።
ማተብ
ከተበጠሰ፣
እምነት
ከተገረሰሰ፤
ታናሽ
እና
ታላቅ፤
አባት/እናት
እና
ልጅ
ቦታ
ከተቀያየሩ
በኋላ፤
አገር
ባድማ ከሆነና እንስሳት ሳይቀሩ ከተሰደዱ በኋላ … በኋላ … በኋላ … ”ያውሬ መውለጃ …” (ዘፈን) ከሆነ በኋላ … የትኛውስ ሕግ ሊከበር፤ ማንኛውስ ሰው ሊያስከብረው? በሚለው ከወዲሁ ልናስብ፣ ልንቆዝምም ይገባል።
ደቡብ አፍሪካ፣ ያው የታወቀ ነው። ናይጄሪያ በ”ሕግ አለ” እና በ”የለም” መካከል ሲዋዥቅ ቆይቶ አሁን ወደ ”የለም” እያዘነበለ ይገኛል። በተለምዶ “ከሰሃራ በታች” የሚባለው የአህጉሪቱ ቀንድ አካባቢ ከሰላም ጋር ከተራራቀ መሰንበቱ እንጂ በሕግ የበላይነት ስለ መመራቱ ብዙም ሲነገር አይሰማም። ሶማሊያ፣ እግዚሀር ይሁናት። እራሷ አሜሪካ፣ የራሷ እያረረባት …. እንዲሉ የትምህርት ተቋማቷ ሳይቀሩ በጠብመንጃ የበላይነት (እነሱ በዳቦ ስሙ ”Mass shootings” ይሉታል) እየተዳደሩ ነው። ባጭሩ፣ የሕግ የበላይነት ችግር የትም አለ። አንዳንዱ ጋ እንዲኖር ተፈልጎ፤ አንዳንዱ ጋ ደግሞ በተቃራኒው። ወደ ራሱ፣ ወደ ሕግ የበላይነት እንመለስ።
ባለሙያዎቹ በዓለማችን ለሕግ የበላይነት መንጠፍ ዋና ዋናዎቹ ምክንያቶች ሶስት (poverty, illiteracy, and ignorance) ናቸው ቢሉም በርካቶች የሚስማሙበት ሆኖ አልተገኘም። ምክንያታቸውም አገራት ከዚህ ቀደም ከዛሬው በባሰ ሁኔታ በሶስቱ (ድህነት፣ መሃይምነት እና ድንቁርና) ውስጥ ይኖሩ ነበር። በዛን ሰአት የሕግ የበላይነት ይከበር ነበር። ነገሮች የተበለሻሹት በዚህ በአሁኑ፤ በ21ኛው ክፍለ ዘመን አጋማሽ ላይ ባለው ድህረ ዘመናዊነት ዘመን ነው የሚል ነው። ክርክሩን ለጊዜው እንዝለለውና የሕግ መከበርን አስፈላጊነት እናውራ።
እንደ ባልቲሞር ዩኒቨርሲቲው ተመራማሪ Mortimer Sellers (”What is the rule of law and why is it so important?” በሚል ስራቸው) አስተየያየት በአንድ ሉዓላዊት ሀገር የሕግ የበላይነት መከበር ”[…] ዘፈቀዳዊ አሰራርንና ውሳኔን ይከላከላል፤ ፍትህን ያነግሳል፤ እንዲሁም፣ ጭቆናንና የግፍ አገዛዝን ያስወግዳል” (prevents arbitrary judgments, secures justice, and prevents tyranny and oppression)። በመሆኑም፣ የሕግ የበላይነትን የማስከበር ነገር የምርጫ ጉዳይ ሳይሆን ግዴታ፤ ፋይዳውም መሰረታዊ ነው። ወደ ራሳችን ውስጣዊ (ከ’ነውጫዊ ተፅእኖው) ጉዳይ እንምጣ።
”በአሁኑ ሰአት በአገራችን የሕግ የበላይነት ነው ያለው ወይስ የጉልበተኞች አገዛዝ?” የሚለውን፣ በዚህ ሁኔታዎች አሳሳቢ በሆኑበት ወቅት፣ ሰዎች መልሱን ዱብ እንዲያደርጉ መጠበቅ ”ተገቢ ነው/አይደለም” የሚለው እንዳለ ሆኖ የሕግ የበላይነት ስለ መኖር አለመኖሩ ማሳያዎችን እንመልከት።
ማንም ሊከራከርበት የማይችለው መሰረታዊ ጉዳይ ቢኖር፣ በአሁኑ ሰአት በአገራችን አናርኪዝም መኖሩ አንዱ ነው። በሀሰት ፕሮፖጋንዳ፣ ሽብርን በመንዛት፣ በአሉባልታ፣ በሀሰት ትርክት ሰዎችን እርስ በእርስ ማጋጨት የተወሰኑ ቡድኖች የእለት ተእለት ተግባር ከሆነ ጊዜው ዛሬ ሳይሆን ከማህበራዊ ሚዲያው እድሜ እኩል ነው። (የሁለተኛው የሂትለር የዘር ጥላቻ ቅስቀሳ (ኮልድ ብለድድ) እንደነበረው ሁሉ፤ የ1ኛው ዓለም ጦርነት መነሻ ምክንያት አናርኪዝም መሆኑን ነው ታሪክ የሚያስረዳው።)
ሕገ-ወጥ የገንዘብ ዝውውር፣ ተገቢ ያልሆነ የዋጋ ማናር፣ እጥረት በሌለበት ሰው ሰራሽ የምርት እጥረትን መፍጠር፣ ደላላ መር የገበያ ሥርዓት፣ ነዳጅ ሳይቀር ወደ ውጭ አገር መልሶ በመላክ ለገበያ ማዋል፣ ሕገወጥ የመሳሪያ ዝውውር፣ የደራ የጥይት ገበያ፣ ሙስናዬ፣ የዜጎች የፀጥታና ደሕንነት ስጋት መኖር፣ የሕዝብ አንድነትንና አብሮነትን መረበሽ፣ በብሔር ስም ሕዝብና ሕዝብን ማጋጨት፣ የልማት ሥራዎችን ማደናቀፍ፣ የለሙትን ማውደም፤ ፆታን፣ ብሔርን፣ ሃይማኖትን፣ ግለሰባዊ ማንነትን … መነሻ ያደረጉ ጥቃቶች፤ በኋላ ከጎረቤት አገራት የምንበደር እስኪመስለን ድረስ የመሬት ወረራ፣ ኢፍትሀዊ የሀብት ክፍፍል፣ አድሏዊነት…. በዛሬዬቱ ኢትዮጵያ አሉ ወይስ የሉም?? እነዚህን መመለሱ ብቻ፣ ድምፃዊው “ቀላል ይሆናል” እንዳለው፤ ሁሉንም ቀላል ያደርገዋል።
እርግጥ ነው፣ እኛ ሰዎች ያ’ለን እንደ ሌለ፤ የሌለን እንዳ’ለ አድርጎ የማቅረብ ችሎታ አለን ይባላል። በተለይ ወደ ፖለቲካው ዓለም ለተቀላቀሉቱ ይህ እዚህ ግባ የማይባል እጅጉን ቀላልና ሲበዛም የሚዘወተር (ራስንና የራስን ቡድን ነፃ ለማድረግ ሲባል የሚደረግ – Political correctness) ነው ይላሉ። ተረትና ምሳሌው ደግሞ ከዚህ በተቃራኒው “ተሸፋፍነው ቢተኙ፤ ገልጦ የሚያይ አምላክ አለ” ይላል። ይህ ብቻም አይደለም፣ “አለባብሰው ቢያርሱ በአረም ይመለሱ”ም ሲል ተግባሩ ከንቱና ጊዜያዊ ብልጠት መሆኑን ያሰምርበታል።
እውነቱ ይህ ከሆነ ታዲያ “ለሕግ የበላይነት መከበር መፍትሄው ምንድን ነው?” የሚል ግዙፍ ጥያቄ ሊመጣ ይችላል፤ የግድም ይመጣል። የዚህ ግዙፍ ጥያቄ መልስ፣ ልክ እንደ ጥያቄው ሁሉ መልሱም ግዙፍ ሲሆን፤ እሱም “የመንግሥት ቁርጠኝነትና የህዝብ ተባባሪነት” የሚል ነው የሚሆነውና ሌላው በዚህ ጥላ ስር የሚካተት መሆኑን እያስታወስን ሀሳባችንን እናጠቃልላለን።
ግርማ መንግስቴ
አዲስ ዘመን ሰኔ 10 /2014